Sunday, April 24, 2016

በጋምቤላ ሕዝብ ለተቃውሞ ወጣ – “መንግስት ግድያውን ለፖለቲካ ፍጆታና ኦሮሚያን እና ጎንደርን ለማረጋጋት ተጠቅሞበታል” – ጋምቤላ አልተረጋጋችም

በጋምቤላመንግስት የለም ወይ?” ያሉ ነዋሪዎች ሰሞኑን የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝና መንግስትም ይህንን የሕዝብ ሞት ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ አዎሎታል በሚል ሕዝቡ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ሲያሰማ መዋሉን ለዘ-ሐበሻ የደርሰው መረጃ አመለከተ::

ልጆቻችን ይመለሱ…. በሃገራችን ሰላም አጣንመንግስት በኛ ሞት የፖለቲካ ድል ማግኘቱን ያቁም…” እና ሌሎችንም መፈክሮች ሲያሰሙ የነበሩት የጋምቤላ ነዋሪ ሰልፈኞች መንግስትን ሲያወግዙ ውለዋል::

ሕፃናቱን ለማስለቀቅ ከብቤያለሁ እያለ ሲፎክር የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ወታደር እስካሁን ልጆቹን ባያስለቅቅም የትናንቱን ገድያ ተቃውመው ለሰልፍ የወጡትን ኢትዮጵያውያን ግን ዛሬ ጋምቤላ ላይ ሲቀጠቅጥና ለመበተንም ሲሞክር ታይቷል::
በጋምቤላ የተለያዩ ከተሞች በአሁኑ ወቅት መረጋጋት አለመኖሩን የሚገልጹት የአካባቢው ምንጮች ማን ከየት መጥቶ ገድሎ እንደሚሄድ እንደማይታወቅና ሕዝቡም እርስ በራሱ ተፈራርቶ እንደሚገኝ ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል::

በጋምቤላ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት የታህሳስ 13 መታሰቢያ ንቅናቄ ተወካይ አቶ ኦዶል ኦዶል ለዘ-ሐበሻ በሰጡት አስተያየት የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት የሰሞኑን ግድያ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ አድርጎታል ብለዋል:: እንደ እርሳቸው አባባል መንግስት እየነገረን ያለው ትንሹን ግድያና በተለይም ሙርሌዎች ያደረሱትን እንጂ ከዛ በፊት 15 ቀናት በፊት ስለሞቱት ሰዎች የነገረን ነገር የለም ብለዋል::: እንደ ኦዶል ገለጻ መንግስት በኦሮሚያና በጎንደር የተነሳበትን ሕዝባዊ ቁጣ ለማብረድና ሃሳብን ለማስቀየር የሙርሌዎችን ግድያ ከመጠቀሙ በላይ ምንም ያደረገው ነገር የለም ብለዋል::

በተለይም በትናንትናው ዕለት በጋምቤላ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለተገደሉት 15 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ጠይቀናቸውገዳዮች ናቸው የተባሉት ሰዎች የገደሉት አማሮችን እና ኦሮሞዎችን ብቻ መርጠው ነው; ይህም ማን ከበስተጀርባው እንዳለ ያሳየናልብለውናል::

አቶ ኦዶል ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት የጋምቤላ አክቲቭስቶች ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ መረጃዎችን ለሕዝብ ቶሎ ቶሎ ማድረስ አለባቸው ብለዋል:: ሕዝቡ መንግስት የሚለውን ብቻ በመስማት መንግስት አሸናፊ እንዳይሆን መረጃዎችን ከፎቶዎች ጋር በማውጣት ማጋለጥ ይገባቸዋል ብለዋል::

ይህ እንዲህ እንዳለ ትናንት ጃዊ በተባለ የስደተኞች ጣቢያ ስለተገደሉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሏክ ቱት ኩዃት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የሞቱትን ቁጥር ወደ 10 አሳንሰውታል:: ለትናንቱ ግድያ መነሻም ሴቭ ዘችልድረን የተባለ የግብረሰናይ ድርጅት መኪና በስደተኞቹ ካምፕ ላይ በደረሰበት አደጋ የሁለት ስደተኞች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ ነው ሲሉ ተናግረዋል:: ስደተኞቹ ከመኪና አደጋው ጋር ተያያዥነት በሌላቸው 10 ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውንም ገልጸዋል::

ጋምቤላ ተወጥራለች…. -ሐበሻ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዳገኘች ትመለሳለች::

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/53659


Friday, April 22, 2016

ከጀልባዋ በህይወት የተረፉት ስለ ተአምረኛዋ ስልክ ይናገራሉ

ኢትዮጵያዊውና ሱማሊያዊው ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በሚያመሩ ሁለት ጀልባዎች ውስጥ ተሳፍረው ነበር፡፡ከጥቂት የባህር ላይ ጉዙ በኋላም በሁለቱ ጀልባዎች የነበሩት ስደተኞች ወደ ሰጠመችው መርከብ መሸጋገራቸውንም ይናገራሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊዎች በአደጋው 500 ሰዎች በባህሩ መስጠማቸውን ተናግረዋል፡፡

የ25 ዓመቱ ሙዓዝ ማሐሙድና የ28 ዓመቱ ሞውሊድ ኢስማን የነበሩባቸው ጀልባዎች እያንዳንዳቸው 200 ሰዎች የጫኑ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ከትንንሾቹ ጀልባዎቹ ከፍ ወዳለችው ጀልባ እንዲሸጋገሩ በሰው አዘዋዋሪዎቹ ሲታዘዙም አዲሷ ጀልባ ውስጥ 300 ያህል ሰዎች እንደነበሩ ለጀርመኑ ዶቼቬሌ ጠቅሰዋል፡፡

በአደጋው የተመለከቱት ነገር ምስክርነታቸውን በሚሰጡበት ሰዓት ጭምር የፈጠረባቸው ጭንቀት፣ፍርሃትና ልብን የሚሰብርን ሐዘን ከገጽታቸው መመልከት ይቻላል፡፡

ማሐሙድ ‹‹ወደ ትልቁ ጀልባ እንደተሸጋገርን ጀልባዋ መስመጥ ጀመረች፡፡የሁለት ወር ዕድሜ የነበራት ልጄና የ21 ዓመቷን ባለቤቴን ባህሩ ነጠቀኝ››በማለት በግሪክ ለሚገኙት የእርዳታ ሰራተኞች ነግሯቸዋል፡፡

ሁለት ሰዎችን ከሞት ማዳኑን የሚናገረው ማሐሙድ በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ ከነበሩት 500 ሰዎች በህይወት የተገኙት 41ዱ ብቻ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

ሁለቱ ወጣቶች መጀመሪያ ተሳፍረውባቸው ከነበሩት አነስተኛ ጀልባዎች አንዷን ቢያገኙም ሰው አዘዋዋሪዎቹ ሊጠብቋቸውና ከሞት ጋር ግብግብ ገጥመው የነበሩትን ሊሎች ሊረዷቸው ሳይፈቅዱ ጥለዋቸው እንደሄዱ ይናገራሉ፡፡

በአደጋው ሁለት እህቶቹንና የእህቱን ልጅ ያጣው ሞውሊድ ‹‹በአይናችን የሞቱ ሰዎች ተመልክተናል››ይላል፡፡የጀልባዋ የነዳጅ መያዣ እንደተሰበረም ሰው አዘዋዋሪዎቹ የመጣችላቸውን ሶስተኛ ጀልባ በመጠቀም ተመልሰው በመምጣት እንደሚወስዷቸው ቃል በመግባት ጥለዋቸው መሄዳቸውንም ሞውሊድ ይናገራል፡፡

‹‹ለሶስት ቀናት ያህል በባህሩ ላይ ነበርን››የሚለው ሞውሊድ የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር ሳያገኙ መቆየታቸውንም መስክሯል፡፡እንደ ዕድል አንድ ሞባይል አንድ የስልክ ቁጥር ብቻ ተመዝግቦበት ያገኙት እነ ሞውሊድ ወዳገኙት ቁጥር ይደውላሉ፡፡ስልኩ የጣልያን ፖሊስ ነበር፡፡ የጣሊያን ፖሊሶች በስልክ ለደረሳቸው የህይወት አድን ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የባህር ኃይል ሰዎችን ወደ ስፍራው በመላካቸውም እነ ሞውሊድ ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል፡፡

በህይወት መትረፍ ከቻሉት 41 ሰዎች ውስጥ 37ቱ ወንዶች ፣ሶስቱ ሴቶችና አንደኛው የሶስት ዓመት ታዳጊ መሆናቸውን የጣሊያን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ፣የጣሊያን፣የግሪክና ወይም የግብጽ የባህር ኃይል ሰራተኞች እስካሁን ድረስ ሰጠመች የተባለችውን ጀልባም ሆነ አስከሬኖችን ስለማግኘታቸው አልገለጹም፡፡

http://www.satenaw.com/amharic/%E1%8A%A8%E1%8C%80%E1%88%8D%E1%89%A3%E1%8B%8B-%E1%89%A0%E1%88%85%E1%8B%AD%E1%8B%88%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%88%A8%E1%8D%89%E1%89%B5-%E1%88%B5%E1%88%88-%E1%89%B0%E1%8A%A0%E1%88%9D%E1%88%A8/

Monday, April 18, 2016

በጋምቤላው እልቂት ዙሪያ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ባለ3 ነጥብ መግለጫ አወጡ

ሚያዚያ 6 ቀን 2008 በጋምቤላ ክልል ነዋሪ በሆኑ ሰላማዊ የኑዌር ብሔረሰብ አባላት ላይ በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ነዋሪ በሆኑ ታጠቂዎች የተፈጸመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመስማታችን መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ እጅግ ልብ የሚሰብር ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል፡፡

ከመንግሥት ባገኘነው መረጃ መሠረት ብቻ 208 ዜጎቻችን በዚሁ ጭፍጨፋ በአንድ ሌሊት ሕይወታቸውን ማጣታቸውና 102 ሕፃናት ታፍነው መወሰዳቸው በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛና ዘግናኝ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ዜጎቻችን ለዚህ ያህል ትልቅ ጥቃት የተዳረጉት ደግሞ ቀደም ሲልም ጥቃት ሲፈጸሚባቸው እንደነበረ እየታወቀ የኢህአዴግ መንግሥት እራሳቸውን የሚከላከሉበትን ትጥቅ በማስፈታቱ የመከላከያ መሣሪያ እንዳይኖራቸው በመደረጉና ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ሁኔታ ለደህንነታቸው ተገቢው ጥበቃ ስላልተደረገላቸው መሆኑን መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባሉ፡፡

ከዚህም ሌላ ቀደም ባሉት መንግሥታት በየጠረፉ አከባቢዎች ይመደብ የነበረው ጠረፍ ጠባቂ ኃይል እንዳይኖር በመደረጉ የውጭ ሀገር ታጣቂዎች እንደፈለጉ ድንበር ጥሰው የሚገቡበትና ወገኖቻችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል፡፡

ስለዚህም፡-

1
ኛ፡- በጥቃቱ ምክንያት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ላጡ የኑዌር ብሄረሰብ አባላት ለሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደዚሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን፡፡

2
ኛ፡- በአጥቂዎቹ ታፍነው የተወሰዱት ሕፃናት በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መንግሥትና የዓለም ማሕበረሰብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ተገቢውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

3
ኛ፡- ለወደፊቱ በጋምቤላም ሆነ በሌሎች ክልሎች በጠረፍ አከባቢዎች በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ሕዝቡ ራሱን መከላከል የሚያስችልበትና ተገቢውን የደህንነት ጥበቃ የሚያገኝበት ሁኔታ በአስቸኳይ በመንግሥት በኩል እንዲመቻች አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ሰላም ለሕዝባችን!!
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ
ሚያዚያ 9 ቀን 2008
አዲስ አበባ

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/53487