Thursday, May 3, 2018

ኦዶ ሻኪሶ: ወርቅ ‘መርዝ’ የሆነባት ምድር (BBC)

ወ/ሮ ሑጤ ደንቆ የሁለት ልጆቻቸው ሞት እንዲሁም የሴት ልጃቸው አካል መጉደል ካደርሰባቸው የሐዘን ስብራት ጋር በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ዲባ በቴ ቀበሌ ውስጥ ይኖራሉ። እኚህ እናት የመጀመሪያ ልጃቸውን ሁለት እግሯን አልታዘዝ ከማለት በተጨማሪ በኋላ የወለዷቸው ወዲያውኑ እንደተወለዱ ሞተውባቸዋል።
ወ/ሮ ሑጤ ነፍሰጡር በነበሩበት ወቅት ከባድ የጤና እክል አጋጥሟቸው የነበረ ቢሆንም አሁንም የአጥንት ሕመም ህይወታቸውን አቀበት አድርጎባቸዋል። የእሳቸውን እና የልጆቻቸውን ጤንነት ይከታተሉ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች የእሳቸው አጥንት ህመምም ሆነ የልጃቸው እግር አጥንት መልፈስፈስ ምክንያቱ ከፋብሪካው የሚወጣው መርዛማ ኬሚካል መሆኑን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ወ/ሮ ሑቴ የሚኖሩበት ዲባ በቴ ቀበሌ የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ የሚገኝበት ነው። “ነፍሰጡር ሴቶች ያስወርዳቸዋል፤ ሕፃናት ሲወለዱ ያለጭንቅላት ይወለዳሉ። ጭንቅላታቸው መጠኑ በጣም ያነሰ ነው። እጅና አይናቸውም ተጎድቶ ይወለዳሉ። ሰው ታሞ ወደ ሐኪም ቤት ሲሄድ ከ ‘ነርቭ’ ጋር የተያያዘ ችግር ነው ይባላል።” በማለት የቀበሌው ነዋሪ የሆኑት አቶ ዱቤ ጋሸራ ሚጁ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚሁ ቀበሌ ተወልደው ያደጉት እኚህ አዛውንት “ድሮ ይህንን የሚመስል ችግር አልነበረም”ይላሉ።
“መንግሥት የወጣቱን ቅሬታ ከመስማት ውጭ ምንም የለወጠው ነገር የለም።”
ዓይናቸው ከማምረቻው ውስጥ በሚወጣ ኬሚካል መጎዳቱን እንዲሁም በአግባቡ ቆመው መሄድ እንደሚያቅታቸው ነግረውናል። በተጨማሪም ከዚሁ ችግር የተነሳ በከብቶች እና በዱር እንስሳት እየደረሰ ያለው እልቂት ለትልቅ ችግር አጋልጦናል ይላሉ።
‘ሳናይድ’ እና የአካል ጉዳተኝነት
የሚድሮክ ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ወርቅና ነሐስ በሚያመርትበት ወቅት ወርቁን ለማፅዳት የሚጠቀምበት ኬሚካል ‘ሳናይድ’ ይባላል። ይህ ኬሚካል ራስ ምታት፣የልብ፣ የአእምሮ እና የነርቭ ህመሞች እንደሚያስከትል የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጦና ዋሬ ነግረውናል። ከዚህም ባሻገር የሰው አጥንት ለማጠንከር የሚረዱ እንደ ብረት(አይረን) ያሉ ንጥረ ነገሮች ከሰው እና ከእንስሳት አካል ውስጥ መጠኑን ይቀንሳል።
ይህም ለአጥንት መሳሳት እና መሰባበር እንደሚያጋልጥ አቶ ጦና ዋሬ ያስረዳሉ። የወርቅ ማምረቻው የሚገኝበት ዲባ በቴ ቀበሌ ውስጥም የአካል ጉዳተኝነት ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው።

የቢቢሲ ሪፖርተር በአካል በቀበሌው ተገኝቶ አንድ ኪሎ ሜትር ባልሞላ መንደር ውስጥ ሶስት የአካል ጉዳት ያለባቸው ህፃናትን አይቷል። በህፃናት ላይ የሚደርሰው የአካል ጉዳት በቀበሌው ውስጥ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ነዋሪዎች ወልደው ለመሳም እየተሳቀቁ እንደሆነ ይናገራሉ። ወ/ሮ ደምበሊ ሔጦ የአካል ጉዳት ያለባት ህፃን አላቸው፤ “ልጆቼ በታመሙ ቁጥር ስጋት ያድርብኛል። ሌላ ተጨማሪ ልጅ ለመውለድ እንደዚሁ ልጅ ይሆንብኝ ይሆን ስል እሰጋለሁ” ይላሉ። በተጨማሪም ነፍሰጡር ሴቶች ልጃቸውን ወልደው ከአካል ጉዳት ነፃ መሆኑን እስኪያረጋግጡ ድረስ ማርገዛቸውን እንደሚደብቁ፣ የአካል ጉዳት ያለበትን ህፃን የወለዱ እናቶችም ከሰው አይን ከልለው በቤት ውስጥ ደብቀው እንደሚያሳድጓቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በተጨማሪም የሳይናይድ ኬሚካል የተቀላቀለበት ወራጅ ውሃ የሚጠጡ እንስሳት ወዲያውኑ እንደሚሞቱ፣ የተበከለ አየር ውስጥ የሚቆዩት ደግሞ ከወደቁ በኋላ መነሳት እንደማይችሉ፣ አጥንታቸውም በቀላሉ እንደሚሰበር የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
“ድጋሚ ተመሳሳይ ችግር ይደርስብኝ ይሆን ብዬ እሰጋለሁ።”
የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች
የፋብሪካው የጥበቃ ሰራተኞች በህብረተሰቡ ላይ ልዩ ልዩ ችግሮችን እንደሚያደርሱ ቅሬታዎች ይሰማሉ። ይህንን ቅሬታ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የወረዳው አስተዳደር ሰራተኞችም ይጋሩታል። ለፋብሪካው ከሚደረገው ከፍተኛ ጥበቃ የተነሳ መንግስት በሰጣቸው ኃላፊነት ተጠቅመው በፋብሪካው ውስጥ ገብተው የቁጥጥር እና ክትትል ስራ ማድረግ እንዳልቻሉ የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቦሬ ጦና ይናገራሉ። ሰራተኞችንም በሚቀጥሩበት ወቅት ህጉ በሚያዘው መሰረት እንደማያሳትፏቸወው ከድርጅቱ የሚያገኙት ምላሽም “እኛ በእናንተ ሳእሆን በፌደራል መንግስት ነው የምንመራው” የሚል እንደሆነም ይናገራሉ። የስራ እድል ማግኘትን ጨምሮ በወረዳው ውስጥ ከሚገኙ የማእድን አምራች ድርጅቶች ጥቅም እያገኘን አይደለም፤ ከዚህም አልፎ ችግር እየደረሰብን ነው በማለት የወረዳው ነዋሪዎች በተለያየ ጊዜ ሰልፍ ወጥተዋል። ምላሽ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ቅሬታ መልስ ለማግኘት ወደ ማእድን ማምረቻው በሄድንበት ወቅት የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት መልስ የሚሰጡን የስራ ኃላፊዎች እንደሌሉ ነግረውናል። ነገር ግን ይህ ፅሁፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጣ በኋላ ሚድሮክ ለቢቢሲ በፃፈው ደብዳቤ ጉዳቱን አላደረስኩም ብሏል።
የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ሳናይድ የተባለው ኬሚካል በሕዝብና በአካባቢ ላይ ጉዳት አለማድረሱን በደብዳቤው ገልጿል። በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶ ሻኪሶ ወርቅ በማምረት የተሰማራው ይህ ኩባንያ አካባቢውን በጠበቀና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እየሰሩ መሆኑንም ጭምር ገልፀዋል።
“በአካባቢ ላይም ሆነ በሰዎች ላይ ከኬሚካል ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር የለም” ብሏል።
ሚድሮክ በአካባቢው የተባሉት ችግሮች ተከስተው ቢሆን ኖሮ የሚያውቅበትም ዕድል እንደነበር ገልፆ የአካባቢን ጉዳዮች ለመከታተል ራሱን የቻለ ክፍል እንዳቋቋሙ ጠቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ በአዶ ሻኪሶ አካባቢ በማዕድን ማውጣት ስራ ላይ የተሰማራው ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኩባንያዎች በአካባቢው በመኖራቸው ከኬሚካል ጋር ተያይዞ ደረሰ የተባለው ጉዳት በእርግጥ ከሚድሮክ ጋር ብቻ የተያያዘ ስለመሆኑ ማረጋጋጫ የለም ብለዋል። ሚድሮክ በአካባቢው ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልጾ፤ ትምህርትቤቶች፣የጤና ኬላዎች፣ የመንገድ ግንባታ ላይ በመሳተፍ ለብዙ ሰዎችም የስራ ዕድል እንደፈጠሩ አስታውቋል። በማእድን ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የአካባቢ እና የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኑት ወ/ሮ እናት ፋንታ ግን “እስከ መጋቢት 2009 ዓ.ም ባደረግነው ክትትልና ቁጥጥር መሰረት በኬሚካል የደረሰ ጉዳት አላየንም፤ ከማህበረሰቡም ሆነ ከመንግስት አካል የደረሰንም ቅሬታ የለም” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሻኪሶ ከተማ የማዕድን፣ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ግን በሚድሮክ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችችን ለመፍታት ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር መስራት አለበት። ኬሚካል እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ እየደረሰ ያለው ጉዳትም በ አስቸኳይ በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት እንዳሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል። ይሁን እንጂ ጥያቄው የወርቅ ምርቱ ተጠቃሚነት ሳይሆን በህይወት የመቆየት ስጋት የሆነባቸው የዲባ ባቴ ነዋሪዎች “ከመንግስት በኩል መፍትሄ እንፈልጋለን” እያሉ ነው።
የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር በ1989 ዓ.ም የለገደንቢን የወርቅ ማእድን ከመንግስት እጅ በ172 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለ20 ዓመታት በሊዝ ነበር የተረከበው። ድርጅቱ በ2014 እኤአ በአለም ባንክ በተዘጋጀው ፎረም ላይ ባቀረበው ሪፖርት መሰረት የሚድሮክ ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ እኤአ ከ 1997-2014 ድረስ ባሉት 16 አመታት 52 0444.71 ኪሎ ግራም ወርቅ እንዲሁም 14 670.6 የብር ማእድን አምርቶ 17.24 ቢሊዮን ብር እንደሸጠ ያሳያል።
ድርጅቱ ለ20 ዓመታት የተፈራረመው ውል አሁን በያዝነው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ የሚጠናቀቅ ሲሆን ስምምነቱ እንዲታደስለት አመልክቷል።
****
ምንጭ፦ 


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/90416