Monday, June 29, 2015

32ኛው የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል በሜሪላንድ በድምቀት ተከፈተ

በሰሜን አሜሪካ በየዓመቱ የሚደረገው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በሜሪላንድ በርድ ስታዲየም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በድምቀት ተከበረ::

ከአሜሪካ እና ከካናዳ የመጡ ከ30 በላይ ቡድኖች በስታዲየሙ በመገኘት በዚሁ በመክፈቻ ዝግጅት ላይ ራሳቸውን አስተዋውቀዋል:: በዚህ ዝግጅት ላይ ለእንግሊዙ አርሰናል ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው ጌድዮን ዘላለም የተገኘ ሲሆን ከሕዝቡም ደመቅ ያለ አድናቆት ተችሮታል::

በዚሁ የመክፈቻ ዝግጅት የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ ባሰሙት ንግግር የዘንድሮው ዝግጅት በርካታ ሕዝብ በመገኘት በመከፈቱ መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ቀናት ደማቅ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል:: እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ረቡዕ ምሽት የብሄራዊ ትያትር 60ኛ ዓመት በዓል በታሪካዊ ሁኔታ ይከበራል; የፊታችን ሐሙስ አርብና ቅዳሜም ከ እግር ኳሱ በተጨማሪ ታላላቅ አርቲስቶች የሚገኙባቸው ትልልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች እንደተዘጋጁና ሕዝቡም በነዚህ ስፍራዎች እየተገኘ እንዲዝናና ጥሪያቸውን አቅርበዋል::

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን 32ኛ ዓመት በዓል መታሰቢያነቱ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ላለቁት ኢትዮጵያን መታሰቢያ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወካይ ባሰሙት ንግግር የሊቢያውን ሰቆቃ አስታውሰው “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አይረሳትም” ብለዋል::

የመድሃኔዓለም ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ተወካይ ቄስ በሪሁን መኮንን በሊቢያው ሰቆቃ ሊያስተምረን ስለሚገባ ነገር ተናግረዋል:: የሁሉም የሃይማኖት መሪዎች ልዩነት ሳይበግራቸው በአንድነት በመቆም ሊሰሩ እንደሚገባ ይህ ሃዘን አስተምሮናል ብለዋል:: በሰሜን አሜሪካ የሙስሊም ኮሙዩኒቲ ተወካይ ሼክ ሱለይማን ነስረዲን በበኩላቸው በሊቢያ የተገደሉት ወገኖች የተገደሉት ክርስቲያን በመሆናቸው ሳይሆን ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሃይማኖቶች መከባበር ለመጠቆም ሞክረዋል::


በዛሬው የመክፈቻ ጨዋታ የላስቬጋሱ አበበ ቢቂላ የሲያትሉን ዳሸን 2ለ0 – ዴንቨር የሚኒሶታውን ኒያላ 4ለ0 – ቺካጎ ፒላደልፊያን 2ለ1 – ኦሃዮ ቦስተንን 4ለ1 ሲያሸንፉ የሎሳንጀለሱ ዳሎል የዲሲው ዩናይትድ 1ለ1 እንዲሁም የሎሳንጀለሱ ስታርስ ከሜሪላንዱ ከቅዱስ ሚካኤል ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል::
በሌላ በኩል የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ያሬድ ነጋሽ ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት በዛሬው የመክፈቻ ዝግጅት መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ቀናት በርካታ ሰው እንደሚገኝ ያላቸውን ግምት ገልጸዋል:: በሃይማኖት አባቶቹ መል ዕክት መደሰታቸውንም ገልጸዋል::
በድምቀት የተከፈተው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫልን በስፍራው የሚገኙት የዘ-ሐበሻ አዘጋጆች በየቀኑ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ይዘግቡላችኋል::



http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44692



Saturday, June 27, 2015

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ኢትዮጵያን አስጠነቀቀች


የአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ የአገራቱን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው
-
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ

  
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚገኙበት ሁኔታና አያያዛቸው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ጋርዲያን ዘገበ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው የቆንስላ ድጋፍ ማግኘት በማይችሉበት ወይም ይግባኝ የመጠየቅ መብት ባላገኙበት ሁኔታ በግልጽ በማይታወቅ ስፍራ ከሰው ተነጥለው ለብቻቸው መታሰራቸውን ያወገዙት ውጭ ጉዳይ ሚነስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በግለሰቡ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ማሻሻል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ ባለፈው ረቡዕ ከኢትዮጵያው አቻቸው ከዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ዙሪያ በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ ግለሰቡ እስሩን በህግ ለመቃዎም ዕድል ባላገኙበት ሁኔታ ከሰው ተነጥለው ላለፈው አንድ አመት በእስር ላይ መቆየታቸው ያሳስበኛል ብለዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸውን በየጊዜው ለመጎብኘት የምንችልበት ሁኔታ እንዲመቻችልን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል ከመግባት ባሻገር ተገቢ ምላሽ ሊሰጠን አለመቻሉ አሳዝኖኛል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ አለመስጠቱ ተቀባይነት የለውም፣ በግለሰቡ ጉዳይ ዙሪያ ይህ ነው የሚባል መሻሻል አለመታየቱም ትልቅ ስፍራ የምንሰጠውን የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለዶ/ ቴዎድሮስ መናገራቸውንም ጋርዲያን ዘግቧል፡፡የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ለቤተሰባቸው የሚያደርገውን
የቆንስላ ድጋፍ ለወደፊትም እንደሚቀጥል ሃሞንድ ተናግረዋል፡፡የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ቤን ኩፐር በበኩላቸው፤ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቡ ከሰው ተነጥለው መታሰራቸውንና መጎብኘት እንዳለባቸው በማረጋገጥ እስሩን መቃወሙ አስደስቶናል፣ ይሄም ሆኖ የእንግሊዝ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተለቀው ወደ እንግሊዝ በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልን እንጠይቃለን ማለታቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የተመድ የስቃይ ጉዳዮች ምርመራ ልዩ ባለሙያ ጁዋን ሜንዴዝ በበኩላቸው፤ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አያያዝ በተመለከተ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ
ለሁለቱም አገራት መንግስታት ማስታወቃቸውን ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=16399:%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%8A%E1%8B%9D-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B3%E1%88%AD%E1%8C%8B%E1%89%B8%E1%8B%8D-%E1%8C%BD%E1%8C%8C-%E1%8C%89%E1%8B%B3%E1%8B%AD-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%8C%A0%E1%8A%90%E1%89%80%E1%89%80%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%89%A3%E1%88%88&Itemid=101

Friday, June 26, 2015

ራሱ እግር እግሩ ራስ የሆነበት፣ በአፍጢሙ የተደፋ የሕግ ስርዓት (በወይንሸት ሞላ ዙሪያ)

ላይ ላዩን ስናየው የጨለመ ቢመስለንም በርግጥ የኢትዮጵያ ትንሳኤ መድረሱን የሚያመላክቱ ብዙ ምልክቶች እያታዩ ነው። ከነዚህ ምልክቶች መካከል በዋናነት ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ፣ የሚገርሙ፣ የሚያስደንቁና ወኔ የሞላባቸው ጀግና ልጆች እየተፈጠሩ መሆናቸው ነው።
ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ስለ አሁኑ የለዉጥ ፈላጊ ትዉልድ ሳስብ፣ በፊቴ የሚደቀኑ እጅግ ወገኖች በጣም ብዙ ናቸው። ከነዚህ ወገኖች መካከል ዛሬ ስለ አንዲት እህት እጽፋለሁ። ከፍተኛ የሆነ የዘረኛው ህወሃት አገዛዝ ዱላ ያረፍባት። ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ፣ ከአንድ አመት በፊት “የማታውቋት ካላችሁ፣ በሰውነት ‹‹ቀጫጫ ነች›› ብዬ ብነግራችሁ አልተሳሳትኩም፡፡ ግን ጥንካሬዋ ይገርመኝ ነበር” ሲል የጻፈላት።


                       ወይንሸት ሞላ
ቀኑ የካቲት 30 2006 ዓ.ም ነው። እሑድ ቀን ። የሴቶች የ5000 ሩጫ ተዘጋጅቷል። በርካቶች ይሮጣሉ። ቢጫ ኬኔቴራ ለብሰዋል። ሩጫዉ እንደተጀመረ ድምጾች መሰማት ጀመሩ። የስድብ፣ የክፉ አይደለም። «የጣይቱ ልጆችን ነን፤ የሚኒሊክ ልጆች ነን፣ ለነጻነት ነው የምንሮጠዉ፣ እርቦናል፣ መብታችን ይከበር፣ የታስሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ …» የሚሉ ድምጾች። በሌሎች ሯጮች ላይ ጠጠር አልተወረወረም። የወደመ ንብረት የለም። መንገዶች አልተዘጉም። ሩጫዉ አልተስተጓጎለም። በሰላም ተጀመሮ በሰላም ነው ያለቀው። ሆኖም ሕወሃቶች ተቆጡ። ሕግ አክብረው፣ ሕግ ምንግስቱ የሚፈቅድላቸውን መብት ተጠቅመው ሰላማዊ የነጻነት ድምጾችን ያሰሙት ወጣት ሴቶችን ያዟቸው። ለሶስት ሳምንታት አስረው ከፍተኛ ግፍ ፈጸሙባቸው። እነዚህ ልጆች የጣይቱ ልጆች ተብለው ይታወቃሉ። ከነዚህ መካከል አንዷ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆነችው፣ ወይንሸት ሞላ ናት 

ብዙም አልቆየም፣ በአኑዋር መስኪድ አካባቢ በዚያ ሙስሊሞች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመታዘብ ወይንሸት በሄደችበት ጊዜ፣ እንደገና ፖሊሶች ይይዟታል። ከፍተኛ ድብደባ ይፈጽሙባታል። ጭንቅላቷ በደብደባ ተጎድቶ የተሰፋ ሲሆን፣ የቀኝ እጇን ቀጥቅጥው ሰብረዉታል። አዚዛ መሃመድ ከምትባል የአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ ፎቶ ግራፍ አንሺ ጋር, ፍርድ ቤት ትቀርባለች። ብዙ ሰቃይ ለሳምንታት ከተቀበለች በኋላ እንደገና ትፈታለች።

በአዲስ አበባ ከፍተኛ ተቃዉሞ በቀረበት በሚያዚያ 14 ቀን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ( 8 AM ) ፣ ኢያስፔድ ተስፋዬ ከሚባል የሰማያዊ ከፍተኛ አመራር ጋር በስልክ ታወራለች። ያኔ ፖሊሶች አሁን ይይዟታል። ኢያስፔድ ለአንድ ለአመራር አባላቱ ወይንሸት መታሰሯን ያሳውቃል። በሶሻል ሜዲያም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ( 9 AM) ይለጥፋል። ሌላ የሰማያዊ አመራር አቶ ወሮታው ዋሴ ወዲያው በሶስት ሰዓት ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሯን ያረጋግጣል።

የሕወሃት ፖሊሶች ወይንሽትን ጨምሮ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ማስተዋል ፍቃዱ እና ቤተልሄም አካለወርቅ የተባሉ የሰማያዊ አባላትን ብዙ ካንገላቱ በኋላ ፍርድ ቤት ያቀርቧቸዋል። “አራት ሰዓት ተኩል ላይ መስቀል አደባባይ ሲበጥብጡ ያዝናቸው” የሚል ክስ ይመሰርታሉ። ወይንሸት የተያዘችው ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት በሌላ ቦታ፤ ፖሊስ ግን በሌሎች እስረኞች ማድረግ እንደለመደው የዉሽትና የፈጠራ ክሱን አዥጎደጎደው። እንደው ተሳስትው እዉነት መናገር የማይችሉ ፍጥረቶች !!!
እነ ወይንሸት ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት፣ ተያዙ በተባሉበት ወቅት መስቀል አደባባይ ላይ እንዳልነበሩ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ያሰማሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ወረታው ዋሴን እና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ወጣት እያስፔድ ተስፋዬን በመከላከያ ምስክርነት ወይንሸት አቀረበች፡፡ ሌሎችም እስረኞች እንደዚሁ በቦታው በተባለው ወቅት እንዳልነበሩ ምስክር አቀርቡ። ፍርድ ቤቱ ለዉሳኔ ሰኔ 15 ቀን ቀጠሮ ይሰጣል። ሰኔ 15 ቀን፣ “የወንይሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤትሄልየም አካለ ወርቅ የመከላከያ ምስክሮች ተከሳሾቹ በቦታው እንዳልነበሩና ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ አላስረዱም በሚል” ፍርድ ቤቱ ጥፋተኞች ይላቸዋል። የተከሰሱበት ወንጀል እስከ 6 ወር እንደሚያስቀጣ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ እነ ወይንሸት ሞላ የሁለት ወር እስር ፈርዶባቸው፣ የታሰሩት ከሚያዝያ 14/ 2007 ጀምሮ ሁለት ወር ከአንድ ቀን ስለሆነ ከ እስር እንዲፈቱ ይወስናል።

አቅቢ ህግ ዜጎችን ሲከስ፣ ወንጀል ስለመስራቱ መረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ሆኖም በአገራችን ያለው የፍርድ ሂደት ዜጎች ሲታሰሩ ጥፋተኛ የሚባሉት፣ አቃቤ ሕግ ጥፋት ስለመፈጸማቸው በቂ ማስረጃ ሲያቀርብ ሳይሆን፣ ተከሳሾች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን መረጃ ሲያቀርቡ ነው። ራሱ እግር ፣ እግሩ ራስ የሆነበት ፣ በአፍጢሙ የተደፋ የሕግ ስርዓት !!!!!
የአገራችችን አሰቂኝና አሳፋሪ የሕግ ስርዓት ድራማ እዚህ ላይ አላበቃም። ሰኔ 15 ቀን ቄራ የሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲፈቱ ትእዛዝ ቢሰጥም የሕወሃት ፖሊሶች እንደገና የፍርድ ቤትን ትእዛዝ ጨፈለቁ። በነጋታው፣ ስኔ 16 ቀን፣ እነ ወይንሸት ሞላን እንደ ወንበዴ፣ የፍርድ ቤት መዛዣ ሳይዙ አፍነው ወሰዱ።

እንግዲህ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይችን ትመስላለች። ኢትዮጵያዉያንን ልብን በሚያደማ ሁኔታ ፣ ስልጣኔ ባልገባቸው፣ በቂምና በጥላቻ በተሞሉ ፣ ከጫካ አስተሳሰብ ባልተላቀቁ፣ ፍጹም ኋላ ቀርና ዓዉሬ በሆኑ ዘረኞች፣ አንገታችቸው ደፍተው፣ ፈርተዉ፣ ተሽማቀውና ተዋርደው፣ ጥቅሮች በአፓርታይድ ዘመን ይኖሩ እንደነበረው በባርነት የሚኖሩባት አገር !!!

ደግነቱ ግን ባርነት፣ ጭቆና በቃን ብለልው የተነሱ በብዛት ያሉበት፣ ትዉልድ ነው የአሁኑ ትዉልድ። “በሀገራችን፣ ብዙ እንስቶቻችን በፍርሃት ወጥመድ ሥር ወድቀው፣ በጣም ልስልስ የሆነ የህይወትን መስመርን ምርጫቸው አድርገውና ‹‹ፖለቲካን በሩቁ!›› በሚል መሪ ቃል የዘወትር ድግግሞሻዊ ሕይወት ውስጥ በምርጫ እየተጓዙ ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ፣ እንደወይንሸት አይነት ጥቂቶችን በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ስመለከት እንደኢትዮጵዊ ዜጋ ደስታን ይፈጥርብኝ ነበር” ሲል እንደጻፈው ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ፣ እኔም እንደ ወይንሸት ያሉ ፣ ብረትና ታንክ የማይፈሩ፣ “ነጻነቴን ከምትወስዱብኝ ሞቴን ስጡኝ” የሚሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየበዙ መምጣታቸው በርግጥ ኢትዮያጵያችን የምትታሰብበት ጊዜ መድረሱን፣ የጨቃኝ፣ ቂመኛ፣ ከፋፋይና ዘረኛ አገዛዝም ፍጻሜ መድረሱን የሚያሳይ ነው።

http://satenaw.com/amharic/archives/8107