Saturday, December 27, 2014

ከድንበር ጋር በተያያዘ በአማራና በትግራይ ክልል ከፍተኛ ውጥረት ነግሶአል


ታኀሳስ ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ታህሳስ 16 ቀን 2007 ዓም በሶረቃ ከተማ ከ70 ያላነሱ ከትግራይ ክልል የመጡ ታጣቂዎች፣ ከምስላል ወደ ስላንዴ በረሃ የሚሰራውን መንገድ ለማስቆም ተኩስ በመክፈታቸው 2 አርሶ አደሮች ሲቆስሉ፣ በአብራጅራ ወረዳ የሚገኙ ጸረ ሽምቅ እየተባሉ የሚጠሩ ሃይሎች ከህዝቡ ጋር በመሆን የአጸፋ ተኩስ በመክፈታቸው ታጣቂዎች ከአካባቢው ተሰውረዋል።

ፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው በመሄድ ህዝቡን ለማነጋገር ሙከራ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በኩል ያሉ የአራት ወረዳ ህዝብ እስከ ታህሳስ 30 ድንበራችን ካልተከለለ እና የታሰሩ ሰዎች ካልተፈቱ እርምጃ እንወስዳለን በማለት ማስጠንቀቃቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል 


ሌሎች ወገኖች እንደሚሉት ደግሞ የትግራይ ክልል እያስታጠቀ የሚልካቸው ታጣቂዎች በአማራ ክልል ያሉ ብአዴኖችን እያስቆጣ ነው። ግጭቱንም የሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ግጭት አድርገው የሚወስዱት ወገኖች አሉ። ሁለቱም ክልሎች የድንበር ችግሩን እስካሁን ለመፍታት አለመቻላቸው በአካባቢው ለሚነሳው ተደጋጋሚ ግጭትና ለሚጠፋው የሰው ህይወት ምክንያት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ህወሃት ስልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያዎቹ አመታት ከአማራ ክልል መሬት በመውሰድና ወደ ትግራይ በማካለል የቀድሞ የህወሃት ታጋዮችን አስፍሮበታል በሚል በተደጋጋሚ እንደሚተች ይታወቃል።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37552

Friday, December 26, 2014

የአምባሰደሩ የአንዳርጋቸው ጽጌ ጉብኝት ተከትሎ የእንግሊዛዊ ቱሪስት የተቀነባበረ ግድያ ድንጋጤ ፈጥሯል::

የባህር ዳሩ ገዳይ ካለምንም ጥያቄ በቀጥታ ለፖሊስ እጁን ሰቷል::

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ካሳንቺስ ከቀድሞ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ጀርባ ከሚገኘው ድብቅ የደህንነት እስር ቤት ውስጥ በመገኘት በከፍተኛ የሴኩሪቲ ጥበቃ የነጻነት ታጋይ የሆነውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር Greg Dorey እንዳነጋገሩ ሲታወቅ ከአንዳርጋቸው ጋር ያደረጉትን ቆይታ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ባይገኝም በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሲገልጹ የኤምባሲው ምንጮች እንዳሉት ስለ አንዳርጋቸው መረጃ ያላቸው ለስርአቱ ቅርብ የሆኑ ክፍተኛ የደህንነት አባላት እና የአንድ ብሄር ተወላጅ የሆኑ አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሆኑ ገልጸዋል::እንዲሁም አመነስቲ ኢንተርናሽናል አንዳርጋቸውን በተመለከተ ከታፍነ 6 ወር መሆኑን ገልጾ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ሲል ለእንግሊዝ መንግስት አቤት ያለበተን መግለጫ ባሳለፍነው ሳምንት መግለጫ አውጥቶ ነበር::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ድብ አንበሳ እየተባለ በሚጠራው ሆቴል አካባቢ አንድ አርሶ አድር ታጣቂ ሚሊሻ በሚመስል ጸጉረ ልውጥ ሰው የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ቱሪስት መገደሉ ታውቋል::የአምባሰደሩ የአንዳርጋቸው ጽጌ ጉብኝት ተከትሎ የእንግሊዛዊ ቱሪስት መገደል ድንጋጤ ፈጥሯል::ገዳዩ ለግድያው እንደተዘጋጀበት በሚያስታውቅ መልኩ በአከባቢው አድብቶ ሲጠባበቅ የነበረ እና ወዲያው እንግሊዛዊውን እንደገደለው ለፖሊስ ያለምንም ጥያቄ እጁን ሰቷል::በአከባቢዉም የታጠቁ ፖሊሶች የነበሩ ሲሆን ግድያው ሲፈጸም ምንም ያደረጉት መከላከል አልነበረም::ግድያው የተቀነባበረ ነው ሲል የባህር ዳር ህዝብ እየተናገረ ነው::
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)
http://satenaw.com/amharic/archives/3175

ኢትዮጵያዊውን የገደለው ቻይናዊ ‹‹ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት›› ሲባል ክሱ መቋረጡ ተጋለጠ

በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ውስጥ ኢትዮጵያዊውን የገደለው ዠንግ ቢንዥንግ የተባለ ቻይናዊ ‹‹በቸልተኝነት ሰው በመግደል›› ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የነበር ቢሆንም ‹‹ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት›› በሚል ትዕዛዝ ክሱ መቋረጡን ከክልሉ ፍትህ ቢሮ የተገኘው ሰነድ አጋለጠ፡፡የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለአቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ተከሳሹ ካሳ ከፍሎ መውጣቱ ለሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት እንደሚበጅ በጻፈው ደብዳቤ ክሱ እንዲቋረጥ መደረጉን ‹‹በአማራ ፍትህ ቢሮ የምዕራብ ጎጃም ዞን የፍትሕ መምሪያ የወንጀል መዛግብት መርምሮ መወሰንና ተከራክሮ ማስወሰን የስራ ሂደት›› ለሰሜን አቸፈር ፖሊስ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ተመልክቷል፡፡ በትዕዛዙ መሰረትም ክሱ ቀሪ ሆኖ የምርመራ መዝገቡ ተመላሽ መደረጉን በደብዳቤው ላይ ተገልጾአል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37535

Wednesday, December 24, 2014

በነ ሀብታሙ አያሌው የክስ ጉዳይ የተሰየመው ችሎት ‹አስገራሚ› ውሎ፣ ተከሳሾቹ ‹‹ዘረፋ›› ተፈጽሞብናል ብለዋል

December 24, 2014

∙ተከሳሾቹ ‹‹ዘረፋ›› ተፈጽሞብናል ብለዋል !! ∙‹‹ለማን አቤት ይባላል?›› ሀብታሙ አያሌው
ዛሬ ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር፡፡ የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ተሟልተው ፍርድ ቤት ተገኝተዋል፡፡

ችሎቱ የተሰየመው ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ተከሳሾች በቀረበባቸው የሽብር ክስ ላይ የሰጡትን መልስ በተመለከተ 7ኛ ተከሳሽ መልስ በዕለቱ ባለማቅረባቸው አሟልተው እንዲቀርቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ስለነበር ይህን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ማብራሪያውን ለመስማት ነበር፡፡

የተከሳሾች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በጥየቃ ወቅት በተለየ መዝገብ ይመዘገባሉ የተባለውን አቤቱታ በተመለከተ፣ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደብዳቤ መልስ መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ‹‹ማረሚያ ቤቱ በሰጠው መልስ እስረኞች ከሌሎች በተለየ የደረሰባቸው ችግር የለም›› ማለቱን ገልጾ ይህንኑ መልስ ሙሉ ለሙሉ መቀበሉን አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በዛሬው የችሎቱ ውሎ ላይ ተከሳሾች ለየት ያለ አቤቱታ በጠበቆቻቸው በኩል አቅርበዋል፡፡ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ለችሎቱ እንዳስረዱት ደንበኞቻቸው ከሌሎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ አቶ ተማም አባቡልጉ በታህሳስ 12 ለ13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀምሮ ደንበኞቻቸው ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የግል ማስታወሻዎቻቸው፣ ገንዘብ እና በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ እያዘጋጁት የነበረው መቃወሚያና መከራከሪያ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹ደንበኞቼ ላይ እየተደረገ ያለው ጉዳይ ለህይወታቸውም የሚያሰጋቸው ነው፡፡ በማረሚያ ቤቱ በሌሊት ፍተሻ ያደረጉባቸው ሰዎች ቀደም ሲል በምርመራ ወቅት ‹ህገ-ወጥ› ተግባራት ሲፈጽሙባቸው የነበሩ የፌደራል ፖሊስና የደህንነት አባላት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ደንበኞቼ ያውቋቸዋል፡፡ ስለሆነም ፍተሻው የተከናወነው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አልነበረም ማለት ነው፡፡ 
ድርጊቱ የተፈጸመው የተለየ የስም ዝርዝር ተይዞ ከሌሎች በተለየ መልኩ ነው፡፡ ለአብነት ደንበኞቼ አቶ አብርሃ ደስታና በሌላ የክስ መዝገብ የተከሰሰው አብዱራዛቅ አክመድ ላይ የሆነው ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ነው፡፡ ፍተሻው ስለት ነገር አልያም ሌላ ህገ-ወጥ ቁሳቁስ ለመያዝ የተደረገ አለመሆኑን ከተወሰዱት ንብረቶች ማየት ይቻላል›› ሲሉ አቶ ተማም ለፍርድ ቤቱ በደንበኞቻቸው ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አስረድተዋል፡፡

ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ‹‹ማረሚያ ቤቱ መንግስት ዜጎች ታንጸው እንዲወጡ ያሰራው ነው፡፡ ይህን አሰራር ለመጠበቅም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ ስራዎችን ሊሰራ ይችላል፡፡ እየቀረበ ያለው አቤቱታም ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ነው›› ብለዋል፡፡

ጠበቃ ተማም የደንበኞቻቸውን አቤቱታ ከህግ አንጻር ያስረዱ ሲሆን፣ ‹‹በመሰረቱ ፍተሻ ሊካሄድ መቻሉ ላይ አይደለም አቤቱታው፡፡ የተካሄደው ፍተሻ ግን ህገ-ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍተሻው የተከናወነበት ሰዓት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ሳይሆን ሌሊት 8 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ፍተሻው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አይደለም የተከናወነው፡፡ በደህንነቶችና የፌደራል ፖሊሶች ነው ፍተሻው የተደረገው፡፡ ይህም ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ እንደሌለው ያሳያል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙት አካላትና በማን ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡

ጠበቃ ተማም በተጨማሪ ከደንበኞቻቸው ላይ በፍተሻው ወቅት የተወሰዱባቸው ንብረቶችና ማስታወሻዎች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ‹‹የተለየ ከፍተኛ በደል ደርሶብኛል›› በሚል ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበሩት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የጠየቁት የመናገር እድል ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል፡፡

በጠበቆቹ አማካኝነት የቀረበው አቤቱታን በተመለከተ ችሎቱ አስተያየት የሰጠ ሲሆን በተለይ ጠበቃ ተማም አቤቱታውን ባቀረቡበት ወቅት ‹‹ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎትም ብቃትም የለውም›› ያሉት አገላለጽ ተገቢ ስላልሆነ እንዲታረሙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በቃል የገለጹት የመሐል ዳኛው፣ ‹‹እንዲህ አይነት አገላለጽ ማረሚያ ቤቱ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋ እንዳይሆን…›› በማለት ሌላ አስገራሚ መነጋገሪያ ከፍተዋል፡፡

ይህን የዳኛውን ንግግር ተከትሎ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌው የመናገር እድል ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ ለአጭር ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡ እናም፣ ‹‹እርስዎ እያሉት ያለው ነገር ተገቢ አይደለም፡፡ በህይወቴ ላይ የደህንነት ስጋት አለብኝ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ይህንን ስጋቴን ለችሎት እያስረዳሁ ነው፡፡ ግን እርስዎ ‹የበቀል እርምጃ› እንዲወሰድብን ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ በእርግጥ አሁንም የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድብን ማረጋገጫ የለንም፡፡ እሺ ለማን አቤት ይባላል? የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት ከማስረዳት ውጭ ለማን አቤት እንላለን….አሁን እኮ ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤቱ ጋር መወገኑን ነው እያየን ያለነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የእኛን አቤቱታ እየሰማ አይደለም፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ ለማን አቤት እንበል?›› ሲል አቤቱታውን በስሜት ውስጥ ሆኖ አስረድቷል፡፡

የሀብታሙን ንግግር አዳምጠው አንደኛ ዳኛ ‹‹እኛ ሳንሆን ህጉ ነው ይህን እንድንል የሚያደርገን›› በማለት አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡


በዚህ መልኩ ቀጥሎ የዋለው ችሎት በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ፍርድ ቤቱ ይህን ጉዳይ የማየት ስልጣን አለው ወይስ የለውም በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት፣ እና መደበኛ ክሱን ለማየት ለታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተጥቷል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37482

መንግስት ተጠለፈብኝ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሔሊኮፕተር አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ

መንግስት ሄሊኮፕተሬ ተጠለፍብኝ ካለ በኋላ ሪፖርተር ጋዜጣም ዛሬ የሚከተለውን ዜና አስነብቧል:: ለግንዛቤ ይረዳዎታል ያንብቡት::


የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንብረት የሆነ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ባለፈው ዓርብ ተጠልፎ ኤርትራ ግዛት አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ፡፡ የዘወትር የበረራ ልምምድ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሩሲያ ሠራሽ ኤምአይ 35 ተዋጊ ሔሊኮፕተር ይዞ ወደ ኤርትራ የኮበለለው ዋና አብራሪ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ ይህንን ዓይነት ተግባር ይፈጽማል ብለው እንደማያስቡ ባልደረቦቹ ገልጸዋል፡፡

ከሻምበል ሳሙኤል ጋር በኢትዮጵያ አየር ኃይል አብረው የሠለጠኑና የሠሩ የሥራ ባልደረቦቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግለሰቡ መልካም ባህሪ ያለውና በፖለቲካ አቋሙ ገለልተኛ የሚባል ነው፡፡ ‹‹እጅግ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚ አልነበረም፡፡ ራሱን ከፖለቲካ ጉዳዮች የሚያገል፣ ሥራውን ብቻ የሚሠራና ልጆቹን በኃላፊነት የሚያሳድግ ሰው ነበር፤›› ብለው በድርጊቱ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በትንሽ ነገር የሚከፋና የሚደሰት፣ በቅጽበት የሚለዋወጥ ባህሪ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በግል ሕይወቱም የሚበሳጭበት ጉዳይ እንደነበርና አልፎ አልፎም በዚሁ ጉዳይ ይደበት እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ ሻምበል ሳሙኤል ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል የገባው በ1994 ዓ.ም. ሲሆን፣ የቅጥር ውል የፈረመው በታህሳስ ወር 1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ለ12 ዓመታት አገልግሏል፡፡ በ2003 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ወደ ዳርፉር ሱዳን ያሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል በመሆን ለአንድ ዓመት ያህል እንዳገለገለና በዚያም ተልዕኮ ዳጐስ ያለ ዶላር ይዞ መመለሱን ባልደረቦቹ ተናግረዋል፡፡

ሻምበል ሳሙኤል ተወልዶ ያደገው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ መሆኑን፣ ወላጆቹ የመቀሌ ነዋሪ መሆናቸውን ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ቢሾፍቱ እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለፈው ዓርብ ማለዳ ከረዳት አብራሪው መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝና የበረራ ቴክኒሺያን ፀጋ ብርሃን ግደይ ጋር በኤምአይ 35 ተዋጊ ሔሊኮፕተር የዘወትር የልምምድ በረራ ለማድረግ ከጠዋቱ 2፡35 ሰዓት ድሬዳዋ ከሚገኘው የአየር ኃይል ቤዝ እንደተነሱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዋና አብራሪው ከአጭር ጊዜ በረራ በኋላ የበረራ ከፍታውን በመቀነስ ወደ ኤርትራ በማቅናት ሔሊኮፕተሩን አሰብ ማሳረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ ተዋጊ ሔሊኮፕተሩን ዋና አብራሪው ይዞ ወደ ኤርትራ መኮብለሉን አምኗል፡፡ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ዋና አብራሪው ቴክኒሺያኑንና ረዳት አብራሪውን በማስገደድ ኤርትራ ማረፉን አስታውቋል፡፡

ሔሊኮፕተሩ ባለፈው ዓርብ ከጠዋቱ 2፡35 ሰዓት ጀምሮ በመደበኛ የሥልጠና ልምምድ ላይ እንደነበር ጠቅሶ፣ ሔሊኮፕተሩ ከግንኙነት ውጪ በመሆኑ ሠራዊቱ በአካባቢው ማኅበረሰብና አጋሮች ለተከታታይ ቀናት ፍለጋ ሲደረግለት መቆየቱን አትቷል፡፡

‹‹ሆኖም ሔሊኮፕተሩ በከሀዲው ዋና አብራሪ አማካይነት ቴክኒሻንና ረዳት አብራሪውን በማስገደድ ኤርትራ ማረፉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፤›› ብሏል፡፡ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች ዋና አብራሪው የሔሊኮፕተሩ አዛዥ በመሆኑ የትም ወስዶ ሊያሳርፈው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

‹‹ረዳት አብራሪው ጀማሪ ነው፡፡ የበረራ ቴክኒሺያኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን መከታተል ነው፡፡ ዋና አብራሪው ረዳት አብራሪውና ቴክኒሺያኑ እያወቁም ወይም ያለነሱ ዕውቅና የፈለገበት ወስዶ ሊያሳርፍ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ወር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ጠንከር ባለ ግምገማ ተወጥረው መክረማቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር መትረየስና ተወንጫፊ ሮኬቶች የተገጠሙለት ዘመናዊ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ነው፡፡ ከኋላው ስምንት ወታደሮችን ወይም ሁለት የቁስለኛ አልጋዎችን መያዝ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኤምአይ 17 እና ኤምአይ 8 የትራንስፖርት ሔሊኮፕተሮች ሲኖሩት፣ ለውጊያ የሚጠቀምባቸው በደርግ ጊዜ የተገዙ ኤምአይ 24 ሔሊኮፕተሮችን ነበር፡፡

 በግንቦት 1990 ዓ.ም. የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር አሥር ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተሮች የተገዙ ሲሆን፣ በጦርነቱ ወቅት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

የ1997 ዓ.ም. ሦስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ የተነሳውን ግርግር ተከትሎ ሁለት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች (ሻምበል አብዮት እና ሻምበል በኃይሉ) አንድ ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር ይዘው ወደ ጐረቤት አገር ጂቡቲ መኮብለላቸው ይታወሳል፡፡

ብዙም ሳይቆይ የጂቡቲ መንግሥት አብራሪዎቹን አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠ ሲሆን ሔሊኮፕተሩንም መልሷል፡፡

 አብራሪዎቹ የጦር ፍርድ ቤት ቀርበው በአሁኑ ወቅት በእስር እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ ወቅት በቤላሩስ በሥልጠና ላይ የነበሩ ሰባት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኤስዩ 27 ተዋጊ ጀት አብራሪዎች ከድተው ጥገኝነት መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ አብራሪዎቹ በተለያዩ የምዕራብ አገሮች ጥገኝነት ማግኘታቸው ይነገራል፡፡

ቀደም ሲል ሻምበል ተሾመ ተንኮሉ የተባለ የአየር ኃይል ባልደረባ በ1995 ዓ.ም. ኤል 39 የተሰኘ የመለማመጃና ቀላል የውጊያ አውሮፕላን ለልምምድ በረራ ከመቀሌ ቤዝ ይዞ እንደተነሳ ወደ ኤርትራ ኮብልሎ ነበር፡፡


እስከ ማክሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የኤርትራ መንግሥት ስለተጠለፈው ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጠም፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37480

Monday, December 22, 2014

የሚሊዮኖች ድምፅ የመጀመሪያው በባህርዳር በቅርቡ ይደረጋል! ለትውስታ በ feb.24.2014 በባህርዳር የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ይህን ይመስል ነበር ( ቪዲዬ )

Dec.22.2014

ገዢው ፓርቲ ሕወሃት/ኢሕአዴግ የእምነት ነጻነትን በመጋፋት ፣ ታቦት ቢወጣበትና የጥቅምት በዓል በሚከበርበት በባህር ዳር የመስቀል አደባባይ “ልማት” በሚል ስም ለባለሃብቶች ቦታዎች ሊሰጥ ማሰቡን ተከትሎ ሕዝቡ ለአስተዳደሩ ብሶቱን በደብዳቤ ለማስገባት፣ በቦታው ሄዱ ለማነጋገር ቢሞክር፣ ለሕዝብ ጥያቄ ደንታ የሌላቸው የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት፣ ቦታውን ለባላሃብቶች ለመስጠት በመወሰናቸው፣ ሕዝቡ የእምነት ነጻነቱን ለማስከበር ባለስልጣናት ዉሳኔያቸዉን እንዲቀለብሱ ለማድረግ፣ በራሱ አነሳሽነት ፣ በሺሆች በመሆን ሰለፍ መዉጣቱ ይታወቃል።
ሆኖም በሰላም የወጣው ሕዝብ ላይ ተኩስ የከፈቱት ደህንነቶች ከአምስት ያላነሱ ዜጎችን የገደኩ ሲሆን፣ በርካታዎችን አቁስለዋል። በአገሪቷ በሙሉ መዋቅር ያለው አንድነትለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን የሚያካድ እንደሆነ የሕዝብ ግንኑነት ክፍላ ሃላፊው አቶ አስራት አብራሃም የገለጹ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሰልፉም የሚጀመረው በባህር ዳር ከተማ እንደሆነ ለማወቅ ትችሏል። “ የመጀመሪያው ሰላማዊ ሰልፍ የወንድሞቻችንና የእህቶቻቸን ደም ባለፈው ሳምንተ በፈሰሰባት ባህርዳር ከተማ ይሆናል” ያሉት አቶ አስራት ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጹንም እንደሚያሰማ ያላቸውም እምነት ገልጸዋል።
በባህር ድር የሚደረገውን የሚሊዮሞች ድምጽ ሰልፍ መኢአድ ከአንድነት ጋር በጋራ የሚሰራ፣ የቅድመ ዉህደት ስምምነትም ያደረገ እንደመሆኑ ይቀላቀላል የሚል እምነት ያለ ሲሆን፣ በሰማያዊ በኩል ግን ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም።
የአንድነት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ ዉጭ ከተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች መካከል በአይነቱም ሆነ ብብዛት ደማቅ ሰላማዊ ስለፍ በባህር ዳር ማድረጉ ይታወሳል። በወቅቱ ወደ ሶስት መቶ ሺህ ከሚጠጋ የከተማዋ ነዋሪ ወደ 80 ሺህ የሚሆነው በሰልፉ መገኘቱ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማስታወስ የሚከተለውን ይመልከቱ


http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/16650

Saturday, December 20, 2014

የገዢው መንግስት ወታድሮች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ እየወሰዱ ያሉት እርምጃ እንዲቆም የሃይማኖት አባቶች ጠየቁ፡፡


ታኀሳስ ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በትላንትናው እለት በባህርዳር ከተማ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የገዢው መንግስት ወታደሮች በህዝቡ ላይ እያደረሱ ያለውን ተመጣጣኝ ያልሆነ  እርምጃ የባህርዳር ከተማ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በአስቸኳይ እንዲያቆም በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የሃይማኖት አባቶችን ከሁለት ቀን በፊት በመሰብሰብ በመስቀል አደባባይ ላይ ሊሰሩት ያሰቡትን ጉዳይ እንዳወያዩዋቸው የገለጹት የሃይማኖት አባቶች ይህንን ጉዳይም ለሚመለከታቸው የእምነቱ ተከታዮች ለማሳወቅ ቢነጋገሩም የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ግን  በሁለተኛ ቀኑ የአጥር  ማፍረስ ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህን ጉዳይ በመያዝ ወደ ምዕመኑ ተወካዮች በቀረቡ ጊዜም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳላገኘ ሊቀ አዕላፋት ራዳዊት እንግዳው የገለጹ ሲሆን በተወካዮች የቀረቡት ጥያቄዎችን ሲናገሩ   ́በሚወሰደው መሬት ምትክ የሚሆን ቦታ እንዴት እናገኛለን ? ʼ  ́ለባእለ ጥምቀቱ መሰናክል አይሆንብንም ወይ  ? ʼ የሚል ተቀባይነት ያለው ጥያቄ  በማቅረብ ህዝቡ እየበዛ የባእሉ አከባበር እየሰፋ በመሄዱ የምትክ መሬቱ ጉዳይ መነሳቱን የሃይማኖቱ አባት ተናግረዋል፡፡ ሊቀ አዕላፋት በመግለጫቸው አክለው እንደተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ ሳይኖሩ ይህን ለማሰባሰብ ይቻልወታል ወይ? በማለት ሊቀ ጳጳሱ ሳይኖሩ መሰባሰብና ውሳኔ መስጠቱ አግባብ እንዳልሆነ በእርሳቸው ላይ ጥያቄዎች  መቅረባቸውን አልሸሸጉም፡፡

ምእመኑ ይህን ጉዳይ ከሰማ በኋላ የመስቀል አደባባይ ትክ ሳይሰጥና የጥምቀት በአል ሊከበር አንድ ወር ብቻ በቀረበት ጊዜ አጥር ማፍረስና  ቁፋሮ ለመጀመር የከተማ አስተዳደሩ እንቅስቃሴ መጀመሩ የበዓሉን ሂደት ሆን ብሎ ለማበላሸት ነው በሚል ዓርብ ከጠዋቱ በአንድ ሰዓት በፈለገ ጊዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ቅጥር ግቢ በመገናኘት ተቃውሟቸውን ለማሰማት እንደ ተሰባሰቡ የሃይማት አባቱ ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ችኩልነቱን በመተው እንዲያስብበት ህዝቡም ተጮኸ ሲባል ለወገኑ ፈጥኖ መድረስ ለነገ የሚባል ነገር  አይደለም በማለት ተናግረዋል፡፡

በመግለጫው አሰጣጥ ላይ ከተገኙት በርካታ የሃይማኖት አባቶች መካከል  የፈለገ ጊዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን የወከሉት አባት ሲናገሩ  ጥያቄው አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ሳይጣራ የቅዱሳንን ምስል በመያዝና መንፈሳዊ መዝሙሮችን በማሰማት ተቃውሞውን በሚገልጽ ምዕመን ላይ ድብደባ መካሄድ እና በጥይት እርምጃ መውሰድ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸው፤መንግስት ጉዳዩን በተረጋጋ መንፈስ በማየት ስራውን ሊሰራ የሚችልበትን መንገድ እንዲያመቻች መንግስትን ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በትላንትናው እለት  በሰላማዊ ሰልፉ በተሳተፉ ምዕመኖች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን የፌደራል ፖሊሶች በመንገድ ዳር ሁለት ወይም ከዛ በላይ ተሰባስበው የሚቆሙ ማንኛውንም የከተማዋ  ነዋሪዎች ያለ ርህራሄ በዱላ በመምታት እንደሚበትኑ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች እና የክልሉ ካቢኔ ባደረጉት ምክክር ማምሻውን እንደተነገረው በተገደሉ የተቃውሞ ሰዎች እና መብታችውን በጠየቁ ንፁሃን ላይ የተወሰደው እርማጃ ቀጣዩ ምርጫ አደጋ ነው ሲሉ ርዕሰ መሰተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለካቢኔው ተናግረዋል፡፡ ምሺቱን በሰላም አርጊው ማርያም ቤተ ክርስቲያ ፆለተ ፍትሃት ተደርጎላቸው ቃብራቸው በተፈፀመው አራት ወጣቶች እና አንድ የቆሎ ተማሪ ላይ እንኳን ተገኝቶ ሃዘኑን የገለፀ አንድም የመንግስት አካል ባለመኖሩ ‹‹ ምሺቱ በቅዱስ ጊዩርጊስ ቅዱስ ሚካኤል እና በቤተክርስቲያን አድባራት እና ገዳማት ምዕመናኑ ተቃውሞውን ሲያሰማ ያመሸ ሲሆን ‹‹ ገዱ አይመራንም›› መንግስት የለንም›› ስርዓቱን ለማፍረስ ምርጫው ጦርነት ነው፡፡ ፖሊሲ እና መከላከያ የኛ አይደሉም የፖለቲካ ፓርቲ ናቸው፡፡ ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡  በቀብሩ ላይ የአንዱ ስርዓቱን የጠበቀ ሲሆን የአራት ወጣቶች ግን በቀጥታ እንዲፈፀም የምንዕራብ ዕዝ ጦር  እና የፊድራል ፖሊስ ውሳኔ መሰረት ፍታሀተ ጸሎት ሳይደረግ አፈር ለብሰዋል፡፡

በባር ዳር እና በአማራ ህዝብ ላይ ከባድ ጠባሳ እንደሚሆን የመከረው መድረኩ ልማቱን ካልፈከለጋችሁ ሊቀሩ ይችላል እየተባለ የፊዝ እና ስላቅ መግለጫ መሰጠቱ ህዝቡ እንዳልተቀበለው የኮሚኒኬሺን ጉዳይ ለመድረኩ ገልፆል፡፡ የአመፁ እና መብታቸውን የጠየቁ ህዝቦችን አሸባሪ ሲል የፈረጀው የመንግሰት አካል ፤ሁከቱን የፈጠሩት ማህበረ ቅዱሳን እና የሰንበት ትምህርት ቤት አሰተባባሪዎች ናቸው ሲል ሃሳብ ቢያቀርብም፣  የመንግስት የደህንነት ሰዎች በበኩላቸው በተነሳው ተቃውሞ ማህበረ ቅዱሳን እጃቸው የለበትም ሃሳቦ በመሉ ህዝበ ክርስቲያን የወከለ ነው ብለዋል፡፡

ምሺቱን ቤት ለቤት ወጣቶች እየታሰሱ ተይዘዋል።  ምሽተና ሌሊቱን በየመንደሩ ጩህት እና ልመና ይሰማ ነበር።  በርካቶች በግዳጅ ቤቶችን እየበረገዱ በሚገቡ የፊድራል ፖሊሶች በሰደፍ እና በዱላ  ተደብድበዋል። 36 የሚሆኑ ወጣቶች በሁለተኛ እና በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሌሊቱን ታስረዋል፡፡

ባበንዴ,ራው እና በኢትዩጵያ አምላክ ሲለምኑ ያደሩት እናቶች  እየተደበደቡ ልጆቻቸውን ከጉያቸው ሲነጠቁ ማመሸታቸውን ያይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ልጆቻቸውን ከገዳይ የፖሊስ ቅጥረኛ ሃይሎች ለመታደግ ወላጆች በአልጋ ስር እና በጣራ ሲደብቁ ያደሩት እናቶች የልጆቻውን መደብደብ እና በደል በእሪታ ሲያሰተጋቡ ሌሊቱን ማሳለፋቸውን  ወኪላችን ገልጻለች፡፡

ደርግ ተመልሶ መጠዋል ያሉት ያይን እማኞች መንግሰት  እና እኛ በቅቶናል ተለያይተናል ብለዋል፡፡ የእምነት አባቶች ከምንግሰት ጋር በመወገን በሰጡት መግለጫ ምሺቱን ህዝቡ ቤታቸውን ከቦ በማደሩ እና እርማጃ እንወስዳላን ማለቱን ተከትሎ በመግለጫው የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች በፖሊስ እና በደህንንት እየተጠበቁ ነው፡፡

በሌላ በኩል በርካታ አስተያየቶች በኢሳት ፌስ ቡክ ላይ ቀርበዋል። የተወሰኑት እንደሚከተለው ቀርበዋል።ወያኔዎች የአላህን ፍርድ ታዩታላችው እንደዚህ እንደጠገባችሁ አትኖሩም!! መቸ ትፈርዳለህ አምላክ ለልጆችህ!!ለሞቱት አባቶቻችንና ወድሞቻችን የሰማታትን በረከት ይስጥልን።ግን መገፋታችን እስከ መቼ……………………?

እኒን የሚገርመኝ በባዶ እጁ የወጣ ሕዝብ ላይ ይሄን ሁሉ ጥይት መተኮስ ምን አመጣዉ ??

እረ ጎበዝ እኔ ሙሥሊም ነኝ ግን የማንኛውም እምነት መነካት የለበትም ግን አንድ ጥያቄ ለኢትዬጲያ ህዝብ መጀመሪያ ሙሥሊሙን ሲያጠቃ ዝም አልን አሁን ደግሞ እምነት የለሹ ኢህአዴግ አፈሙዙን ወደ ኦርቶዶክሥ እሺ ከዚህ በላይ ምንድን ነው ምንጠብቀው አሁን ሙሥሊም ክርሥቲያን ሳትል ሁልህም በአንድ ካልቆምክ ውርደቱ የሀገር ነው ልብ ያለው ልብ ይበል

በጣም ያሳዝናል:ወያኔ ህግ አለ ዲሞክራሲ ከደርግ በተሻለ አምጥተናል እያሉ ወሪያቸው በጎተራ የሚላካ አረመኔዎች የሰው ደም እንደውሃ የሚጠጡ ጅቦች : የደሃዎች ነብስ እግዚአብሔር ይማር ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

ኢትዮጲያዬ! ሙስሊም ክርስቲያኑ ተፋቅሮ ተዋዶ፣ ተሳስቦ ሚኖርባት፣ የጥቁር ህዝብ መመኪያ፣ ያኩሪ ድንቅ ባህል ባለቤት፣ ጥንት ጠላት እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ ቢመጣ መለኮታዊ እሳትን (ታቦተ ጊዮርጊስን) ተሸክማ ወራሪ ፋሺስት ጣሊያንን ያሳፈረች የእነ ጴጥሮስ ሀገር ዛሬ ምነው ሀሞቷ ፈሰሰ? የአባት የእናቶቿ የጀግንነት መንፈስ ከወዴት ተለያት? ስንቱ ጀግና እንዳልተፈጠረባት የወላድ መካን ይመስል ዛሬ በቀኝ አገዛዝ ስር ወድቃ እንዲህ ነጻነቷን ትጣ፣ አሁን ወዴት ይኬዳል? ወደማንስ አቤት ይባላል? አልበዛም እንዴ ወገን? ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መገዳደር ለማንስ ጠቀመ? ለፈርኦን ወይስ ለጎልያድ? ዛሬ የመሸ ቢመስል ሊነጋ ሲል እንዲጨልም ማን በነገረው።

አፎይ ኣረ ውስጤ ተቃጠለ መተማንም ሸጠ የጤና ሳይንስ ኮሌጆችን ክፍያ አቁኣርጦ የተማሪዎችን ስነልቦና ሲጎዳ ቆየ የሰውን ጤና ደግሞ ከጣውላ ጋር መደበ ስለዚ ኢሀዲግ ከስሩ ካልተነቀለ አማራ ክልል ሰላም የለንም!!!!ለማነኛውም ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚኣብሄር ይጠብቀን።አሜን!!

ይህ መንግስት ህዝብን ሊበላ ሊገድል ሀገርን ሊያወድም የቆመ አረመኔ ወንበዴ ስብስብ ነው ይህን ሰላማዊ ህዝብ ምን አድርግ ብለው ነው ይህን ሁሉ ሲቃይ ሚያወርዱበት መብቱን ፍላጎቱን የመግለፅ ነፃነቱን ለምን ይገፈዋል  እውን እውነት ለሃገሪቱ ያሚያስብ መሪ ቢኖርር ይህ ይደርስ ነበር

ይህ መንግስት ለዜጎች እንደማይጨነቅ አሳይቶናል የእምነታችን ነፃነት ገፎናል ስለዚህ የአንዱ መብት ሲጣስ ሌላው ዝም ማለት የለበትም ሁላችንም አንድ ወገኖች ነንና ስለዚህ ለመብትህ ማስከበር ሁልህም ተነስ። እንደዚህ ተባለ ብቻ ምንም ዋጋ የለዉም

ማሰር፣ መደብደብ፣ማሳደድ፣ ማሸማቀቅ፣መግደል፣ እና የሕዝብ ንብረትና ሀብት መንጠቅ አንድን መንግስት ስልጣን ላይ የሚያቆይ ብሆን ኖሮ ደርግ አይወድቅ ነበር። ኢህአዴግ ኢትዬጵያን በቀጣይ ዓመታትም እኔ ብቻ አስተዳድራለሁ ብሎ ከማሰብ ቢቆጠብ ጥሩ ነው።

መዉረጃዉ የደረሠ ተሳፋሪ ያንቀዠቅዠዋልም አይደል የሚባለዉ

http://ethsat.com/amharic/%E1%8B%A8%E1%8C%88%E1%8B%A2%E1%8B%8D-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%8B%88%E1%89%B3%E1%8B%B5%E1%88%AE%E1%89%BD-%E1%89%A0%E1%8A%A6%E1%88%AD%E1%89%B6%E1%8B%B6%E1%8A%AD%E1%88%B5/