Thursday, September 8, 2016

” . . . . . የደም እንቁጣጣሽ . . . . . .”

በዝናም ማበቡ: ዘመን ተሽሮብሽ፣
ያልተለመደ ግብር: ዘንድሮ አየንብሽ፣
ያፈራሽውንም: አንችው ትበያለሽ፣
ምንድነው የሆንሽው: እስኪ ልጠይቅሽ
አብቅለሻል አሉ: የደም እንቁጣጣሽ።

ነሐሴን ስጠብቅ: ጳጉሜም ስትገባ፣
ጋራውን እያየሁ: ስወጣ ስገባ፣
ላዲስ ዓመት ልቆርጥ: የአደይ አበባ፤
አልፈነዳ ብሎ: የቋጠረው እምቡጥ፣
ዓይኖቸን ሳማትር: ሸለቆውን ስረግጥ፣
የደም እንቁጣጣሽ: አየሁ በጎንደር ገጥ።
የደም እንቁጣጣሽ: አየሁ በጣና ፈርጥ።
የደም እንቁጣጣሽ: አየሁ ኦሮሞ ውስጥ።

አባይ ቀልቶ አይቸው: ሲወርድ እያጎራ፣
ትቶት የነበረው: ሲፎክር ሲያቅራራ፤
ምን ሆነሃል ብየ: ብጠይቀው ሲመሽ፣
ባልጣመው ነገር ላይ: አልሰጠኝም ምላሽ፣
እንኳን አደረሰህ: ሳይለኝ አለ ገሸሽ፣
ለካ እሱም ይዟል: የደም እንቁጣጣሽ።

ወይ ሰኔና ሰኞ: ያመጣብን ጣጣ፣
እኔስ ትቸዋለሁ: አበባ ቆረጣ፣
የደም እንቁጣጣሽ: እደጀ ሳላጣ።
በሉ ቂጣ ብሉ: ግዳይ የጣላችሁ፣
ሰውንም ዱሩንም: እንዲህ መንጥራችሁ፣
ዘመን ለሁሉም ነው: እኛም አናጣችሁ፣
የደም እንቁጣጣሽ: ከርሞ እስክንላችሁ።

ተይው አትሳቂ: ምድር አታብቢ፣
አመትባል አይደምቅም: በደም ስትቀቢ።
ሌሊት በፀበሉ: መታጠብ ቀፈፈኝ፣
የደም እንቁጣጣሽ: ነክቶታል መሰለኝ።
አልጠብስም በእሳት: በግ ስጋ ዘልዝየ፣
በሳት የሞቱትን: ይዞ ህሊናየ፣
አከብራለሁ እንጅ: እንዲሁ ዝምብየ፣
የደም እንቁጣጣሽ: አድርጌ ችቦየ፣
ሁለት ሽህ ዘጠኝ: ቢታየኝ ጤናየ።
… … … … … “
የደም እንቁጣጣሽ … … … … … … …
… … …
ባንድም በሌላም ምክንያት ባሳለፍነው ዓመት ለእውነትና ለሃገር ሲሉ ህይወታቸውን ለገበሩ እህት ወንድሞቻችን መታሰቢያ … … 

http://www.satenaw.com/amharic/archives/20778


Wednesday, September 7, 2016

“መንግስት በእብሪተኝነቱ ቀጥሏል! የታሳሪዎችን ደህንነት ለማወቅ የሞከሩ ቤተሰቦች ተደብድበዋል! ” ድምጻችን ይሰማ

በዛሬው እለት መንግስት ተጨማሪ የግፍ ዱላ በቂሊንጦ ታስረው በነበሩ ግለሰቦች ቤተሰብ ላይ አድርሷል፡፡ ‹‹ታሳሪ ቤተሰቦቻችን በህይወት ካሉ አሳዩን! ሞተው ከሆነም አስከሬናቸውን ስጡን!›› እያሉ በእንባ እየታጠቡ ሰልፍ የወጡ ቤተሰቦችን ጥያቄያቸውን በመመለስ ፋንታ ሰልፉን በትነው የተወሰኑትንም አስረዋል፡፡ ከታሰሩት ውስጥ የአያተልኩብራ ነስረዲንና የሺሀቡዲን፣ እንዲሁም የሙጂብ አሚኖ እናቶች ይገኙበታል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በደረሰው የእሳት አደጋ መንግስት የሀሰተኛ ሪፖርት ማውጣት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡ የሞቱትንም ሆነ በህይወት ያሉትን እስረኞችም ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥ አልቻለም፡፡ ‹‹የሞተው እስረኛ አንድ ብቻ ነው›› ሲል ከቆየ ከቀናት በኋላ 23 ሆናቸውንና ያመነ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በጥይት የሞቱት ሁለት ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡ የተቀሩት እስረኞችም ወደሌሎች ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተዛውረዋል ቢባልም የተባሉት ማረሚያ ቤቶች ግልጽ ማረጋገጫ መስጠት አልቻሉም፡፡ ይህ በቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት እየፈጠረ ሲሆን መንግስት ይህን የህገ ወጥነት መንገድ ተከትሎ መቀጠል መምረጡም ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ መንግስት የታሳሪ ቤተሰቦችን መረጃ መከልከሉና ለጥያቄያቸውም እነሱን መልሶ ማሰሩ በእርግጥም አገራችን ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ሶስት ነጥቦችንም እንድናሰምርባቸው ያደርጋል፡-

1. ለግድያው ተጠያቂው መንግስት ነው፤
2.
የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት የጅምላ ግድያ ወንጀል የተፈፀመበት ቦታ (CRIME SCENE) ነው፤
3.
በህይወት የተረፉት ታሳሪዎች መንግስት ለፈፀመው የግድያና አግቶ ደብዛ የማጥፋት ወንጀል ምስክሮች ናቸው፤

በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት መረጃን በመደበቅና ጊዜን በማራዘም እሱ የሚፈልገውን ዓይነት ‹‹አዲስ እውነታ›› መፍጠር እንደማይችል አውቆ በአፋጣኝ በዛሬው ሰልፍ ያገታቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች አንዲለቅ፣ የገደላቸውን ታሳሪዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያስረክብና አግቶ ደብዛቸውን ያጠፋቸውን ታሳሪዎች ያሉበትን ቦታ አሳውቆ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርግ እናሳስባለን፡፡ ህዝቡም መረጃ ስጡን ስላሉ ጥቃት የደረሰባቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች በመጠየቅ አጋርነት እንዲያሳይ እንጠይቃለን፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/65473

Sunday, September 4, 2016

(አሳዛኝ ዜና) ጳውሎስ፣ ጦር ኃይሎች እና ፖሊስ ሆስፒታሎች ከቂልንጦ እስር ቤት በመጡ 49 አስከሬኖች ተጨናንቀዋል ተባለ

(ይህን ዜና ስጽፈው እጄ እየተንቀጠቀና እምባዬ እየወረደ እንደሆነ ይታወቅልኝ – ከዘ-ሐበሻ አዘጋጆች አንዱ)


 በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ትናንት የተነሳውን ቃጠሎ ተከትሎ የመንግስት ወታደሮች እስረኞች ሊያመልጡ ነበር በሚል በመተኮስ የገደሏቸው እስረኞች ቁጥር እያሻቀበ ነው::

ከአዲስ አበባ የመጡ የታማኝ ምንጮች ዘገባ እንደሚያመለክተው ጦር ኃይሎች ሆስፒታል፣ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል እና ፖሊስ ሆስፒታሎች በአስከሬኖች ተጨናንቀዋል::

እንደዘገባዎች ከሆነ በአጠቃላይ ትናንት የተገደሉት እስረኞች ቁጥር ወደ 49 አሻቅቧል:: በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አሉ የተባሉ አስከሬኖች ቁጥር እስካሁን ያልታወቀ በመሆኑ ቁጥሩ ከ49 በላይም እንደሚያድግ የሚገልጹት ምንጮች በጦር ኃይሎች ሆስፒታል 13 የ አስከሬኖች; በጳውሎስ ሆስፒታል 22 እንዲሁም በፖሊስ ሆስፒታል 14 እስረኞች አስከሬን እንዳለ ገልጸዋል:: የ ሟቾች ቁጥር እስካሁን አልታወቀም:: ብዙ ቤተሰብ ተጨንቆ ወደ ቅሊንጦ ቢያመራም እስረኞችን ማየት እንደማይችሉ ተገልጾላቸው ተመልሰው ነበር:: ሌሎች እስረኞች ዛሬ ሌሊት በ20 መኪኖች ተጭነው ወደ አልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም::

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/65275