Wednesday, June 24, 2015

የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስራች ዳዊት አስራደ ከሀገር ተሰደደ!! እየጎመዘዘኝ የሰማሁት ዜና ነው!!

ወጣቱ ፖለቲከኛ ዳዊት አስራደ የሚወዳቸውን ቤተሰቡንና ልጁን ትቶ ከሀገር መሰደዱ ተሰምቷል፡፡ ዳዊት ከ13ቱ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የብሄራዊ ምክር ቤት አባልና የአንድነትን የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድም ከሌሎች የፓርቲው አመራሮች ጋር በመሆን የነደፈ ሙሉ ማንነቱን ለሀገር ትግል የሰጠ ቁርጥ ኢትዮጵያዊ ልጅ ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም በአማራ ክልል ምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያለ በመኪና ተገጭቶ ለ6 ወራት ተኝቶ ከሞት ድኗል፡፡ 
በ97 ዓ.ም በቅንጅት ፓርቲ ውስጥ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን የጀመረው ዳዊት አስራደ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስራች አባልም ነበር፡፡ ዳዊት በፓርቲው የተለያዩ ሓላፊነቶች ላይ የሰራ ሲሆን ለአብነትም 

– በወጣቶች የትምህርትና ስልጠና ዘረፍ

– የብሄራዊ ምክር ቤት ቋሚ አባል

– የብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ዋና ጸሀፊ

– የኢኪኖሚ ጉዳዮች ሃላፊና በተለያዩ የአድሆክ ኮሚቴዎች ውስጥ በሀላፊነትና በአባልነት ሰርቷል፡፡ 

የአንድነትን የ5 አመት እቅድና ስትራቴጂ ከነደፉት ሰዎች መካከልም ዳዊት አለበት፡፡ በ2002 ምርጫ አንድነት መድረክን ወክሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምዕራብ ጎጃም ዞን በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወዳዳሪ ነበር፡፡ ሆኖም በ2007 የአንድነት ፓርቲ በምርጮ ቦርድ ለነ ትግስቱ አወል መሰጠቱን በመቃወም ከፓርቲው ሙሉ በሙሉ ቢገለልም በገጠመው ተደጋጋሚ እስርና እንግልት ምክንያት ሀገሩን ትቶ ሂዷል፡፡ 

መንግስት በሽብር ቡድኖች በሊቢያ የተቀጠፉ ኢትዮጵያውያንን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ቪዲዮ ቀርጻሃል›› በሚል ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በፖሊስ ተይዞ ቄራ ፖሊስ ጣቢያ ገባ፡፡ ሰልፉን በሞባይል በቀረጸበት የ25000.00 ብር ዋስ እንዲለቀቅ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአቃቂ ምድብ ችሎት ወሰነ፡፡ ሆኖም አቃቢ ህግ ወዲያውኑ በ14 የተደረገውን ሰልፍ ለማወክ በ13 ከ200-300 የሚሆኑ ወጣቶችን አደራጅተሃል የሚል ተጨማሪ ክስ መሰረተበት፡፡ ይህን ክስ ደግሞ በ6000.00 ብር መያዣ ይፈታ ሲባል በእለቱ ስብሰባው ላይ ችግር ፈጥረሃል የሚል ክስ ታከለለት፡፡ ለዚህ ደግሞ 5000.00 ብር አስይዝ ተባለ፡፡ 

ሚያዚያ 14 በቄራ፣ ከሚያዚያ 15- 21 በፔፕሲ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስሮ ቆየ፡፡ ሚዚያ 21 ቀን ባስያዘው ገንዘብ ተፈቶ ሳይሰደድ ሲቀር ይምሰላል በግንቦት 3 ቀን ከፔፕሲ ፖሊስ ጣቢያ ተደወለለት፡፡ ያስያዝከውን ንብረት ውሰድ ነጻ ነህ አሉት፡፡ ሲሄድ ግን ታሰረ፡፡ ሶስት ቀን ፔፕሲ ፖሊስ ጣቢያ ከቆየ በኋላ ወደ ማእከላዊ ተወሰደ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዘያት እስከ ሰኔ 5 ቀን በማእከላዊ እስር ላይ ቆይቶ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአቃቂ ምድብ ችሎት በእለቱ እንዲፈታ ወሰነ፡፡ እስካሁን ያዝያዘው 36000.00 ያልተመለሰለት ሲሆን ሰኔ 19 ቀን ፍርድ ቤት እንዲገኘ ሌላ ቀጠሮ ተሰጠው፡፡ 

ዳዊት በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ባሉ መርማሪ ፖሊሶች ከኢህአዴግ ጋር እንዲሰራ ግብዣ ቀርቦለት ነበር፡፡ 

ዳዊት አስራደ በተለያዩ ባንኮች በተለያየ የሃላፊነት ቦታ ላይ ሰርቷል፡፡ አገር ጥሎ በወጣበት ወቅትም በህብረት ባንክ ዋና መስሪያ ቤት የአንድ ክፍል ዋና ሓላፊ እና ጥሩ ደመዝ ተከፋይም ነበር፡፡ ዳዊት የአንድ ልጅ አባትና ባለትዳር ነው፡ 

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስርዓቱ እግር ተወርች አስሮ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በዚህ ሳምንት አገሩን ጥሎ መጥፋቱ ተገልጧል፡፡ 

(ዛሬ የሰማሁት መራር ዜና ነው- የዳዊት አስራደ ስደት፡፡ ይህን ቆራጥ ሰላማዊ የዲሞክራሲ ታጋይ በቅርበት አውቀዋለሁ፡፡ የሚወደውን ልጁን፣ የሚያፈቅራትን ሚስቱን እና ሀገሩን ትቶ መሰደዱን ስሰማ ከልቤ አነባሁ፡፡ ) 

http://satenaw.com/amharic/archives/8067


Tuesday, June 23, 2015

ህወሓት እና የሀውዜኑ ጭፍጨፋ

በደርግ ዘመን ከተፈፀሙት ጭፍጨፋዎች መካከል ሀውዜን ከተማ ላይ የተደረገው በዘግናኝነቱ ይጠቀሳል፡፡ ይህን ጭፍጨፋ ያከናወነው ደርግ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ህወሓት በጭፍጨፋው ላይ እጁ እንዳለበት የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የጠራ አመለካከት ሳይያዝ ቀጥሏል፡፡

የቀድሞው የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ‹‹A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilization in Ethiopia›› በተሰኘ መጽሃፋቸው እ.ኤ.አ በ1983 ትግራይ ውስጥ ይደረግ የነበረው ትግል የኢትዮጵያ አብዮት አንድ አካል መሆን አለመሆን ላይ አለመግባባቶች እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ እንደ አባይ ጸሃዬና መለስ ዜናዊ የመሳሰሉ አመራሮች አብሮ ለመስራት የሚያስችል ድርጅት ባለመኖሩ ህወሓት የትግራይን ነፃ መንግስት ለመመስረት በተቀረፀው ማንፌስቶው መሰረት መታገል እንዳለበት ውሳኔ ይተላለፋል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ አብዛኛው ታጋይ እነ አቶ መለስ ባስቀመጡት አላማ መሰረት ትግሉ ቀጠለ፡፡

ሆኖም የህወሓት ሰራዊት ትግራይን ነጻ ማድረግ ከጀመረ በኋላ አቋሙን ቀይሮ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም ወሎና ጎንደር እንዲዘምት ያዛል፡፡ በዚህ ወቅት አብዛኛው እነ አቶ መለስና አባይ ጸሃዬ ባሰረጹት ጥላቻ አዘል ብሄርተኝነት ያታነጸ አብዛኛው የህወሓት ሰራዊት ‹‹በማንፌስቴው መሰረት የራሳችን የትግራይን መንግስት እናቋቁማለን›› በሚል ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ለመዝመት ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል፡፡ ስለሆነም እነ አቶ መለስ ደርግ እስካልተደመሰሰ ድረስ የትግራይ ህልውናም አደጋ ላይ መሆኑን በማሳየት ሰራዊቱን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ስልት መንደፍ የግድ ሆነባቸው፡፡ የሀውዜን ጭፍጨፋም ደርግ በትግራይ ልይ የሚፈጥረውን አደጋ በማሳየት ይህን ሰራዊት ለማንቀሳቀስ የተጠነሰሰ የወቅቱ ሴራ መሆኑን ይነገራል፡፡

የገብረመድህን ምስክርነት 

ስለ ሀውዜን ጭፍጨፋና ስለ ሌሎች የህወሓት ሚስጥሮች በቀዳሚነት እየተናገሩ ከሚገኙት መካከል ገብረ መድህን አርዓያ የተባሉ የቀድሞ የህወሓት አመራር ይገኙበታል፡፡ አቶ ገብረ መድህን እንደሚሉት የሀውዜን ጭፍጨፋ ሚስጥር የሚጀምረው የህወሓት ሰራዊት ከትግራይ ውጭ መዋጋት እንደማይፈልግ አቋን በገለፀበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ የህወሓት አቋም ያልተስማማው 10 ሺህ ያህል ሰራዊት ከጦር ሜዳ አፈግፍጎ ወደ ትውልድ ሰፈሩ ተመልሷል፡፡ ይህ የሰራዊቱ አቋምም የህወሓትን የመጨረሻ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባ ነበር፡፡ በመሆኑም እነ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ገብሩ አስራትና ሌሎቹም ሰራዊቱ ድረስ በመሄድ ለማግባባት ጥረዋል፡፡ አልሆን ሲል ከጦር ሜዳ ያፈገፈጉት የሰራዊቱ አባላትም ታድነው እንዲያዙ ተደርገዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውም የተመለሱትን የሰራዊቱን አባላት ይዘው እንዲሰጡ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ታስረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ የሰራዊት አባለት ጠፍተው መቅረታቸውን የሚገልጹት አቶ ገብረ መድህን በድሮው የእነ መለስ አስተሳሰብ አምነው ‹‹እኛ ትግራይን ነፃ አውጥተናል›› ብለው በተመለሱ የሰራዊቱ አባላት ላይ ግድያ መፈፀሙንም መስክረዋል፡፡

ይህ የህወሓት እርምጃ ግን ሰራዊቱ ወደ ቀሪው ኢትዮጵያ ክፍል እንዲዘምት ለማሳመን በቂ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሌላ ስልት መነደፍ ነበረበት፡፡ ሀውዜንን ማስጨፍጨፍ፡፡ አቶ ገብረ መድህን አርዓያ እንደሚሉት ህወሓት የትግራይን ከተሞች በማስደብደብ ህዝብን ማንቀሳቀስ የጀመረው በሀውዜን አይደለም፡፡ ከሀውዜን ቀደም ብሎም በተንቤን፣ አብአዲና ጭብሃ የተባሉ አከባቢዎች ላይም የህወሓት አመራሮችና ሰራዊቱ ከተሞቹ ውስጥ እንዳለ በማስመሰል ከተሞቹን በደርግ አስደብድቦ ህዝብን ለማንቀሳቀስ ጥሯል፡፡


ሀውዜንን በማስደብደብ ሰራዊቱ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲዘምት ያስችላል የተባለለትን ስልት የቀየሱት አቶ መለስና ስብሃት ነጋ መሆናቸውን ገብረ መድህን አርዓያ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ህወሓት ሀውዜን ውስጥ ትልቅ ሰሚናር እንደሚያካሂድ ማስመሰልና ‹‹ሚስጥሩም›› ወደ ደርግ እንዲሾልክ ማድረግ ነበረበት፡፡ ህወሓት ስለሚያደርገው ሰሚናርም አሳማኝ መረጃ በወቅቱ የትግራይ ክፍለ ሀገር ገዥ ለነበረው ለገሰ አስፋው እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ይህ ሚስጥራዊ የተባለ መረጃ መቀሌ ለሚገኘው የክፍለ ሀገሩ ገዥ እንዲደርስ የተደረገውም በወቅቱ የወታደሩ ደህንነት የነበረው ሀይሉ በርሄ የተባለ ሰው አማካኝነት መሆኑን ገብረ መድህን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ጥብቅ የተባለ መረጃም ከለገሰ አስፋው ወደ ማዕከላዊ መንግስቱ ይላካል፡፡ 


አቶ ገብረ መድህን እንደሚሉት ህወሓት በለገሰ አስፋው የደረሰው መረጃው ትክክል መሆኑን ለደርግ ለማሳየት ሌሎች መንገዶችንም በመጠቀም ሀውዜን ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ አሰቃቂ እንዲሆን በርትቶ ሰርቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው ለአካባቢው ህዝብ ሃውዜን ውስጥ የህወሓት ስብሰባ እንዳለ ውስጥ ውስጡን ማስወራት ነበር፡፡ በሁለተኝነት ደግሞ ሰሚናሩ ይካሄድበታል በተባለው ሰሞን የህወሓት ሰራዊትን ሀውዜን ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡
ድብደባው ቅዳሜ ሊደረግ አረብ ቀን በታደሰ ወረደ የሚመራና ሌላ አንድ ክፍለ ጦር ሀውዜን ውለውን እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ በተራውም ሌላ ክፍለ ጦር መጥቶ ለቅዳሜ እንዲያድር ይደረጋል፡፡ ከሀገር ገዥው፣ ከህዝቡና ሽርጉድ ይል ከነበረው የህወሓት ሰራዊት አንጻር ሰሚናር መኖሩን እርግጠኛ የሆነው ደርግም ህወሓትን ለመደምሰስ ዝግጅት አድርጎ መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ሲዘጋጅ የሰነበተው ደርግም ህወሓት በሌለበት በገበያ ቀን ከተማው ውስጥ የነበረውን ከ3000 በላይ ህዝብ ጨፍጭፏል፡፡


አቶ ገብረ መድህን የሀውዜን ጭፍጨፋ የህወሓት እጅ አለበት ሲሉ የሚያቀርቡት ማሳመኛ መካከል በወቅቱ ህወሓት ያደረገው ያልተለመደና አነጋጋሪ ቀረጻ አንዱ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው የህወሓት ታጋይ ከሀውዜን በፊት ሀወሓት ህዝብን ለማንቀሳቀስ ሲልም ያስደበደባቸውም ሆነ ደርግ በራሱ ጥቃት ያደረሰባቸው የትግራይ ከተሞች ላይ ድብደባ ሲደረግ ህወሓት በከተሞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የመቅረጽ ልምድም ሆነ አቅም አልነበረውም፡፡ የሀውዜን ጭፍጨፋ በዘመናዊ ካሜራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ህወሓት እንደቀረጸው የሚጠቅሱት ገብረ መድህን ሴራውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ባይ ናቸው፡፡ እንደ ገብረ መድህን እነ አቶ መለስ ሀውዜንን ለማስጨፍጨፍ እቅድ እንዳወጡ 12 ያህል ታጋዮችን ወደ ሱዳን ልከው ስለ ካሜራ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ወደ ሱዳን በመሄድ ስልጠና አግኝተው ደርግ በከተማዋ ላይ የሚያደርገውን ድብደባ ከቀረጹት 12 ታጋዮች መካከል እያሱ በርሄና ሱራፌል የተባሉ የህወሓት ታጋዮች እንደሚገኙበትም አቶ ገብረ መድህን በትውስት ይናገራሉ፡፡ የእነዚህ ስለ ስለ ቀረጻ ስልጠና የወሰዱ ታጋዮችም ቦታ ቦታቸውን ይዘው የደረግን ጥቃት መጠባበቅ የጀመሩት ድብደባው ከሚደረግበት አንድ ቀን ቀደም ብለው ነው፡፡


ደርግ ከተማዋን በበርካታ ሚጎች ሲያወድም ከተለያየ አቅጣጫ ይጠባበቁ የነበሩት ታጋዮች ትዕይንቱን በካሜራቸው ሲያነሱ መዋላቸውን አቶ ገብረ መድህን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ሲቀረጽ የዋለው ፊልምም ወደ ሱዳን ተልኮ ጭፍጨፋው በተደረገበት ቀን ማታ በበርካታ ቴሊቪዥኖች መታየት ችሏል፡፡ ደርግ ድብደባውን ባደረገበት ወቅት ምንም አይነት የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ ሀውዜን ውስጥ እንዳልነበረ የሚጠቅሱት አቶ ገብረ መድህን በውጭ አገር ቴሊቪዥኞች ይተላለፍ የነበረው ህወሓት ሲያስቀርጸው የዋለው ፊልም መሆኑን ይናገራሉ፡፡



ህወሓት ለሀውዜኑ ጥቃት ድርግ ብቸኛው ተጠናቂ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ በተቃራኒው የህወሓት አባላት ደግሞ ህወሓትም ደርግ ያደረገውን ጥቃት አቀነባብሯል በሚል ቀዳሚ ተጠያቂ ያደርጉታል፡፡ በወቅቱ ጭፍጨፋውን በበላይነት አስፈጽመዋል የተባሉት አቶ ለገሰ አስፋውን ጨምሮ በርካታ የደርግ አባላት በዚህ ተጠያቂነታቸው ተፈርዶባቸዋል፡፡ በአንጻሩ በፓርቲው አባል በነበሩ አካላት ሳይቀር የሚወቀሰው ህወሓት እስካሁን ተጠያቂ አልሆነም፡፡ ህወሓት በአባላቱ የሚደርስበትን ወቀሳ እውነት አለመሆኑን ለማሳየትም አጣሪ አካል አለመመደቡም ጉዳዩ እስካሁንም ግራ እንዳጋባ ቀጥሏል፡፡

ህወሓት ይህን ክስ የሚያስተባብልበት አሳማኝ መረጃ ማቅረብ ካልቻለ ህዝብ ሊያምን የሚችለው በእነ ገብረ መድህን ምስክርነት ነው፡፡ በተቃራኒው የደርግ አባላት ፍርዳቸውን ቢጨርሱም የህወሓት አባላት እያወጡት የሚገኘው ሚስጥር ላይ ተጨባጭ መረጃ በማቅረብ ከጭፍጨፋው በስተጀርባ ህወሓት መኖሩን ማረጋገጥ ቢችሉ የተሸከሙትን የህሌና እዳ ማቃለል እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ በሌላ በኩል በችግሩ ላይ የህወሓት እጅ እንዳልነበረበት ማረጋገጥ ቢችሉም ህዝብ በጉዳዩ ላይ የጠራ አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ ግዴታቸውን መወጣት ይችላሉ፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44555

Saturday, June 20, 2015

መድረክ በኦሮሚያ 2፣ በደቡብ 1 እንዲሁም በትግራይ 1 አባላቶቹ መገደላቸውን ይፋ አደረገ

 መድረክ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞንና በትግራይ ክልል ሁለት አባላቱ በ3 ቀናት ልዩነት እንደተገደሉበት አስታወቀ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በትግራይ ክልል የመድረክ አባል የነበረው አቶ ታደሰ አብርሃ እንደተገደለበት በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ደግሞ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን አቶ ብርሃኒ ኤረቦ የተባሉ የመድረኩ አባል ተገድለው ትናንት ጠዋት አስከሬናቸው መገኘቱን የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በምዕራብ ትግራይ ዞን የአረና/መድረክ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው በዘንድሮው ምርጫ በዞኑ የምርጫውን ሥራ በማደራጀት፣ በመቀስቀስና ታዛቢዎችን በመመደብ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩት አቶ ታደሰ አብርሃ አርአያ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተደብድበው መገደላቸውን መድረክ አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ለጊዜው ማንነታቸው በግልጽ ተለይቶ ያልታወቁ 3 ሰዎች ወደ ቤታቸው በመግባት በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ሕይወታቸውን ያጡት አቶ ታደሰ፤ በምርጫው ቅስቀሳ ወቅትም በኢህአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል ያለው መድረክ፤ “ምርጫው ሲያልፍ አንድ በአንድ እንለቅማችኋለን፤ የትም አታመልጡንም” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያም ደርሶባቸው ነበር ብሏል፡፡

በዞኑ በሚገኘው ማይካድራ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ታደሰ አብርሃ፤ ድብደባው እንደተፈጸመባቸው ጉዳዩን የሰሙት አቶ መሰለ ገ/ሚካኤል /በዞኑ የአረና/መድረክ ተወካይ/ ለጉዳተኛው የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ለማስተባበርና ወንጀለኞችንም ተከታትሎ ለማስያዝ ከቤታቸው በሞተር ብስክሌት ወጥተው ሲንቀሳቀሱ ፖሊሶች ይዘው “መንጃ ፈቃድ በእጅህ አልያዝክም” በሚል ሰበብ ሞተር ብስክሌታቸውን ወስደው ፖሊስ ጣቢያ በማስገባታቸው፣ለተጎጂው ከመድረሳቸው በፊት ሕይወታቸው ማለፉን መድረክ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የ48 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ታደሰ አብርሃ፤ ባለትዳርና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበሩ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በነጋታው ረቡዕ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት ተፈጽሟል ብሏል፡፡በሌላ በኩል በትግራይ ክልል በምርጫው ሰሞን ዕጩዎች በሚቀርቡበት ወቅት የታሰሩ 17 የአረና/መድረክ አባላት አሁንም በመቀሌ ወሕኒ ቤት ታስረው እንደሚገኙ መድረክ አስታውቋል፡፡ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎችም በአባላቱና በምርጫው ወቅት በታዛቢነት ያገለገሉ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ መከራዎችና እንግልቶች እየተፈፀሙ መሆኑን የፓርቲው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ በእሳት ቤት ንብረትን ማቀጠልን ጨምሮ ከቤት ማፈናቀልና እስራት በአባላትና ደጋፊዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያለው መድረኩ፤ “ተቃዋሚዎችን መርጣችኋል ወይም ህዝቡ እንዲመርጣቸው ቀስቅሳችኋል” በሚል ግለሰቦችን ማሰቃየቱና ማዋከቡ ተጠናክሮ እንደቀጠለ አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎችም ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እስካሁን 640 አባላትና ደጋፊዎቹ መታሰራቸውን የጠቀሰው መድረኩ ሁለት አባላት ሲገደሉ 66 መደብደባቸውን፣ 7 አባላቱም በጥይት ተመተው እንደቆሰሉ መድረክ በመግለጫው አመልክቷል፡፡ በመድረኩ አባላት ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ እንግልትና ስቃይ በተመለከተ በዝርዝር ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረባቸውን የጠቆሙት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ “በአባላቶቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ግድያ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እየሆነብን ችግር ላይ ነው ያለነው” ብለዋል፡፡


መንግስት በጉዳዩ ላይ ሊያነጋግራቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕ/ር በየነ፤ መድረኩ በአባላቱ ላይ እየደረሱ ነው ላለው በደል ድምፁን ከማሰማት ወደኋላ እንደማይል ገልፀዋል፡፡ አክለውም ከትናንት በስቲያ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን የመድረክ አባል የሆነና በምርጫው ጉልህ ተሣትፎ የነበረው አቶ ብርሃኑ ኤረቦ፣ ፖሊሶች ከቤት አስገድደው ከወሰዱት በኋላ ወንዝ ውስጥ ሞቶ አስከሬኑ
አርብ ጠዋት እንደተገኘ ፕ/ር በየነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44509

Friday, June 19, 2015

‹‹በምርጫው ምክንያት ሊበቀሉን ነው ቤታችን በክረምት ያፈረሱት›› ኢህአዴግን አልመረጣችሁም በሚል የለገጣፎ ነዋሪዎች ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ገለጹ

በ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ኢህአዴግን አልመረጣችሁም በሚል ቤታቸው እንደፈረሰባቸው በለገጣፎ አባኪሮስ፣ ገዋሳ አካባቢ ነዋሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ፖሊስና ካድሬዎች ቤታቸውን በቀይ ቀለም ከቀቡ በኋላ በተደጋጋሚ ገንዘብ ሲቀበሏቸው እንደቆዩና ከሰኔ 09/2007 ዓ.ም ጀምሮ በምርጫው ሰበብ ቤታቸውን እያፈረሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ህዝብ ‹‹ቤትክን እናፈርሳለን!›› እየተባለ በደተጋጋሚ በሚከፍለው ሙስና የተማረረው እንደሆነ የገለጹት ነዋሪዎቹ በአካባቢው ኢህአዴግ እንዳልተመረጠ ገልጸዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ኢህአዴግን ያልመረጡ በተለይም ሰማያዊ ፓርቲን መርጠዋል የተባሉ ነዋሪዎች ቤት ቀይ ምልክት ተቀብቶ እንዲፈርስ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ቤታቸው እንዲፈርስ ቀይ ምልክት ከተቀባባቸው መካከል ለፖሊስና ካድሬዎች ጠቀም ያሉ ገንዘብ የከፈሉ ነዋሪዎች እንዳይፈርስባቸው ሲደረግ ገንዘብ መክፈል ያልቻልነው ቤታችን ፈርሶብናል ብለዋል፡፡

ነገረ ኢትዮጵያ ቢሮ ድረስ በመምጣት መረጃውን ያቀበሉን ነዋሪዎቹ ‹‹ኢህአዴግን አልመረጣችሁም፣ ሰማያዊ ፓርቲን ነው የመረጣችሁት በሚል ቤታችን ፈርሶ በአሁኑ ወቅት ከእነ ልጆቻችን ጎዳና ላይ ወድቀናል፡፡›› ብለዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ቤታችሁን እናፈርስባችኋለን ብለው በማስፈራራት ከፍተኛ ገንዘብ ሲያስከፍሉን ቆይተዋል፡፡ ቆርቆሮ ገንጥለው ለቆርቆሮው እስከ 2 ሺህ ብር አስከፍለው እንደገና ቆርቆሮውን ይመልሱልን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በምርጫው ምክንያት በአካባቢው ህዝብ ቂም ይዘዋል፡፡

 በምርጫው ምክንያት ሊበቀሉን ነው ቤታችን በክረምት ያፈረሱት›› ያለው አንድ ወጣት ሙስና ከፍለው ቤታቸው እንዳይፈርስ ካደረጉት ባሻገር እየዞሩ ቤት የሚያፈርሱት ፖሊሶችና ደህንነቶች በአካባቢው በርካታ ቤቶችን ማስገንባታቸውና የእነሱ ቤት እንደማይፈርስባቸው ገልጾአል፡፡ የካድሬዎች፣ የፖሊሶችና ገንዘብ የሚከፍሉት ሲቀር ‹‹ኢህአዴግን አልመረጣችሁም፡፡

 የመረጣችሁት ተቃዋሚዎችን በተለይም ሰማያዊ ፓርቲን ነው›› ተብለው ቤታቸው እንደሚፈርስ ተነግሯቸው ሙስና መክፈል ያልቻሉት ነዋሪዎች ቤት ተመርጦ እየፈረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ገዋሳ፣ ጪሚሲና ሚሽን የተባሉ አካባቢዎች ቤቶች እየፈረሱ መሆኑን የገለጹ በለገጣፎ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ ‹‹የነዋሪዎች ቤት እየፈረሰ የሚገኘው በምርጫው ምክንያት ነው፡፡ ለገጣፎ አካባቢ ምርጫው መጭበርበሩን ያጋለጡ ሰዎች ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸዋል፡፡ እኔ ጋርም እንዳይገናኙም ወከባ ይፈፀምባቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ህዝቡ ኢህአዴግን ባለመምረጡ ቤቱን እያፈረሱበት ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44486

Thursday, June 18, 2015

በህውሀት ኢህአዴግ በሽብርተኝነት የተከሰሱ የአየር ኃይል አባላት ነገ ፍ/ቤት ይቀርባሉ


ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የሽብርተኝነት ክስ የቀረበባቸው ሰባት የአየር ኃይል አባላት ነገ ሰኔ 12/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ይቀርባሉ፡፡

አቃቤ ህግ በሰኔ 7/2007 ዓ.ም ባቀረበባቸው ክስ ላይ እንደተመለከተው፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 32(1)(ሀ)ን እና የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 7(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በሽብተኝነት ተከስሰዋል፡፡በክሱ የተመለከቱት ተከሳሾች የሚከተሉት ናቸው፣ 

1ኛ. መ/አ ማስረሻ ሰጤ……አድራሻ ድሬዳዋ 
2ኛ. መ/አ ብሩክ አጥናዬ……. ›› ድሬዳዋ 
3ኛ. መ/አ ዳንኤል ግርማ…… ›› ድሬዳዋ 
4ኛ. ገዛኸኝ ድረስ………. ›› ድሬዳዋ 
5ኛ. ተስፋዬ እሸቴ…….. ›› ምስራቅ ጎጃም
 6ኛ. ሰይፉ ግርማ……. ›› አዲስ አበባ
 7ኛ. የሻምበል አድማው…… ›› ምስራቅ ጎጃም፣ ናቸው፡፡

 በአቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመለከተው ተከሳሾች ‹‹….ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፈራረስ ዓላማ ይዘው ….በሽብር ድርጅት ውስጥ አባል በመሆንና በሽብር ድርጅት ተግባር ላይ ለመሳተፍ በማሰባቸው….›› የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ተከሳሾች ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል በመክዳት ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሊያመሩ ሲሉ ባህር ዳር እና ጎንደር ላይ እንደተያዙ በክሳቸው ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሽብር ድርጅት አባል በመሆን፣ ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በመመልመል እና መረጃ በማቀበል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ የአየር ኃይል አባላት ተከሳሾቹ በነገው ዕለት አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተከሳሾች ለወራት ከቆዩበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወጥተው በአሁኑ ወቅት ቂሊንጦ እስር ቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

http://satenaw.com/amharic/archives/7879

Wednesday, June 17, 2015

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ጥልቅ የሐዘን መግለጫ! የሰማዕታት ደም ይጮሃል፤ ይጣራል!!!

አንድ በስልጣን ላይ የተቀመጠ አካል ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ጤነኛ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ የሚገነዘበው ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ እንደ እርግማን ዛሬ በኢትዮጵያ የስልጣን እርካቡን የተቆጣጠረው ቡድን የሚገዛቸውን ዜጎች የሚያያቸው እንደጠላት እንጅ የመንግስትን ጥበቃ እንደሚፈልጉ፤ በጠላትነት የፈረጃቸው ዜጎች በከፈሉት ግብር ስልጣን ላይ መቆየት መቻሉን እንኳን ባለስልጣናቱ መረዳት ተስኗቸዋል፡፡

ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ እጅግ በሚሰቀጥጥ ጭካኔ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ የተገደላው የሰማያዊ ፓርቲ ቆራጥ ታጋይ ሳሙኤል አወቀ የስርዓቱ አገልጋዩች ለዓመታት ሲያስፈራሩት፣ ሲደበድቡት፣ ሰርቶ የመኖር መብቱን ሲጋፉት፣ ያልተሳከ የመግደል ሙከራ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲፈፅሙበት መቆየታቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ተይዘዋል፡፡ ሳሙኤል ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነችና ጥበቃ እንዲያደርጉለት የጠየቃቸው የፀጥታና የፍትህ አካላት በተገላቢጦሽ ተጨማሪ ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርሱበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አንድ ወጣት በተወለደበት ምድር በሕይወት የቆየባቸውን ጊዚያት በስጋት እንዲኖር ከተፈፀመበት ግፍ በተጨማሪ በሕይወት የመኖር መብቱ በአረመኔዎች እጅ ስትነጠቅ የህዝብን ፀጥታና ደሕንነት እናስከብራለን የሚሉ አካላት በመሃል ከተማ እንኳን ደርሰው ለመታደግ አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ አልነበራቸውም፡፡

ሳሙኤል በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደሉ በፊት በተለያዩ ጊዚያት ለሚመለካታቸው አካላትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላልፋቸው የነበሩ መልዕክቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ ግንቦት 25 2007 ዓ.ም በራሱ ገፅ በሆነው “የፌስ ቡክ” ማህበራዊ ሚዲያ ካስተላለፈው መልዕክት መረዳት እንደሚቻለው በተደራጀ ሁኔታ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነች አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ሆኖም የሚሰማውና የሚጠብቀው ምንም አካል እንዳልነበረ ይልቁንም ለመገደሉ ተባባሪ የሆኑ የመንግስት አካላት እንደነበሩ ስጋቱን በገለፀ በቀናት ውስጥ ሕይወቱ በአሰቃቂ ሁኔታ መቀጠፏ ጉልሕ ማስረጃ ነው፡፡

በሰላማዊ ትግል ፅኑዕ እምነት የነበረው ሳሙኤል አወቀ ይደርስበት የነበረውን ለቁጥርና ለዓይነት አታካች የሆነ በደል ተቋቁሞ፣ ትግሉን እንዲያቆም ወይም የሚወዳትን ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠላትን ሐገሩን ለቆ እንዲሰደድ ይህ ካልሆነ ግን የእሱን ሕይወት ለማጥፋት እጅግ ቀላል መሆኑን የስርዓቱ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ደጋግመው ቢነግሩትም በጭቆና ስር ለሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ከማጠፍ ይልቅ ሕይወቱን ለመሰዋት እንደሚቀለው የገባውን ቃል በተግባር አስመስክሮ አልፏል፡፡ በማሰርና በመደብደብ አላማውን እንደማያስቀይሩት፤ ከገደሉት ግን ቀሪ ታጋዮች በተለይም የእድሜ አቻዎቹ የሆኑ የእርሱ ትውልድ የሚሰዋለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርሱ “ትግሌን አደራ!! አደራ!!” በማለት ተማፅኖ አስቀምጧል፡፡

እኛም እንላለን፡፡ አደራህ ከባድ ነው፡፡ ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!!!
ይህ ስርዓት በህግም በሞራልም ኢትዮጵያን የማስተዳደር ብቃት የለውም፡፡ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ እያልንም አናላዝንም፤ ወንጀለኞቹ የመንግስት አካላት ናቸውና፡፡ በወንድማችንና ገና በለጋ እድሜው በተቀጨው የትግል አጋራችን ላይ የተፈፀመውን ግፍ አይቶ እንዳላዬ ዝም ያለ መንግስት ከዚህ የተሻለ መልካም ነገር ያመጣል ብለን አንጠብቅም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን መልዕክት አለን፡፡ እስከ መቼ በግፍ እንገደላለን?!! ሸፍጠኞችስ እስከ መቼ ይዘባበቱብናል?!! ትግል ለውጤት የሚበቃው በተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መፍጨርጨር ብቻ ባለመሆኑ የግፍ ስርዓት እንዲያበቃ ሁላችንም የሚገባንን የዜግነት ድርሻ እንድንወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በአባላቱና በደጋፊዎቹ በአጠቃላይም የተለየ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ በካድሬዎች የሚታሰሩ፣ የሚገረፉ፣ የሚሳደዱ፣ የሚዋረዱና የሚገደሉ ዜጎች ለከፈሉት መራራ ፅዋ ክብር ይሰጣል፡፡ መስዋዕትነታቸውም በከንቱ እንዳይሆን እሰከመጨረሻው ይታገላል፡፡

ሳሙኤል “ብታሰርም፣ ብገደልም ይህን ሁሉ የማደርገው ለሐገሬና ለነፃነቴ ነው” ያልከው ቃልህ ከመቃብር በላይ ነው!!!! ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!! ትግል ይቀጥላል . . .
ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

http://ecadforum.com/Amharic/archives/15212/

Saturday, June 13, 2015

“ለህዝባዊ እምቢተኝነት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል” የእስክንድር ነጋ መልዕክት ከቃሊቲ እስር ቤት


በሰላማዊ ትግል ውስጥ ሁለት አብይት የትግል ስልቶች አሉ አንደኛው ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትና ህግጋት ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ የሚደረግ ህዝብን ያሳተፈ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ ሲባል ዝም ተብሎ ለማስመሰልና የአምባገነኖችን የስልጣን እድሜ ለማራዘሚያነት የሚደረገውን አይጨምርም፡፡ ምርጫ ሲባል ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ያሉት ነው፤ መመዘኛዎችን ባሟላ መልኩ የሚደረግ ምርጫ፣ ምርጫ ሊባል ይችላል፡፡
አምባገነን ስርዓቶች ምርጫ ሲያደርጉ አስተውለናል፤ ግን የይስሙላ ነው፡፡ ግብጽ በሙባረክ ጊዜ ምርጫ ታደርግ ነበር፡፡ ብዙ አምባገነኖች ምርጫ አደረግን ይላሉ፡፡ ኢህአዴግም ምርጫ አደረግሁ ይላል፡፡ በእነዚህ ስርዓቶች የተደረጉት ምርጫዎች ግን ዴሞክራሲያዊ ሆነው አላየናቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ምርጫን እንደ ሰላማዊ የትግል ስልት አማራጭ አድርገው ይመለከቱ የነበሩ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ፊታቸውን ወደ ሌላኛው ስልት እንዲያዞሩ ይገደዳሉ፤ እሱም ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው፡፡ በግብጽ የሆነው ይኸው ነው፡፡

አንድ ነገር ማስተዋል አለብን…የምርጫ ስልት ተዘጋ ማለት ሰላማዊ ትግል አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ወደሌላኛው ምዕራፍ ተሸጋገረ ማለት እንጂ፡፡ ምርጫ ሲያበቃለት ህዝባዊ እምቢተኝነት አማራጭ ይሆናል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ለህዝባዊ እምቢተኝነት ተመቻችተዋል፡፡ አሁን ህዝቡ በምርጫ ላይ ያለውን አሰራር አስረጅ ሳያስፈልገው ራሱ አይቶታል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ አማራጩ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደሆነ መገንዘብ ግድ ይለናል፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት ህጋዊና ሰላማዊ የትግል ስልት መሆኑን ዓለም ይገነዘባል፡፡

በዚህ ወቅት ስለህዝባዊ እምቢተኝነት የሚሰሩ አካላት ካሉ መንገዳቸው ልክ ነው፤ ሊገፉበትም የሚገባ ነው፡፡ በእርግጥ ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ በቅድሚያ መግባባት ላይ መድረስ ያለባቸው አካላት አሉ፣ ዋነኛዎቹ ‹አክቲቪስቶች› ናቸው፡፡ አክቲቪስቶች መግባባት ላይ ደርሰው ህዝቡን የማነቃነቅ ስራቸውን በጋራ ቢያከናውኑ አንድነቱን ያጠናከረ እንቅስቃሴ መተግበር ይቻላል፡፡

እስካሁን በተገለጸው የ2007 ‹‹ሀገራዊ ምርጫ›› (በትምህርተ ጥቅስ አስገባልኝ) ውጤት እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ አዎ፣ የተለያየ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተስማምተው አንድ ፓርቲ መረጡ ቢባል ለሰሚውም ቀልድ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ያልሆነ ውጤት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢህአዴግ ለማጭበርበር እንኳ አቅም እንዳጠረው ነው፡፡ ለዚህም ነው በውጤቱ ደስ የተሰኘሁት፡፡ ውጤቱ በግልጽ የሚነግረን ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ህዝባዊ እምቢተኝነት ዋናው ገፊ ምክንያት ኢህአዴግና የኢህአዴግ ስርዓት መሆኑን ነው፡፡ እናም ህዝባዊ እምቢተኝነት በኢትዮጵያ ‹ጀስቲፋይድ› ነው፡፡

በእርግጥም አሁን ያለው የኢህአዴግ ስርዓት ለራሳቸው ለኢህአዴግ አባላት እንኳ አሳፋሪ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የማስመሰል ካባው እንኳ አላስፈለገውም፤ ሁሉንም ነገር ከርችሞታል፡፡ እናም ቀጣዩ ትግል የነጻነት ትግል ነው፡፡ ይህን የነጻነት ትግል ዳር የሚያደርሰው ማሳረጊያ ደግሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት ኢህአዴግ ራሱ መርጦ ለህዝቡ የተወው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡ የታፈነ ህዝብ ሲነሳ ማዕበል ነው፣ አምባገነኖችን ይጠራርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አፈና ህዝባዊ እምቢተኝነት አይቀሬነቱን በግላጭ ያረጋግጣል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44332