Tuesday, June 7, 2016

ይቺ ቆራጥ ኢትዮጵያዊት ነጻ ናት… ፍቷት!

ይቺ ቆፍጣና ወጣት እየሩሳሌም ተስፋው በመባል ትታወቃለች። እርሷ ፍቅረማሪያም አስማማው እና ብርሃኑ ተክለ ያሬድ ሆነው በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በማበር፤ የኢህ አዴግን ብልግና ለማረቅ ከዛም አልፎ ከስልጣኑ በማውረድ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት በማሰብ፤ ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ ነበር።

ነገር ግን የመንግስታችን ነገር ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ… ብለው እንዲተርቱ እና በአለት ላይ ውሃ ማፍሰስ ብለው እንዲጨምሩ አይነት ሰላማዊ ትግል የሚገባው አልሆነም። እንኳንስ ሊገባው ሰላማዊ ታጋዮቹን በሙሉ ወደ እስር ቤት እያስገባ አሸባሪ ብሎ በመሰየም እያሸማቀቀ የትግል ምህዳሩን አጠበበው።

ይሄ ነገር ተስፋ ያስቆረጣቸው እነ እየሩሳሌም ኢህ አዴግን በሚገባት ቋንቋ ሊያነጋግሯት ወደ ጫካ ሲወርዱ ተያዙ… እኔ ብሆን ወደ ቻካ ልገባ ስል ብያዝ… አዎ ልዋጋ ነው ብዬ የማምን አይመስለኝም፤ በጣም ከተቸገርኩ እና የምለው ካታሁ…. ‘’እንጨት ልልቀም ነው…’’ የምል የሚመስለኝ።
እነ እየሩሳሌም ግን ለፖሊሶችም ለፍርድ ቤት ዳኞችም አዎን ትጥቅ ወዳነገቡት ታጋዮች እየሄድን ነበር። ኢህ አዴግ ሰላማዊ ትግሉ ሊገባት ስላልቻለ በሚገባት ቋንቋ ልናነጋግራት ነበር። ብለው ተናገሩ!

እነ ኢየሩሳሌም ግንቦት ሰባት አርበኖችን ለመቀላቀል ማሰባቸን ወንጀል አይደለም። ብለው እየተከራከሩ ነው። ይሄንን ለማስረዳት በርካታ የቀድሞ ታጋዮችን ምስክርነት ጠርተዋል። ነገር ግን የሃገሬ ፍርድ የጭቦ ነውና፤ ልጆቹ ምስክር ማሰማት እንኳ እንዳይችሉ ተከልክለው ለምን ሆድ ባሳችሁ… ለምን ተከፋችሁ ለምንስ ዱር ቤቴ አላችሁ በሚል ብይን ሊሰጥባቸው ለ ሃምሌ አስራ ሶስት ተቀጥረዋል።

ፍርድ ቤቱ ቀና ቢሆን ኖሮ እነ እየሩሳሌም የሰሩት ስራ ምንም ወንጀል እንዳልሆነ ለመረዳት አንድ ሁለት የግንቦት ሃያ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ማየት ይበቃው ነበር።

እነ ህውሃት ለዛምን ምንም አይነት ሰላማዊ ትግል ሙከራ ሳያደርጉ ጫካ ሲገቡ ጀግና ተብለው እነ እየሩስ ሰላማዊ ትግሉን አይተውት መንገዱ ሲዘጋባቸው ሌላ መንገድ መምርጣቸው በምንም መስፈርት ወንጀል ሊሆን አይችልም!!!

እየሩሳሌም ዛሬ ፍርድ ቤት ስትቀርብ ሙሉ ጥቁር ለብሳ እጇ ላይ የሃገሯን ሰንደቅ አላማ አድርጋ ነበር።


እነ ኢህ አዴግ ሆይ ለሴቶች እኩልነት ቆመናል የምትሉ ከሆነ (ካልሆነም)  ይቺ ቆራጥ ኢትዮጵያዊት ነጻ ናት… ፍቷት!

http://www.abetokichaw.com/?p=91

Saturday, May 21, 2016

የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተግባራዊ ሊደረግ ነው (ቪኦኤ)

የኢትዮጵያ መንግሥት በፀር ሽብር ሕጉን በሀገር ውስጥ ፖለቲካው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው በሚል መከሰስ ከጀመር አራት ዓመታት ተቆጥሯል። አሁን ደግሞ የኢንተርኔት አምደኞች እና ፖለቲከኞች ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን የበለጠ ስጋት ላይ የሚጥል አዲስ የኮምፒዩተር ረቂቅ ወንጀል ዐዋጅ ወጥቷል።

በሚያዝያ ወር 2008 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ እየተተቸ ከሚገኝበት ነገር አንዱ ሐሳባቸውና የግል አመለካከታቸውን በኢንተርኔት አማካኝንት የሚገልጹ ግለሰቦችን የኢትዮጵያ መንግሥት አሥሮ የሚቀጣበት አንቀጽ ማካተቱ ነው።
ዳንኤል ብርሃኔ በኢትዮጵያ የሚገኝ የኢንተርኔት አምደኛ ነው። የራሱ ድረ ገጽም አለው። አዲሱ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ ሐሳቡን በኢንተርኔት አማካኝነት በሚገልጽ በማንኛውም ግለሰብ ላይ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ዐዋጅ ነው ብሎ ያምናል።
“ይሄ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉም ኾነ በመገናኛ ብዙሐን ሕጉ የተሰጡንን መብቶች የሚጥስ ነው። እስካሁን ካሉት ሕጎች ሁሉ የበለጠ ከልካይ ነው። በአንድ ዓረፍተ ነገር ብቻ ይከለክላል” ይላል።
የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጁ በአብዛኛው ትኩረት የሚያደርገው በኢንተርኔት አማካኝነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው በኢንተርኔቱና በኮምፒዩተሩ አማካኝነት ወንጀል ፈጽሟል ብቻ ሳይኾን ወንጀል ተፈጽሞበታል ተብሎ ከተገመት ያለ ምንም ፍርድ ቤት ፍቃድ እና ትእዛዝ ብሔራዊ ደሕንነት ኮምፒዩተሩን በአካል ሳይነካ እንዲመረምር ሥልጣን የሚሰጠው አንቀጽ በረቂቁ ውስጥ ተካቷል።
በኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ዳይሬከተር የኾኑት አቶ በላይይሁን ይርጋ ረቂቅ ዐዋጁ ሐሳባቸውን በኢንተርኔት በነፃነት ከሚገልጹ ሰዎች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ይላሉ።
“አንድ ሰው የእራሱን ሐሳብና አመለካከት ከተናገረ ብቻ በወንጀል ተጠያቂ አይኾንም። የዚህ ሕግ ዋና ዓላማ ግን ሰዎች ከስም ማጥፋት ጋር በተያያዘ ለድርጊታቸው የሚኖራቸው ዓላማ ነው። ዋነኛ ዓላማቸውና ግባቸው ስም ማጥፋት ከኾነ ተጠያቂ ይኾናሉ።ም ክንያቱም ስም ማጥፋት ወንጀል ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በኢንተርኔት አማካኝነት ሐሳባቻውን የሚገልጹ ግለሰቦችን በማሰቃየት፣በማሰር እና ረጅም ዓመታት በመፍረድ በተደጋጋሚ ትወቀሳለች። በዚህ ሰለባ ከኾኑት መካከል 18 ዓመት እስር ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር
ነጋ አንዱ ነው። እንዲሁም የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ከአንድ ዓመት በላይ እስር ቤት ማሳለፋቸው ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።
የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው አስተያየት አማካኝነት ከታሠረ ስድስት ወራት ተቆጥሯል።
ሃበን ፈቃዱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሠራተኛ ነች የኢትዮጵያ መንግሥት በፀር ሽብር ሕጉን በሀገር ውስጥ ፖለቲካው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው ትላለች። የአቶ ዮናታንን ጉዳይም በምሳሌነት ትጠቅሳለች።
“በዮናታን ክስ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች በጣም አሳሳቢና መንግሥት አንድን ግለሰብ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በሚጽፋቸው ነገሮች ላይ ተመስርቶ እንዲያሥር የሚፈቅድ ነው። ዮናታን የታሠረው በጸር ሽብር ሕጉ አማካኝነት ነው። ምን አይነት ማስረጃ እንደሚቀርብበት እንኳን ሳያውቅ ነው ፍርድ ቤት የቀረበው” ትላለች።
ይሄ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ በሚቀጥለው ሳምንት ተግባራዊ የደረጋል ተብሏል።
ማርታ ቫንዶርፍ ከአዲስ አበባ ያደረሰችን ዘገባ ጽዮን ግርማ ታቀርበዋለች። ዝርዝሩን ከተያያዘው ድምጽ ያድምጡ።
http://www.satenaw.com/amharic/archives/16661

Sunday, May 8, 2016

መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ጋዜጠኛና ደራሲ ፋሲል ተካልኝን ጥርሱን አወለቁት

በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በጋዜጠኝነት የሚታወቀው ደራሲና ጋዜጠኛ ፋሲል ተካልኝ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ክፉኛ እንደደበደቡት አስታወቀ:: ፋሲል በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ገጠመኙን እንዳሰፈረው ከሆነ በድብደባው ጥርሱን አጥቷል::

ገጠመኙን እንደወረደ አንበቡት:-

እንዲህ ሆነላችሁ፡፡
ሚያዚያ 6 ቀን 2008 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 4 ሰዓት (ከአዲስ አበባ ሬስቱራንት ጀርባ) አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቅራቢያ አካባቢ መሣሪያ ያነገቱ አምስት ሰዎች ተረባርበው ደበደቡኝ፡፡ራሴን ሳትኩ፡፡ከዚህ በኋላ የሆነውንና የተደረገውን አላውቅም፡፡ ስነቃና ራሴን ሳውቅ ሆስፒታል ውስጥ ድንክ አልጋ በመሰለና ቁመቱ በረዘመ ስትሬቸር ላይ ተኝቼያለሁ፡፡ በግራ እጄ አይበሉባ ግሉኮስ ተሰክቷል፡፡ ማን አመጣኝ? ፣ እንዴት መጣሁ? ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ዳሩ ግን ማስታወስ የቻልኩት ራሴን እስክስት የነበረውን ብቻ ነው::

በነጋታው ሆስፒታል የተኛሁበት ተኝቼ ካለሁበት ድንገተኛ ክፍል ድረስ በመምጣት ሲናገር እንዳደመጥሁት የፖሊስ ቃል ከሆነ ሸራተን ምግብ ቤት አካባቢ መንገድ ላይ ወድቄ እንዳገኙኘኝና ወደ ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ይዘውኝ እንደመጡ ነው፡፡ ማለዳ ላይ የተለያዩ ወጣት ሐኪሞች የተካተቱበትና በአንድ አንጋፋ ሐኪም በሚመራ ቡድን ተጎበኘሁ፡፡ በጉብኝቱ መሪ ሐኪም ምን እንደሚሰማኝ ተጠየቅሁ፡፡ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ጉሉኮሱ እንዲነቀልልኝና ወደ ጥርስ ህክምና ክፍል እንድሄድ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ወጡ፡፡እንደወጡ ወደ ጥርስ ህክምና ተወስጄ ተመረመርኩ፡፡ ተመርምሬም መድኃኒት ታዘዘልኝ፡፡ በመጨረሻም በሕይወት ወደ ቤቴ ለመግባት ችያለሁ፡፡

ይሁን እንጂ በጎድን አጥንቴና በጀርባዬ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ ሆስፒታል እስክወሰድ ድረስ መንገድ ላይ ወድቄ በነበርኩበት ሰዓት ብዙ ደም ፈሶኛል፡፡በዚህም ምክንያት እስካሁን ያዞረኛል፡፡ሁለት የግራና የቀኝ የላይኛው መንጋጋ ጥርሶቼ ተነቃንቀዋል፡፡ የላይኛውና የፊት ለፊቱ አራት ሰው ሰራሽና ከታች የሚገኙ ሁለት የፊት ለፊት በድምሩ ስድስት ጥርሶቼ ሙሉ ለሙሉ ወልቀዋል፡፡

በተጨማሪም በወቅቱ አድርጌ የነበረውን ሸራ ጫማን ጨምሮ ለጡዘት ቁጥር 2 የግጥም መድበል የተሰናዱ የተለያዩ ግጥሞችና ሌሎች ጽሑፎችን የያዘውን ተንቀሳቃሽ ስልኬን በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ( ጥቂት የተለያዩ ውጭ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች ያሉበት) የተለያዩ መታወቂያዎችንና የኤ.ቲ.ኤም ካርድ ይዞ የነበር ቦርሳዬ ተወስዷል፡፡


የሆነው ሆኖ በሀገራችን የዜግነት ክብር ይሉት ሐረግ ያለው በብሔራዊ መዝሙር ውስጥ ነው እንጂ በገሐድ እንደሌለ በተለያዩ አጋጣሚዎች
ከማረጋገጥ ባሻገር መንግስት ተብዬውም ለሥልጣኑና ለሥርዓቱ እንጂ  ለዜጎቹ ጥበቃ እንደማያደርግ እንደዚሁም ደንታ ቢስና ግድ የለሽ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ስለዚህ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ማንንም አልከስም፡፡ከማንም መፍትሔ አልጠብቅምም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከዚህ ከሰፊው መንደር መጥፋቴን ተከትላችሁ፣አለመኖሬ አሳስቧችሁ፣በስልክም ሆነ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ በሙሉ ልባዊ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/60253