ሕገወጥ ገንዘብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ የሚከለክል ጥብቅ ሕግሕገወጥ ገንዘብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ የሚከለክል ጥብቅ ሕግ ሊወጣ ነው
ለፖለቲካ ተፅዕኖ የተጋለጡ ግለሰቦች ሀብት ምንጭ እንዲመረመር ያስገድዳል
በዮሐንስ አንበርብር
በወንጀል
ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን (መኒ ላውንድሪንግ) እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ
መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚል ስያሜ የተሰጠው ረቂቅ አዋጅ በዚህ ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ቀረበ፡፡ ረቂቅ አዋጁ ተመሳሳይ ስያሜ ያለውንና በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘውን ‹‹የመኒ ላውንድሪንግ›› እና
ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን የሚከላከል አዋጅ ሙሉ በሙሉ የሚተካ ሲሆን፣ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 684 ሙሉ
ለሙሉ ይሰረዛል፡፡
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ማለት ለወንጀል ፍሬ
ምንጭ የሆነና ቢያንስ የአንድ ዓመት ቀላል እስራት ከሚያስቀጣ ወንጀል ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ
የተገናኘ ነው ሲል አዋጁ ያብራራል፡፡
በመሆኑም ማንኛውም ሰው ንብረቱ የወንጀል ፍሬ
መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የንብረቱን ሕገወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ንብረቱን የለወጠ ወይም
ያስተላለፈ እንደሆነ፣ ከ10 እስከ 15 ዓመታት በሚደርስ እስራትና ከአንድ መቶ ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ
እንደሚቀጣ ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል፡፡
በተመሳሳይ ማንኛውም ሰው ንብረቱ የወንጀል ፍሬ
መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ንብረቱን፣ የንብረቱን ትክክለኛነት፣ ምንጩን፣ ቦታውን፣ ዝውውሩን ወይም
የባለቤትነት መብቱን የደበቀ ወይም እንዳይታወቅ ያደረገ እንደሆነ ተመሳሳይ ቅጣት ይጣልበታል፡፡
ንብረቱን የተረከበ፣ ይዞታው ያደረገ ወይም የተጠቀመ እንደሆነም በተመሳሳይ ከ10 አስከ 15 ዓመተት እስራትና እስከ አንድ መቶ ሺሕ ብር ይቀጣል፡፡
በ2001
ዓ.ም. የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ የፀደቀ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ለፓርላማ የቀረበው ‹‹የመኒ ላውንድሪንግ›› ሕግ
ግን ተጨማሪ ትርጉሞችን ለሽብርተኝነት ይሰጣል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው የፀረ ሽብር አዋጅ የሽብርተኝነት ድርጊትን
በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተፈጸመ አድርጐ ነው የሚቆጥረው፡፡ ይኼኛው ረቂቅ አዋጅ ግን የሽብርተኝነት ድርጊትን፤
‹‹በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታ የተፈጸመ እ.ኤ.አ በ1999 ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል
በወጣው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን አባሪ ከሆኑት ስምምነቶች በአንዱ የተፈጻሚነት ወሰንና ትርጓሜዎች የሚሸፈን የወንጀል
ድርጊት›› በማለት ዓለም አቀፍ ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡
የተጠቀሱትን ወንጀሎች ከመፈጸማቸው
በፊት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ተቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው ረቂቅ አዋጁ፣ ለወንጀሉ ተጋላጭ የሆኑ የገንዘብ ተቋማትና
ገንዘብ ነክ ያልሆኑ የንግድና የሙያ ሥራዎችን በዋናነት ቁጥጥር እንዲያደርጉ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ የገንዘብ ተቋማት
ማለት ባንክ፣ መድን ሰጪ ኩባንያ፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም፣ የፖስታ፣ የቁጠባ ድርጅት፣ የሐዋላ ድርጅት ወይም
ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው ሕግ የሚሰየም ድርጅት ናቸው፡፡
የሪል ስቴት ወኪሎችና ደላሎች፣
የከበሩ ድንጋዮች ወይም የከበሩ ብረቶች ነጋዴዎች፣ ሪል ስቴት መግዛትና መሸጥ፣ የደንበኛውን ገንዘብ፣ የገንዘብ
ሰነዶች የማስተዳደር፣ ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ የሒሳብ ባለሙያዎች ጠበቆችና ሌሎችንም ገንዘብ ነክ ያልሆኑ የንግድና
የሙያ ሥራዎች በማለት ይሰይማቸዋል፡፡
በመሆኑም ገንዘብ ነክ የሆኑትም ሆኑ ገንዘብ ነክ
ያልሆኑ ዘርፎች ከደንበኛ ጋር የንግድ ግንኙነት ከመመሥረታቸው ወይም ሒሳብ ከመክፈቸው በፊት፣ በአገር ውስጥ ወይም
ወደ ውጭ በኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ለማስተላለፍ ከሚፈልግ ደንበኛ ጋር ግብይት ከመጀመሩ በፊት፣ ቀደም ሲል የተወሰደ
ደንበኛ መረጃ ትክክለኛ ወይም ያልተሟላ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ሲፈጠር የደንበኛን ማንነት ለማወቅ የሚያስችሉ የጥንቃቄ
ዕርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
ለፖለቲካ ተፅዕኖ ተጋለጭ ከሆኑ ግለሰቦች
ጋር ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት የድርጅቱን የሥራ ኃላፊ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው፣ እንዲሁም
ከእንደዚህ ዓይነት ግለሰብ ጋር ግንኙነት ከተመሠረተ የሀብት ምንጮችን የመመርመር ግዴታ አለባቸው፡፡
ለፖለቲካ
ተፅዕኖ የተጋለጠ ሰው ማለት በማንኛውም አገር ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ኃላፊነት
የተሰጠው ወይም ተሰጥቶት የነበረ ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ሲሆን፣ የእዚህን ሰው ቤተሰብ አባል ወይም ከዚህ ሰው ጋር
የቅርብ ግንኙነት ያለውን ማንኛውም ሰው ይጨምራል በማለት ረቂቅ ሕጉ ይተረጉመዋል፡፡
posted by Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment