Wednesday, December 30, 2015

ወያኔ ሀገራችንን ቆርሶ ለሱዳን ሊሰጥ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተነሥ!!!

የወያኔ ባለሥልጣናት በሰነድ ደረጃ ከዓመታት በፊት ለሱዳን ስለሰጡት በተግባር መሬት ላይ ደግሞ ሰሞኑን ሊያስረክቡት ሽር ጉድ እያሉበት ስላለው ጉዳይ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ሲጠየቁ “ይሄንን ፈጥረው የሚያወሩት ግርግር ፈጥረው የራሳቸውን ጥቅም ማስጠበቅ የፈለጉ ቡድኖች ናቸው፤ ከእኛ ጋ ጭራሽም በአጀንዳ ደረጃም እንኳን የለም!” ሲሉ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡

እንዲህ ብለው እየተናገሩ ግን የሱዳን መንግሥትና የወያኔ ባለሥልጣናት ይሄንን ሰሞን ርክክቡን መሬት ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ ሽርጉዱን አጧጡፈውታል፡፡ ለሱዳን ሊሰጡት ባሰቡት መሬት ላይ ያለውን አርሶአደርም እያፈናቀሉና እየጠረጉ መሬቱን ነጻ ሲያደርጉ ከራርመዋል፡፡ የተፈናቀሉ ገበሬዎች በጎንደር ከተማና በሌሎችን ስፍራዎች ሜዳላይ ፈሰው ይሄንን ሰሞን ጨምሮ በተለያየ ጊዜ ተመልክተናል፡፡ ለምን? ተብሎ ሲጠየቅ የወያኔ ባለሥልጣናት ከሰባት ዓመታት በፊት ይሰጡት የነበረው መልስ በሬቱን የሱዳን ባለሀብቶች እንዲያለሙት በሊዝ ተሰጥቷቸዋል” የሚል ነበር፡፡

በአሁኑ ሰዓት የወያኔ ሠራዊት ለሱዳን የሚሰጠውን መሬት ርክክብ ኮሽታ በማይሰማበት ሁኔታ ለማስፈጸም በቦታው ሰፍሮ እየተጠባበቀና እንቅፋት ይፈጥራሉ ተብለው የተጠረጠሩትን ያካባቢውን አርሶ አደሮች ለመፍጀት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይንን የመሬት ርክክብ በመቃወም ሊነሣ የሚችለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመቀነስ ከተቻለም ለማስቀረት ሲባልም ቅማንትንና አማራን የማተላለቅ የማባላት ሴራ ተጠንስሶ ተፈጻሚ በማድረግ የሕዝቡን ትኩረት ከድንበር መሬቱ ላይ አስነሥተው የእርስ በእርስ ፍጅት ላይ እንዲጠመድ በማድረግ መሬቱን ለማስረከብ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ቻልን ብለው አስበዋል፡፡

ከአቶ መለስ በኋላ ሁለተኛው የሱዳን ጠ/ሚ በኢትዮጵያ አቶ ኃይለማርያም ለወያኔ “የሕዝብ” ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “ለሱዳን ተቆርሶ የተሰጠና የሚሰጥም መሬት የለም! በመሬት ጉዳይ ላይም ከሱዳን መንግሥት ጋር ተደራድረን አናውቅም!” በማለት ወያኔ እንዲናገሩ የሰጣቸውን መልእክት ተላላኪው ሰውየ አድርሰውናል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ለሱዳን ተቆርሶ ስለሚሰጠው መሬት የተናገሩት ንግግር ስለዚህ ጉዳይ አቶ መለስ አንድ ወቅት ላይ ከተናገሩት ንግግር ምንም የጨመሩት የቀነሱትም አንዲት ነገር ሳይኖር ነበር ያችኑ ሸምድደው መጥተው የተፉት፡፡

“በደናቁርት ቤት ሀን ማወቅ ሊቅነት ነው” እንዲሉ ወያኔም ብልጥ ሆነና ሊያቄለን በማሰብ ይሄንን ቃል ተናገረ፡፡ “ታዲያ እየተፈናቀለ ያለው ገበሬስ በምን ሒሳብና ለምንስ ነው ከቀየው እየተፈናቀለ እንዲለቅ እየተደረገ ያለው?” ተብለው ሲጠየቁ ደናቁርቱ፣ አሕዮቹ፣ የእንግዴ ልጆቹ፣ ጉግማንጉጎቹ፣ በክህደት ተፀንሰው በክህደት የተወለዱቱ፣ ክህደት አሳድጎ ክህደት ያስረጃቸው ጭንጋፎቹ ወያኔዎች ቅንጣት ታክል እንኳን ሐፍረት ሳይሰማቸው በዚያ እርጉም አንደበታቸው “የሱዳን ባለሀብቶች እንዲያለሙት በሊዝ ተሰጥቷቸዋል” ሲሉ የነበረውን የበፊት ሐሰተኛ ምክንያት ትተው ምን ብለው ይመልሳሉ “አይ እሱማ መሬቱ የሱዳን ነው! ሱዳኖቹ መሬታቸውን ለአማራ ገበሬዎች እያረሱ እንዲጠቀሙበት ለረጅም ዓመታት ፈቅደውላቸው ስለነበረ ነው የአማራ ገበሬዎች እዚያ መሬት ላይ ሊገኙ የቻሉት እንጅ መሬቱ የሱዳን ነው!” ብለው በአደባባይ በብዙኃን መገናኛ እንቅጩን ነግረውን አረፉት፡፡

ይንን የሚሉበት ምክንያት እንግዲህ ብልጥ ተሁኖ ተሙቶ “እነዚህ እርጉሞች መሬት እኮ ቆርሰው ሰጡ! ኧረ! እነዚህ ምን ጉዶች ናቸው! እንዴት ዓይነት ከሀዲዎች ቢሆኑ ነው? እንዴት ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ እሠራለሁ እታገላለሁ የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ ከሚል አካል በገዛ ሀገሩና ሕዝቡ ላይ በየትኛውም የዓለማችን መንግሥታት ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ በገዛ ሀገሩና ሕዝቡ ዘንድ ክህደት ፈጽሞ ለባዕድ ሀገር መሬትን ያህል ያውም 1600 ኪሎ ሜትር (ግዝፈ ጉዝ) እርዝመት በ20 እና 40 አንዳንድ ቦታ ላይም በ60 ኪ.ሜ. (ግ.ጉ.) ስፋት የሚያህል አገር የሚያክል መሬትን ይሰጣል? የፈለገውን ያህል ከሀዲና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይ እራስ ወዳድ ቢሆኑ እንዴት በዚህን ያህል የክህደት አረንቋ ውስጥ እራሳቸውን ያሰጥማሉ?” ተብሎ ጉድ እንዳይባልና ሕዝቡም መሬቱን ላለማስነጠቅ እንዳይቆም፣ አይሆንም! አይደረግም! ብሎ እንዳይቆጣ በለመዱት ክህደት እብለት በተሞላ ሐሰተኛ ነውረኛ ስድ አንደበታቸው “ተቆርሶ ለሱዳን የሰጠነውም የምንሰጠውም መሬት የለም! መሬትን በተመለከተ ከሱዳን ጋር ያደረግነው ምንም ዓይነት ድርድር የለም!፣ አይ እሱማ መሬቱ የሱዳን ነው! ሱዳኖቹ መሬታቸውን ለአማራ ገበሬዎች እያረሱ እንዲጠቀሙበት ለረጅም ዓመታት ፈቅደውላቸው ስለነበረ ነው የአማራ ገበሬዎች እዚያ መሬት ላይ ሊገኙ የቻሉት እንጅ መሬቱ የሱዳን ነው!” ብለው ካዱ፡፡

እንዲህ ብለው ክደው ሲያበቁ ግን ከላይ በገለጽኩላቹህ መልኩ አርሶ አደሩን እያፈናቀሉም እየገደሉም ነጻ ሲያደርጉ ቆይተው መሬታችንን ለሱዳን ለማስረከብ ተጠናቀው ተቀምጠዋል፡፡ መቸ ያፍሩና! ሰው ቢሆኑም አልነበር ሊያፍሩ ሊሸማቀቁ ስቅጥጥ ሊላቸው ይችል የነበረው? መቸ ሰዎች ናቸውና? ሕዝቡ እንደራሱ ዓይን አፍንጫ እጅ እግር ይዘው ሲያያቸው ሰው እየመሰላቸው በሚያደርጉት ዕብለት ክህደት ጥፋት “እንዴት! ግን?” እያለ በመደነቅ እጅግ ይገረማል ግራ ይጋባል፡፡ እነሱ የሰው አካል ይዘው ይታዩ እንጅ እንደ ሰው ይናገሩ እንጅ አሁን የወያኔ ግሪሳ ምናቸው ነው ሰው የሚያሰኛቸው በሞቴ?

ጥሩ እንግዲያውስ ያገሬ ገበሬ ቀየ ሱዳኖች እያረሰ እንዲጠቀምበት ለረጅም ዓመታት ፈቅደውለት ሲያርሰው የኖረ መሬት ከሆነ ሕዝቡ “የለም! አይደለም ደማችንን ስናፈስለት አጥንታችን ስንከሰክስለት የኖርነው የኢትዮጵያ መሬት ነው! እንኳንና ይሄንን ያህል መሬት አንዲት ሳንቲ ሜትር (ቅንጠ ጉዝ) እንኳን አንሠጥም!” እያለ ነውና እየቀጠቀጣቹህ እየጨፈጨፋቹህ ከገዛ መሬቱ አጽድታቹህ አፈናቀላቹህ ለሱዳን ከማስረከባቹህ በፊት የምትሉት መሬት የሱዳን ለመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በብዙኃን መገናኛ ማስረጃ አቅርቡልና!!!

እውነቱ ግን አይደለምና ይሄ የአሀሬ ገበሬ ከአያት ቅድመ አያት ቅምቅማቱ እየወረሰው እየተረከበው የመጣው፣ እየተጨፈጨፈ እንዲነሣ እንዲለቀው እየተደረገበት ያለው መሬት ይቅርና ስናር ድረስ ያለው መሬት የኢትዮጵያ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ሞልተዋል፡፡ ቱርኮች በበርካታ መድፎች ታግዘው ድንበር አልፈው ስናርን በያዙ ጊዜ ዐፄ ቴዎድሮስ ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ልቀቁ ቢሉ እምቢ በማለታቸው ሊገጥሙ እንደሆነ በጻፏቸው ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ መግለጻቸውን ማንም የሚያውቀው ታሪክ ዘግቦ የያዘው ሀቅ ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ገና በሽፍትነታቸው እያሉ ጀምረው ወራሪዎቹ ድንበር እየተሸገሩ ስናር በገቡ ቁጥር ሔደው በመውጋት ድል እያደረጉ እያባረሩ ጠብቀው ያቆዩት መሬት ነበር፡፡

እነሱ ግን ሳይታክቱ ሳይሰለቹ በየጊዜው ድንበር እየዘለሉ እየመጡ ዛሬ ሊወስዱት አቆብቁበው ካሉበት ድረስ ደረሱ፡፡ እጅግ የሚገርመኝ ነገር የሱዳን መሬት ከኛን ሀገር ከእጥፍ በላይ 2,505,813 ስኩዌር ኪሎ ሜትር (አራት ማዕዘናዊ ግዝፈ ጉዝ) ሆኖ እያለ የሕዝባቸው ቁጥር ደግሞ ከእኛ ሕዝብ ከግማሽ በታች አርባ ሚሊዮን (አእላፋት) ሆነው እያለ የዚህን ያህል መስበድበዳቸው ነው፡፡ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” ነው የሚባለው?

ወያኔዎች እውነት በሀገርና በሕዝብ ላይ ጸያፍና አስነዋሪ ክህደት የፈጸማቹህ ካሆናቹህና በድርጊታቹህ የማታፍሩ ከሆነ መሬቱ የኢትዮጵያ ለመሆኑ ጠንቅቀው የሚያውቁ ማስረጃና መረጃ የያዙ ተቆርቋሪ ወገኖች አሉና ከእነሱ ጋፍ ፊት ለፊት በመገናኘት የያዙት ማስረጃና መረጃ የተሳሳተ የውሸት መሆኑን እንድንረዳ እንድናውቅ አድርጋቹህ አሳፍራቹህ ስትሰዷቸው እንያቹሃ? እስኪ ወንድ ከሆናቹህ ከሀዲ፣ ነውረኛ፣ ወራዳ ወንበዴ ካልሆናቹህ ይሄንን አድርጉና በሉ እንያቹሃ?

መንጋ ጭንጋፍ የእንግዴ ልጅ ሁላ!!! እኔ አይደለም እናንተን ሆኘ መኖርን ላስብ ልመኝ ይቅርና እናንተን በማየቴ በእናንተ ዘመን በመኖሬ ራሱ እንዴት ዓይነት ልገልጸው ከባድ ሐፍረት መሸማቀቅ ውርደት እንደሚሰማኝ እንዴት አድርጌ በነገርኳቹህ!!! እንዴትስ አድርጌ ብነግራቹህ እናንተን ይገባቹሀል እንዴ?

የነውረኛነታቹህ ነውረኛነት ጭራሽ “ሀገሬ ተቆርሳ ባዕድ አይወስዳትም ይሄንን በዓይኔ ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ!” እያለ ከሱዳን ወታደር ጋር ጉርቦ ለጉርቦ የሚተናነቀውን ጀግና ቆፍጣና ያገሬን ገበሬ “እንደ አማራ ክልል ሽፍቶች ጠብ ጫሪነት ቢሆን ኖሮ የሱዳንና የኢትዮጵያ ግንኙነት ይሻክር ነበር። ሱዳኖች ታግሰውናል!” ብላቹህ ጀግኖቹን ቆራጦችን የቁርጥ ቀን ብርቅና ድንቅ ዕንቁ ወገኖቻችንን “ሽፍታ” ብላቹህ አዋርዳቹህ ስትጠሩ እንዲያው ጥቂት እንኳን አታፍሩም? ለነገሩ ሀገር ማለት ድንበር ማለት ምን ማለት እንደሆነ የት ታውቁትና ምድረ ምናምንቴ የእርግማን ልጅ ቆሻሻ ሁላ!

እንግዲህ ልዩነታችን ይሄንን ያህል ነው፡፡ ምንም እንኳን እናንተ ያልተማራቹህ የደናቁርት ጥርቅም ብትሆኑም ቅሉ “ያልተማረ” እያላቹህ የምትገልጹት ያገሬ ገበሬ ለአንድያ ለፍሱ ሳይሳሳ ለውድ ሀገሩ ለክቡር ድንበሩ መሥዋዕትነትን ሲከፍል “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” የሚለውን የአሕያ አስተሳሰብ የሁለንተናቹህ መርሕ ያደረጋቹህት እናንተ የጉግ ማንጉግ ጥርቅሞች ግን “የእኛ (ወያኔ) ህልውና አደጋ ላይ ከሚወድቅ የምናባቱ ሀገር፣ የምናባቱ ሉዓላዊነት፣ የምናባቱ ብሔራዊ ጥቅም” እያላቹህ ከሀገር መሬት እስከ ሕፃናት ሴቶች ልጆቻችን ድረስ ለባዕዳንና ለጠላት አሳልፋቹህ በመስጠጥ የጠላት መጫዎቻ መቀለጃ በማድረግ ይህች ሀገርና ይሄ ሕዝብ አይቶት ሰምቶት ለማያውቀው ውርደት ዳረጋቹህት፡፡ የኢትዮጵያዊነት የሰውነት ልዩነታችንን ርቀት ልብ አላቹህት? ይሄንን ያህል ናቹህ ምድረ ወራዳ! እንዴት ብላቹህ ልብ ትሉታላቹህ? መቸ የሰውነት መገለጫ አላቹህና!
እንዲያው በሞቴ አንድ ጥያቄ ልጠይቃቹህ፡- ስንት ዓመት ለመኖር ነው በዚህ ደረጃ ዘቅጣቹህ አድፋቹህ ጎድፋቹህ እረክሳቹህ የገዛ ሀገራቹህን የገዛ ሕዝባቹህን ጥቅም አሳልፋቹህ በመስጠት እራሳቹህን ለማኖር የምትጥሩት? ሰው እንዴት በዛ ቢባል ከ80 ዓመት በላይ ለማይኖረው ዕድሜ የዚህን ያህል እራሱን ያዋርዳል? ሽህ ዓመት ትኖራላቹህ እንዴ? እንዲህ እያደረጋቹህ “ኢትዮጵያዊያን ነን” ስትሉ እንዲያው ትንሽም አታፍሩም? ሰው ብትሆኑ ነበራ! በነውረኛ ድርጊታቹህ በክህደታቹህ ልታፍሩ ልትሸማቀቁ ትችሉ የነበረው፤ እናንተ ምናቹህ ሰው ነው?

ወገናዊ ጥሪ ሀገሩን እያገለገለ ለሚመስለው የወያኔ ሠራዊት፡-

በገዛ ሀገራቹህና ሕዝባቹህ ላይ ታሪካዊ ክህደት በመፈጸም ወደ ሱዳን ተቆርሶ የሚሰጠውንና ተቆርሶ የሚከለለውን መሬት ለማስረከብ የሀገራቸውን መሬት አሳልፈው ላለማሰጠት ሲዋደቁ ለቆዩትና ለመዋደቅ የተዘጋጁትን ያገሬን ገበሬዎች “በአፈጻጸሙ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ችግር ፈጣሪዎች!” ብሎ በመፈረጅ በእነሱ ላይ እርምጃ ለመውሰድ አቆብቁበህ ያለህ የወያኔ ሠራዊት ሆይ! እባካቹህ የዚህ ምስኪን ሕስብና ምስኪን ሀገር አካ መሆናቹህን አስቡ! መገመት እንደሚቻለው ማሰብ ማሰላሰል የምትችሉ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነን ብላቹህ እንደምታስቡም ያታወቃል፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ እንደወታደርነታቹህ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ከባዱ ግዴታና ኃላፊነት ያለው በእናንተ ላይ ሆኖ ሳለ ወያኔ እናንተን በመጠቀም የሀገርን ሰፊ መሬት አሳልፎ ለባዕድ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት እንደምን በጸጋ ተቀብላቹህ አስፈጻሚዎች ትሆናላቹህን???
እስኪ ልብ ብላቹህ አጢኑት? እውን ሀገር ለማስገኝጠል ሉዓላዊነቷን ለማስደፈር ነው ወይ ወደ ውትድርናው የተቀላቀላቹህ? “የገዛ ሀገሩን ያፈራረሰው ብቸኛውና የመጀመሪያው ከሀዲ ሠራዊት” ሠራዊት ተብለህ በታሪክ ተወቃሽ ተከሳሽ መሆን ትፈልጋለህ ወይ? ካልሆነ በወገንህ ላይ ልታርከፈክፈው ያዘጋጀኸውን አረር ከውስጥህ ለሀገር ሳይሆን የሀገርን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ለወያኔ ህልውና ታማኝ ሆነው ታጥቀው እየሠሩ ባሉት ከሀዲዎችና በሱዳን ወራሪ ወታደሮች ላይ አርከፍክፈውና ታሪክ ሠርተህ የዜግነት ግዴታህን ተወጣ! ስምህን ከባንዶች ሳይሆን ከጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ተርታ አሰልፍ! አስቀምጥ! ይሄንን ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ የተጣለብህን ታሪካዊ አደራ ተወጣ! አደራ በሀገሩ ፍቅር ተለክፎ ሰክሮ ነሁልሎ የሀገሩ መሬት በከሀዲያን በባንዶች ለባዕድ መሰጠቱ ኅሊናውን ባሳተው ባንገበገበው ባሳበደው ወገንህ ላይ እንዳታዘንበው በሰማይና በምድር ንጉሥ በመድኃኔዓለም ክርስቶስ፣ በአጋእዝተ ሥላሴ ስም የተገዘትክ የታሠርክ ያድርግህ!

ወገናዊ ጥሪ የወያኔን የውንብድናና የጠላትነት ተግባር እንዲህ እየተመለከትክ ለወያኔ በመሥራት ወያኔን እያገለገልክ ሀገርን የምታገለግል ለሚመስልህ የመንግሥት ሠራተኛ የወያኔ ደጋፊ ሁሉ፡-

እንደምታዩት ወያኔ ከራሱ በላይ ቅንጣትም እንኳን ብትሆን ለሀገርና ለሕዝብ የማያስብ የነውረኞች የጉዶች ቡድን ነው፡፡ ይሄ የጉዶች ቡድን ከራሱ በላይ ለማንም እንደማያስብ ለራሱ ጥቅም ከሆነ ግን አላደርገውም የሚለው ምንም ነገር የሌለው ከሀዲ እርጉም የባንዳ ጥርቅም መሆኑን እያያቹህ “እኛን እስከጠቀመ ድረስ፣ በልተን እስካደርን ድረስ” በሚል ይሄንን ግዙፍ ጸያፍ የክህደት ተግባሩን በቸልታ ብትመለከቱ አስተሳሰቡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንደመሆኑ ይሄ በሀገር ላይ የጨከተ የአውሬና የደናቁርት መንጋ ነገ ለእያንዳንዳቹህም የማይመለስ መሆኑን ጠንቅቃቹህ በመረዳት “በቃኝ! ከዚህ በኋላ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የወያኔ የጥፋትና የክህደት ሥራ ተባባሪ አልሆንም!” ብላቹህ በአንድነት በመነሣት ከራሱ በስተቀር “ኧረ እንዲያው ድንቁርናቸው ነው እንጅ ለራሳቸውም እኮ አይጠቅምም ነበር!” ለማንኛውም ከራሱ በስተቀር ለማንም በማያስበው ከሀዲ መንጋ ላይ በመነሣት እራስህን ሀገርህን እንድታድን በልዑል እግዚአብሔር ስም ትጠየቃለህ፡፡ ይሄንን ባታደርግ ግን ብዙ ሳትቆይ የሚቆጭህ መሆኑን አበክሬ ላስገነዝብህ እወዳለሁ “ወይኔ! ምነው ያኔ ተነሥቸ በነበርኩ!” የምትልበት መራራ ጊዜ ከፊትህ መጥቶ አፈር ድሜህን ያስግጥሀል፡፡ ልብ አድርግ፡፡

ወገናዊ ጥሪ ለትግሬ ሕዝብ፡-

የትግሬ ሕዝብ ሆይ! ወያኔ የህልውናው መሠረቱና አለኝታው የባዕዳን ሀገራት መንግሥታና ሆዳም አሕያ የየብሔረሰቡ አድር ባይ ሹማምንት አገልጋዮቹ መሆናቸው ቢታወቅም የአንተ አቅም ለእሱ ህልውና የሚያበረክተው ኢምንት እንደሆነ ቢታወቅም አንተን መሠረቴ አለኝታየ እያለ ህልውናው መሆንህን እየተናገረ በስምህ በመነገድ እንደኖረና እንዳለ አሳምረህ ታውቀዋለህ፡፡ 

እስከአሁንም ወያኔ በዚህች ነገርና ሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ ክህደት ሲፈጽም “በስማችን እየገዛህማ እንዲህ ልታደርግ አትችልም!” ስትል ታይተህ ተሰምተህ አታውቅም፡፡ ይልቁንም የሚመካበትን ሙሉ ድጋፍ ስትሰጥ ነው የኖርከው፡፡ እንኳንና እዚህ ሀገር ውስጥ ያለኸው ይቅርና በውጪ ሀገራት በነጻነት መቃወም በሚያስችላቸው ሀገራት ያሉ ልጆችህ እንኳን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገን ጋር ሆነው የወያኔን የክህደት ተግባር ሲያወግዙ ሲቃወሙ ታይተው ተሰምተው አይታወቁም፡፡

ወያኔ የህልውናው መሠረትና አለኝታው አንተ እንደሆንክ እንድትታሰብ ማድረጉና ያደረገውን ቢያደርግ ዝም ማለትህ ወያኔ በፈጸመው ክህደትና ወንጀሎች ነገ ተጠያቂው አንተ መሆንህን ልብ ብለኸዋል ወይ? ከዚህ በላይ መቸና ምንስ ቢያደርግ ነው “አይ! በስማችን እየተጠቀምክማ እንዲህ ልታደርግ አትችልም! አንተ ነገ አላፊ ነህ እኔ ግን እንደ ሕዝብ ኗሪ ነኝ ነገ አንተ በፈጸምከው ግፍ ወንጀልና ክህደት ሁሉ እኔ ተጠያቂ ዕዳ ከፋይ መሆኔ ስለማይቀር እንዲህ እንኳን ልታደርግ አትችልም!” የምትለው መቸና ምንስ ቢያደርግ ነው? የወያኔ ነውረኛ ቆሻሻ ወራዳ ማንነት እንደ ሕዝብ አያሸማቅቅህም ወይ? አያሳፍርህም ወይ? እባክህ ይሄ የወያኔ አሳፋሪና አዋራጅ ክህደት መንቂያህ ይሁንና “ዞር በል ወራዳ አዋራጅ አላውቅህም! አልይህ!” በማለት ከሌሎቹ ወገኖችህ ጋር ቁም ተሰለፍ! “አንተን የሚበላ ጅብ እኔንም ይብላኝ” ከሚለው አስተሳሰብህ ተላቀቅ!!!

ወገናዊ ጥሪ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፡-

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ዝምታህ እስከመቸ ነው? ከቶ ምን ቀረህ? ይሄ የወያኔ ክህደት ምንም ቢሆን ልትታገሳቸው ከማትችላቸው ጉዳዮች እንዳልሆነ እያወክ የዝምታህ ምሥጢር ምንድን ነው? ምን ዓይነት አዚም ነው አፍዝዞ አደንዝዞ እያስበላህ ያለው? ኧረ እባክህ ንቃ! ኧረ እባክህ ጨርሰህ ሳትጠፋ በቃ! በል?

አንድ ላይ ሆ! ብለህ ይሄንን ግፈኛ ነውረኛ ወራዳ አገዛዝ እንዳትገላገል ያደረጉህን እንደወትሮህ ሀገር ስትነካ ቀፎው እንደተነካበት ንብ አንድ ላይ ሆ! ብለህ በመነሣት የሀገርህን ድንበር ብሔራዊ ጥቅምህን እንዳታስጠብቅና እንዳታስከብር ወያኔ ኦነግና ሌሎቹ የጥፋት ኃይሎች በዘር በሃይማኖት ከፋፍለው የጥንካሬህን ምንጭ አንድነትህን አፈራረሱት የአንደኛህ ሕመም ለሌላኛህ የማይሰማህ የጎጥህ እንጅ የሀገርህ ጥፋትና ጉዳት የማይገድህ የማትተባበር አድርገው የግፍ አገዛዙ በአፍ ጢምህ እስኪደፋህ በሰብእናህ እስኪጫወትብህ ሀገር አልባ አድርጎ እንደባሪያ እንደመጻተኛ በሀገርህ ጉዳይ የማያገባህ ባዕድ እስኪያደርግህ አገርህን ሲያፈራርሳት ድረስ ተሸክመኸዋል፡፡

በፊት ከነበረህ የላቀና የሠለጠነ አስተሳሰብህ ማለትም ጠባብ ጎጠኝነት ጠባብ ብሔርተኝነት ጎጅ እንጅ ጠቃሚ አለመሆኑን፣ ጠባብ ብሔርተኞች ሥልጣን ይዘው ሆነው እንደምናያቸው ፀረ ዲሞክራሲያዊና (መስፍነ ሕዝባዊና) ፀረ ሰብአዊ አስተሳሰብ መሆኑን፣ የሰው ልጆችን ዕኩል ያለማየት ለማየትም ያለመፈለግ አድልኦ የሞላበት ኢፍትሐዊ አስተሳሰብ የተጣባው የተቆራኘው መሆኑን፣ ሀገር የሚያፈርስ ነቀርሳ አስተሳሰብ መሆኑን ጠንቅቀህ ተረድተህ አንድነትን የነገሮችህ ሁሉ መሠረት በማድረግ በምንም ነገር ብትፈተን ምንም ዓይነት ችግር ቢደርስብህ ጨቋኞችና ሀገር የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን በመገንዘብ አንድነትህን ለድርድር ሳታቀርብ በሀገርህና በህልውናህ ላይ የሚመጣብህን ፈተና ስትመክት፣ ስታከሽፍ፣ ስታሸንፍ ከኖርክበት የሐሳብ ልቀትህና የሠለጠነ ሥነልቡናዊ ልዕልናህ ከፍታህ አውርደው የድንቁርና አስተሳሰብ በሆነው፣ ጠንቅ፣ ችግር፣ ሞት በሞላበት ጠባብ የጎጠኝነት ነቀርሳ የመረዙህንና በጠንቅ በምስቅልቅል ማጥ ውስጥ ላትወጣ እያሰመጡህ ያሉትን ወያኔን ኦነግንና ሌሎች የጥፋት ኃይሎችን ከነደንቆሮ አስተሳሰባቸው ከጫንቃህ ላይ አሽቀንጥረህ ወርውረህ በአንድነት መድኃኒትህ እራስህንና ሀገርህን ከሞት ከጥፋት ከመፈራረስ ታድን ትታደግ ዘንድ የእነ አርበኛው አቡነ ጴጥሮስን ግዝት የሰማችው ምድር ለአንተ ደግሞ አፍ አውጥታ “የኔ ሞት ያንተ ሞት ነው! የኔ መፈራረስ ያንተ መፈራረስ ነው! የኔ መጥፋት ያንተ መጥፋት ነው! ልብ አድርግ ስማ! ስማ! ስማ!” እያለች ትማጸናለች ለራስህ ብትል ስማ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!


ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/49582

No comments:

Post a Comment