Saturday, May 21, 2016

የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተግባራዊ ሊደረግ ነው (ቪኦኤ)

የኢትዮጵያ መንግሥት በፀር ሽብር ሕጉን በሀገር ውስጥ ፖለቲካው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው በሚል መከሰስ ከጀመር አራት ዓመታት ተቆጥሯል። አሁን ደግሞ የኢንተርኔት አምደኞች እና ፖለቲከኞች ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን የበለጠ ስጋት ላይ የሚጥል አዲስ የኮምፒዩተር ረቂቅ ወንጀል ዐዋጅ ወጥቷል።

በሚያዝያ ወር 2008 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ እየተተቸ ከሚገኝበት ነገር አንዱ ሐሳባቸውና የግል አመለካከታቸውን በኢንተርኔት አማካኝንት የሚገልጹ ግለሰቦችን የኢትዮጵያ መንግሥት አሥሮ የሚቀጣበት አንቀጽ ማካተቱ ነው።
ዳንኤል ብርሃኔ በኢትዮጵያ የሚገኝ የኢንተርኔት አምደኛ ነው። የራሱ ድረ ገጽም አለው። አዲሱ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ ሐሳቡን በኢንተርኔት አማካኝነት በሚገልጽ በማንኛውም ግለሰብ ላይ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ዐዋጅ ነው ብሎ ያምናል።
“ይሄ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉም ኾነ በመገናኛ ብዙሐን ሕጉ የተሰጡንን መብቶች የሚጥስ ነው። እስካሁን ካሉት ሕጎች ሁሉ የበለጠ ከልካይ ነው። በአንድ ዓረፍተ ነገር ብቻ ይከለክላል” ይላል።
የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጁ በአብዛኛው ትኩረት የሚያደርገው በኢንተርኔት አማካኝነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው በኢንተርኔቱና በኮምፒዩተሩ አማካኝነት ወንጀል ፈጽሟል ብቻ ሳይኾን ወንጀል ተፈጽሞበታል ተብሎ ከተገመት ያለ ምንም ፍርድ ቤት ፍቃድ እና ትእዛዝ ብሔራዊ ደሕንነት ኮምፒዩተሩን በአካል ሳይነካ እንዲመረምር ሥልጣን የሚሰጠው አንቀጽ በረቂቁ ውስጥ ተካቷል።
በኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ዳይሬከተር የኾኑት አቶ በላይይሁን ይርጋ ረቂቅ ዐዋጁ ሐሳባቸውን በኢንተርኔት በነፃነት ከሚገልጹ ሰዎች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ይላሉ።
“አንድ ሰው የእራሱን ሐሳብና አመለካከት ከተናገረ ብቻ በወንጀል ተጠያቂ አይኾንም። የዚህ ሕግ ዋና ዓላማ ግን ሰዎች ከስም ማጥፋት ጋር በተያያዘ ለድርጊታቸው የሚኖራቸው ዓላማ ነው። ዋነኛ ዓላማቸውና ግባቸው ስም ማጥፋት ከኾነ ተጠያቂ ይኾናሉ።ም ክንያቱም ስም ማጥፋት ወንጀል ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በኢንተርኔት አማካኝነት ሐሳባቻውን የሚገልጹ ግለሰቦችን በማሰቃየት፣በማሰር እና ረጅም ዓመታት በመፍረድ በተደጋጋሚ ትወቀሳለች። በዚህ ሰለባ ከኾኑት መካከል 18 ዓመት እስር ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር
ነጋ አንዱ ነው። እንዲሁም የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ከአንድ ዓመት በላይ እስር ቤት ማሳለፋቸው ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።
የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው አስተያየት አማካኝነት ከታሠረ ስድስት ወራት ተቆጥሯል።
ሃበን ፈቃዱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሠራተኛ ነች የኢትዮጵያ መንግሥት በፀር ሽብር ሕጉን በሀገር ውስጥ ፖለቲካው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው ትላለች። የአቶ ዮናታንን ጉዳይም በምሳሌነት ትጠቅሳለች።
“በዮናታን ክስ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች በጣም አሳሳቢና መንግሥት አንድን ግለሰብ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በሚጽፋቸው ነገሮች ላይ ተመስርቶ እንዲያሥር የሚፈቅድ ነው። ዮናታን የታሠረው በጸር ሽብር ሕጉ አማካኝነት ነው። ምን አይነት ማስረጃ እንደሚቀርብበት እንኳን ሳያውቅ ነው ፍርድ ቤት የቀረበው” ትላለች።
ይሄ የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ ዐዋጅ በሚቀጥለው ሳምንት ተግባራዊ የደረጋል ተብሏል።
ማርታ ቫንዶርፍ ከአዲስ አበባ ያደረሰችን ዘገባ ጽዮን ግርማ ታቀርበዋለች። ዝርዝሩን ከተያያዘው ድምጽ ያድምጡ።
http://www.satenaw.com/amharic/archives/16661

Sunday, May 8, 2016

መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ጋዜጠኛና ደራሲ ፋሲል ተካልኝን ጥርሱን አወለቁት

በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በጋዜጠኝነት የሚታወቀው ደራሲና ጋዜጠኛ ፋሲል ተካልኝ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ክፉኛ እንደደበደቡት አስታወቀ:: ፋሲል በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ገጠመኙን እንዳሰፈረው ከሆነ በድብደባው ጥርሱን አጥቷል::

ገጠመኙን እንደወረደ አንበቡት:-

እንዲህ ሆነላችሁ፡፡
ሚያዚያ 6 ቀን 2008 / በግምት ከምሽቱ 4 ሰዓት (ከአዲስ አበባ ሬስቱራንት ጀርባ) አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቅራቢያ አካባቢ መሣሪያ ያነገቱ አምስት ሰዎች ተረባርበው ደበደቡኝ፡፡ራሴን ሳትኩ፡፡ከዚህ በኋላ የሆነውንና የተደረገውን አላውቅም፡፡ ስነቃና ራሴን ሳውቅ ሆስፒታል ውስጥ ድንክ አልጋ በመሰለና ቁመቱ በረዘመ ስትሬቸር ላይ ተኝቼያለሁ፡፡ በግራ እጄ አይበሉባ ግሉኮስ ተሰክቷል፡፡ ማን አመጣኝ? እንዴት መጣሁ? ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ዳሩ ግን ማስታወስ የቻልኩት ራሴን እስክስት የነበረውን ብቻ ነው::

በነጋታው ሆስፒታል የተኛሁበት ተኝቼ ካለሁበት ድንገተኛ ክፍል ድረስ በመምጣት ሲናገር እንዳደመጥሁት የፖሊስ ቃል ከሆነ ሸራተን ምግብ ቤት አካባቢ መንገድ ላይ ወድቄ እንዳገኙኘኝና ወደ ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ይዘውኝ እንደመጡ ነው፡፡ ማለዳ ላይ የተለያዩ ወጣት ሐኪሞች የተካተቱበትና በአንድ አንጋፋ ሐኪም በሚመራ ቡድን ተጎበኘሁ፡፡ በጉብኝቱ መሪ ሐኪም ምን እንደሚሰማኝ ተጠየቅሁ፡፡ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ጉሉኮሱ እንዲነቀልልኝና ወደ ጥርስ ህክምና ክፍል እንድሄድ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ወጡ፡፡እንደወጡ ወደ ጥርስ ህክምና ተወስጄ ተመረመርኩ፡፡ ተመርምሬም መድኃኒት ታዘዘልኝ፡፡ በመጨረሻም በሕይወት ወደ ቤቴ ለመግባት ችያለሁ፡፡

ይሁን እንጂ በጎድን አጥንቴና በጀርባዬ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ ሆስፒታል እስክወሰድ ድረስ መንገድ ላይ ወድቄ በነበርኩበት ሰዓት ብዙ ደም ፈሶኛል፡፡በዚህም ምክንያት እስካሁን ያዞረኛል፡፡ሁለት የግራና የቀኝ የላይኛው መንጋጋ ጥርሶቼ ተነቃንቀዋል፡፡ የላይኛውና የፊት ለፊቱ አራት ሰው ሰራሽና ከታች የሚገኙ ሁለት የፊት ለፊት በድምሩ ስድስት ጥርሶቼ ሙሉ ለሙሉ ወልቀዋል፡፡

በተጨማሪም በወቅቱ አድርጌ የነበረውን ሸራ ጫማን ጨምሮ ለጡዘት ቁጥር 2 የግጥም መድበል የተሰናዱ የተለያዩ ግጥሞችና ሌሎች ጽሑፎችን የያዘውን ተንቀሳቃሽ ስልኬን በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ( ጥቂት የተለያዩ ውጭ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች ያሉበት) የተለያዩ መታወቂያዎችንና የኤ..ኤም ካርድ ይዞ የነበር ቦርሳዬ ተወስዷል፡፡


የሆነው ሆኖ በሀገራችን የዜግነት ክብር ይሉት ሐረግ ያለው በብሔራዊ መዝሙር ውስጥ ነው እንጂ በገሐድ እንደሌለ በተለያዩ አጋጣሚዎች
ከማረጋገጥ ባሻገር መንግስት ተብዬውም ለሥልጣኑና ለሥርዓቱ እንጂ  ለዜጎቹ ጥበቃ እንደማያደርግ እንደዚሁም ደንታ ቢስና ግድ የለሽ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ስለዚህ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ማንንም አልከስም፡፡ከማንም መፍትሔ አልጠብቅምም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከዚህ ከሰፊው መንደር መጥፋቴን ተከትላችሁ፣አለመኖሬ አሳስቧችሁ፣በስልክም ሆነ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ በሙሉ ልባዊ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/60253

Wednesday, May 4, 2016

ዮናታን ተስፋዬ በፌስ ቡክ ገጹ የለጠፋቸው ጽሁፎቹ የክስ ማስረጃ በመሆን ቀረቡበት

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም የወጣውን አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ዛሬ ሚያዝያ 26/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክሱ በዳኞች ቢሮ በንባብ የተሰማበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24/2008 ዓ.ም ጀምሮ ተከሳሹ በሚጠቀምበት ደረ-ገጽ በተለይም ፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ‹‹አመጽና ብጥብጥ›› ለማስቀጠል የኦነግን አላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦበታል፡፡ አቃቤ ህግ ለመሰረተው ክስ  የማስረጃ ዝርዝር በማድረግ ያቀረባቸው በማህረሰብ ሚዲያ የለጠፋቸውን ፅሁፎች ናቸው፡፡
ተከሳሹ ‹የኦነግን  አላማ ለማሳካት አመጽና ብጥብጡ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በሚጠቀምበት ደረ-ገጽ (ፌስቡክ) ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመጻፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር፣ እና ማነሳሳት ወንጀል› መከሰሱን የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል፡፡
አቃቤ ህግ ማስረጃ በማድረግ የጠቀሳቸው የዮናታን ጽሁፎች መካከልም ቀን 08/04/2008 ዓ.ም ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በተመለከተ የጻፈው፣ በ11/04/2008 ዓ.ም ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም በሚል የጻፈው፣ 06/04/2008 ዓ.ም ሲጀመር ምንም ማስተር ፕላን የለም በሚል የጻፈው፣ 01/04/2008 ዓ.ም የተቃውሞ ትግሉ ቀጥሏል በሚል የጻፈው፣ 28/03/2008 ዓ.ም እንሆ 7 መልዕክት ብሎ በጻፈው እና በሌሎችም ጽሁፎች አማካኝነት ቅስቀሳ አድርጓል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ጠቅሷል፡፡
ዮናታን ተስፋዬ ብቻውን የተከሰሰ ሲሆን፣ ዛሬ ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ጉዳዩ በቢሮ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ዮናታን የክስ መቃወሚያውን ይዞ እንዲቀርብ ለግንቦት 15/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
http://www.satenaw.com/amharic/archives/16267