Wednesday, May 4, 2016

ዮናታን ተስፋዬ በፌስ ቡክ ገጹ የለጠፋቸው ጽሁፎቹ የክስ ማስረጃ በመሆን ቀረቡበት

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም የወጣውን አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ዛሬ ሚያዝያ 26/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክሱ በዳኞች ቢሮ በንባብ የተሰማበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24/2008 ዓ.ም ጀምሮ ተከሳሹ በሚጠቀምበት ደረ-ገጽ በተለይም ፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ‹‹አመጽና ብጥብጥ›› ለማስቀጠል የኦነግን አላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦበታል፡፡ አቃቤ ህግ ለመሰረተው ክስ  የማስረጃ ዝርዝር በማድረግ ያቀረባቸው በማህረሰብ ሚዲያ የለጠፋቸውን ፅሁፎች ናቸው፡፡
ተከሳሹ ‹የኦነግን  አላማ ለማሳካት አመጽና ብጥብጡ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በሚጠቀምበት ደረ-ገጽ (ፌስቡክ) ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመጻፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር፣ እና ማነሳሳት ወንጀል› መከሰሱን የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል፡፡
አቃቤ ህግ ማስረጃ በማድረግ የጠቀሳቸው የዮናታን ጽሁፎች መካከልም ቀን 08/04/2008 ዓ.ም ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በተመለከተ የጻፈው፣ በ11/04/2008 ዓ.ም ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም በሚል የጻፈው፣ 06/04/2008 ዓ.ም ሲጀመር ምንም ማስተር ፕላን የለም በሚል የጻፈው፣ 01/04/2008 ዓ.ም የተቃውሞ ትግሉ ቀጥሏል በሚል የጻፈው፣ 28/03/2008 ዓ.ም እንሆ 7 መልዕክት ብሎ በጻፈው እና በሌሎችም ጽሁፎች አማካኝነት ቅስቀሳ አድርጓል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ጠቅሷል፡፡
ዮናታን ተስፋዬ ብቻውን የተከሰሰ ሲሆን፣ ዛሬ ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ጉዳዩ በቢሮ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ዮናታን የክስ መቃወሚያውን ይዞ እንዲቀርብ ለግንቦት 15/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
http://www.satenaw.com/amharic/archives/16267

No comments:

Post a Comment