Friday, December 6, 2013

ለእምነት፣ ለእውነትና ለሕሊና የሚስማማ ሥራ እንስራ

ከእውነት መስካሪ
የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ በዘመናት ካጋጠሟት ፈተናዎችና ችግሮች ሁሉ ምናልባትም በአይነቱ ብቻ ሳይሆን በስፋቱም ለየት ያለው ይህ አሁን በእኛ ዘመን የተከሰተው የአባቶች መከፋፈል ወይንም በፖለቲካ ጣልቃገብነት የተፈጠረው የቤተክርስቲያኗ አመራር ክፍፍል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በአጠቃላይ በክርስትና ላይ የደረሰውን ፈተና ትተን በእኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ብቻ የደረሰውን እንኳን ብናይ በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣በ15ኛው መ/ክ/ዘ በግራኝ መሐመድ፣በ18ኛው መ/ክ/ዘ በእንግሊዝ፣ በ19ኛውና በ20ኛው መ/ክ/ዘ በፋሺሰት ኢጣልያ ወረራ በቅርቡም በደርግና አሁን ደግሞ በወያኔ ኢህአዴግ መንግሥታት በቤተክርስቲያናችን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን በቀደመው ዘመን የነበሩት አባቶቻችን በእምነትና በእውነት እየተመሩ ለህሊናቸው ብቻ ሳይሆን ለትውልድም የሚያኮራ ስራ ትተውልን አልፈዋል፡፡
በዮዲት ጉዲት 40 ዓመት የመከራ ዘመን መከራው ስለበዛባቸው 10ኛው ወይንም 20 ኛው አመት ላይ እንግዲህ በቃን እስከመቼ እንዲህ ሞተንና ተሰደን እንዘልቃለን ልጆቻችንስ እስከመቼ እንዲህ ሆነው ያድጋሉ በማለት እጃቸውን ለጨፍጫፊዋ ዮዲት አልሰጡም። 40 የመከራ አመታትን በሰማእትነት፣በስደትና በመከራ አሳልፈው ተዋሕዶ እምነታችንን እስከነምልክቷ አስተላልፈውልናል። በዘመነ ግራኝም እምዲሁ ሰማእትነትን ከፍለው ታቦታቱን በዋሻ ደብቀው ከአገር አገር ተንከራተው ኃይማኖታችንን ከነክብሯ አስተላልፈውልናል።
ፋሺት ኢጣልያንም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን አቃጥሏል። በተለይም ታላቁን የደብረሊባኖስ ገዳም ከማቃጠሉ በተጨማሪ ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሆኑ ገዳማዊያንን በግፍ ጨፍጭፏል። ይሁን እንጂ የቀደሙት አባቶቻችን በእምነታቸው ጽናት ለጨፍጫፊዎችና ወራሪዎች ሳይንበረከኩ ኃይማኖትን ከነምልክቱ አገርን ከነነጻነቱ አቆይተውልናል። በጣልያን የኋለኛው ወረራ ወቅት የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ አባት የነበሩትን ፃድቁ ሰማእትና አርበኛ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ጣሊያን በአደባባይ ከገደለ በኋላ ለጣሊያን መንግሥት ያደሩ አንዳንድ ባንዳ ‘አባቶች’ ከጣሊያን ጎን ተሰልፈው ሕዝቡ ለጣሊያን እንዲገዛ ሲያደርጉ የነበሩ መኖራቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በተለይም በሰማእቱ አቡነ ጵጥሮስ ወንበር አቡነ አብርሃም የተባሉ አባት ለጣሊያን አድረው በአቡነ ጵጥሮስ ቦታ ተሾመው ነበር። ጀግኖች አባቶቻችን ግን ይህን አይነቱን ክህደት አንቀበልም በማለት በዱር በገደሉ ለአገራቸውና ለኃይማኖታቸው ነጻነት ተጋድለዋል።
በተጋድሎአቸውም ተዋሕዶ እምነታችንን ከካቶሊክነት ኢትዮጵያንም ከቅኝ ግዛት ታድገዋታል። እንግዲህ እኛ አባቶቻችን የምንላቸው ሰማእታት ሆነው፣ተሰደውና በእምነታቸው ጸንተው እምነታችንን ከጠላቶቻችን ታድገው ያቆዩልንን እንጂ በክህድት፣በፍርሐት፣በወገኝተኛነት፣በዘርና በመሳሰሉት ምክንያት ከጠላት ጎን ሆነው ኃይማኖታቸውንና አገራቸውን የከዱትን አይደለም።
በዚህ በእኛም ዘመን ያለን የተዋሕዶ አማኞች አባቶቻችን የምንላቸው እነማንን ይሆን?
የኢትዮጵያ ክብር ሲዋረድና ሕዝቦቿ ሲሰደዱ ይህን ከሚያደርገው አካል ጋር የቆሙትን?
ወይንስ የአገር ዳር ድንበር መፋለስና የህዝቦቿ አንድነት መሸርሸር የለበትም ብለው ከተሰውና ከተሰደዱትን ጋር?
በቤተክርስቲያን ላይ በመጠን ሊገለጽ የሚከብድ ጥፋትን እያደረሰ ካለ ኃይል ጋር የቆሙትን? ወይንስ ይህን የቤተክርስቲያንን መጠቃት የሚቃወሙትን ነው አባቶቻችን የምንል?
ምናልባተ በዘመናችን በእውነት ስለኃይማኖትና ስለአገር ብቻ ሳይሆን የራስንም ክብርና ምኞት ለማሳካት የሚደረግ ነገር በሁሉም ዘንድ አንዳለ ቢታየን አምላካችን በእውነት እስኪገለጥልን በያለንበት እንጽና እንዳለው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከአጥፊዎችና ከጥፋቱ ተባባሪዎች ጋር ከመቆጠር ራሳችንን ልናቅብ ይገባናል። እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድ አለው፤በኃይለኛ ውኃ ውስጥ መተላለፊያ ያደርጋል እንዳለ ነብዩ ኢሳ.43፥13 ሁሉ በእግዚአብሔር ጊዜ ስለሚፈጸም፤ የቤተክርስቲያን ልዕልናና የኢትዮጵያ ትንሳዔ መምጣቱ ስለማይቀር ያለነው ትውልዶች ለእምነት፣ለእውነትና ለሕሊና የሚስማማ ሥራ ሰርተን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!

   Posted By.Dawit Demelash

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/10534


ኔልሰን ማንዴላ እና ኢትዮጵያ!!

December 6, 2013
የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በ95 አመታቸው ከዚህ አለም ሲለዩ፤ የተለያዩ አገሮች እንደየራሳቸው ግንኙነት የራሳቸውን ታሪክ ሲያወሩ ነበር። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ሃዘናቸውን ሲገልጹ ከማንዴላ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመግለጽ ነበር። እኔ በምኖርበት አትላንታ ከተማ ዜናው ሲቀርብ፤ ኔልሰን ማንዴላ አትላንታ በመጡበት ወቅት፣ ከነአንድርው ያንግ ጋር ሆነው የማርቲን ሉተር ኪንግ ማዕከልን ስለመጎብኘታቸው ነበር – ዋናው ዜና። ሁሉም አገር ስለማንዴላ የየራሱ ትዝታ አለው። ኢትዮጵያውያንም ስለኔልሰን ማንዴላ የራሳችን ታሪክ እና ትዝታ አለን። እናም ማንዴላ የዛሬ 51 አመት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ስለነበረው ጉዳይ በማውጋት ታሪካችንን እንጀምራለን።
Nelson Mandela, the revered statesman who emerged from prison after 27 years
በዳዊት ከበደ ወየሳ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ በ1962 ዓ.ም አራተኛው የፓን አፍሪካ ስብሰባ በኢትዮጵያ እንዲደረግ ጃንሆይን ፍቃድ ጠየቁ። ጃንሆይ በጉዳዩ ተስማሙና በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም የአፍሪካ ታዋቂ የነፃነት ታጋዮች ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ከእነዚህም መሃከል ሚስተር ኦሊቨር ታምቦ፣ ሚስተር ሮበርት ሙጋቤ፣ ሚስተር ኬኔት ካውንዳ እና ሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ይገኙበታል። (በኋላ ላይ እነዚህ ወጣት ታጋዮች የየአገራቸው ፕሬዘዳንት ሆነዋል) ይህ ጉዞ በተለይ ለኔልሰን ማንዴላ በህይወታቸው ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጡት ነው።
Nelson Mandela and Col. Tadesse in Addis Ababa, Ethiopia
የኔልሰን ማንዴላ አሰልጣኝ ከነበሩት መካከል፣ ኮሎኔል ታደሰ አንዱ ነበሩ። ይህ ፎቶ ማንዴላ እና ኮ/ል ታደሰ (በሗላ ጄነራል) ለመታሰቢያ የተነሱት ነው
የኔልሰን ማንዴላን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ያሰናዱት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ። በወቅቱ በአፓርታይድ የዘረኝነት ቀንበር ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ዜጎችዋ ያለፈቃድ አገሪቱን ለቀው እንዳይወጡ የሚያዝ ህግ አውጥታ ነበር። ይህ ህግ ለኔልሰን ማንዴላ ጉዞ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጠረ። በመሆኑም አቶ ከተማ ይፍሩ ለኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልፅ ፓስ ፖርት ካዘጋጁላቸው በኋላ ነበር፤ በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፤ ወቅት ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።
በወቅቱ ለኔልሰን ማንዴላ የተዘጋጀው ፓስፖርት ላይ ማንዴላ እንደጋዜጠኛ ሆነው፤ ስማቸው ዴቪድ ሞሳማይ ተብሎ ነበር የተጻፈው። ስሙን የተጠቀሙት ደቡብ አፍሪካ እያሉ አብሯቸው ከነበረው ጓደኛቸው ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ስለነበረው ጉዞ እናውጋ። ኔልሰን ማንዴላ “Long Walk To Freedom” በሚለው መፅሃፋቸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አየር መንገድ ድረስ መጥተው እንዴት እንደተቀበሏቸው ገልፀዋል። እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ ኔልሰን ማንዴላ…
ለንደን የነበሩትን ጓደኞቼን በወዳጅነት ስሜት ተሰናብቼ ወደ አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ ተጓዝኩ። እስካሁን ባለው ህይወቴ ለማላውቀው ወታደራዊ ስልጠና ነው የምሄደው። የስድስት ወር ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ በያዝኩት ፕሮግራም መሰረት ነው ወደ ኢትዮጵያ የምጓዘው። አዲስ አበባ ስደርስ መጀመሪያ ተቀብለው ያነጋገሩኝ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከተማ ይፍሩ ነበሩ። ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። ከዚያም “ኮልፌ” ወደሚባለው አንድ የከተማው ክፍል ወሰዱኝ።
የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ የሚሰለጥነው እዚህ ኮልፌ የሚባለው ሰፈር ነው። የባታሊዮኑ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው ከዚህ ነው። አኔ ወታደራዊ የሳይንስ ጥበብ እንድማር የተመደብኩበትም ስፍራ እዚህ ነው። እስካሁን ባለኝ ልምድ ጀማሪ ቦክሰኛ ከመሆን ውጭ ስለጦር ሜዳ ፍልሚያ የረባ እውቀትም የለኝም። አሰልጣኜ መቶ አለቃ ወንድሙ በፍቃዱ ይባላል። በጣልያን ወረራ ግዜ የደፈጣ ተዋጊ የነበሩ ልምድ ያላቸው ወታደር ናቸው።
በአዲስ አበባ መውሰድ የጀመርነው የስልጠና ፕሮግራም ጥብቅ ነው። ከጠዋቱ 2፡00 ሰአት እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ ስልጠና ላይ እንቆያለን። ከዚያ የምሳ ሰዓት ነው። ከዚያ ከሰዓት ከ8፡00 እስከ 10፡00 ስልጠናው ይቀጥላል። ከ10፡00 ሰዓት በሁዋላ እስከምሽቱ ድረስ ስለ ወታደራዊ ሳይንስ የንድፈ ሃሳብ ገለጻ ይደረግልናል። ይህንን ስልጠና የሚያደርጉልን ኮሎኔል፤ የፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ናቸው። በንጉሱ ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲከሽፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በስልጠናው የአውቶማቲክ መሳሪዎች እና የሽጉጥ አጠቃቀምን ተማርኩ።
መጀመሪያ ኮልፌ ከዚያም ከኮልፌ 50 ማይልስ የምትርቅ ቦታ ከወታደሮቹና ከንጉሱ የክብር ዘበኛ አባላት ጋር ሄጄ የኢላማ ተኩስ ተለማመድኩ። የሞርታር ተኩስና እንዲሁም የቦንንብ አሰራሮችን፤ ፈንጂዎችን የማክሸፍ ዘዴንም ተማርኩ። አሁን እያደር ወታደር እየሆንኩ ስሄድ ይታወቀኛል። እንደ ወታደር ማሰብ ለመድኩኝ። ወታደር መሆን እንደ ፖለቲከኛ ከማሰብ የሚለይበት የራሱ መንገድ አለው።
እዚህ ቦታ ላይ በጣም የወደድኩት ጠዋት ተነስተን የምናደርገው የማለዳ ጉዞ ነው። ጠመንጃ፣ ጥይትና ጥቂት ውሃ እንይዛለን። እናም በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ ያንን ርቀት ተጉዘህ የታዘዝከውን ፈፅመህ መድረስ አለብህ። በዚህ ወታደራዊ ጉዞ የአገሪቱን ገጠራዊ ክፍሎች ለማየት እድሉን አገኘሁ። የመሬቱ አቀማመጥ በጣም ቆንጆ ነው። ጥቅጥቅ ያለ ደንና ከፍተኛ ቦታዎችን አየሁ። ገጠሩ በጣም ሁዋላ ቀር ነው። ሰዎች በእንጨት መቆፈሪያ ነው የሚያርሱት። ምግባቸውም ትንሽና በቀላሉ የሚዘጋጅ ነው። እቤት የሚጠመቅ ቢራ ወይም ጠላ አላቸው፤ ኑሯቸው እዚህ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ መከረኞች ጋር ተመሳሳይ ነው። መቼም ደሃ ሰዎች የትም ቢኖሩ ኑሯቸው አንድ አይነት ነው፤ ብዙም አይለያዩም።
በስልጠናዬ ወቅት ኮሎኔል ታደሰ ብዙ ጉዳዮችን እያነሱ ያስተዋውቁኛል። ስለ ደፈጣ ውጊያ፤ ሃይል እንዴት ማዋቀር እንደሚቻል አንድን ጦር እንዴት ማዘዝና መምራት እንደሚቻል፤ በጦር ውስጥ ወታደራዊ ስነ ስርአትን ለማስፈን ምን ማድረግ እንደሚገባ ያስተምሩኛል።
አንድ ምሽት እራት ላይ ለደቡብ አፍሪካ ትግል ምን አይነት ጦር እንደሚያስፈልገንና የሰራዊቱ ባህሪ ምን መሆን እንዳለበት አጫወቱኝ። “ይኸውልህ ማንዴላ… አንተ የምትመሰርተው ነፃ አውጪ ሃይል እንጂ መደበኛ ጦር አይደለም። የናንተን ጦር ሰዎች የምትቀርፅበት ስልት ከመደበኛው ጦር አሰራር የተለየ ነው። አንተ መመስረት ያለብህ ነፃ አውጪ ጦር ነው። በትግል ላይ ስትገባም የምትመራቸው ተከታዮችህ ፍፁም እርግጠኝነት እንዲሰማቸውና ሁሉም ሃሳብህን እንዲከታተሉ ማድረግ መቻል አለብህ። ይህ በመደበኛው ጦርም ውስጥ ያለ ነው። ከስራ በሁዋላ በእረፍት ሰዓትህ ማድረግ የሚገባህ ግን ከመደበኛው ደንብ ውጪ ይለያል። አንተና የመጨረሻው ተራ ተዋጊ እኩል መሆናችሁን የሚያሳይ አቀራረብ ሊኖርህ ይገባል። የሚበሉትን ትበላለህ፤ የሚጠጡትን ትጠጣለህ። ምግብህን ወደ ግል ክፍልህ መውሰድ የለብህም። እራስህን ገለል አታድርግ፤ እዚያው አብረሃቸው ሁን።” አሉኝ። የኮሎኔልን ሃሳብ ተረድቻለሁ። ሃሳቦቹ የሚደነቁና መልዕክት ያዘሉ ናቸው። እንደነዚህ ያሉ ቁም ነገሮችን በየፕሮግራሙ መሃል ይነግሩኝ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለስድስት ወር ስልጠና ነው። ስምንት ሳምንት እንደሆነኝ ግን ከድርጅቴ ‘የአፍሪካ ኮንግረስ’ አንድ የቴሌ ግራም መልዕክት ደረሰኝ። ባስቸኳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንድመጣ የሚጠይቅ ነው። የዚያን ጊዜ የነፃነት ትግሉ መፋፋም ጀምሯል። እናም የግንባሩ አዘዥ እዚያው ቦታው ላይ መገኘት ስላለበት ነው የጠሩኝ። ኮሎኔል ታደሰ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የምሄድበትን መንገድ ቶሎ አዘጋጁልኝ። ስንሰነባበት አንድ ሽጉጥና ሁለት መቶ ጥይት ስጦታ አበረከቱልኝ። ስለ ስልጠናውም ሆነ ሰጡኝ ትምህርት ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ገለጽኩና ጉዞዬን ጀመርኩ። መሳሪያ ተሸክሞ ረዥም መንገድ መጓዝን ብለማመድም የተሰጠኝ መሳሪያ ከባድ ነው። ሁለት መቶ ጥይት ጀርባ ላይ መታጠቅ ህጻን ልጅ በጀርባ እንደማዘል ነው የሆነብኝ።
ኦገስት 5 ቀን፣ 1962 ላይ… ኔልሰን ማንዴላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ኤርፖርት ሲደርሱ ጥብቅ ፍተሻ ተደረገባቸው። ከጦር መሳሪያው በተጨማሪ በኪሳቸውም ውስጥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልጽና የአቶ ከተማ ይፍሩ ፊርማ ያለበት ፓስፖርት ተገኘባቸው። በኢትዮጵያ መቆየታቸውን የሚገልጽ የጃንሆይ ማስታወሻና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ አነስተኛ ፎቶ ነበር። እነዚህን ጨምሮ 173 መረጃዎች በሪቮንያ የአፓርታይድ ችሎት ላይ ቀረበባቸው – 1963።
እነዚህና ሌሎች መረጃዎች በሪቮንያ ፍርድ ቤት ቀርቦ በኔልሰን ማንዴላ ላይ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው፤ በዚሁ አመት በ1963 ሮቢን ደሴት ላይ ወደሚገኘው ወህኒ ተወረወሩ።
Nelson Mandela with Mengistu Haile Mariam
ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በሗላ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በወቅቱ ፕ/ት መንግስቱ ሀይለማርያም አቀባበል ሲያድርጉላቸው
ከብዙ ውጣ ውረድና የ27 አመታት ትግል በኋላ ማንዴላ ከእስር ተፈቱ። እናም መጀመሪያ ከጎበኟቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። በፓስፖርታቸው ላይ ያሉት የመጀመሪያ ቪዛዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። መጀመሪያ ከጎበኟቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆነች። በኋላ ላይ በመጽሃፋቸው ላይ ሲጽፉ፤ “ኢትዮጵያ በኔ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላት። በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ያደረኳቸው ጉብኝቶች ቢደመሩ እንኳን፤ በኢትዮጵያ ከነበረኝ ቆይታ አይበልጡም።” በማለት ለኢትዮጵያ ያላቸውን ልዩ ስሜት ገልጸዋል። (በነገርዎ ላይ የኔልሰን ማንዴላን የህይወት ታሪክ የሚገልጽ፤ በኢትዮጵያ ያሳለፉትንም ወታደራዊ ስልጠና ህይወት የሚያሳይ ትልቅ ፊልም ተሰርቷል)
ኔልሰን ማንዴላ ከ እስር ቤት ከወጡ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በወቅቱ እነ ጄነራል ታደሰ ብሩ በህይወት አልነበሩም። ጊዜውም ተለውጧል። ቆየት ብሎ ኔልሰን ማንዴላ በህይወት ካገኟቸው ሰዎች መካከል አቶ ከተማ ይፍሩ አንዱ ነበሩ።
ከሰላሳ አመት በፊት አብረው የተነሱት ፎቶ ማንዴላን ለእስር እንዳላበቃቸው፤ አሁን ግን በነፃነት እንደገና ተገናኝተው የመታሰቢያ ፎቶ ለመነሳት በቁ። (አቶ ከተማ ይፍሩም ከጥቂት አመታት በፊት አልፈዋል)
ከመሰናበታችን በፊት… በአንድ ነገር እንሰነባበት። የኔልሰን ማንዴላ የልደት ቀን ሲመጣ፤ ተማሪዎችን ጨምሮ ህዝቡ በሙሉ ልደታቸውን ያከብራል። ለኔልሰን ማንዴላ ትልቁም ትንሹም “ማዲባ ሃላላ፣ እንወድሃለን አባባ” እያሉ ይዘምሩላቸዋል።
Madiba, Halala
Happy birthday to you!
Happy birthday to you!
Happy birthday dear Tata!
We love you Tata
We love you Tata
Nelson Mandela. Ha hona
Ya tshwanang le wena (there is no like you)
Yeep yeep!
Hooray!
እኛም በዚሁ ስንሰናበት፤ አንድ ነገር ለማለት ወደድን። አሁን የውሸት ወይም ድራማዊ ለቅሶ ሳይሆን፤ የእውነት ሃዘን የምናይበት ጊዜ ይሆናል።
ነፍስ ይማርልን!
 Posted By.Dawit Demelash

Thursday, December 5, 2013

ኢትዮጵያን በሙስና ከሚታወቁ የዓለም አገሮች ተርታ ያሰለፈው ሪፖርት ይፋ ሆነ


corruption index


ትናንት ኅዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በመላው ዓለም ይፋ የሆነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ተቋም የሙስና አመላካች ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከሙስና ጽዱነት ተርታ ውጭ ከሆኑና በሙስና ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈረጁ አገሮች አንዷ ሆና መገኘቷን ይፋ አደረገ፡፡
ሪፖርቱ በሚከተለው የሙስና መለኪያ ሚዛን መሠረት፣ ከሙስና ጽዱ የሚባሉ አገሮች ከዘጠና እስከ መቶ ነጠብ የሚያገኙት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል፣ የሙስና ጎሬ ሆነዋል ተብለው የሚታሰቡ አገሮች ደግሞ ከመለኪያው ከ50 በመቶ በታች የሚያስመዘግቡት ናቸው፡፡ በመንግሥት ተቋሞች ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል ተብለው ከተለዩት ውስጥ ኢትዮጵያ 33 ከመቶ የመለኪያውን ነጥብ በማስመዝገብ ከከፍተኛ ሙስኞች ተርታ እንደምትሰለፍ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ ከ177 አገሮች ውስጥ 111ኛውን ደረጃ መያዟም በሪፖርቱ ይፋ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው አገሮች ለሙስና ተጋላጭነት ከሚለኩባቸው መመዘኛዎች መካከል፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የተጠያቂነትና የሰዎች የመደመጥ መብት፣ የፍትሕ አካላት ከተፅዕኖ ነፃ መሆን፣ የሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ ልማት መለኪያና ሌሎችም ጠቋሚዎች እንደሚካተቱ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በድረ ገጹ ይፋ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከ179 አገሮች 127 ደረጃን በመያዝ የፕሬስ ነፃነት ከሌሉባቸው አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ በፍትሕ አካላት ነፃነትና ከተፅዕኖ ውጭ ካልሆኑ አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን ከ142 አገሮች ውስጥም 93ኛ መሆኗ ይፋ የተደረገው ዓምና ነበር፡፡
ተቋሙ 177 አገሮችን በሙስና እንደሚጠረጠሩበት ደረጃቸው በመመዘን ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገሮች 90 ከመቶው ለሙስና በሚያስጠረጥራቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆነው አግኝቷቸዋል፡፡ ቦትስዋና ከሰሐራ በታች አገሮች ዝቅተኛ የሙስና ወንጀል የሚፈጸምባት ስትሆን፣ ሶማሊያ ከሁሉም አገሮች በታች በመሆን ሙስና የተንሰራፋባት ተብላለች፡፡ በዓለም ላይ ከ177ቱ ውስጥ 69 ከመቶ አገሮች ከፍተኛ የሙስና መናኸሪዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያረጋግጣል፡፡
ከሰሐራ በታች የሚገኙትን አገሮች በሙሰኝነት ተፈርጀው የሚመሩት የምሥራቅ አውሮፓና እስያ አገሮች ሲሆኑ፣ 95 ከመቶ በላይ አገሮች ከፍተኛ ሙሰኞች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
በዓለም ላይ ከፍተኛ ሙስና ከተንሰራፋባቸው አሥር አገሮች ስድስቱ ከሰሐራ በታች አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ (ሪፖርተር)
 Posted By.Dawit Demelash

የመስቀል ክብረ በዓል የዓለም ቅርስ ሆነ

mesqel


የኢትዮጵያው የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ዩኔስኮ አስታወቀ፡፡ ዩኔስኮ የመስቀል ክብረ በዓልን (Commemoration feast of the finding of the True Holy Cross of Christ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ኅዳር 25 ቀን ይፋ ያደረገው፣ በኢንታንጀብል (መንፈሳዊ) ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ክብካቤ ላይ የሚሠራው ኮሚቴው ስምንተኛውን ጉባኤ እያካሄደባት ካለው የአዘርባጃኗ  ባኩ ከተማ ነው፡፡
ስለቅርሱ የመረመረው ኮሚቴ ባቀረበው ውሳኔ ሐሳብ ላይ እንደተመለከተው፣  የመስቀል ክብረ በዓል የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ መምጣቱና በአገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትንና የርስ በርስ ትስስርን፣ ብዝኃነትንም የሚያንፀባርቅ፣ በበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች መካከል ትስስርን የፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን አሟልቷል ብሎታል፡፡
የዩኔስኮ ኮሚቴው በረቡዕ ስብሰባ ውሎው  ከመስቀል ሌላ ከተለያዩ አገሮች 13 መንፈሳዊ ባህላዊ ቅርሶችን በሰው ዘር ቅርስነት መመዝገቡንም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መስቀልን ጨምሮ እ.ኤ.አ. በ2013 የተመረጡትን የ14ቱ መንፈሳዊ ባህላዊ ቅርሶች ገጽታ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችና ፎቶዎችም በዕለቱ በድረ ገጹ ላይ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በመላ አገሪቱ በአደባባይ ደመራ የሚከበረው የመስቀል ክብረ በዓል የመጀመርያው መንፈሳዊ (ኢንታንጅብል) ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበላት ኢትዮጵያ፣  ዘጠኝ  ግዙፍ (ታንጀብል) ቅርሶች ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
  Posted By.Dawit Demelash

መድረክ የጠራው ሰልፍ ተከለከለ

 December 5, 2013
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም ለማድረግ ያሳወቀው ሰልፍ ተከለከለ፡፡ መድረክ ሰልፉን ለመጥራት በሀገራችን መሰረታዊና ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን እንዲሁም በሰውዲና በአለም ዙሪያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ መሰረቱ የስደት መንስኤው ላይ በመሆኑ መንግስትን በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡
ሰልፉን ለማድረግ የታቀደው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር ፊት ለፊት ከሚገኘው የመድረክ ቢሮ በመነሳት በአምስት ኪሎና ስድስት ኪሎ አድርጎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ድረስ ለመጓዝ ነበር፡፡ ነገር ግን የአድስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንትባ ፅ/ቤት “ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እውቅና የጠየቃችሁበት ስፍራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ አሰራር ስነ-ስርዓት አንቀፅ አምስት ሀ እና መ የሰላማዊ ሰልፍ የማይካሄድባቸው ቦታዎች ተብለው የተጠቀሱ በመሆናቸው የተጠየቀው የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና መስጠት የማንችል መሆናችንን እንገልፃለን” ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው የመድረክ ስራ አስፈፃሚና የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አቶ አስራት ጣሴ “መልሱ የመድብለ ፓርቲ ቅልበሳ ከመሆን አይዘልም” ይላሉ፡፡ አስተዳደሩ ጠቅሶ እውቅና ለመንፈግ የተጠቀመበት ደንብ ማንም የሚያውቀው መሆኑን የተናገሩት አቶ አስራት በማያውቁት ህግ እንደማይደኙ ገልፀውልናል፡፡ በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ላይ የወጣው አዋጅ መወቅ ቢችሉ እንኳ በተባለው ደንብ እንደማሻር አክለዋል፡፡
በ1983 ዓ.ም የወጣው የሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 3 1983) የተከለከሉ ብሎ የሚጠቅሳቸው ቦታዎች እንደሌሉና ከኤምባሲዎች፣ ት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የሀይማኖት አምልኮ ስፍራዎች፣ በገበያ ቀን (ከገበያ ስፍራ) መቶ ሜትር መራቅ እንዳለበት ማዘዙን አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከጦር ካምፕና የደህንነት ተቋማት 500 ሜትር መራቅ እንዳለበት አዋጁ ማስገደዱን ያስረዱት አቶ አስራት ከዚህ ቀደም አንድነት መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም በጠራው ሰልፍ ይህንን አዋጅ በመሻር በጦር ካምፕና በደህንነት መስሪያቤቶብ በተከበበው ጀንሜዳ እንድንወጣ ነግረውናል ብለዋል፡፡
በተሰጠው መልስ ላይ አቋም ለመያዝ የመድረክ አመራር እንደሚሰበሰብ ከአቶ አስራት ጣሴ ለማወቅ ችለናል፡፡

መድረክ ህዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም መድረክ ለጠራው ሰልፍ አስተዳደሩ ከተደራራብ የስብሰባ ጫና የተነሳ የፖሊስ ሀይል ስለሌለኝ ጥበቃ ለደደርግለት አልችልም በሚል እውቅና መንፈጉ ይታወቃል፡፡
Posted By.Dawit Demelash

Wednesday, December 4, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ የአጼ ምኒልክን 100ኛ ዓመት የእረፍት ቀን ለመዘከር በጃንሜዳ የጠራው ኤግዚቢሽን እና የፓናል ውይይት ተከለከለ


ከብርሃኑ ተ/ያሬድ
የፊታችን ታህሳስ 3 የእምዬ ምኒልክን 100ኛ እረፍት በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት እንደሚዘክር የታወቀ ነዉ፡፡ በፕሮግራሙ ላይም በርካታከሀገር ዉስጥና ከዉጪ ሀገር ምሁራን ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ይገኛሉ ተብሉ ይጠበቃል፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ሰማያዊ ፓርቲ ለዝግጅቱ በሚያስፈልጉ ጉዳዩች ላይ ስራ እየሰራ ይገኛል! በስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ አዋጅ መሰረትም ስብሰባ እንደሚያደርግ ለስብሰባና ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ በትናንትናዉ እለት ያስገባ ሲሆን ዘሬ በደብዳቤ የተመለሰዉ መልስ እጅጉን አስቂኝና አጠያያቂ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
በደብዳቤዉ ላይ ለምታደርጉት ስብሰባ እዉቅና ልነሳጥችሁ አንችልም ምክንያቱም የፖሊስ ጥባቃ መመደብ አንችልም የሚል ነዉ፡፡ የሚገርመዉ ደግሞ የፅፈት ቤቱ ሀላፊ ተብዬዉ አቶ አሰግድ በንቀት ደግሞ ማናችሁና ምኒልክ ምናምን የምትሉት ደግሞ ምኒልክ ማነዉ በሚል በእብሪት የመለሰዉ መልስ ነበር፡፡
እንኳን ድንኳን ጥሎ ለመሰብሰብ ይቅርና ጎዳና ሙሉ ህዝብ በመላበት የሩጫ የሰልፍ መሰል የገዢዉ ፓርቲ መልካም ፈቃድ ያገኙ ፕሮግራሞች ከህዝቡ እኩል ፌደራል ፖሊስ ለጥበቃ እንደሚታዘዝላቸዉ እየታወቀ ፤ በሌላ መልኩም በድፍረት እንወጣለን ብለን በተለያየ ምክንያት በተጠሩ ሰልፎች ላይ ለድብደባ የሚላከው ቁጥር ስፍር የሌለዉ የፀጥታ ሀይል አሁን ምን ቢውጠው ነዉ የጥበቃ የሚሆን የሰዉ ሀይል ልናስተባብር አንችልም ስለዚህ ዝግጅታችሁን እዉቅና አንሰጠዉም መባሉ??? ይህ ከእብሪት በላይ ምን ሊሆን ይችላል!!!?
ያም ሆነ ይህ ዝግጅቱ በታቀደለት ምልኩ እንደሚፈፀም በተለመደ ቁርጠኝነት ላይ ነን! ሲፈልጉ ለጥበቃ የከለከሉትን ሀይል ለድብደባ ይላኩት!!! እኛ የምንዘክራቸዉ ፍርሃት ካልፈጠረባቸዉ ሞተዉም መንፈሳቸዉ ካልተለየን እምቢ ባይ አባቶቻችን ተወልደናል፡፡
ድል ለኢትየጵያ ህዝብ!!!

   Posted By.Dawit Demelash