የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ በዘመናት ካጋጠሟት ፈተናዎችና ችግሮች ሁሉ ምናልባትም በአይነቱ ብቻ ሳይሆን በስፋቱም ለየት ያለው ይህ አሁን በእኛ ዘመን የተከሰተው የአባቶች መከፋፈል ወይንም በፖለቲካ ጣልቃገብነት የተፈጠረው የቤተክርስቲያኗ አመራር ክፍፍል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በአጠቃላይ በክርስትና ላይ የደረሰውን ፈተና ትተን በእኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ብቻ የደረሰውን እንኳን ብናይ በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣በ15ኛው መ/ክ/ዘ በግራኝ መሐመድ፣በ18ኛው መ/ክ/ዘ በእንግሊዝ፣ በ19ኛውና በ20ኛው መ/ክ/ዘ በፋሺሰት ኢጣልያ ወረራ በቅርቡም በደርግና አሁን ደግሞ በወያኔ ኢህአዴግ መንግሥታት በቤተክርስቲያናችን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን በቀደመው ዘመን የነበሩት አባቶቻችን በእምነትና በእውነት እየተመሩ ለህሊናቸው ብቻ ሳይሆን ለትውልድም የሚያኮራ ስራ ትተውልን አልፈዋል፡፡
በዮዲት ጉዲት 40 ዓመት የመከራ ዘመን መከራው ስለበዛባቸው 10ኛው ወይንም 20 ኛው አመት ላይ እንግዲህ በቃን እስከመቼ እንዲህ ሞተንና ተሰደን እንዘልቃለን ልጆቻችንስ እስከመቼ እንዲህ ሆነው ያድጋሉ በማለት እጃቸውን ለጨፍጫፊዋ ዮዲት አልሰጡም። 40 የመከራ አመታትን በሰማእትነት፣በስደትና በመከራ አሳልፈው ተዋሕዶ እምነታችንን እስከነምልክቷ አስተላልፈውልናል። በዘመነ ግራኝም እምዲሁ ሰማእትነትን ከፍለው ታቦታቱን በዋሻ ደብቀው ከአገር አገር ተንከራተው ኃይማኖታችንን ከነክብሯ አስተላልፈውልናል።
ፋሺት ኢጣልያንም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን አቃጥሏል። በተለይም ታላቁን የደብረሊባኖስ ገዳም ከማቃጠሉ በተጨማሪ ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሆኑ ገዳማዊያንን በግፍ ጨፍጭፏል። ይሁን እንጂ የቀደሙት አባቶቻችን በእምነታቸው ጽናት ለጨፍጫፊዎችና ወራሪዎች ሳይንበረከኩ ኃይማኖትን ከነምልክቱ አገርን ከነነጻነቱ አቆይተውልናል። በጣልያን የኋለኛው ወረራ ወቅት የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ አባት የነበሩትን ፃድቁ ሰማእትና አርበኛ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ጣሊያን በአደባባይ ከገደለ በኋላ ለጣሊያን መንግሥት ያደሩ አንዳንድ ባንዳ ‘አባቶች’ ከጣሊያን ጎን ተሰልፈው ሕዝቡ ለጣሊያን እንዲገዛ ሲያደርጉ የነበሩ መኖራቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በተለይም በሰማእቱ አቡነ ጵጥሮስ ወንበር አቡነ አብርሃም የተባሉ አባት ለጣሊያን አድረው በአቡነ ጵጥሮስ ቦታ ተሾመው ነበር። ጀግኖች አባቶቻችን ግን ይህን አይነቱን ክህደት አንቀበልም በማለት በዱር በገደሉ ለአገራቸውና ለኃይማኖታቸው ነጻነት ተጋድለዋል።
በተጋድሎአቸውም ተዋሕዶ እምነታችንን ከካቶሊክነት ኢትዮጵያንም ከቅኝ ግዛት ታድገዋታል። እንግዲህ እኛ አባቶቻችን የምንላቸው ሰማእታት ሆነው፣ተሰደውና በእምነታቸው ጸንተው እምነታችንን ከጠላቶቻችን ታድገው ያቆዩልንን እንጂ በክህድት፣በፍርሐት፣በወገኝተኛነት፣በዘርና በመሳሰሉት ምክንያት ከጠላት ጎን ሆነው ኃይማኖታቸውንና አገራቸውን የከዱትን አይደለም።
በዚህ በእኛም ዘመን ያለን የተዋሕዶ አማኞች አባቶቻችን የምንላቸው እነማንን ይሆን?
የኢትዮጵያ ክብር ሲዋረድና ሕዝቦቿ ሲሰደዱ ይህን ከሚያደርገው አካል ጋር የቆሙትን?
ወይንስ የአገር ዳር ድንበር መፋለስና የህዝቦቿ አንድነት መሸርሸር የለበትም ብለው ከተሰውና ከተሰደዱትን ጋር?
በቤተክርስቲያን ላይ በመጠን ሊገለጽ የሚከብድ ጥፋትን እያደረሰ ካለ ኃይል ጋር የቆሙትን? ወይንስ ይህን የቤተክርስቲያንን መጠቃት የሚቃወሙትን ነው አባቶቻችን የምንል?
ምናልባተ በዘመናችን በእውነት ስለኃይማኖትና ስለአገር ብቻ ሳይሆን የራስንም ክብርና ምኞት ለማሳካት የሚደረግ ነገር በሁሉም ዘንድ አንዳለ ቢታየን አምላካችን በእውነት እስኪገለጥልን በያለንበት እንጽና እንዳለው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከአጥፊዎችና ከጥፋቱ ተባባሪዎች ጋር ከመቆጠር ራሳችንን ልናቅብ ይገባናል። እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድ አለው፤በኃይለኛ ውኃ ውስጥ መተላለፊያ ያደርጋል እንዳለ ነብዩ ኢሳ.43፥13 ሁሉ በእግዚአብሔር ጊዜ ስለሚፈጸም፤ የቤተክርስቲያን ልዕልናና የኢትዮጵያ ትንሳዔ መምጣቱ ስለማይቀር ያለነው ትውልዶች ለእምነት፣ለእውነትና ለሕሊና የሚስማማ ሥራ ሰርተን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!
Posted By.Dawit Demelash
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/10534
No comments:
Post a Comment