Tuesday, September 8, 2015

የሕወሓት መንግስት የታጠቁ ኃይሎቹን እና ካድሬዎቹን በማሰማራት በአርማጭሆ ሕዝብ ላይ ሰቆቃ እየፈጸመበት እንደሚገኝ ተዘገበ

የአርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ እንደዘገበው የህወሓት አገዛዝ የታጠቁ ኃይሎቹን፣ ደህንነቶቹንና ካድሬዎቹን በማሰማራት በላይ አርማጭሆ ህዝብ ላይ እንደዘመተበትና ሰቆቃ እየፈፀመበት እንደሚገኝ ታወቀ፡፡
የህወሓት አገዛዝ በታጠቁ ቡድኖቹ፣ በደህንነቶቹና በካድሬዎቹ ቁም ስቅሉን እያሳየው የሚገኘው በላይ አርማጭሆ ማሂን አቦ፣ ዳዚሆን፣ ገንበራ-አንገረባ፣ ሌዳሆ ማርያም፣ ኩርቢና በሌሎችም በርካታ መንደሮች የሚኖረውን በድህነት የሚማቅቀውን የገበሬ ህዝብ ነው፡፡

የህወሓት አገዛዝ የታጠቁ ኃይሎች፣ ደህንነቶችና ካድሬዎች በጉልበት አልገዛ ያላችውን የአርማጭሆ ህዝብ ‘የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን ትቀልባላችሁ’ እና ‘መረጃ ትሰጣላችሁ’ በማለት እየወቀሷቸውና እየከሰሷቸው ሲሆን በተጨማሪም አርበኞች ግንቦት ሰባትን በአካል የተቀላቀሉ ልጆቻቸውን ከበርሃ ካላስመለሱ በእነሱ ላይ ከመቸውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ እርምጃ እንደሚወስድባቸው የአርማጭሆን ነዋሪዎች እያስፈራሯቸው ይገኛሉ፡፡


የህወሓት አገዛዝ የታጠቁ ኃይሎች የአርማጭሆን ገበሬ የሚያረባቸውን ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች በጥይት እየጨፈጨፉ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡


ህዝቡ ደግሞ በበኩሉ በተቃራኒው ምሬቱ አንገቱ ድረስ ደርሶ የበለጠ ዘረኛውን የህወሓት ቡድን ተፋልሞ ነፃነቱን ለመጎናፀፍ ቆርጦ መነሳቱንና እየተዘጋጀ መሆኑን የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች በላኩልት መረጃ አስታውቀዋል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46524


Monday, September 7, 2015

የህወሓት ካድሬዎች ሰሞኑን ደግሞ በፕሮፍ ላይ እየየየየየ! እያሉ ነው

ጥላቻ የማያውቁትን ሰው በጥላቻ የተመረዙ ናቸው ብለው እየከሰሱ ነው፡፡ ምን ያድርጉ ሰውዬው ለህወሓት ነቀርሳ ሆኑኮ፡፡ ባንዳ አይወዱ፣ ሀገር የሚሸጥ አይወዱ፡፡

ሌላው ይቅርና ትግራይ ውስጥ ርሃብ ሲከሰትኮ የደረሱት እነ መለስ፣ እነ ስብሃት፣ እነ አባይ አይደሉም፡፡ እነሱማ ዓለም ለምስኪኖቹ የላከውን ስንዴ አሸዋ ውስጥ ደበቁት፡፡ የሞተው ሞቶ ዛሬ እነሱ በዛ ገንዘብ ‹‹ኢፈርት›› የሚባል አቋቁመናል ብለው ሲያወሩ እንኳ አያፍሩም፡፡ የሚዘንጡበት፣ የሚበሉትና የሚጠጡት የደም ገንዘብ፣ የወገን አጥንትና ደም አይመስላቸውም፡፡ ፕሮፌሰር ግን ኪሳቸው ውስጥ የነበረቻቸውን አራግፈው ሰጥተው ባዷቸውን ነው የተመለሱት፡፡


ህወሓትና ካድሬዎቹ በልጦ የሚገኝን ሰው ይጠላሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉትን፡፡ ቴዲ አፍሮም የዚሁ ሰለባ ነው፡፡ እንደ እነሱ የደም ገንዘብ ያልበላ፣ ለሀገር ያገባኛል ያለ፣ ለእውነት የቆመ ጠላታቸው ነው፡፡ እንደ እነሱ ወርዶ ካልተገኘ የማይሰጠውና የማይለጠፍበት ስም የለም፡፡ እንደ ህወሓት መሆን ከዛም ሲያንስ ከእሱ መውረድ ደግሞ እውነትም ከሰውነት መውረድ ነው፡፡ ቁልቁለት!

http://satenaw.com/amharic/archives/10224

Sunday, September 6, 2015

የዋሽንግተን ዲሲ ግብረሃይል በ13 አርቲስቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አሳሰበ


ይህቺን ታሪካዊ አገር ከነኩሩ ህዝቧ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ የተነሳን ጠላት መጥላት ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት መነሳትም የሚገባ የትውልዳችን አደራ ነው።ይህን የወያኔ መርዘኛ ስርዓት ለማስወገድና በምትኩም ህዝባዊና ኢትዮጵያዊ መንግስት ለመመስረት ዛሬ ባራቱም ማዕዘናት በትጥቅም፣ በህዝባዊ እምቢተኝነትም፣ በሰላሙም፣ በጸሎትም ዜጋው ሁሉ የአቅሙን ጸረ ወያኔ ትግል እያካሄደ ይገኛል። ታዲያ ጠላቱን በጠላትነት የፈረጀ ህብረተሰብ በጠላቱ ላይ ማዕቀብ መጣሉ ተገቢና ቀላሉ የትግል ስልቱ ነው።

ወያኔ ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ እንደ አልቅት ተጣብቆ ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ እየመጠጣት ይገኛል፤ ይህንንም ለመዘርዘር መነሳት ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል።የህዝብን ትግል ለማኮላሸት መለሳለስንም መስበክ ለሞተው ስርዓት እስትንፋስን መለገስ ይሆናል።

በወያኔ እና በአጋሮቹ ላይ ማእቀብ በማድረግ ሳንቲም እንዳያገኙ እንዲሁም የሸቀጣቸውም ማራገፊያ ላለመሆን ይረዳል። የማእቀብ ጥሪ ያልታወጀበት ጊዜ የለም፤ ነገር ግን አብዛኛው አሁንም የበጎ ፈቃድ ሸቀጥ መራገፊያ በመሆን የወያኔን ሸቀጥ ተሰልፎ ሲሸምት መታየትን ቀጥሏል ይህንንም የመሰለ አሳፋሪ ነገር የለም። በሌላም በኩል በሰሜን አሜሪካ የህዝብ ተቋማቶችን ወያኔ እጁን አርዝሞ ለመቆጣጠር ያደረገውን ጥረት እድሜ ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ተቋቁመውት ዛሬ የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌደሬሽን የሕዝብ ተቋም ሆኖ ከቀጠለ ዘንድሮ ፴፪ኛ አመቱን በታላቅ ብሄራዊ ስሜት አክብሮታል። በአንጻሩም በወያኔ በሚዘወረው እና ከወገኖቻችን በግፍ በተዘረፈ የደም ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው AESAONE በቱጃሩ ሊስት ላይ ስማቸው የሰፈሩ ጥቂት የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ገዝተው አሁንም በያመቱ በባዶ ሜዳ ሲያለፏቸው ይታያል።

እነዚህን ከጠላት እያወቁ ያደሩትን እንዲያውም ህዝብን በመናቅ በዚሁ አጥፊና አሳፋሪ ስራቸውን በመቀጠላቸው በሚሳተፉበት ማንኛውም ዝግጅት ላይ ባለመሳተፍ እና የደረሱበት ባለመድረስ ማእቀብ ይጣልባቸው በማለት ጥሪ እናቀርባለን፤ እንዲሁም ማንኛውም የልማትም ሆነ የሰብአዊ እርዳታ አዘጋጆች ከእነዚህ ማእቀብ ከተደረገባቸው ግለሰቦች ጋር ምንም አይነት ዝግጅት ባለማዘጋጀት የህዝብን ድምጽ ያከብሩ ዘንድ እንጠይቃለን። እነዚህን አፍቃሪ ወያኔዎች አውቀው በድፍረት የሚያደርጉትን እኛም አውቀን በእምነት ይታቀቡ እንላለን፤ በድግሳቸውም ሆነ በሃዘናቸው ጸረ ወያኔ የሆነው ሃይል በሙሉ ያቅብባቸው እንላለን። በተጨማሪ በቀጣይንትም በእንዲህ አይነት አሳፋሪ ሁኔታ የሚሳተፉ ካሉ እያጣራን ማእቀቡ በእነሱም ላይ የሚቀጥል መሆኑን በቅድሚያ እናሳውቃለን። ለአሁኑ በተጨባጭ ማስረጃ ያለንን ስማቸውን እንደሚከተለው እንዘረዝራለን።

፩ ሀይሉ ፈረጃ
፪ ራስ ብሩክ ባርኪ
፫ ታደለ ገመቹ
፬ ኩሪባቸው ወ/ማሪያም
፭ ንዋይ ደበበ
፮ ኤደን ገብረስላሴ
፯ ደረጀ ደገፋው
፰ አብርሃም ገ/መድህን
፱ ሀና ሸንቁጤ
፲ የኔሰው ተፈራ
፲፩ ቴዎድሮስ ብርሃኑ
፲፪ ተክሉ ደምሴ
፲፫ በሱፍቃድ


በመጨረሻም ማእቀባችን በሁሉም ዘርፍ የወያኔን ኤኮኖሚ በሚያንኮታኩት መልኩ እንዲሁም ለወያኔ የሚያደሉ ፕሮፓጋንዲስቶችንም ጭምር ወደፊት ደረጃ በደረጃ እናሳውቃለን።
የጸረ ወያኔው ትግል ተፋፍሞ ይቀጥላል!!! ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!


የዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረሃይል dcjointtaskforce@gmail.com

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46449

Friday, September 4, 2015

ሀብታሙ አያሌው ቂሊንጦ እስር ቤት ላይ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

‹‹ችሎቱ ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው›› አቶ ሀብታሙ አያሌው

አቶ ሀብታሙ አያሌው ነሀሴ 14/2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከተከሰሰበት የሽብር ወንጀል ነጻ ነው በማለት ከእስር እንዲፈታ የሰጠው ትዕዛዝ ተከብሮ እንዲፈታ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደርጓል፡፡


ዛሬ ነሀሴ 29/2007 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው እና መልስ እንዲሰጥ የተጠራው የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ተወካዮች ሲሆኑ፣ የእስር ቤቱ የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ ሱፐር ኢንቴንደንት ጣዕመ ደምሴ አቶ ሀብታሙ አያሌውን ለምን ከእስር እንዳልለቀቁ አስረድተዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚሉት አቶ ሀብታሙ ከቂሊንጦ እስር ቤት ያልተፈታበት ምክንያት እስር ቤቱ ከአቃቤ ህግ ይግባኝ እንደተጠየቀበት እና ይህን ተከትሎ ተያይዞ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጻፈ የእግድ ትዕዛዝ ስለደረሳቸው ነው፡፡

ሱፐር ኢንቴንደንት ጣዕመ ደምሴ እንደገለጹት የመፈቻ ደብዳቤው እና የእግድ ትዕዛዙ የደረሳቸው ነሀሴ 15/2007 ዓ.ም ሲሆን፣ አቶ ሀብታሙ ግን ከእስር መፈቻ ትዕዛዙ የተጻፈለት ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ነጻ ናችሁ የሚል ብይን በተሰጠበት ዕለት፣ ማለትም ነሀሴ 14/2007 ዓ.ም ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ ሀብታሙ የማስፈቻ ደብዳቤው እንደተጻፈለት ከእስር ሊለቀቅ ይገባ ነበር፡፡ በእርግጥም የማስፈቻ ደብዳቤው በ14/2007 ዓ.ም እንደተጻፈ ነገረ ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች፡፡

በሌላ በኩል አቶ ሀብታሙ አያሌው ይግባኝ እንደተጠየቀበትና የእግድ ትዕዛዝ ለቂሊንጦ እንደተጻፈ በወቅቱ በደብዳቤ ጭምር መረጃ የጠየቀ ቢሆንም እንዳልተነገረው ለተረኛ ችሎቱ አስረድቷል፡፡ በዚህም ቤተሰቦቹ ለእንግልት፣ አቶ ሀብታሙ ደግሞ ለሞራል ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግሯል፡፡ ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ግን ይህን ባለመቀበል በጊዜው መረጃ መስጠቱን ይከራከራል፡፡

ተረኛ ችሎቱ የቀረበለትን አቤቱታ እና የአስተዳደሩን መልስ ከሰማ በኋላ ቂሊንጦ እስር ቤት ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሰውን ትዕዛዝ እንዳስፈጸመ በመጥቀስ ትክክለኛ ነው ሲል በይኗል፡፡ በመሆኑም አቶ ሀብታሙ አያሌው በእስር ቆይቶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ብይን እንዲጠብቅ ታዝዟል፡፡ አቶ ሀብታሙ የተረኛ ችሎቱን ብይን ከሰማ በኋላ ‹‹ይህ ችሎት ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው፤ የውሳኔ ግልባጩ ይሰጠኝና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው አደርጋለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡

አቶ ሀብታሙ አያሌው ከሌሎች አራት ተከሳሾች ጋር መስከረም 21/2008 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46408

Thursday, September 3, 2015

የመኢአድ ሕጋዊው ፕ/ት አቶ ማሙሸት አማረ እንገድልሃለን ብለዋል እስኪገሉኝ ትግሉን እቀጥላለሁ አሉ

አቶ ማሙሸት አማረ ፍርድ ቤት በነጻ ከለቀቃቸው ያለ አንዳች ምክንያት ለአምስት ተጨማሪ ቀናት ታስረው ትላንት ቢፈቱም ዛሬም ባሉበት ቤት አካባቢ በፍርድ ቤት በሀሰት የቆሙባቸውን ጨምሮ ሌሎች የደህነት አባላት ክትትል እያደረጉ እንዳሉ ከመውጣታቸውም በፊት በእስር ላይ ሳሉ <<አንተን ከዚህ በሁዋላ አስረን የሚዲአ መነጋገሪያ አናደርግም አርፈህ የማትቀመጥ ከሆነ በማንኛውም ሰዓት እናስወግድሃለን>> እንዳላቸው ገልጸዋል። እስኪገሏቸው ድረስ የጀመሩትን ሰላማዊ ትግል አጠናክረው እንደሚገፉበት ለህብር ሬዲዮሶስት ወር ከሃያ ሁለት ቀን እስር በሁዋላ ከእስር ቤት እንደወጡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገለጹ።

ከምርጫ 97 በፊትና በሁዋላ ከቅንጅት መሪዎች አንዱ ሆነው የታሰሩትን ጨምሮ ለስምንት ጊዜያት በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የተንገላቱት አቶ ማሙሸት አማረ ሕጋዊው የመኢአድ ፕ/ት ሲሆኑ ምርጫ ቦርድ በሕገወጥ መንገድ ፓርቲውን ለተለጣፊው የእነ አቶ አበባው መሐሪ ቡድን ሲያስረክብ ከቢሮ ተባረው ቦርዱን ከሰው በክርክር ላይ ሳሉ ግንቦት 5 ቀን 2007 ከቤታቸው አቅራቢያ በደህነቶች ታፍነው መታሰራቸው ይታወሳል።በተደጋጋሚ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ ከእስር ቤት እስር ቤት ሲመላለሱና ሁለቴ በነጻ አንዴ በዋስ ይፈቱ ተብለው ሳይፈቱ መቆየታቸውን በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው አብራርተዋል።

<<በእስር ቤት ከዚህ ወጥተህ እንቅስቃሴ ብታደርግ እናስወግድሃለን ከዚህ በሁዋላ አንተን አናስርም>> የሚል ጠበቅ ያለ ማስፈራሪያ የተሰጣቸው አቶ ማሙሸት አማረ <<በማንኛውም ሰዓት ሊገድሉኝ ይችላሉ ትግሉን ግን እስከመጨረሻው አላቆምም።በጀመርኩት ሰላማዊ ትግል እቀጥላለሁ >> ብለዋል።

አገዛዙ ከግንቦት 16ቱ ምርጫ በፊት እሳቸውን ባሰረበት ወቅት በምርጫው ላይ ችግር ስለሚፈጥሩ እንዳይፈቱ ሲል ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን ያወሱት አቶ ማሙሸት እሳቸውም ሆነ ዛሬም ድረስ በአዲስ አበባና በክልል እየታደኑ የታሰሩ የመኢአድ አመራሮችና ጠንካራ አደራጆች ለአገዛዙ ስጋት ስለፈጠሩና መኢአድን ለማፍረስ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።

<<በሃያ አራት ዓመት ውስጥ አንድ ዳኛ የተቀነባበረውን የፈጠራ ክስና የተዘጋጁትን የሀሰት ምስክሮች በማየት ምስክርነቱን ውድቅ አድርጎ በነጻ ይፈታ ሲል አምስት ቀን ሳልፈታ ቆይቻለሁ>> ያሉት አቶ ማሙሸት ለኢትዮጵአ ሕዝብ እኩልነት ለሕግ የበላይነት የሚያደርጉትን ትግል በእንገድልሃለን በሚለው ዛቻ እንደማይተውና ሰላማዊ ትግሉን የሚከፈለውን መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል። በማንኛውም ጊዜ ሊገድላቸውም ሆነ መልሰው በፈጠራ ሊያስሯቸው እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።ዛሬም በተለያዩ እስር ቤቶች ያሉ የሕጋዊው መኢአድ አመራሮችና ጠንካራ አባላት እንዲፈቱ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸው እሳቸውን ጨምሮ የታሰሩት ሁሉ በአገዛዙ በኩል ሲጠየቁ የነበረው ምርጫ ቦርድ <<መኢአድ>>የሚለውን ስምና ቢሮ ያስረከባቸውን አቶ አበባው መሀሪ ጋር ለምን አብራችሁ አትሰሩም የሚል ጭምር እንደነበር ገልጸዋል።


በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አለው ሕዝብ ትግሉ ሞቀ ቀዘቀዘ ሳይል ጠንክሮ የሚፈለገው የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲአዊ ለውት እስኪመጣ መደገፍ መስዋዕት የሚከፍሉትን በርቱ ማለት አለበት ብለዋል። ከአቶ ማሙሸት አማረ ሕጋዊው የመኢአድ ፕ/ት ጋር ከእስር እንደወጡ ያደረግነውን ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ሰሞኑን ይዘን እንቀርባለን።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46380

በእስር ላይ የሚገኙ ሦስት የሰማያዊ አባላት በዓለም ላይ ከተመረጡ 20 የፖለቲካ እስረኞች መካከል ተካተቱ

ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የአንድ ወር ዘመቻ ያደርጉላቸዋል

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


በአሜሪካ መንግስት ኦፊሳላዊ ድረ ገጽ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አስተባባሪነት በዓለም ላይ ለተመረጡ 20 ሴት የፖለቲካ እስረኞች ለአንድ ወር የሚቆይ ዘመቻና ማስታወሻ ሊደረግላቸው ነው፡፡ ከ20ዎቹ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ሁሉም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡

ከዛሬ 20 አመት በፊት ሴቶችን ለማብቃት፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን እና የልጃ ገረዶችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ የቤጂንግ መርሃ ጉዞ ተቀምጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ 20 አመታት ልክ ከዓለም ሀገራት በፖለቲካ እስረኝነታቸው የተመረጡ 20 ሴት እስረኞችን ለማሰብ የሚደረገው ዘመቻ መነሻው ይህ መርሃ ጉዞ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ ብሌን መስፍን፣ ንግስት ወንዲፍራው እና ሜሮን አለማየሁ የተካተቱ ሲሆን ከቻይና እንዲሁ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች ተመርጠው ይታወሳሉ፡፡ ከብዙ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል እነዚህ ጥቂቶች መሆናቸውን የጠቀሰው ድረ ገጹ በመስከረም ወር ‹‹ሴቶችን አብቋቸው፣ አትሰሯቸው!›› በሚል መርህ ዘመቻው ይደረጋል፡፡ በዚህም መንግስታት ሴቶችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ማሰር አቁመው ማብቃት ላይ እንዲያተኩሩ መልዕክት ይተላለፍበታል፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ ዘመቻው ለታሳሪ ቤተሰቦችና ለራሳቸው ለታሳሪዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑና እንዳልተዘነጉ ለማሳየት ታስቦ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡


በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ በኢትዮጵያ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች በዚህ ደረጃ መጠቀሳቸው በሀገራችን ያለውን ስርዓት ዓለም እንደተረዳውና ኢትዮጵያ በመጥፎ እንድትነሳ እያደረጋት መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡


ዘመቻው እንዲደረግላቸው ከተመረጡት መካከል ከኢትዮጵያና ቻይና ሶስት ሶስት፣ ከቬትናም፣ አዘርባጃንና በርማ ሁለት ሁለት እንዲሁም ከኢራን፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቬንዞዌላ፣ ሶሪያ፣ ሩሲያ/ዩክሬንና ሰሜን ኮሪያ አንድ አንድ ሴት የህሊና እስረኞች ናቸው፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46394

Wednesday, September 2, 2015

ኮንቴይነር በተገኘ ቁጥር ‹‹ኢትዮጵያዊ ተደብቋል› ›መባል ተጀምሯል – የ10 ዓመት ታዳጊ ይገኝበታል


በዛምቢያ ሴሬንጄ በተሰኘች ግዛት ፖሊስ 100 ኢትዮጵያዊያንን በመኪና ተጭነው ሲያመሩ መያዙን የአገሪቱ ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

ስደተኞቹ ከናኮንዴ ሳይነሱ እንዳልቀሩ የጠቀሰው ፖሊስ ካኖና በተባለ የፍተሻ ኬላ በመኪናው ላይ በተደረገ ፍተሻ ሰዎቹ ተደብቀው መገኘታቸውን ጠቅሷል፡፡መኪናው በጫነው ኮንቴይነር በዛምቢያ ተወዳጅ የሆነውን ካፔንታ (የደረቀ አሳ) ሲያመላልስ የነበረ መሆኑን ጋዜጣው አውስቷል፡፡


ፖሊስ በናኮንዴ ድንበር አቋርጠው ኢትዮጵያዊያኑ ያለ ህጋዊ ፈቃድ በመግባታቸውና እነርሱን ለማዘዋወር ክፍያ የተፈጸመላቸውን ዛምቢያዊያንን እንደሚከስም ፖሊስ ነገረኝ ያለው ጋዜጣው ዘግቧል፡፡


ሎምቤ ካሙኮሺ ኮሚሽነር ናቸው ለጋዜጣው ‹‹100 ህገ ወጥ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ያሳፈረ መኪና መያዛችንን አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ከእኛ ጋር በመስራት ላይ የሚገኘው የስደተኞች መስሪያ ቤታችን ስደተኞቹን የኢቦላ ምርመራ ያደረገላቸው ሲሆን ሌሎች ምርመራዎችንም እያደረገ ይገኛል››ብለዋል፡፡



ኮሚሽነሩ ህገ ወጥ ያሏቸውን ስደተኞች ያዘዋወሩ ያሏቸውን ሶስት የአገራቸውን ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም አስረድተዋል፡፡ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ከ10 -50 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ የሚበዙት ወጣቶች ናቸው ማለታቸውን ጋዜጣው አስፍሯል፡፡


100ዎቹ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በዛምቢያ ሙኮቤኮ በተባለ ወህኒ ቤት ይገኛሉ ተብሏል፡፡በቅርቡ በሞያሌ ድንበር በማቋረጥ ወደ ኬንያ የገቡ 100 ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን የአገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ስደተኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማምራት የተንቀሳቀሱ መሆናቸውም ይነገራል፡፡ከኬንያ እስከ ደቡብ አፍሪካ መዳረሻ ያሉ አገራት ኮንቴይነሮችን የጫኑ መኪኖችን በድንበር አካባቢ ሲያገኙ‹‹ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ››በማለት ጠንከር ያለ ፍተሻ ማድረግ መጀመራቸውን በሂደቱ የተሳተፉ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46364