Wednesday, February 17, 2016

የህወሓትን‬ አገዛዝ በመቃወም ኤም.አይ-35 ሄሊኮፕተር ይዘው ከሀገር የወጡት እነ ሳሙኤል ግደይ የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ተበየነባቸው

ሳሙኤል ግደይ፣ ፀጋ ዘአብ ግደይ እና ቢልልኝ መኮንን የህወሓትን አገዛዝ በመቃወም ኤም.አይ-35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር በማብረር ከምስራቅ አየር ምድብ ድሬዳዋ በውሎ የጠፉት በ2007 ዓ.ም ሲሆን የህወሓት አገዛዝ የጦር ፍርድ ቤት የካቲት 4 2008 ዓ.ም በሌሉበት በሞትና እድሜ ልክ እስራት ቀጥቷቸዋል፡፡

የሄሊኮፕተሯ ዋና አብራሪ ሳሙኤል ግደይ በሞት ሲቀጣ ፀጋ ዘአብ ግደይ እና ቢልልኝ መኮንን የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል፡፡

ከእነ ሳሙኤል ግደይ በፊትም በ1993 ዓ.ም ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ ኤል-39 ተዋጊ ጀት እያበረረ ከመቀሌ ተነስቶ ኤርትራ መግባቱ፤ መቶ አለቃ በኃይሉ ገብሬ እና መቶ አለቃ አብዮት ማንጉዳይ ኤም.አይ-35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር እያበረሩ ጅቡቲ ማረፋቸው የሚታወስ ነው፡፡ መቶ አለቃ በኃይሉ ገብሬና አብዮት ማንጉዳይ በጅቡቲ መንግስት ለህወሓት ተላልፈው ተሰጥተው የእድሜ ልክ እስራት እና የ15 አመት እስር ተፈርዶባቸው መቶ አለቃ አብዮት የእስር ጊዜውን ጨርሶ በመፈታቱ በአሁኑ ጊዜ አርበኞች ግንቦት 7ን ተቀላቅሎ ኤርትራ በረሃ እንደሚገኝ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡



የኤም.አይ-35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር አዛዥ እና የበረራ አሰተማሪ የነበረው ሻለቃ አክሊሉ መዘነም ከአመታት በፊት ስርዓቱን በመቃወም ወደ ኤርትራ መጥቶ አርበኞች ግንቦት 7ን በመቀላቀል ትግል ላይ ይገኛል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/51131

Monday, February 15, 2016

የኢትዮጵያ የርሀብ ጽጌረዳዎች ‘በሰው መከራ የተመረቱ አበቦች ከአውሮፓ ገበያ ይደርሳሉ’

አዲስ አበባን ሁሪያዋን በመኪና እየዞሩ ቢያይዋት በተርታ የተደረደሩት በፕላስቲ የተሸፈኑት የአውሮፕላን ጋራጅ የመሰሉትን ቤቶች ማንም አያጣቸውም። ቀረብ ብሎ ላያቸው ደግሞ ለምን እንደተሰሩ ምን እንደሚከናውንባቸው መለየት ያስችለዋል። አበባ ተመርቶ ለገበያ የሚቀርብባቸው ናቸው፤ለዚያውም ለአውሮፓ ህብረት ። የአበባው ኢንዱስትሪ ህወሃት መሩ መንግስት ልማት ሰራሁ ብሎ የሚፏልልበት ነው። ዛሬ እንዲህ ያሉ ሰባ ዘጠኝ3 እርሻዎች ይገኛሉ።ከእኒህ ከሩቁ አንጸባራቂ ከሆኑት የአበባ ማምረቻ ቤቶች በተረፈ ሜዳ ላይ የተንሰራፉም ሌሎች እርሻዎች ይገኛሉ።

ህወሃት መሩ መንግስት እያበበ ስላለው የአበባ ኢንዱስትሪ ቢያወራም ተጨባጩ ሁኔታ ሌላ ነው።አጥፊ ውጤቱ ዜጎችን የበደለ፤ አየር ንብረቱንም የበከለ ነው። ይህ ደግሞ ሊደበቅ የማይቻል ነው።ሰዎች ከመሬታቸው ተፈናቅለዋል። የመጠጥ ውሃ በሚጎዱ መርዞች ተበክሏል።ሰዎች ለረጅም ሰዓታት በመስራት ይበዘበዛሉ።ይህ ለጥቂቶች ሲሳይ ለብዙሃን ስቃይ የሆነን አሳዛኝና አፋኝ የፖለቲካ ና የኢኮኖሚ ውጥረት ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ የለውም።በቀበሌ፤ባውራጃ፤ባገር አቀፍም ቢሆን በህወሃት ጨቋንኝ መዳፍ ተይዞ ይገኛል።

ጥቂት ኪሎሜትሮች ሄደት ብዬ አንድ በጭቃ ምርጊት የተሰራ የቆርቆሮ ቤት አገኘሁ።ምርጊቱ ገና የደረቀ አልነበረም።ርጥቡን ጭቃ ነካ እያደረግሁ

“እዚህ መቼ አመጣህ እና እንዴት ሰፈርክ ?” ብዬ ባለቤቱን ጠየቅሁ። “አምስት ቀን በፊት ልጄ ረድቶኝ” አለኝ “ከዚህ በፊትስ የት ትኖር ነበር ?”
“እኔና ቤተሰቤ እዚሁ በዚህ ግድም እንኖር ነበር” “የሞላ ቤት ነበረን። እኔና ባለቤቴ ልጆች እናሳድግበት የነበረ”” “ለምን ታዲያ ቦታችሁን ለቀቃችሁ ?” አስከትዬ ጠየቅሁት።

“በግዳጅ ተፈናቅለን” አለኝ
“ምን ማለትህ ነው ተገደን ስትል ማንስ አስገደደህ?” አልኩት
“በዚች አገር ያልወደድከው እንድታደርግ ማድረግ የሚችል መንግስት ነው” “ለምን እንድትፈናቀል ያደርጋሉ? መሬቱስ ያንተ አይደል? “ አልኩት


“መሬቱማ የኔ ነው እነሱ ግን ለአበባ አምራቾች ሊሰጡት ፈልገው ነው። አበባ አምርተው ውጭ አገር ለመሸጥ ለሚፈልጉ” “ስትፈናቀል ካሳ አግኝተሃል?” እዲነግረኝ ገፋፋሁት።

“ትንሽ ምንዛሪ አንድ በግም የማትገዛ ሰጡኝ። አልቀበልም አልኩ” አለኝ ኔዴቱ እንዳዲስ እየተሰማው።
“መላ ቤተሰቤን ይዠ ጎዳና ላይ መውደቁ ይመራል” አለኝ


“ይህ መሬት ካያት ከቅድማያት የወረስነው። እትብታችን የተቀበረበት። ሁለት ዓመታት ጎዳና ተዳዳሪ ሆንን። ሜዳ ላይ እየተኛን። ለምነን እየበላን።ራሳችንን ችለን እንኖር የነበረ ዛሬ በቀን አንዴም አንበላ። ይህ ለውጥ ኑሮአችንን አሰተጓጎለ ህብረተ ሰባችንን ጎዳ።ለማኞች አደረገን።”

“ማነው በዚህ የሚጠቀም?” አልኩት

“የመንግስት ባለስልጣኖችና ጓደኞቻቸው” አለኝ የድሮ ቤቱን ምስል እያሳየኝ። አያዳመጥሁት ይህ በኔና ቤተሰቤ ላይ ቢደርስ ምን አደርግ ይሆን እያልኩ ባሳብ ዋዠኩ።ባንዴ ሃዘንም ንዴትም ዋጠኝ። ያየሁት በደል በሚሊዮኖች ቤት ተከስቷል።ሃዘን ብቻ ይበቃል ? አልኩት እራሴን።

ብሩክ በመጀመሪያዎቹ ሃያ አመቶችዋ ላይ የምትገኝ ወጣት ሴት ናት።ለሶስት ዓመታት በአበባው ማምረቻ ቤት ሰርታለች።ከስራ ውጭ አግኝቼ ስለ ስራዋ ሁኔታ እንድት ነግረኝ አደረግሁ።

“በአበባው ማምረቻ ቤት ስራሽን ትወጅዋለሽ?” ስላት
ሳቅ ብላ “ምንስ ምርጫ ኖሮኝ” አለችኝ። “ሌላ ስራ የለ ።ያገኘሁት ይሄው ነው።” አለችን በክሰል ምድጃ ቡና እየቆላች። እጆችዋ ላይ አዲስና የቆዩ ቁስሎችን አያለሁ።

“በስራሽ ላይ ነው እንዲህ የቆሳሰልሽው?” አልኳት ወደ ቁስሎችዋ እየጠቆምሁ። “አደጋ መከላከያም የለሽ?” “እንዲያውም “ አለች
“የጅ ጓንት ሆነ ሌላ እንዲው ምንም የለንምን ?” ብዬ አከታትዬ ጠየቅኋት።


“ጤናማ ነበርኩ። ይሄው ዛሬ ግን መተንፈስ ያስቸግረኛል። ይህ የሆነው ስድስት ወራት በአበባው ማምረቻ ቤት ከሰራሁ በኋላ ነው። ሀኪም ቤት ስሄድ በስራሽ የተነሳ ነው ብለውኛል። መተንፈስ ይጨንቀኛል። ቆዳዬን ያሳክከኛል። ያስለኛል።” አለችን ሀዘን በሞላው ገጥታዋ።

የኢትዮጵያው “የራብ ጽጌረዳዎች” በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ወይም ሴራሊዮን ከሚመረተው “የደም አልማዝ” የተለዩ አይደሉም።ሁለቱም የሰው መከራና ስቃይ ውጤቶች የተፈጥሮ ውድመቶችም ናቸው።ሁለቱም የአምባገነኖች የሃብት ምንጭና መደጎሚያ ናቸው።ባአበባው ሽያጭ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በዓለምም በአፍሪካ አቻ የማይገኝለት አምባገነን ያነግሳል።ለወያኔ ሲሳይ ነው።ከዚህም በላይ አበባ ማምረቻው መሬት የሚበላ እህል ማምረቻ የነበረ ነው።ስለሆነም ሚሊዮኖች ለራብ ተዳርገዋል።
ጃነዋሪ 26 2016 የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያን ሁኔታን ሲገልጥ “ቀስ እያ እየቀረበ ያለ ትልቅ አደጋ” ብሎታል። ዛሬ ጦርነት እዳፈራረሳት ሶርያ ያስምስለዋል። “ዛሬ ሁለት ትላልቅ ቅድሚያ የሰጠናችው የአደጋ ቀጠናዎች አሉን።ሶርያ አንደኛ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ናት።” ብለዋል ካሮላይን ማይልስ። ማዳም ማይልስ Save The Children የተባለው ህጻናት አድን የተራድኦ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ናቸው።የኢትዮጵያ ሁኔታ “ቀስ እያ እየቀረበ ያለ ትልቅ አደጋ” ተብሎ ሲገለጥ ህወሃት “ጥጋብ ነው በምግብ ራሳችንን ችለናል” ብሎ በለፈፈ ማግስት ነው።

በሜይ 28 2014 የህወሃት ሃያ አራተኛው የድል በዓል ሲከበር ሀይለ ማርያም ደሳለኝ “ከራብ በመላቀቃችን እንኮራለን።ከዚህ ወዲያ በራብና ጠኔ መታወቃችን ቀርቷል” ብሎ ነበር።

በአፍሪካ ለዘለቄታው የቅኝ አገዛዝ የእርሻ ስራን አመሳቅሎአል።ነፍስ ወከፍ ራሳቸውን የቻሉ ገበሬዎች ተፈናቅለው በትላልቅ ገንዘብ አምንጭ ሰብሎች ለምሳሌ ቡና፤ኮካዎ፤ትንባሆ፤ስኳር፤ጥጥና ጎማ ተተክተዋል።እኒህ ለውጭ ንግድ የሚመረቱ ናቸው። ከበርቴዎችን ቅኝ ገዥዎችን የሚያከብሩ ማለት ነው።በዚህ ሂደት ታዲያ ሚሊዮኖች ደህይተዋል።ካባታቸው መሬት ተፈናቅለዋል። ታሪካቸው ጠፍቷል።ኢትዮጵያ የሚካሄደውም የአበባ እርሻ ምርት ከቅኝ አገዛዙ ልዩነት የለውም።ያው ቅኝ አገዛዝ ያደረገው እየተደገመ ነው። የጥንቱ ቅኝ “አገዛዝ ኋላ ቀር ህዝቦችን ለማሰልጠን” ይባልም ነበር።በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ይህን ማለት ያዳግታልና የአሁኑ “ኢንቬትሜንት፤አምራችነት ። ስራ ፈጠራ። ውጭ ባለ ሃብቶች ጋር መስራት” የሚል ስም ይሰጠዋል። ስም እንጂ ልዪነት የላቸውም። ዘመን አመጣሽ ባርነት እንጂ ከዚያ ከጥንቱ ቅኝ አገዛዝ የሚለይ አደለም።

በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ እንዲህ ብላ ጠየቀችኝ። ይህን እስቲ መልስልኝ አለችኝ። “እንዴት ሁኖ ነው አንድ በባዛት አምሮበት የተመረተ የአበባ ምርት ለአውሮፓ ገበያ ሊያቀርብ የቻለ አገር የራሱን ህዝብ መመገብ ያልቻለበት ?” በተጨማሪ “እንዴት ብሎ ነው በኢኮኖሚ እድገት ክ10 እስክ 11 እጅ ለተከታታይ ዓመታት ውጤት አምጥቻለሁ የሚል መንግስት ከዓለማቀፍ ተራድኦ ህዝቡን ለማብላት እርጥባን ጠያቂ የሚሆነው?” እኒህ ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ናቸው። በተለይ የዜና ስርጭቱ ሁሉ በራብና ድርቁ ላይ ሲሆን። የኒህ ጥያቄዎች መልስ ከተራበውና ከተጠማው አርሶ አደር ስቃይ ይገኛል። ከወጣትዋ የአበባ ማምረቻ ሰራተኛ ይገኛል።ከመክረኛውም ህዝብ ሁሉ። ጭብጡ ሁኔታ ይህ “እድገት” ይህ “አምራችነት” የህዝብ ኑሮ ጨርሶ እያወደመ፤በጣም ተፈላጊ የሆነው ውሃ ለአበባ ማምረቻ ይውላል።ተፈጥሮም በመርዘኛ ጸረተባይ ዲ ዲ ቲ እና ሌላ መዳኒት ይበከላል።

የዛሬውን የቫላንታይን ቀን በትኩሱ በተቆረጡ አባቦች ስታከብሩ በግፍ ከኖሩበት ቀዬ የተፈናቀሉትን ገበሬዎች አስቧቸው። ወጣትዋን ብሩክን አስቧት።በመርዝ የሾቀ ቦታ ሰርታ የምትኖረውን አስቧት።ከሁሉም በላይ 10 ሚሊዮን ራብተኞችን ከዚህም 400000 ህጻናት ለጠኔ ተዳርገው ለም መሬታቸው እህል ሳይሆን አበባ የሚመረትበት መሆኑን እናስብ። እራሳችሁን ደግማችሁ ጠይቁ እንዴት አበባ ለአውሮፓ አቅራቢዋ አገር ራብተኛ ልትሆን ቻለች ብላችሁ።እንዲያው ምን ህሊና ይፈርዳል እንዲህ የመረተውን አበባን መግዛት ? ከበርቴ ትርፉን ሲል ሚሊዮኖች የለት ጉር ያጣሉ። ይህ ወንጀል ነው።ተባባሪም ደጋፊም አትሁኑ። ክዚህ ይልቅ ለኢኮኖሚም ለፖለቲካም ፍትህ የምትታገሉ ሁኑ።

ደራሲውን ለማግኘት

alem6711@gmail.com

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/50970


Friday, February 12, 2016

” ዲሞክራሲ -101″…”መካሪ አያሳጣህ!” ተጳፈ ለሀይሌ ገ/ስላሴ – በኤርምያስ ለገሰ

                    ኤርምያስ ለገሰ

 ተፃፈ ለሀይሌ ገ/ስላሴ

ይቺን አጭር ፅሁፍ ለመጫር የገፋፋኝ በዛሬው እለት አትሌት ሐይሌ ለአንድ የውጭ ሚዲያ የሰጠውን አስተያየት በማዳመጤ ምክንያት ነው። አላማዬ ሐይሌ የተናገረውን ሁሉ ለመቃወም አይደለም። ወይም አንዳንድ ” ልወደድ ባይ ደካማ” ሰዎች እንደሚያስቡት አትሌቱ የተጐናፀፈውን ዝና ለማጉደፍ አስቤ አይደለም።

ለእኔም ሆነ ለመላው ኢትዬጲያውያን ሐይሌ በአለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያዊ አርማችን ነው። አርማን ማቆሸሽ ደግሞ ሐገርን ከመክዳት የሚተናነስ አይደለም። ሀይሌ የማይቻል የሚመስል ነገርን በአለም አቀፍ መድረክ እንደሚቻል ያሳየልን በአርአያነት የምናወድሰው ብሔራዊ ሃብታችን ነው። ሐይሌ ሃይላችን ነው። በስደት አለም እንኳን አንዳንድ ሰዎች ሀገራችንን ጠይቀውን ማወቅ ከተሳናቸው ለማስረዳት ከምናነሳቸው ብርቅዬ ስሞች አንዱ ሐይሌ ገ/ሥላሴ የሚለውን ነው።
ይሔ ማለት ግን አትሌት ሐይሌ ተራራ የሚያካክሉ ስህተቶችን እየሰራ እያየን እና እያዳመጥን ዝምታን እንመርጣለን ማለት አይደለም። አንፃራዊ ትምህርት እና ንቃት የሚጠይቅ ቦታ ላይ እየገባ ” አላዋቂ ሳሚ” ሲሆን በአርምሞ አንመለከተውም ።…አካፋን አካፋ ማለት ይኖርብናል ። አስተውሎ ለተመለከተው የሀይሌ መውረድ የእኛም መውረድ ነው፣…የሀይሌ አልቦነት የእኛም አልቦነት ነው፣… የሀይሌ መካሪ ማጣት ሀገሪቷ አዋቂ ሽማግሌ የላትም ወይ የሚያስብል ነው። እንደዚህ አይነት ግድፈቶች በእንጭጩ ካልተስተካከሉ ደግሞ ውርደቱ ከግለሰብ ተሻግሮ አገራዊ ይሆናል። አይበለውና አትሌቱ አሁን የሰጠውን አስተያየት “የአውሮፓ ህብረት” ስብሰባ ላይ በእንግድነት ተገኝቶ ቢናገረው ምን ይውጠን ነበር?…በማርቲን ሉተር ኪንግ ግዛት የሆነችው አትላንታ ተገኝቶ የደሰኮራት ቢሆን ምን ያህል ያሸማቅቀን ነበር?…
( ወግን ወግ አነሳውና አንድ ነገር ትዝ አለኝ ። ወጉን ያጫወቱኝ በአትላንታ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያን ናቸው። በተመሳሳይ መንገድ እንደራሴ የማምነው የኢሳት ባልደረባም በቦታው በአካል ተገኝቶ ስለነበር ይህንኑ አውገቶኛል።
እንዲህ ነበር የሆነው፣
በአትላንታ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያን ክብር ለሚገባው ክብር ለመስጠት ሰፊ ፕሮግራም ያዘጋጃሉ። ከእነዚህ ታላቅ ኢትዬጲያውያን መካከል አትሌት ሐይሌ ገ/ሥላሴ ይገኝበታል። ፕሮግራሙ ሲጀመር ከነሙሉ ክብሩ ወደ መድረክ የተጠራው አትሌት ሐይሌ ሙቀቱ በፈጠረለት ወኔ ተነሳስቶ ታሪካዊ ንግግር አደረገ። ንግግሩ በከፍተኛ ጭብጨባ በመታጀቡ ሐይሌ ማቆም አልቻለም። በማሳረጊያውም በረጅሙ ተንፍሶ ” ኢትዬጲያ ብሆን ይሔን አልናገርም ነበር፣ የሚደርስብኝን ስለማውቅ !” በማለት ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለሕዝቡ በቁጭት አስረዳ ።በድጋሚ ከአዳራሹ የተሰማው ጭብጨባ፣ ፊሽካና ሳቅ ከአትላንታ ተነስቶ፣ አትላንቲክን አቋርጦ የሚኒሊክ ቤተመንግሥት ተሰማ።)
ወደቀደመው ጉዳያችን ስንመለስ አትሌት ሐይሌ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፎርሸው በምን ምክንያት ነው?… የሚናገረውን ነገር በጥልቀት ያውቀዋል ወይ?…ከጀርባ ሌሎች ምክንያቶች ይኖሩት ይሆን?…ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ማቅረብ ተገቢ ይሆናል። በእኔ እምነት አምስት መሰረታዊ ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል፣
1• ” የእውነተኛ ዲሞክራሲን” ትርጉም ያለማወቅ
2• የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ማጠንጠኛ ” የእውነተኛ ዲሞክራሲ እጦት” መሆኑን ያለመገንዘብ
3• “ፓለቲካ ሳይንስም ጥበብም” መሆኑን ያለማወቅ
4• ለከት የለሽ የሀብት ማሰባሰብ ፍላጐት እና
5• አገዛዙ የደረሰበት ( በድብቅ ሳያውቅ ያስፈፀመው) ከባድ ወንጀል መኖር
ለዚህ አጭር ማስታወሻ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ነጥቦች ላይ ትዝብቴን ማስፈር እፈልጋለሁ ።
1• “የእውነተኛ ዲሞክራሲን” ትርጉም ያለማወቅ
እንኳን ለሀይሌ የተለያዩ የፓለቲካል ኢኮኖሚ መጵሀፍቶችን ላገላበጡ ምሁራን የዴሞክራሲ ትርጉም ግልፅ አይደለም። በቃሉ ትርጉም መግባባት ሳይደረስ ” ዲሞክራሲ ያስፈልጋል /አያስፈልግም?…አለ ወይስ የለም? ” በሚለው እሰጣገባ ውስጥ የተገባበት አጋጣሚዎች አሉ። በዛ ላይ “ዲሞክራሲ” የሚለው ቃል እንደ ቃልኪዳን ቀለበት የስም ማስጌጫ ጣቱ ላይ ያላጠለቀ አለመገኘት ትርጓሜውን አደናጋሪ ያደርገዋል። እስቲ ይታያችሁ ባለፋት ሁለት ወራት ከ150 በላይ ኢትዬጲያውያንን በጠራራ ፀሐይ የገደለው ህውሀት የለበሰው ” ኢሕአዴግ” የሚባል ጭምብል በውስጡ “ዲሞክራሲ” የሚል ቃል አለው።
ስለዚህ እንደ አትሌት ሐይሌ ያሉ ሰዎች በትርጉም እና አስፈላጊነት ላይ ተደናግረው ብንመለከት ሊገርመን አይገባም። አብዛኛውን ጊዜ እነ ሐይሌ አዲስ እውቀት የሚጨምሩት በቃላት ትርጉም ላይ ልሂቃን እና ድርጅቶች ተስማምተው ተመሳሳይ ንግግር ሲናገሩ ካዳመጡ ብቻ ነው። ድፍረት ባይሆንብኝ የእነ ሐይሌ የእውቀት መጨበጫ ስልቱ በአይን የሚታይ የተግባር እንቅስቃሴ እንጂ በንባብ እና ምርመራ የሚገኝ አይደለም ።
በንባብ የሚገኝ ቢሆንማ ኖሮ አንጋፋው ፕሮፌሰር መስፍን ” ዴሞክራሲ ወይም ስልጣነ ሕዝብ ምንድነው? ” በሚለው ፅሁፋቸው ያሰፈሩትን በመመልከት ብቻ ግንዛቤ መጨበጥ በተቻለ ነበር። ፕሮፌሰር እንዲህ ይላሉ ፣
” ዴሞክራሲ ማለት የስልጣን ባለቤት ሕዝብ የሆነበት ስርአት ማለት ነው። መነሻው እና መድረሻው ይህ የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ነው። የሥልጣን ኮርቻው ላይ መውጣትም ሆነ ከዚያ ኮርቻ ላይ መውረድ የሚቻለው በሕዝብ ፍቃድ ብቻ ነው” በማለት ይገልፁታል።
ፕሮፌሰሩ የዲሞክራሲን ትርጉም ብቻ አልሰጡንም። ዲሞክራሲን በራሳቸው መነጵር ሲመለከቱት ምን እንደሚሰማቸው እንደሚከተለው ገልጸዋል ፣
” እኔ ዴሞክራሲን የማየው ምንግዜም ደማቅ ብርሐን ያለበት ለጥ ያለ ሜዳ ላይ እንደተንጣለለና መጨረሻው እንደማይታይ ጥሩ የአስፋልት መንገድ ነው። ቁም ነገሩ እዚያ መንገድ ውስጥ መግባቱ ነው። ብርሃኑ ማንኛውንም ነገር አጋልጦ የሚያሳይ ሲሆን ለጥ ያለው የአስፓልት መንገድ ደግሞ እንደልብ የሚያስጋልብ ነው።”
2• የኢትዬጲያ ችግር ማጠንጠኛ ” የዲሞክራሲ እጦት” መሆኑን ያለመረዳት
ዛሬ አገራችን ኢትዬጲያ የምትገኝበት ሁኔታ ከመቼውም በባሰ አስቸጋሪ ሆኗል። በተለይም ባለፏት ሩብ ምዕተ አመት በኢትየጵያ ህዝብ ላይ ተንሰራፍቶ የተቀመጠው አገዛዝ ሀገራችን የመኖር እና ያለመኖር የህልውና ጥያቄ ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። ስርአቱ በዚህ መልኩ ከቀጠለ እና ስር ነቀል ለውጥ ካልመጣ ይቺ በነጥቆ በራሪ ( roving bandits) የተወረወረች ምስኪን ሀገር ወዴት ልታመራ እንደምትችል መገመት አያዳግትም።
ከአንድ ሳምንት በፊት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊ/መንበር በአሜሪካ ሀገር ሜሪላንድ ግዛት ለህዝብ ንግግር ሲያደርግ ተገኝቼ ነበር። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ባደረገው ንግግር ሀገራችን የገባችበት አዘቅት መሰረታዊ ምንጩ ” ዲሞክራሲያዊ ስርአት” ባለመኖሩ እንደሆነ በቀይ ብእር አስምሮበታል። የሕዝብ ከመኖሪያው መፈናቀል፣ የህዝቡ በስርአቱ መማረር፣ የመንግስት በህዝብ ተቀባይነት ማጣት፣ አድሎአዊ የሆነ ስርአት መስፈን፣ የወጣቶች ስደት፣ ረሐብ እና የኢኮኖሚ ድቀት መንስኤው የእውነተኛ ዲሞክራሲ አለመኖሮ መሆኑን አስረድቷል። የሟሸሸና ጭንጋፍ መንግሥት ባለበት ሁኔታ ዲሞክራሲ ሊመጣ እንደማይችል አስገንዝቧል ። በዚህ አባባል ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ ።
ርግጥም ፕሮፌሰሩ እንደተገለፀው በኢትየጵያ “እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት” እስካልመጣ ድረስ የህግ የበላይነት ሊሰፍን አይችልም። ፀረ ዲሞክራሲ ዙፋኑን በጨበጠበት ሁኔታ ሁሉም ዜጐች በኢትዬጲያዊነታቸው ብቻ በህግ ፊት እኩል የማይታዩበት ፣ የዜግነት መብታቸው በተግባር የማይረጋገጥበት ሁኔታ ይፈጠራል። ተፈጥሯልም።
ዛሬ በህዝቦች መካከል በታቀደ መልኩ ጥርጣሬ እና ጥላቻ እንዲሰፍን እየተደረገ ነው። የወጣቱ የወደፊት ተስፋ ጨልሞ ስደትን እንደ አማራጭ ወስዷል። በጥቂት የሞራል ድህነት እና የበታችነት ስሜት በተጠናወታቸው ጠባብ ዘረኞች ሀገራችን ወደ መቀመቅ እየተገፋች ነው። የዜጐች የመናገር፣ የመጳፍ፣ የመደራጀትና ሌሎች መሰረታዊ መብቶች የ50ኛ አመቱን ” Golden Jubuilee” እያከበረ ካለው የኢቲቪ መስኮት ውጭ ማየት አልተቻለም።
3• “ፓለቲካ ሳይንስም ጥበብም” መሆኑን ያለመገንዘብ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ በበርካታ ድንቅ ንግግራቸው ይታወቃሉ። በተለይም ” ፓለቲካ ጥበብ (አርት) እና ሙያ… ያውም የተከበረ ሙያ ነው” በማለት አጠንክረው መግለጳቸው በብዙዎች ይታወሳል። ታዲያ ይህን ባህርዩን የተከበረ ሙያ እና ላቅ ያለ ማህበራዊ ሳይንስ መሆኑን ባለማወቅ አንዳንድ እንደ ሐይሌ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ” አዳፋ ቃላትን” ሲናገሩ ይደመጣል።
ክፋቱ ደግሞ የሚናገሩት ከሕዝብ ፊት ስለሆነ ከንፈራቸው ተከፍቶ ሳይዘጋ ጉዳቱ በራሳቸው ላይ ይደርሳል።
እናም አትሌት ሐይሌ ፓለቲካና የዲሞክራሲ ጵንሰ ሐሳብ መረዳት በማለዳ ተነስቶ ” 84 ኪሎ ሜትር ልሩጥ” እንደ ማለት የቂል ድፍረት አይደለም። የአገር እና ህዝብን ሁለንተናዊ ሕይወት የሚመለከት እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል የህልውና ጥያቄ ነው። የእውነተኛ ዲሞክራሲ መስፈን እና ያለመስፈን ጥያቄ በአሁን ሰአት ኢትዮጵያ የገባችበትን ቀውስ የመሻገር አሊያም ላታንሰራራ የመውደቅ ነው!!

http://www.satenaw.com/amharic/archives/12710


Wednesday, February 10, 2016

የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች የነበሩ ተከሳሾች ሕይወታችን አደጋ ላይ ነው


በተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ወንጀል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ‹‹መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናብተዋል›› ቢላቸውም፣ ይግባኝ ተጠይቆባቸው በእስር ላይ ሆነው እየተከራከሩ የሚገኙት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ፣ የአረና ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የነበሩት ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ መሆኑን፣ ለይግባኝ ሰሚው ችሎት የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. አሳወቁ፡፡

አቤቱታቸውን ያቀረቡትና አመራሮች የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ (አንድነት)፣ አቶ አብርሃ ደስታ (አረና) እና አቶ የሺዋስ አሰፋ (ሰማያዊ) ሲሆኑ፣ በተለይ አቶ ዳንኤል የተከሰሰበት ዋና ጉዳይ እንደማያሳስበው ገልጾ፣ ፍርድ ቤቱ እንዲያውቅለት የሚፈልገው ሕይወቱ አደጋ ላይ መሆኑ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የታሰረው በኮንቴይነር ውስጥ መሆኑን፣ ምግብ እንዳይገባለት መከልከሉን፣ ዘመድም ሆነ ቤተሰብ እንደማይጠይቀውና ዛቻም እንደሚፈጸምበት ለይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልክቷል፡፡ አቶ አብርሃና አቶ የሺዋስም ተመሳሳይ ድርጊት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ይግባኝ ሰሚው ችሎት የይግባኝ መዝገቡን ቀጥሮት የነበረው፣ ይግባኝ ባይ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በአመራሮቹ ላይ ያቀረበውና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለው ማስረጃ ዋናው እንዲቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ቀን (ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም.) ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፍትሕ ሚኒስቴር ለማዕከል መመርመርና ውሳኔ ማሰጠት ዳይሬክቶሬት፣ እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴር ደግሞ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት በጻፉት ደብዳቤ መሠረት ውሳኔው ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡


ብሔራዊ መረጃና ደኅነነት አገልግሎት በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ከተቋሙ የተገኘውንና ተከሳሾቹን ያደረጉትን የመልዕክት ልውውጥ በሚያሳይ መልኩ ተስተካክሎ እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሥራ የሚሠሩ አካላት ካለባቸው የሥራ ጫናና መደራረብ ምክንያት እንደማይችልና የአንድ ሳምንት ጊዜ ቢሰጠው ሠርቶ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጾ ለሚኒስቴሩ መግለጹ ተነግሯል፡፡


ዓቃቤ ሕግም ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ሀብታሙ አያሌው በፍርድ ቤቱ እምነት ማጣቱን ገልጾ እየተጉላሉ መሆኑንም ተናግሯል፡፡


ይግባኝ ሰሚው ችሎት ከሦስት ሳምንታት በፊት ያስተላለፈው ትዕዛዝ፣ ዓቃቤ ሕግ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳገኘው የገለጸውን የኢሜል፣ የኢንተርኔትና የድምፅ ማስረጃ እንዳለ ዋናው (Original) እንዲቀርብለት ነበር፡፡ በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ በተለይ በደል ተፈጽሞብናል ያሉትን ተከራካሪዎች፣ በሚመለከት፣ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በማስረጃው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/50855

Tuesday, February 9, 2016

በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ አላስተማመነም የዕርዳታ ሠራተኞች ወደ መስክ እንዳይወጡ ተከለከሉ

       February 9, 2016 09:05 am


በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታና ደኅንነት ሁኔታ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አለመሆኑ ተነገረ፡፡ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ወደ መስክ የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት ተከለከለ፤ የፕሮጀክት ሥራዎች ሊደናቀፉ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ ኢህአዴግ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞችን ወደተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይንቀሳቀሱ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው መሆኑን መረጃው የደረሳቸው ለጎልጉል አስታውቀዋል፡፡

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይ የአማራ ክልልና በምዕራብ ደግሞ የጋምቤላ ክልል አካባቢ ያለው ውጥረት እጅግ እያየለ በመምጣቱ በቦታዎቹ ላይ የሚንቀሳቀሱ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ሊደርስባቸው ስለሚችል ጉዳት ተጠያቂ እንደማይሆን ኢህአዴግ በሰጠው ማሳሰቢያ አስታውቋል፡፡

ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው የዕርዳታ ድርጅቶች መካከል የካቶሊክ ዕርዳታ አገልግሎት አንዱ ሲሆን በውሳኔው ምክንያት ድርጅቱ በተለይ በጋምቤላ የሚያከናውነው ፕሮጀክት ችግር ላይ እንደሚወድቅ ተነግሯል፡፡

ኢህአዴግ ማስጠንቀቂያውን ካስተላለፈ በኋላ በተዋረድ ከአለቆቻቸው ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሠራተኞች ወደ ተጠቀሱት ቦታዎች እንዳይሄዱ መከልከላቸውን የዜናው አቀባዮች ለጎልጉል አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ እያየለ የመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞና እምቢተኝነት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በገሃድ የሚታይ ሆኗል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ለወራት መቀጠሉ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማምጣቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ እና በሌሎች ክፍለኢኮኖሚዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ባለሙያዎች አሳማኝ ግምቶች ይሰጣሉ፡፡


ህወሃት እንደ ጭቃ ጠፍጥፎ የሠራቸው የአማራውና የኦሮሞው ድርጅት አባሎች ለአንድ ብሔር የበላይነት አንገዛም የሚሉ ጥያቄዎች እያነሱ መምጣታቸው በመለስ አዝማችነት ህወሃት ሁሉ ቦታ ከለኮሰው የዘር እሣት ጋር ተዳምሮ የአገሪቱ መጻዒ ዕድል የሚያሳስባቸው ወገኖች ሁኔታው መላ ሊፈለግለት ያሻዋል ይላሉ፡፡

http://www.goolgule.com/aid-organizations-to-be-aware-of-insecurity/

Friday, February 5, 2016

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ ‹‹የህሊና እስረኛ ነኝ››

በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ 18 አመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ ለሆነው አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክር ሆኖ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከእስር ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ እስክንድር ዛሬ ጥር 27/2008 ዓ.ም ምስክርነቱን ሊያሰማ ችሏል፡፡

ያለጠበቃ በግሉ የሚከራከረው ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጋዜጠኛ እስክንድር እንዲያስረዳለት የሚፈልገው ጭብጥ ጡመራ ምንድነው፣ ከወንጀል ጋርስ ግንኙነት አለው ወይ፣ እና ሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ ስልጠና ስለሚሰጡ ድርጅቶችና የስልጠናው ይዘትን በተመለከተእንደሆነ ቢያስታውቅም በጭብጡ ላይ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ በዚህም አቃቤ ህግ ጡመራ ምንድነው፣ ወንጀልስ ነው ወይ የሚለው በምስክር ሳይሆን በህግ ድንጋጌዎች የሚረጋገጥ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ጡመራ ወንጀል ስለመሆን አለመሆኑ የተያዘውን ጭብጥ ውድቅ በማድረግ ስለ ስልጠናውና አሰልጣኝ ተቋማት የተመዘገበው ጭብጥ ላይ ምስክሩ እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል፡፡ 


ብይኑን ተከትሎ ምስክሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያ በፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ጥያቄዎች መልሷል፡፡ ምስክሩ ሙሉ ስሙን፣ እድሜውን፣ ስራውንና ለምን እንደመጣ፣ እንዲሁም ከተከሳሾች ጋር ስለመተዋወቁ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡ እስክንድር ‹‹ስራ›› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ነበርኩ›› ብሏል፡፡ ‹‹አሁንስ›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቅርቦለት፣ ‹‹አሁን የህሊና እስረኛ ነኝ›› ሲል መልሷል፡፡


ተከሳሹ ዘላለም ወርቃገኘሁ በዋና ጥያቄ ተከሳሹ ውጭ ሀገር ሊወስደው ነበር ተብሎ በክሱ ላይ ስለተጠቀሰው ስልጠና ምስክሩ እንዲያብራሩለት ጠይቋል፡፡ ምስክሩም ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትንም የሚያሳትፍ ስልጠና በሰብዓዊ መብት፣ በሚዲያ ‹ኢቲክስ›፣ እና በዴሞክራሲ ላይ ይሰጣሉ፡፡ ድርጅቶቹ የተለያዩ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መርሃቸው ተመሳሳይና ዓለም አቀፍ ነው›› በማለት መስክሯል፡፡ 


ድርጅቶቹን በስም መጥቀስና የሚገኙበትንም ሀገር ለፍርድ ቤቱ መግልጽ ይቻል እንደሆነ ምስክሩ ተጠይቆ ‹‹የተቋማቱ መገኛ ምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ በዴሞክራሲ የዳበሩ ሀገራት ነው ዋና መቀመጫቸው፡፡ ሲ.ፒጄ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና አርቲክል 19 የመሳሰሉትንም በስም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኔም ከነዚህ ተቋምት ውስጥ በአንዱ የተሰጠ ስልጠና አዲስ አበባ ላይ ተካፍየ ነበር፡፡ ስልጠናው ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ሚዲያ፣ ስለ ዴሞክራሲ የሚያስተምር ነው፡፡ ስልጠናው ከሽብር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ይህ እንደማስረጃ መቅረቡ ኢትዮጵያን ትዝብት ውስጥ የሚከትና የሚያሳዝን ነው›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ 


ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መቼ እንደታሰረ በመስቀለኛ ጥያቄ ተጠይቆ ‹‹መስከረም 2004 የሀሰት ክስ ቀርቦብኝ፣ በግፍ ተፈርዶብኝ ታስሬ እገኛለሁ›› ሲል መልሷል፡፡ እስክንድር ነጋ ጥቁር ሱፍ በደብዛዛ ሸሚዝ ለብሶ፣ ሙሉ ጥቁር መነጸር አድርጎና ነጠላ ጫማ ተጫምቶ ችሎት ፊት ቀርቧል፡፡ 


አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ምስክሩ ምስክርነቱን ማጠቃለሉን ተከትሎ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡለት የጠራቸው ሌላኛው ምስክር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን አለመቅረባቸው መንግስት ግለሰቡን ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ‹‹አሁን የተረዳሁት ነገር ከሳሼ የሆነው መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን ከሚያቀርብ እኔን በነጻ መልቀቅ እንደሚቀለው ነው›› ብሏል ተከሳሹ፡፡


ተከሳሹ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተገናኜ አቃቤ ህግ መጥቀሱን በማስታወስ ምስክሩ መቅረባቸው ያለውን ተገቢነት አስረድቷል፡፡ ‹‹ምስክሩ እንዲቀርቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ከምስክሩ ጋር በተገናኘ ያለውን የክሱ ፍሬ ነገር አውጥቶ በቀሪው ላይ ብይን ይስጥልኝ›› ብሏል ተከሳሹ አቶ ዘላለም፡፡ 



ፍርድ ቤቱም ምስክሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለየካቲት 16/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/50666