Wednesday, September 11, 2013

በህገ-ወጥ ርምጃ ሕጋዊው ሰላማዊ ሰልፋችን አይቀለበስም!!!

September 11.2013

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ላለፉት ሦስት ወራት ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት›› በሚል መሪ ቃል በመላ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ንቅናቄ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በጎንደር፣ በደሴ፣ በባህርዳር፣ በአርባ ምንጭ፣ በጅንካ፣ በፍቼና አዳማ ከተሞች ሕዝቡን ያሳተፉ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ያጋጠሙ የገዥው ፓርቲ እንቅፋቶችን እየተራመደ በተሳካ ሁኔታ ያደረገ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችንም አከናውኗል፡፡ ፓርቲያችን የመጀመሪያውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ለማጠናቀቅም በአዲስ አበባ ከተማ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም የሚካሄደውን የመጀመሪያው ምዕራፍ የማጠቃለያ የተቃውሞ ሰልፍ ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር ለማካሄድ ወስኖ ይህንንም ውሳኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሳወቅ ሰፊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህ ሂደትም አመራሩና የፓቲው አባላት በከፈሉት መስዋዕትነትና ግፊት ህዝቡን ያሳተፉ የተቃውሞ ሰልፎች እንደጅምር አበረታች ናቸው ብለን ብናምንም የህዝቦች መብት ሳይሸራረፍ እስከሚከበር ድረስ፣ ነፃነታችን እስከሚረጋገጥ ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በአዲስ አበባ የምናካሂደውን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማከናወን ከማሳወቅ ጀምሮ የገጠመን ውጣ ውረድና ማደናቀፍ ትልቋ ከተማችን ሃላፊነት በማይሰማቸው አስተዳዳሪዎች የምትመራ መሆኑንም ያረጋገጥንበት አጋጣሚም ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ ላለመቀበል ከማስቸገርም በላይ የቢሮ ሓላፊዎችና ሌሎች በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ስልጠና፣ ስብሰባ፣ እንግዳ ለመቀበልና ሌሎችን ተልካሻ ምክንያቶች በመደርደር ለማደናቀፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ ደብዳቤ ፈርሞ መቀበል የማይችል አካል ሃላፊነት የማይሰማው ነው ከማለትም ባለፈ በህግ የሚያስጠይቅ ሀላፊነትን ባግባቡ አለመወጣትን የሚያመለክት ድርጊት ነው፡፡ ከንቲባውና የከንቲባው ፅ/ቤትም በአግባቡ ካለማስተናገድም በላይ የአንድነትን ከፍተኛ አመራሮች (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና አቶ አስራ ጣሴን) ሀላፊነት በጎደለው ሁኔታ ስለሰላማዊ ሰልፉ እንደራደር በማለት አመላልሰዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ በቂ ቢሆንም ከከንቲባው ጋር መነጋገር ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ለፖሊስ በሚሰጥ የውስጥ መመሪያ እየተካሄደ ያለው ማደናቀፍ እንዲቆም፣ መስተዳድሩ መመሪያ ብሎ ያወጣውና ለወረቀት ብተና፣ ፖስተር ልጠፋ፣ የመኪና ላይ ቅስቀሳና ፔቲሽን ለማስፈረም ልዩ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ የሚያዝ፤ ይህ ካሆነ ፖሊስ ርምጃ እንዲወስድ የሚያደርገውን ሕገ-መንግስት የሚጥስ መመሪያ በተመለከተ ነበር፡፡ ምንግዜም ህጋዊ መስመር ተከትሎ ከማስተዳደር ይልቅ በህገ-ወጥ መንገድ ማፈንና ማደናቀፍ የሚመርጠው ገዥ ፓርቲ ለህጋዊ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄያችን የመረጠው መንገድ ህገ-ወጥነትን ነው፡፡ ይህ ህገወጥነትም መንግስትን ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡ ስለዚህ፡- 1ኛ. ሰላማዊ ሰልፋችንን ለማድረግ ከነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ያሳወቅን በመሆኑ በታቀደው ቀን መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠኋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ይደረጋል፡፡ 2ኛ. ለሰላማዊ ሰልፉ ቅስቀሳና ሂደት ላይ ለሚከሰቱ ማናቸውም ጉዳቶች ተጠያቂው መስተዳድሩና መንግስት ነው፡፡ 3ኛ. ሕገ-መንግስቱን የማስከበር ተልዕኮ ያለው ፖሊስ በህገ ወጥ መመሪያ አባሎቻችንን ከማሰርና ማዋከብ እንዲቆጠብ እንዲሁም ህጋዊ መሰረት ያለውን ሰላማዊ ሰልፋችንን ፀጥታ የማስከበር ሃላፊነት እንዳለበት እያሳሰብን ቅስቀሳ በሚደረግበት ወቅት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣና የህግ የበላይነትን እንዲያስጠብቅ ከአደራ ጋር እናሳስባለን፡፡ ህዝቡም መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ አደባባይ በመውጣት የተቃውሞ ድምፁን በሰላማዊ መንገድ እንዲያሰማ ሃገራዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!!


  Posted By,Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment