Monday, March 10, 2014

ሐረር በእሳት አደጋ፣ በጥይት ሩምታ፣ በሕዝባዊ ተቃውሞና በቆመጥ ድብደባ ስትታመስ ዋለች

(-ሐበሻ) በሐረር ትናንት ምሽት ከግምት ከሶስት ሰዓት ተኩል ጀምሮ ልዩ ስሙ መብራት ሃይል ተበሎ በሚታወቀው የገበያ ቦታ በተነሳ እሳት አደጋ የበርካታ ነጋዴዎች ንብረት ከወደመ በኋላየእሳት አደጋውን የክልሉ መንግስት ሆን ብሎ ያቀነባበረው ነውበሚል የአካባቢው ነዋሪ በዛሬው ዕለት ተቃውሞን ለመግለጽ አደባባይ ወጥቶ እሳቱን ለማጥፋት ውሃ ያልነበረው የክልሉ የእሳት አደጋ ማጥፊያ የተቃውሞ ሰልፈኛውን ለመበተን ውሃና አስለቃሽ ጭስ ሲጠቀም ዋለ። የክልሉ ፖሊስም በጥይት ሩምታ በማውረድ፣ በቆመጥ በመደብደብ ሰልፈኛውን ሲበትን መዋሉን ለዘ-ሐበሻ ከስፍራው የደረሱ ዜናዎች አመልክተዋል።


የዘ-ሐበሻ ተባባሪ ዘጋቢዎች ከሐረር በትናንቱ የእሳት አደጋ ቃጠሎ ንብረታቸው ከወደመባቸው መካከል የተወሰኑትን በማነጋጋር ባጠናቀሩት መረጃየክልሉ መንግስት ነጋዴዎቹ ይሰሩበት የነበረውን ቦታ ይፈልገው ነበር። በተደጋጋሚም እንዲነሱ ጠይቋል። ነጋዴዎቹ ከዚህ ቀደም 3 ዓመታት በፊት ሸዋበር አካባቢ በተመሳሳይ ሴራ ንብረታቸው የተቃጠለባቸው መሆኑን እና በትናንቱ አደጋ ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ በመውደሙ ለተቃውሞ አደባባይ እንዳስወጣቸው መረዳት ችለናል።

በመብራት ሃይል የገበያ ቦታ የተነሳው እሳትን ለማጥፋት የተደረገው ርብርቦሽ በጣም ደካማ እንደነበር የሚገልጹት እነዚሁ ነጋዴዎች ከድሬደዋ እና ከጅጅጋ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ብርጌድ እስኪመጣ ድረስ ብዙ ንብረት ወድሟል። እሳቱ ሳይስፋፋ ነጋዴዎቹም የተወሰነ ንብረት እንኳ ከእሳቱ እንዲያተርፉት አለመደረጉን የገለጹት እነዚሁ ባለንብረቶች መንግስት ወዲያውኑ የተቃጠለውን አካባቢ በግሬደር ማረሱ አስገራሚ ሆኖባቸው ነጋዴዎቹ ዛሬ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።
በብሶት የተወጠረው የሃረር ሕዝብ ባስነሳው ተቃውሞ የክልሉ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ፣ በቆመጥ ድብደባ፣ በውሃ፣ በጥይት ሲበትን የዋለ መሆኑን የገለጹት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች በርካታ ሰዎች መታፈሳቸውንም ገልጸዋል።

በዚህ የተቃውሞ እንስቃሴ ላይ የሞተ ሰው እንዳለ ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ግን ተሰምቷል።

ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሱን እንመለሳለን።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13490




No comments:

Post a Comment