Monday, April 18, 2016

በጋምቤላው እልቂት ዙሪያ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ባለ3 ነጥብ መግለጫ አወጡ

ሚያዚያ 6 ቀን 2008 በጋምቤላ ክልል ነዋሪ በሆኑ ሰላማዊ የኑዌር ብሔረሰብ አባላት ላይ በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ነዋሪ በሆኑ ታጠቂዎች የተፈጸመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመስማታችን መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ እጅግ ልብ የሚሰብር ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል፡፡

ከመንግሥት ባገኘነው መረጃ መሠረት ብቻ 208 ዜጎቻችን በዚሁ ጭፍጨፋ በአንድ ሌሊት ሕይወታቸውን ማጣታቸውና 102 ሕፃናት ታፍነው መወሰዳቸው በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛና ዘግናኝ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ዜጎቻችን ለዚህ ያህል ትልቅ ጥቃት የተዳረጉት ደግሞ ቀደም ሲልም ጥቃት ሲፈጸሚባቸው እንደነበረ እየታወቀ የኢህአዴግ መንግሥት እራሳቸውን የሚከላከሉበትን ትጥቅ በማስፈታቱ የመከላከያ መሣሪያ እንዳይኖራቸው በመደረጉና ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ሁኔታ ለደህንነታቸው ተገቢው ጥበቃ ስላልተደረገላቸው መሆኑን መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባሉ፡፡

ከዚህም ሌላ ቀደም ባሉት መንግሥታት በየጠረፉ አከባቢዎች ይመደብ የነበረው ጠረፍ ጠባቂ ኃይል እንዳይኖር በመደረጉ የውጭ ሀገር ታጣቂዎች እንደፈለጉ ድንበር ጥሰው የሚገቡበትና ወገኖቻችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል፡፡

ስለዚህም፡-

1
ኛ፡- በጥቃቱ ምክንያት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ላጡ የኑዌር ብሄረሰብ አባላት ለሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደዚሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን፡፡

2
ኛ፡- በአጥቂዎቹ ታፍነው የተወሰዱት ሕፃናት በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መንግሥትና የዓለም ማሕበረሰብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ተገቢውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

3
ኛ፡- ለወደፊቱ በጋምቤላም ሆነ በሌሎች ክልሎች በጠረፍ አከባቢዎች በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ሕዝቡ ራሱን መከላከል የሚያስችልበትና ተገቢውን የደህንነት ጥበቃ የሚያገኝበት ሁኔታ በአስቸኳይ በመንግሥት በኩል እንዲመቻች አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ሰላም ለሕዝባችን!!
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ
ሚያዚያ 9 ቀን 2008
አዲስ አበባ

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/53487

No comments:

Post a Comment