የ25 ዓመቱ ሙዓዝ ማሐሙድና የ28 ዓመቱ ሞውሊድ ኢስማን የነበሩባቸው ጀልባዎች እያንዳንዳቸው 200 ሰዎች የጫኑ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ከትንንሾቹ ጀልባዎቹ ከፍ ወዳለችው ጀልባ እንዲሸጋገሩ በሰው አዘዋዋሪዎቹ ሲታዘዙም አዲሷ ጀልባ ውስጥ 300 ያህል ሰዎች እንደነበሩ ለጀርመኑ ዶቼቬሌ ጠቅሰዋል፡፡
በአደጋው የተመለከቱት ነገር ምስክርነታቸውን በሚሰጡበት ሰዓት ጭምር የፈጠረባቸው ጭንቀት፣ፍርሃትና ልብን የሚሰብርን ሐዘን ከገጽታቸው መመልከት ይቻላል፡፡
ማሐሙድ ‹‹ወደ ትልቁ ጀልባ እንደተሸጋገርን ጀልባዋ መስመጥ ጀመረች፡፡የሁለት ወር ዕድሜ የነበራት ልጄና የ21 ዓመቷን ባለቤቴን ባህሩ ነጠቀኝ››በማለት በግሪክ ለሚገኙት የእርዳታ ሰራተኞች ነግሯቸዋል፡፡
ሁለት ሰዎችን ከሞት ማዳኑን የሚናገረው ማሐሙድ በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ ከነበሩት 500 ሰዎች በህይወት የተገኙት 41ዱ ብቻ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
ሁለቱ ወጣቶች መጀመሪያ ተሳፍረውባቸው ከነበሩት አነስተኛ ጀልባዎች አንዷን ቢያገኙም ሰው አዘዋዋሪዎቹ ሊጠብቋቸውና ከሞት ጋር ግብግብ ገጥመው የነበሩትን ሊሎች ሊረዷቸው ሳይፈቅዱ ጥለዋቸው እንደሄዱ ይናገራሉ፡፡
በአደጋው ሁለት እህቶቹንና የእህቱን ልጅ ያጣው ሞውሊድ ‹‹በአይናችን የሞቱ ሰዎች ተመልክተናል››ይላል፡፡የጀልባዋ የነዳጅ መያዣ እንደተሰበረም ሰው አዘዋዋሪዎቹ የመጣችላቸውን ሶስተኛ ጀልባ በመጠቀም ተመልሰው በመምጣት እንደሚወስዷቸው ቃል በመግባት ጥለዋቸው መሄዳቸውንም ሞውሊድ ይናገራል፡፡
‹‹ለሶስት ቀናት ያህል በባህሩ ላይ ነበርን››የሚለው ሞውሊድ የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር ሳያገኙ መቆየታቸውንም መስክሯል፡፡እንደ ዕድል አንድ ሞባይል አንድ የስልክ ቁጥር ብቻ ተመዝግቦበት ያገኙት እነ ሞውሊድ ወዳገኙት ቁጥር ይደውላሉ፡፡ስልኩ የጣልያን ፖሊስ ነበር፡፡ የጣሊያን ፖሊሶች በስልክ ለደረሳቸው የህይወት አድን ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የባህር ኃይል ሰዎችን ወደ ስፍራው በመላካቸውም እነ ሞውሊድ ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል፡፡
በህይወት መትረፍ ከቻሉት 41 ሰዎች ውስጥ 37ቱ ወንዶች ፣ሶስቱ ሴቶችና አንደኛው የሶስት ዓመት ታዳጊ መሆናቸውን የጣሊያን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ፣የጣሊያን፣የግሪክና ወይም የግብጽ የባህር ኃይል ሰራተኞች እስካሁን ድረስ ሰጠመች የተባለችውን ጀልባም ሆነ አስከሬኖችን ስለማግኘታቸው አልገለጹም፡፡
http://www.satenaw.com/amharic/%E1%8A%A8%E1%8C%80%E1%88%8D%E1%89%A3%E1%8B%8B-%E1%89%A0%E1%88%85%E1%8B%AD%E1%8B%88%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%88%A8%E1%8D%89%E1%89%B5-%E1%88%B5%E1%88%88-%E1%89%B0%E1%8A%A0%E1%88%9D%E1%88%A8/
No comments:
Post a Comment