Thursday, February 27, 2014

አብርሃ ደስታ… ታስሮ ተፈታ!!


EMF – በትግራይ ውስጥ የሚደረጉ ግፍ እና በደሎችን ያለመሰለስ በማጋለጡ ይታወቃል:: ለሰብአዊ መብቶች መከበር በመቆሙ ከህወሃት ሰዎች ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ እና ዛቻዎች ሲደርሱበት ነበር:: ባለፈው ሳምንት ቃሊቲን ለመጎብኘት የፖለቲካ እስረኞችንም ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በነበረበት ወቅት “እንዴት የፖለቲካ እስረኛ ለመጠየቅ ከትግራይ ድረስ መጣህ?” በሚልም ለእስር ዳርገውታል:: ሁኔታውን እራሱ አብርሃ ደስታ እንዲህ በማለት ገልጾታል::
አዲስ አበባ ነበርኩ። ሰኞ ጧት ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ለመጠየቅ ቃሊቲ ማረምያቤት ሄድኩኝ። ጥበቃዎቹ ወደ ማረምያቤቱ አስተዳዳሪ ወሰዱኝ። አስተዳዳሪው ምርመራ ይሁን ዛቻ በማይታወቅ መልኩ ካስፈራራኝና ከሰደበኝ በኋላ ከማረምያ ቤቱ ተባረርኩ። አስተዳዳሪው “አንተ ከትግራይ አክራሪ አማራዎችን ለመጠየቅ ስትመጣ አታፍርም?!” አለኝ። ከፈለኩ ብሄር ብመጣም የፈለኩትን ሰው የመጠየቅ መብት አለኝ። የታሰረ ሰው መጠየቅ አያሳፍርም” መለስኩለት። ካሁን በኋላ “ወደ ቃሊቲ የምትገባው ታስረህ ካልሆነ በቀር እነ አንዱኣለምን ለማየት ድርስ አትላትም!” ብሎ ፖሊሶችን እንዲያስወጡኝ አዘዘ።
ወደ ቂሊንጦ ማረምያ ቤት ተጓዝኩ፤ ኡስታዝ አቡበክር አህመድን ለመጠየቅ። “አሸባሪ ለመጠየቅ መጣ” ተብዬ ለሦስት ሰዓታት ታሰርኩ። የቂሊንጦ ማረምያቤት ዋና አስተዳዳሪ እምባዬ ህቡዕ “አሸባሪዎችን ለማበረታታት መጣህ፣ ማረምያቤቱን ለመበጥበጥ ነው የመጣኸው። እንዳውም አሁን በማረምያቤቱ ረብሻ ተነስቷል። ስለዚህ ይታሰር” ብሎ በማዘዙ ወህኒቤት ዉስጥ ቆየሁ።
 ዝርዝር ጉዳዩን ለመፃፍ እሞክራለሁ። አንዱኣለም አራጌና ርእዮት አለሙን አላየኋቸውም። አቡበክር አህመድ (ና ሌሎች ጉደኞቹ) ግን አግኝቻቸዋለሁኝ። እነ አቡበክር አህመድን በማግኘቴ ደስ ብሎኛል።



 http://ethioforum.org/%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%88%AD%E1%88%83-%E1%8B%B0%E1%88%B5%E1%89%B3-%E1%89%B3%E1%88%B5%E1%88%AE-%E1%89%B0%E1%8D%88%E1%89%B3/

Tuesday, February 25, 2014

‘‘ፋሽዝም’’ በኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያ በወያኔ ፈላጭ ቆራጭ ቡድናዊ አገዛዝ ስር ከወደቀችበት እነሆ ሁለት አስርተ ዓመታት ነጐዱ። ወያኔ ስልጣን ላይ ሲወጣ ካለፈው የተሻለ የዲሞክራሲ ለውጥ ይመጣል የሚል በብዙ ሰዎች ዘንድ የተስፋ ጭላንጭል ተጥሎለት ቢኖርምጅብ እስኪነክስ ያነክስእንዲሉ ስልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ ግን ተስፋ የተጣለለትን ዲሞክራሲ ደብዛውን በማጥፋትከፋፍለህ፣ በሆዱ ይዘህ፣ አሸብረህ፣ አደናግረህ፣ አናቁረህና አደንዝዘህ ግዛየሚለውን ሌሎች አምባገነን መንግስታት የሚከተሉትን የጡንቻ አገዛዝ ዘይቤ የዲሞክራሲ ሽፋን በመስጠት ዘላለማዊ ስልጣናቸውን ለማጠናክር ሲሉ በበለጠ ሲጠቀሙበት መቆየታቸው የአደባባይ ሚስጢር ሆኖ ቆይቷል።

በአገራችን ኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ አገዛዝ በዓለም ዙሪያ በተለያየ ዘመን ወደ ሥልጣን ከመጡት መሰል ፀረ-ሕዝብ መንግሥታት ቢብስ እንጂ በምንም መልኩ የተሻለ አይደለም። ፋሽዝምን እንቃወማለን፣ እናወግዛለን እያለ በጫካ ያናፋ የነበረው ወያኔ ዛሬ በዲሞክራሲ ድባብ ሥር እየተገበረው ያለ አገርና ሕዝብን ማዋረድና መዝረፍ፣ መቀጣጫ እያለ በግፍ ማሰርና መግደል ምን ተብሎ ሊጠራ ነው? በአዲስ አበባ በጋምቤላ በአዋሳ በወለጋ በሰሜን እና በአራቱም ማእዘን የኢትዮጵያ ክልሎች በየእለቱ በወያኔ ታጣቂዎች እየተካሄደ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋ ምን ብለው ይጠሩታል?

ወያኔ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ተሸክሞት የመጣውን በቀል አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ አፋሩ፣ ኦጋዴኑ ወዘተ. ዘር የማጥፋት ተግባሩን ፈጽሞታል፤ አሁንም እያጠፋ፣ እየገደለ በየወህኒ ቤቶቹ እየማገደው ነው። ይዞት የመጣው ድህነትና በሽታን ብቻ ነው። ፖሊሲው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዓለም ሃገሮች በድህነት ከወለል በታች ያደረገ ስርዓት ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት በነበረበት ወቅት እራሱን እና ቤተሰቡን አብልቶ ቀሪውን ለገበያ በማቅረብ ሕዝቧ እንደ አቅሙ በልቶና ጠጥቶ ያድር ነበር። የወያኔ መንግስት መሬት የመንግሥት ነው ብሎ በማወጁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገጠሩም በከተማም መሬት አልባ ሆኗል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ ሃገሩ ሁለተኛ ዜጋ ከመሆኑ የተነሳ ሲሞት እንኳን የሚቀበርበት ቦታ ያጣ ሕዝብ ሆኗል። የዚህ ጽሁፌ ዋና አላማ የወያኔ መንግስት የፋሽስት አገዛዝ ስለመሆኑ ምሳሌዎችን አንድ ሁለት በማለት ነቅሸ በማሳየት ማስረገጥ ሲሆን ወያኔ ከምስረታው ጀምሮ ያካሂድ የነበረውን የንፁሃን ወገኖቻችንን ጭፍጨፋ ለማስረጃነት በማንሳት ለማሳየት እሞክራሉ።

ወያኔ 1969 መጀመሪያ በትግራይ ሰላማዊ ዜጋ ላይ ግድያ በመፈፀም ፋሽስታዊ ጉዞውን ብሎ ጀመረ። ግድያው ሳያንሰው የንፁሃን ዜጐችን ሃብትና ንብረትም ወረሰ። ከደደቢት በረሃ የጀመረውን አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው በማለት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች አማራውን በመጨፍጨፍ የዘር ማጥፋት ወንጀልም ፈጽመዋል። ለሴቶች በግዳጅ የማምከኛ መድሃኒት በመስጠት የአማራው ቁጥር እንዳይጨመር አድርገዋል። ከኖረበት ቀየውና መሬቱ በግዳጅ እንዲፈናቀል አድርገዋል።

ወያኔ ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረ 1984/5 መጀመሪያ ጀምሮ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ በመክፈት የግድያ፣ የቤት ማቃጠል፣ ንብረቱን መዝረፍና ከፍ ያለ ሰቆቃ አደረሰ። እንደ አማራው ሁሉ ከመኖሪያ ቦታውና ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሏል። የኦነግ አባል ናችሁ እየተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ ወደ ወህኒ ወርደዋል። በየቦታው በከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት የሚማሩት የኦሮም ልጆች ከትምህርታቸው ተባረዋል። የተባረሩትም፣ መባረራቸው አልበቃ ብሎ ለእስር ተዳርገዋል፤ የተገደሉትንም ቤት ይቁጠራቸው። ደጉና ሩህሩሁ የኦሮሞ ሕዝብ ከእርሻው ተፈናቅሎ የረሃብና የበሽታ ሰለባ በመሆን የፋሽስቱ ወያኔ የግፍ ፅዋ ገፈት ቀማሽ ከመሆን አላለፈም።

ወያኔ በጋምቤላ አኝዋኮች ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማንም ይረሳልዋል ብየ አላስብም? ሕዝቡ ከመሬቱ ተፈናቅሎ አብዛኛው በጎረቤት ሃገሮች ስደተኛ ሆነው በየሃገሩ እየተንከራተተ በችግር ላይም ይገኛሉ።

የኦጋዴን ሕዝብም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል። ቤት ንብረቱ በወያኔ ወታደሮች ተቃጥሎበታል፤ ሴት ልጆቹና ሚስቶቹ ተደፍረውበታል። በተጨማሪም ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሎ ለስደት ተዳርጓል።

የአፋር ሕዝብም በሌሎቹ የኢትዮጵያ ጎሳዎች የደረሰው ደርሶበታል፣ እየደረሰበትም ይገኛል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማሰቃየት ባለፈ ደግሞ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለሱዳን መንግሥት ሸጠዋል። ሃገሪቱን ካለባህር በር አስቀርተዋል። የሃገር ሃብትና ታሪካዊ ቅርሶችን አውደመዋል፣ ሸጠዋል።

እንደው በደፈናው በአገራችን ታሪክ ውስጥ በሕዝባችን ከቶም እንደ አሁኑ ሳንጃ በአንገቱ ላይ ተወድሮ ጦር ተሰብቆበት የሚገኝበት የፋሽስታዊ አገዛዝ ጊዜ የለም። ፋሽዝም ዛሬ በወያኔ/ህወሃት ጊዜ ነግሷል ሥርም ሰዷል። በሥልጣን ላይ ለመቆት፣ ሃብቷን በዝብዞና ሽጦ ለማፈራረስ በታቀደው የአገዛዝ ሽብር ተግባር፣ ፋሽዝም በዴሞክራሲ ታዛ ሥር ወያኔ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ እየፈጸመው ያለ ለመሆኑ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ይረዳውል ብየ አምናለሁ። ፋሽስት ሕዝብ ይጨፈጭፋል፣ ያስፈራራል፤ ፋሽስት የማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳን ያስፋፋል፣ ውሽት ይዋሻል፤ ፋሽስት ትምክህተኛና ጦርነት ፈላጊ ነው። ፋሽስት ራስ ወዳዶችን፣ ሆዳሞችን፣ ግብዞችን፣ ዱርየዎችን መሳሪያ ያደርጋል፤ ፋሽስት ድርጅቶችን ያስፋፋል፣ ተለጣፊ ያበዛል ወዘተ። እንግዲህ የፋሽስት አገዛዝ ባህርያትን ማንሳቴ ወያኔን በነዚህ ባህሪያትም መዝነን ፍረጃችንን ለማጠናከር ይረዳን ዘንድ በማሰብ ነውና መዝኖ ፍርድ መስጠቱን ለእናንተው ትቻለሁ።

ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እጁን በንፁኃን ዜጎች ደም የታጠበው የወያኔ አገዛዝ ሕጋዊ የአምልኮት ነፃነታቸው ያለምንም የአገዛዙ ጣልቃገብነት እንዲከበር የጠየቁ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ በሃይማኖት አክራሪነትና አሸባሪነት ወንጅሎ የግድያ ወንጀል ፈጽሟል። በክርስቲያን እምነት ተከታይ ወገኖቻችንም ተመሳሳይ ግፍ ሲፈፀምባቸው ተመልክተናል። ገዳማትን ማፍረስና መነኮሳትን ማሳደድና መግደል የወያኔ መለዮው ሆኗል። ወያኔ ንፁኃን ዜጎችን ከማሰቃየት፣ ከማሰርና ከመግደል የታቀበበት ወቅት ከቶውንም የለም፤ አልታየምም። ድብደባው፣ ማሰሩና ግድያው እየተፈጸመ ያለው በሁሉም የሃገሪቷ ክፍሎች በሚኖሩ ንፁሃን ዜጐች ሲሆን በግፍና በገፍ ወደ እሥር ቤት የማጎር እርምጃዎች ያልርኅራሄ ተፈጽመዋል፤ እየተፈጸሙም ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ በኢትዮጵያዊ ትዕግሥትና አርቆ አስተዋይነት በፋሽስቱ ወያኔ ወገን ሲደበደብ፣ ሲባረር፣ ሲገደል፣ ሃብት ንብረቱ ሲዘረፍ፣ ዳር ድንበሩ ሲወሰድ፣ በቋንቋ ልዩነት ሲመደብ፣ የተማረ ወገን ሲገደልና ሲሰደድ፣ አገር ለውጭ ባለሃብት ስትሽጥ፣ ይህ ሁሉ ሲሆን እስከ አሁን በደልን ተሸክመህ በዝምታ ታግሰሃል። ዛሬ በፋሽስቱ ወያኔ ኢትዮጵያ ተደፍራለች፣ ሕዝቧ ተዋርዷል፣ የታሪክ ክብሯ ተንቋል። ለብዙ ሺህ አመታት የኛ ቀደምት ትውልዶች አጥንትና ደማቸውን በማፍስስ ታፍራና ተፈርታ የኖረች አገር ዛሬ በዚህ ወቅት የትውልድ መካን ሆና ጥቃቱና ጥፋቱ እጅግ ተነባብሯል። ኢትዮጵያዊ ወገኔ ሆይ! ፍርሃት ከአደጋ የመከላከያ ባህሪ እንጂ እየሸሹ ለመጥፋትና ለመሞት አይደለም። ይህ ጭቆናና ጥቃት ሊያበሳጭ፣ ሊያናድድህና ሊያስቆጣህ ይገባል። ሰው ነህና ለመብትና ለነፃነት መታግልና ለመጭውም ትውልድ ለልጆችህ አገር ማቆየት ይኖርብሃል። የኛ ቀደምት አባቶችና እናቶች እኛ ሞተን አገር ትኑር ብለው ለኢትዮጵያ ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ታሪክ ምስክርነትዋን መዝግባለች። ዛሬም የኢትዮጵያዊያን ወኔና ጀብዱ፣ አትንኩኝ ባይነት ይደገም። ወያኔ ኢትዮጵያዊነት የሌለው አረመኔ ፋሽስት ነውና፤ መወገድ አለበት። ስለዚህ ለትዕግሥት ገደብ እንስጥ፣ አንዋረድ ትውልድ እንጠብቅ፣ አገርና ሕዝብ እናድን።


ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!

  http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13119