-ሁለት ጦማሪያን መደብደባቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ
‹‹ግብረ አበሮቻቸውን መያዝና የምስክሮች ቃል መቀበል ይቀረናል›› የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን
‹‹ችሎቱ ጠባብ ስለሆነ እንጂ ጉዳዩ የሚታየው በግልጽ ችሎት ነው›› ፍርድ ቤት
በህቡዕ ተደራጅተው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ካሉ አሸባሪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ኅብረተሰቡንና መንግሥትን ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ጠበቆች፣
ተጠርጣሪዎቹን ማግኘትና ማነጋገር ካልቻሉ፣ ሁኔታውን ለፍርድ ቤት አስረድተው ጥብቅና መቆማቸውን እንደሚያቋርጡ ተናገሩ፡፡
ጠበቆቹ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ከሚያዝያ 17 እና 18 ቀን
2006 ዓ.ም. ጀምሮ ፍርድ ቤት እስከቀረቡበት እስከ ሚያዝያ 29 ቀን
2006 ዓ.ም. ድረስ፣ ከቤተሰብም ሆነ ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር አለመገናኘታቸውን ገልጸው ለፍርድ ቤት ጠበቆቹ በማመልከታቸው፣ በሦስት የምርመራ መዝገብ ተከፋፍለው ሚያዝያ 29 እና 30 ቀን
2006 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ሲቀርቡ ፍርድ ቤት በቤተሰብና በሕግ አማካሪዎቻቸው እንዲጎበኙ አዞ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተከትለው ግንቦት 1 ቀን
2006 ዓ.ም. ጠበቆቹ አቶ አመሐ መኮንንና ዶ/ር ያሬድ ለገሰ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ማልደው የተገኙ ቢሆንም፣ ‹‹ስብሰባ ላይ ስለሆንን በዚህ ሳምንት አናገናኝም፤›› በመባላቸው ሳያገኟቸው እንደተመለሱ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማይከበርና ተጠርጣሪዎቹን ካላገኟቸው፣ ለመጨረሻ ጊዜ ግንቦት 6 ቀን
2006 ዓ.ም. ሄደው፣ የማያገናኟቸው ከሆነ፣ ሕገወጥ ሥራን መተባበር ስለሚሆን ለፍርድ ቤቱ አስታውቀው ጥብቅናቸውን እንደሚያቆሙ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ሚያዝያ 29 እና 30 ቀን
2006 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ሚያዝያ 29 ቀን የቀረቡት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሣዬ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጦማሪያን ናትናኤል ፈለቀ፣ ጦማሪያን አጥናፉ ብርሃኔ፣ ጦማሪያንና መምህር ዘለዓለም ክብረት ናቸው፡፡
ስድስቱም ተጠርጣሪዎች በአራዳ ምድብ ችሎት ቅጥር ግቢ ተሰብስበው ሲጠብቋቸው በነበሩት ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች አጠገብ ሲያልፉ፣ ከኤዶም በስተቀር አምስቱም እጃቸው በካቴና ታስረውና ወደ መሬት እያዩ ስለነበሩ አንዳቸውም ማንንም ቀና ብለው አላዩም፡፡ ጋዜጠኞችና ከተለያዩ ኤምባሲዎች የተገኙ ዲፕሎማቶች ወደ ችሎት ለመግባት ሲጠጉ፣ አንድ የፍርድ ቤት ተላላኪ ‹‹ችሎቱ ጉዳዩን የሚያየው በዝግ ነው›› ሲል አጃቢ ፖሊሶችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በመከልከላቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ የተናገሩትን ወይም መርማሪው ቡድን ያቀረበባቸውን የጥርጣሬ ክስ መስማት አልተቻለም፡፡
ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ቡድኑንና የተጠርጣሪዎቹን ጠበቆች ክርክር ከጨረሰ በኋላ ፖሊስ የጠየቀባቸውን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዶ ሲጨርስ፣ በዕለቱ በችሎት ተገኝተው የነበሩት ጠበቃ አመሐ መኮንን ከችሎቱ ሲወጡ በቤተሰቦች፣ በጋዜጠኞች፣ በዲፕሎማቶችና በሌሎች ታዳሚዎች ተከበቡ፡፡ ‹‹ምን ተባሉ?›› ለሚለው የሁሉም ጥያቄ ማብራራት የጀመሩት ጠበቃ አመሐ፣ ‹‹እኛ ተጠርጣሪዎቹን አግኝተን ማነጋገር ባለመቻላችን፣ መከራከር አልቻልንም፡፡ አንዳንድ መከራከሪያ ሐሳብም የወሰድነው በደንብ ተደራጅቶና ተዘጋጅቶ የመጣው መርማሪ ፖሊስ ካቀረበው የምርመራ ውጤት ላይ ተነስተን ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ መርማሪ ፖሊሱ ያቀረበውን የምርመራ ውጤትና የሚቀረውን አብራርተዋል፡፡
መርማሪ ፖሊሱ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ስላገኘው የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤቱ ያስረዳውን ነጥብ የገለጹት አቶ አመሐ፣ የ2007
አገራዊ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ኅብረተሰቡን አነሳስተው በመንግሥት ላይ አመፅ ለመቀስቀስ፣ በህቡዕ ተደራጅተው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ካሉ አሸባሪዎች ጋር ግንኙነት መፍጠራቸውን፣ ሥልጠና መውሰዳቸውንና ሌሎችን ለማሠልጠን ሲንቀሳቀሱ እንደተደረሰባቸው ማስረዳቱን ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ሌሎችን ለማሠልጠንና ለመምራት ገንዘብ በመቀበል የመገናኛ መሣሪያዎችን፣ ላፕቶፖች፣ ኮምፒዩተሮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን መግዛታቸውንም መርማሪው ማስረዳቱን አቶ አመሐ አክለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በኬንያና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ሄደው ሥልጠና መውሰዳቸውንና እነሱም ሌሎችን ለማሠልጠን እየተንቀሳቀሱ እንደነበርም መርማሪው ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን አቶ አመሐ ገልጸዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስ ያልተያዙ ግብረ አብሮቻቸውን መያዝ እንደሚቀረው፣ የምስክሮች ቃል አለመቀበሉን፣ የያዛቸውን የተለያዩ ሰነዶች ለይቶ ማስተርጎምና
የቴክኒክ ምርመራም እንደሚቀረው በመግለጽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን መጠየቁን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ የተገለጸላቸው ነገር ባይኖርም ከመርማሪ ፖሊሱ ሐሳብ በመነሳት፣ ጠበቃ አመሐና ጠበቃ ዶ/ር ያሬድ ባቀረቡት መቃወሚያ፣ የተጠርጣሪዎቹን ግብረ አበሮች ለመያዝ እነሱን ማሰር እንደማያስፈልግ፣ ምክንያቱም የሚያዙ ግብረ አበሮች ስላሉ በዋስ ቢለቀቁ ያስጠፉብናል ከተባለ እስካሁን ሊኖሩ እንደማይችሉ፣ ፖሊስ ሰነዶቹንም ስለወሰደና
በግሉ ሊያስተረጉም ስለሚችል ተጠርጣሪዎቹን ማሰር አስፈላጊ አለመሆኑን፣ ተጨማሪ የሚፈልገው ማስረጃ ካለም መጀመሪያውኑ ምርመራውን አጠናቆ መያዝ ይገባው እንደነበር በማስረዳት፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲለቀቁ ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ የሚታለፍ ከሆነ ላለፉት 12 ቀናት የሕግ አማካሪዎችም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው እንዳይጠይቋቸው መከልከል ሕገ መንግሥቱን መጣስ በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎቹ መጎብኘት እንዲችሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን አክለዋል፡፡
ሚያዝያ 30 ቀን
2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡት ጦማሪያን በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላና ማሕሌት ፋንታሁን ናቸው፡፡ መርማሪ ፖሊስ በሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረበው የምርመራ ውጤትና የሚቀረው የምርመራ ሒደት አንድ ዓይነት መሆኑን የገለጹት ጠበቃ አመሐ፣ ለየት ያለ ነገር የቀረበው ጦማሪያን ፍቃዱና አቤል በምርመራ ወቅት መገረፋቸውን ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸው ነው፡፡ መርማሪዎች እንደገረፏቸው ያስረዱ ሲሆን፣ መርማሪ ፖሊስ ግን ተጠርጣሪዎቹ ያሉት ነገር ሊሆን እንደማይችል ተከራክሮ ሐሰት መሆኑን ለፍርድ ቤት በማስረዳት ድርጊቱን ማስተባበሉን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ፣ በሕግ ባለሙያዎችና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብት እንዳላቸው በመግለጽ ማስጠንቀቁንና ትዕዛዝ መስጠቱን አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሌላው ያነሳው የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ በግልጽ ችሎት እየታየ መሆኑን ሲሆን፣ የተከለከለው በዝግ ለማየት ሳይሆን ቦታው ጠባብ በመሆኑ እንደሆነ አስረድቶ፣ ሚያዝያ 30 የቀረቡት ተጠርጣሪዎች የቅርብ ቤተሰባቸውን ተናግረው እንዲያስገቡ ተጠይቀው፣ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ጠበቃ አመሐ ገልጸዋል፡፡ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች ግን አልገቡም፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ችሎት ሲገቡ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ የነበሩ ታዳሚዎች ጩኸት በማሰማታቸው በሚቀጥለው ቀጠሮ ይህ የሚደገም ከሆነ፣ ፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ እንደሚከለከል ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ፖሊስ የጠየቀው ጊዜ ተፈቅዶለት ለግንቦት 9 ቀን
2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/5973-%E1%8C%A0%E1%89%A0%E1%89%86%E1%89%BD-%E1%8B%A8%E1%89%B3%E1%88%B0%E1%88%A9-%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A0%E1%8A%9E%E1%89%BD%E1%8A%95%E1%8A%93-%E1%8C%A6%E1%88%9B%E1%88%AA%E1%8B%AB%E1%8A%95%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%88%9B%E1%8B%AB%E1%8C%88%E1%8A%99-%E1%8A%A8%E1%88%86%E1%8A%90-%E1%8C%A5%E1%89%A5%E1%89%85%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%89%86%E1%88%9D%E1%88%9D-%E1%8A%A0%E1%88%89
No comments:
Post a Comment