Monday, March 30, 2015

የእነብርሃኑ፣ ፍቅረማርምና እየሩሳሌም የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ ተጨማሪ የ28 ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል


በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚገኙት ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ፍርድ ችሎት ቀርበው ተጨማሪ የ28 ቀናት ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡

ሶስቱም ወጣት ተጠርጣሪዎች ችሎት ከመግባታቸው በፊት ሳቅ እና ፈገግ እያሉ በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ የነበሩትን ቤተሰቦቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ሰላም ሲሉ ተስተውሏል፡፡ ብርሃኑና ፍቅረማሪያም የአንገት ልብስ (ስካርፍ) ያደረጉ ሲሆን እየሩሳሌም ጥቁር እስከርፍ አድርጋ ነበር፡፡

በመጀመሪያ ወደ ችሎት ተጠርተው የገቡት ፍቅረማርያም እና እየሩሳሌም ሲሆኑ ከጠበቃ ዳዊት ነጋሽ በስተቀር ማንም መግባት አልቻለም ነበር፡፡ [እኔና ጥቂት ሰዎች ግን ከችሎቱ በር ትንሽ ርቀት ላይ ቆመን የፍርድ ቤት ሂደቱን ለማየት ጥረት አድርገገን በመጠኑ ተሳክቶልናል]

ጠበቃ ዳዊት ከችሎት በኋላ እንደነገሩን ከሆነ፣ መርማሪ ፖሊስ ምርመራ አለመጨረሳቸውን፣ ተጠርጣሪዎች ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውና ይሄንንም በማጣራት ላይ እንደሚገኙ፣ የቴክኒክ መረጃዎች (የኮምፒውተር፣ የኢንተርኔት፣ የስልክና የፌስ ቡክ) እንደሚቀራቸው፣ ለሽብር ተግባር ብር ሲቀበሉ እና ሲልኩ የነበረውን የባንክ ቤት መረጃ እየተከታተሉ መሆናቸውና ቢለቀቁ መረጃዎችን ሊያጠፉ ስለሚችሉ የተጨማሪ የ28 ቀናት ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡


ጠበቃ ዳዊትም መርማሪ ፖሊስ ይቀሩናል ሲል ለፍርድ ቤቱ ያቀረባቸው መረጃዎች ከተጠርጣሪዎቹ ቁጥጥር ውጪ ሆነው በቃላሉ የሚገኙ ስለሆነ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና እንዲለቀቁ ፍርድ ቤትን ጠይቆ ነበር፡፡ ጠበቃው ምክንያቱን ሲያብራራም፣ የኮምፒውተር፣ የኢንተርኔት፣ የስልክና የፌስ ቡክ መረጃዎችን ፖሊስ እስከአሁን ሊያገናቸው ይችል እንደነበረ፣ ከባንክ የሚገኝ መረጃም በአጭር ቀናት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን፣ ግብረ አበሮች አሉ ከተባለም ግብረአበሮች የሚያዙት ተጠርጣሪዎችን በመያዝ አለመሆኑና ተጠርጣሪዎቹ ቢለቀቁም የተለየ ነገር እንደማይመጣ ተናግሯል፡፡

መርማሪ ፖሊስም ‹‹የጦር መሳሪያ ተይዟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በህቡዕ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ከእስር ቢለቀቁ ወደኤርትራ ሰው ወደመመልመል ስራቸው ይመለሳሉ›› የሚል ተቃውሞ በማሰማት የጦር መሳሪያ የታጠቀ የሰው ምስል ለችሎት ማሳየቱንና መሳሪያ የያዘው ግለሰብ ማን እንደሆነ በግልጽ እንደማይታይ ለዚህ ዜና ዘጋቢ ገልጾለታል፡፡

ፍቅረማርያም እና እየሩሳሌምም ቃላቸውን፣ የፌስ ቡክና ሌሎች መረጃዎችን በምርመራ ወቅት ለፖሊስ መስጠታቸውን፣ መሳሪያ ከተባለው ነገር ጋር የሚያገናኛቸው ነገር አለመኖሩንና ይሄም በግልጽ እንደሚታወቅ በመግለጽ ‹‹መረጃዎች ካሉ ክስ ይመስረትብን ካልሆነ ከእስር እንለቀቅ›› የሚል ሀሳባቸውን ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ከተጠየቀባቸው በኋላ ብርሃኑ ተክለያሬድ ከጠበቃ ዳዊት ጋር ወደ ችሎት ገባ፡፡ መርማሪ ፖሊሱ፣ ብርሃኑ ላይም ‹‹የጦር መሳሪያ ተገኝቷል›› የሚለውን ቃል ሳይደግም በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ያረቀበውን ሀሳብ ለችሎቱ ማስረዳቱን ጠበቃ ዳዊት ይናገራሉ፡፡ ጠበቃውም በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ያቀበረቡትን የተቃውሞ ሀሳብ ለብርሃኑም አቅርበዋል፡፡

ብርሃኑም በበኩሉ ‹‹ቃላችንን ለፖሊስና ለፍርድ ቤቱ ሰጥተናል፡፡ የቀረ ነገር የለም፡፡ የእስር ሁኔታችን ከህግ አግባብ ውጪ ነው፡፡ ‹‹ጨለማ ክፍል›› በሚባለው እስር ቤት መብራት 24 ሰዓት ይበራል፡፡፡ እኔ የዓይን ችግር አለብኝ፡፡ በቀን ለ15 ደቂቃ ብቻ ነው ከታሰርኩበት ክፍል ወደ ደጅ የምወጣው፡፡ ቤተሰብና የህግ ጠበቃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከጠበቃ ጋር ሳልማከር ነው ቃሌን ለፖሊስ የሰጠሁት፡፡ የመብት ጥሰት አለ፡፡ ቤተሰቦቻችንን፣ ጠበቃና ጠያቂዎቻችንን መግኘት ይፈቀድልን፡፡ ሌሎች ከእኔ ጋር የታሰሩ እስረኞች ግን ቤተሰቦቻቸው ሲመጡ ለጥየቃ ይወጣሉ፡፡ በዚህ ላይ ትዕዛዝ ይሰጥበት፡፡ …መረጃዎች ካሉ ክስ ይመስረትብን ካልሆነ ከእስር እንለቀቅ›› ብሏል፡፡

[የዚህ ዜና ዘጋቢም ብርሃኑ ድምጹን ከፍ አድርጎ አቤቱታውን ለችሎቱ ሲያቀርብ በከፊል ለማየትና ለመስማት ችሏል]
የችሎቱ ሴት ዳኛም የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመው፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ፣ ከጠበቃ፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸውና ለወዳጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ የሚል ትዕዛዝ በቃል ሰጥተው በብርሃኑም ላይ የ28 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሠጥተዋል፡፡
http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/17698

No comments:

Post a Comment