Monday, March 16, 2015

የኦሞ ስኳር ፕሮጀክቶች ግጭቶችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አለማቀፉ ቡድን አስጠነቀቀ

የተለያዩ የአለም አገራትን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክንና ለጋሽ ተቋማትን ጨምሮ 27 አባላትን የያዘው ዲቨሎፕመንት አሲስታንስ ግሩፕ የተባለ አለማቀፍ ቡድን፤ በደቡብ ኦሞ በመከናወን ላይ የሚገኙ ሰፋፊ የመንግስት የስኳር ፕሮጀክቶች በአካባቢው ግጭቶችን ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ ባለፈው ረቡዕ ማስጠንቀቁን ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር / ሽፈራው ተክለ ማርያም በበኩላቸው፤ በደቡብ ኦሞ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ግጭትን ለመከላከል ያለሙ እንደሆኑና በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦችም የልማት ዕቅዶቹን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማስቻል በስፋት መሰራቱን ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡ 
የስኳር ኮርፖሬሽን ከቻይና ልማት ባንክ ባገኘው ብድር በደቡብ ኦሞ አካባቢ ስድስት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባትና 150 ሺህ ሄክታር ላይ የሸንኮራ አገዳ ልማት ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ የሸንኮራ አገዳ ልማቱ የአካባቢውን ነባር ነዋሪዎች አኗኗር ሊያቃውስ ይችላል ተብሎ እንደሚሰጋ ቡድኑ ማስታወቁን ገልጧል፡፡
በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች በስኳር ፕሮጀክቶቹ ውስጥ ለመስራት ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አካባቢው መግባታቸውም፣ በአካባቢው የጎሳ ግጭቶችን ሊቀሰቅስ ይችላል ያለው ቡድኑ፤ ፕሮጀክቶቹ  በአካባቢው የሚከናወኑ የንብ ማነብ፣ የከብት እርባታ፣ የእርሻና የመሳሰሉ ስራዎች ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የስኳር ፕሮጀክቶቹ ተግባራዊ በሚደረጉበት የደቡብ ኦሞ አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደር ጎሳዎች፣ በፕሮጀክቶቹ ሳቢያ የግጦሽ መሬት እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፤ ፕሮጀክቶቹ በጥድፊያ መከናወናቸውም በአካባቢው ግጭቶች የመከሰት ዕድላቸውን ከፍ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ጉዳዩ በአግባቡ ካልተያዘም በአካባቢው አለመረጋጋት ሊከሰት እንደሚችል ቡድኑ ስጋቱን መግለጹንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
መንግስት በአካባቢው የሚያከናውናቸውን የስኳር ፕሮጀክቶች በተመለከተ ግልጽነትን ማሳደግ፣ የማህበረሰቦችን ሃሳብ ማስተናገድና የፕሮጀክቶቹ ትግበራ ላይ የሚታየውን ጥድፊያ በመቀነስ የልማት ሽግግሩ ግጭትን በማያስከትል መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ይገባዋል ብሏል ቡድኑ፡፡
የቡድኑ አመራሮች ባለፈው ነሃሴ ወር ያደረጉትን ጉብኝት ጨምሮ ባለፉት ሶስት አመታት በተደጋጋሚ ወደ ደቡብ ኦሞ በማቅናት፣ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን በመከናወን ላይ የሚገኘውን የመንግስት የመልሶ ማስፈር ፕሮግራም ተጽዕኖ በተመለከተ ግምገማ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=15819:%E1%8B%A8%E1%8A%A6%E1%88%9E-%E1%88%B5%E1%8A%B3%E1%88%AD-%E1%8D%95%E1%88%AE%E1%8C%80%E1%8A%AD%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8C%8D%E1%8C%AD%E1%89%B6%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%88%8A%E1%8B%AB%E1%88%B5%E1%8A%A8%E1%89%B5%E1%88%89-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%88%9A%E1%89%BD%E1%88%89-%E1%8A%A0%E1%88%88%E1%88%9B%E1%89%80%E1%8D%89-%E1%89%A1%E1%8B%B5%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%8C%A0%E1%8A%90%E1%89%80%E1%89%80&Itemid=101

No comments:

Post a Comment