Monday, November 30, 2015

በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የሕዝብ ተቃውሞ በአደባባይ ቀጥሏል * ፌደራል ፖሊስ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ 3 ተማሪዎችን ገደለ

የአዲስ አበባ አዲሱን ማስተር ፕላን በመቃወም በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ አድማሱን እያሰፋ መሆኑ ተሰማ:: የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳሉት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተጀመረውና ጎማ ጭምር በአደባባይ በማቃጠል የተስፋፋው የሕዝብ ቁጣ ትናንት እና ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ቀጥሏል::

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሰላማዊ መንገድ ቁጣቸውን ለመግለጽ የተሰበሰቡ ተማሪዎች ከፌደራል ፖሊስ በቆመጥና በጠመንጃ ሰደፍ የተደበደቡ መሆኑን በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ለዘ-ሐበሻ ገልጸው በተፈጠረው ብጥብጥ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የ3 ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል::

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ተማሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ምንም ዓይነት ንብረት ሳያወድሙ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ፖሊስ እርምጃ ሊወስድ ችሏል:: አሁንም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ አለመረጋጋት እንዳለ ዘገባዎች ጠቁመዋል::
የኦሮሞ ተማሪዎች ቁጣ በአምቦ እንዲሁም በነቀምቴ ከተሞችም ቀጥሎ ተማሪዎቹ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ውለዋል:: የአይን ዕማኞች ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት በአምቦ ፌደራል ፖሊስ መንገድ በመዝጋት የተማሪዎቹን ቁጣ ለማብረድ ጥረት ቢያደርግም ከከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ መለስተኛ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎቹ ተቃውሞ ገንፍሎ ወጥቷል::

አዲሱን የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃውም በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚደረገው ቁጣ አሁንም እየተስፋፋ ሲሆን ሕዝቡ ይህ ማስተር ፕላን እንዳይተገበር የሕይወት መስ ዋዕትነት ሳይቀር እንደሚከፍል በመዛት ላይ ይገኛል::


በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ማስፋፋት ስም በሰበታ ከተማ ለመለስ ዜናዊ መንደር ግንባታ በከተማው ለባለሃብት የተሰጠ የመሬት ፈቃድን የሚያሳይ ምስጢራዊ ደብዳቤ ዘ-ሐበሻ ከቀናት በፊት ለሕዝብ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል::

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48607

Saturday, November 28, 2015

የሕወሓት አስተዳደር አዲስ አበባን “እናሰፋለን” በሚል ሰበብ የሚሰራው ሸፍጥ ተጋለጠ (ምስጢራዊውን ደብዳቤው ይዘናል)

(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሕዝቡ ሕወሓት የሚመራው መንግስት ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም አደባባይ በመውጣቱ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት እና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት እንደነበር ይታወሳል:: እነዚህ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ የሃገራችን ፍሬዎች ምክንያታቸው በአዲስ አበባን የማስፋፋት ምክንያት ምስኪን ገበሬዎችን በማፈናቀል መሬታቸውን ለባለሃብቶች ለመሸጥ ነው የሚል ነው:: ሕወሓት የሚመራው መንግስት “በልማት” ስም የተለያዩ የሃገራችንን መሬቶች ገበሬዎቹን በማሰናበት ለውጭ ባለሃብቶች በመሸጥ ይታወቃልና ወትሮም እነዚሁ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሕዝቦች አደባባይ ወጥተው ይህን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎችን ያፈናቅላል ያሉትን አዲሱን ማስተር ፕላን ቢቃወሙ አይገርምም::

ዛሬ የተለቀቀው ምስጢራዊ ደብዳቤ በአዲስ አበባን የማስፋፋት ስም በሕወሓት መንግስት የሚደረገውን ጥልቅ ሴራ ያጋለጠ ነው:: ምስጢራዊው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ‘ሆዜ ሂማንተሪያን ፋውንዴሽን” የተሰኘ ድርጅት የመለስ ዜናዊን መንደር በሰበታ አዋስ ወረዳ ያቀረበውን ጥያቄ ወረዳው መቀበሉን ያረጋገጠበት ነው:: ደብዳቤው እንደሚለው ለመለስ ዜናዊ መንደር ግንባታ ለሆዜ ፋውንዴሽን አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሄክታር ወረዳው እንዲያዘጋጅ መጠየቁን እና ይህንንም ማዘጋጀቱን ነው::

እንግዲህ አዲስ አበባን እናስፋፋለን የሚሉት ምስኪን ገበሬዎቹን አፈናቅሎ ምን ለመፍጠር እንደሆነ ከዚህ በታች ከቀረበው ደብዳቤ ይረዱና አስተያይትዎን ያስቀምጡ::


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48562


Tuesday, November 24, 2015

“በአዛዙ የአፈና መዋቅር የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የእኩልነት ትግል አይቀለበስም” – ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ


ህወሓት/ኢህአዴግ በህገ መንግስቱና በሌሎች ራሱ ባወጣቸው ህጎች በርካታ መብቶችን ለይስሙላ ቢደነግግብ ቅሉ፤ በተግባር ግን እነዚህን መብቶች ሆነ ብሎ ባደራጀው የአፈና መዋቅሩ እየደፈቃቸው ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን አገዛዙ የመደራጀት መብትን በወረቀት ቢያሰፍርም ‹‹እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን፤ እግር ሲያወጡ ግን እንቆርጣለን›› በሚል መርህ ፓርቲዎችን በዚሁ የአፈና መዋቅሩ በገሃድ እያፈረሰ ቀጥሏል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ፈቅጃለሁ ቢልም ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በማሳደድና ሚዲያዎችን በመዝጋት አማራጭ ሀሳብ እንዳይራመድ አድርጓል፡፡ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ወረቀት ላይ ቢደነግግም በአስተዳደራዊ መዋቅሩ መሰረት ክርችም አድርጎ ዘግቶታል፡፡ የዜጎችን የመዘዋወር መብት ቢደነግግም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፓስፖርት በመንጠቅ ጉዟቸውን በማተጓጎል ላይ ይገኛል፡፡ የመንግስት አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት አለበት ተብሎ ተደንግጓል፤ ነገር ግን በየ መስርያ ቤቱ ያለ እጅ-መንሻ ዜጎች አገልግሎት ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህ ሁሉ አፈና ሆነ ተብሎ ታስቦበት፣ የአገዛዙን ስልጣን ለማራዘም የሚደረግ መዋቅራዊ ጫና መሆኑን ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡

ዛሬ በሀገራችን ከፍተኛ ርሃብ፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስራ አጥነት፤ ስደት እና ሌሎችም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶች በሰፊው ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ወቅታዊ ጉዳዮች ከህዝብ ጋር ተወያይቶ አቋም ለመውሰድና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመሰንዘር ህዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የእውቅና ደብዳቤ ለማስገባት በተደጋጋሚ ጥረት ያደረግን ቢሆንም የአፈና መዋቅሩ የእውቅና ደብዳቤውን መቀበል ባለ መፈለጉ ለ5 ጊዜ ተጉላልተን በ6ኛው በሪኮመንዴ(በፖስታ) ለመላክ ተገደናል፡፡


የእውቅና ደብዳቤው በሪኮመንዴ የደረሰው አስተዳደሩ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ላይ ሆኖ ‹‹ህዳር 18/2008 ዓ.ም አልፏል›› በሚል ለተጨማሪ ጊዜ ደብዳቤውን ሳያስተናግድ ቀርቷል፡፡ ህዳር 18 ያላለፈ መሆኑን ካስረዳን በኋላ ለሶስት ቀናት በተደጋጋሚ ብንመላለስም ‹‹ከደህንነትና ፖሊስ ጋር ካልተመካከርኩ እውቅና አልሰጥም›› ሲል እምቢታውን ገልጾአል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአባላትና ደጋፊዎቻችን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ልናደርገው የነበረው ውይይት ሊደናቀፍ ችሏል፡፡


ከዓለም የነጻነት የትግል ታሪክ እንደምንገነዘበው በአገዛዝ አፈና የተገታ የህዝብ ጥያቄ ኖሮ አያውቅም፡፡ አፈናው የነጻነትን ጊዜ ቢያዘገይ እንጅ ፈጽሞ ሊያስቀርም አይችልም፡፡ ስለሆነም ጭቆናው ወደ ነፃነት የሚያስኬደውን ጉዞ እልህ አስጨራሽ ከማድረግ በቀር ዘላቂነት ኖሯቸው የነጻነት ጥያቄውን ፈጽሞ ማዳፈን እንደማይችሉ አገዛዙ ሊረዳ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ለማይቀረው የነፃነት ትግል ቆርጦ እንዲነሳና ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48484

Monday, November 16, 2015

መንግስት ረሃቡን ለመደበቅ ከፍተኛ መመሪያ አስተላለፈ ጋዜጠኞችና የረድኤት ድርጅቶች ረሃቡ ወደ ተከሰተበት ቦታ እንዳይሄዱ ተከለከለ

ሕወሓት የሚመራው የኢትዮጵያ ገዢ በኢትዮጵያ የተከሰተውን እና 15 ሚሊዮን ሕዝብን ለረሃብ ያጋለጠውን አደጋ ለመሸፋፈን ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋዳ ሥራዎችን ከመስራት በተጨማሪ መረጃዎች እንዳይወጡ እስከማፈን ደረጃ መድረሱን ምንጮች ለዘ-ሐበሻ አስታውቀዋል::

የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር መስሪያ ቤት; የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስተርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በአንድ ላይ ተቀናጅተው እየሰሩት የሚገኘው የመረጃዎችን የማፈን ሥራ ታች ድረስ ወርዶ እስከ ፓርቲ አባላትና “ደጋፊ” የተባሉ ሰዎች ጭምር እንዲሰራበት እየተደረገ ነው:: “ረሃቡን አስታከው ለውጭ መንግስታት ሊያሳጡን የሚሞክሩትን መታገል አለብን” በሚል እነዚህ ሶስት መስሪያ ቤቶች ባወጡት መመሪያ መሠረት የውጭ ጋዜጠኞችም ሆነ የረድኤት ድርጅቶች ረሃቡ ወዳለበት ቦታ ሄደው ፎቶ እንዳያነሱ; ቭዲዮ እንዳይቀርጹ; ማንኛውንም ቃለምልልስ እንዳያደረጉ ተከልክሏል:: በተለይ ቢቢሲ በቅርቡ በኢትዮጵያ በአንድ ትንሽ ክልል ስፍራ ብቻ በቀን 2 ህፃናት በረሃቡ እየሞቱ እንደሆነ መዘገቡን ተከትሎ አለም አቀፍ ሚዲያዎች እና የአፍቃሬ ሕወሓት መንግስት ደጋፊ የሆኑ ሃገራት ሳይቀር ከዚህ ቀደም “ልማታዊ መንግስት” እያሉ ሲያሞካሹ የነበረውን አፋቸውን በመጠራረግ ረሃቡን እና መንግስት የሚከተለውን ፖሊሲ እንደገና እየመረመሩ እንደሚገኙ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ይናገራሉ::

እንደ ዘ-ሐበሻ ምንጮች ዘገባ በቅርቡ በቢቢሲ የቀረበችውን እናት የአማራ ክልል ጋዜጠኞች አስገድደው ቃለምልልስ ያደረጓት ሲሆን በቅርቡም በመንግስት ሚዲያዎች ላይ “አልራበኝም” ዓይነት ንግግር በማስደረግ የቢቢሲን ዘገባ ለማስተባበል ሥራ እየተሰራ ይገኛል::

ከሥስቱ መስሪያ ቤቶች በተላለፈው መመሪያ መሠረት የመንግስት ሃላፊዎች ከላይ እስከታች በየሶሻል ሚዲያው በመውጣት ችግሩን መንግስት ተቆጣጥሮታል እያሉ መጻፍ እና መናገር አለባቸው:: “ተቃዋሚዎች የመንግስታችንን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት ሆን ብለው የሚያደርጉት ሤራ ነው” እያሉም በውጭ ያሉ ኤምባሲዎችና ተላላኪዎች እንዲያነገሩ ትዕዛዝ ከመተላለፉም በላይ መንግስትን ይደግፋሉ ለተባሉ የውጭ ጋዜጠኞች ወደ ሃገር ቤት እንዲገቡና መልካሙን ነገር ብቻ እንዲዘግቡ ኢምባሲዎች መሥራት እንዳለባቸውም የወጣው መመሪያ ሲያመለክት ስለመንግስት መጥፎ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ የተባሉ ጋዜጠኞች ግን ረሃቡ ወዳለበት ቦታ እንዳይሄዱ/ ምስል መቅረጽና ቃለምልልስ ማድረግ እንዳይችሉ የኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ፈቃድ እንዳይሰጥ ት ዕዛዝ ወርዷል::


በስልጣን ላይ ያለው መንግስት 15 ሚሊዮን ሕዝብ በመራቡ የተነሳ በወዳጅ ሃገሮቹ ሳይቀር በመጥፎ አይን እየታየመምጣቱ በስርዓቱ ውስጥ “ገጽታችን ተበላሸ” በሚል ራሱን የቻለ ሽብር ፈጥሯል::

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48271

Thursday, November 12, 2015

ፕሮፓጋንዳው ሰብዓዊነት ይኑረው !!! ሰው እየሞተ ነው !! ቁጥሩን ቤቱ ይቁጠረው !!!

በሀገራችን ያለው ድርቅ ክብደት ከ1977ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ የመንግሰት ሹም ከሸገር ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ምልልስ አረጋግጠዋል፡፡ ልዩነቱ ግን አሁን መንግሰት ይህን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አለን የሚልው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አቅም ግን መሬት ላይ ወርዶ ስናየ ወኔ ብቻ ይመስላል፡፡ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ የፈረንጆቹን ደጅ እንዳይጠኑ የሚያደርጋቸው አይደለም፡፡

“ደርግ” በ1977 የነበረፈውን ድርቅ ለዓለም ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን የዚያን ጊዜ በነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት መነሻ በሁለቱ ጎራ በሚደረገው ፍልሚያ ግዳይ የሚጣልብት ወቅት ነበር፡፡ ደርግ ለዓለም ህብረተሰብ ጥሪ ባቀረበበት ወቅት የሶሻሊስቱ ተከታይ በመሆኑ ይህ ጎራ ይህን ድጋፍ የሚያደርግበት አቅም የሌለው ሲሆን ይህን ለማድረግ አቅም ያላቸው ምዕራባዊያን ግን ውጤቱን በደንብ ሳናየው ድጋፍ ላለመስጠት መቁረጣቸው ለችግሩ ክብደት አንዱ እንደ ነበር ለመረዳት ሊቅ መሆን አያስፈልግም፡፡ 

በተጨማሪ ለ1997 ድርቅ ተገቢው ምላሽ በምዕራባዊያን እንዳይሰጥ በወቅቱ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት በተለይ ህወሃት እና ሻቢያ የተጫወቱት ሚና ቀላል የማይባል ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ሆነን ስናየው ሰብዓዊነትን ለፖለቲካ ጥቅም እንዳዋሉት ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡


አሁን ባለው ሁኔታ የኢህአዴግ መንግሰት ከምዕራባዊያኑ ጋር ያለው ቅርበት ከደርግ እንደሚሻል ስለሚታመን በተጨማሪ ህውሃትና ሻቢያ በዛን ጊዜ የሰሩትን ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመስራት የሚችል ታጣቂ ሀይል ባለመኖሩ ችግሩን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሰት አቅሙ የከብቶቹን ህይወት ለመታደግ ለምን አልተጠቀመበትም? ካልቻለ ደግሞ ምዕራባዊያኑ ድጋፍ ለማድረግ ከፈለጉ አሁንስ ቢሆን ከብቶቹ ሳይሞቱ እንዲደርሱልን ለምን አልተደረገም? የሚለው ጥያቄ ለማንሳት አርብቶ አድር መሆን አይጠበቅብንም፡፡

ሁሉም የሚረዳው አንድ ሀገር በድርቅ መቼም ቢሆን ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ይህ በዓለም ላይ ተደጋጋሚ ክስተት እንደሆነ ማንም ያውቃል፡፡ ድርቅ ሲኖር ግን ይህን ድርቅ የሌላ ሶሰተኛ ሀገር ድጋፍ ሳይጠየቅ ለመፍታት አቅም መፍጠር መቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባላት ስነ ምህዳር ከዚህ የተሻለ ማድረግ እና ለሌሎች መትረፍ ይገባት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አሰማት ሳይሆን ሊተገበር የሚችል የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብሎ የሚያምን መንግሰት ያስፈልጋል፡፡ ኤክስፖርት የሚደረግ ታንክ ሰራን በፍፁም በዚህ ወቅት ሊያኮራን የሚችል ስ አይደለም፡፡ አሁን የምንረዳው መንግሰት ችግሩን ሪፖርት አድርጊያለሁ ማለትን እንደመውጫ ቀዳዳ እየተጠቀመበት መሆኑን ነው፡፡

አሁን በመሬት ላይ ያለው ሀቅ በምግብ እና ውሃ እጥረት ከብቶች በብዛት እየሞቱ ሲሆን፤ መቼም እንደ እንሰሳቱ በብዛት ሰው እየሞተ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የነበረባቸው የጤና ችግር አግርሽቶም ይሁን አዲስ ጤና መቃወስ ተፈጥሮ ህፃናት ብቻ ሳይሆን አረጋዊያንም ሆኑ ባለጡንቻው ጎልማሳ የሚሞቱበት ሁኔታ እንዳለ ግን መካድ አይቻልም፡፡ ከዚህ ስንነሳ በምግብ እጥረት ምክንያት ሞት የለም ብሎ ፈሊጥ፤ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሁለት ህፃናት በቀን ይሞታሉ ያለው ለሌላ ዓላማ እና የሀገር ገፅታ ለማበላሸት ነው የተባለውን የመንግሰት ሹም መግለጫ ስንሰማ ከማፈር ውጭ ምን ልንል እንችላለን፡፡ የመንግሰት ሹሞቸ ፕሮፓጋንዳውን ጋብ አድርገው ሰብዓዊነት በመላበስ እየሞተ ያለውን ሰው መታደግ የግድ ነው፡፡ ስንት ሰው ሞተ ቤቱ ይቁጠረው፡፡

አንድም ሰው በድርቅ አልሞተም የሚል መግለጫ የሰጡትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ከላይ እንደገለፅኩት ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ የኖረው ችግር ላይ ሲታከል ሰዎች እንደሚሞቱ መገንዘብ አቅቷቸው ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተደረገ መሆኑን ማውቅ ግድ ይለናል፡፡ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ማፈራችን እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ የምናፍረው ደግሞ ከ30 ዓመት በኋላ ድርቅን ለመቋቋም የሚችል ህብረተሰብ ሊገነባ የሚችል ስርዓት መመስረት ያለመቻላችን ነው፡፡ ይህን መንግሰት ዛሬም ስህተቱን “በኤሊኖ” ክስተት አሳቦ በስልጣን እንዲቆይ የፈቀድነው እኛው ነን፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በምንም መመዘኛ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በፈለገ የተራዘመ የተፈጥሮ ችግር ጊዜ ቢሆን እንኳን ምግብ ለመለመን የማትችል ሀገር ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲና ሰትራቴጂ የሌለው መንግሰት እንዳይኖር ማድረግ ካልቻልን ምርጫው የራሳቸን ነው፡፡ ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እኛ ከላፈቀድን መሬትን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ፤ ሴፍቲኔት በሚባል የመንግሰት ድጎማ ስር ህዝቡን በተራዘመ ሰንፍና እንዲኖር በማድረግ በአምስት ዓመት በሚመጣ የይስሙላ ምርጫ ካርድ አግኝቶ አገዛዙን ለማራዘም የሚፈልግ መንግሰት ይህን ዓይነት ሰርዓት ሊዘረጋ አይችልም፡፡ እንዲህ ሲያደርገን እንቢ ብለን መከላከል ምርጫው የእራሳችን ይሆናል ማለት ነው፡፡

በተለጠጠ ዕቅድ ተሰፋ ውስጥ (የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልብ ይሏል) የከተማ ነዋሪውን ሸምቶ ለማብላት የውጭ ሀገር የሰንዴ ገበያን አማራጭ ያደረገ መንግሰት፤ በሀገር ውስጥ በእርሻ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዘመናዊ ገበሬዎች እርሻ መሰሪያና ሌሎች ግብዓቶች ድጎማ አድርግ ሲባል ነፃ ኢኮኖሚ ነው ይለናል፡፡ አንድ በዘመናዊ እርሻ ለመሰማራት የሚፈልጉ ዘመናዊ ገበሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰበሰቡት ስብሰባ ላይ ከጎኔ ቁጭ ብለው የነገሩኝ አስደማሚ ነገር “መንግሰት ሰንዴ ለመግዛት በጨረታ የሚያባክነው ጊዜ እና ገንዘብ ለእኛ ድጋፍ ቢያደርግ ለጨረታ ከሚባክነው ጊዜ ባነሰ በሀገር ውስጥ ሰንዴ ለማምረት እንችላለን” የሚል ነው፡፡ ይህን ሀቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለግብርና ሚኒሰትሩ የኪራይ ስብሰቢዎች ወሬ ነው የሚሆነው፡፡ ግብርና መር ስትራቴጂና ፖሊሲ ብለው ምግብ በሀገር ውስጥ ማሟላት ሳይችሉ ለዘላለም ሊገዙን ሲፈልጉ እሺ ብለን አለን፡፡



ለማነኛው ኢትዮጵያ ሀገራችንን ምድሯ “በኤሊኖ” ክስተት ይሁን በሌላ “ድርቅ” ጎብኝቷታል፡፡ ይህ ድርቅ አድጎ ደግሞ ዜጎችን ህይወት ቀሰ በቀስ እየወሰደ ነው፡፡ ይህን “ችጋር” ለመቋቋም ዜጎች በጋራ መነሳት ይኖርብናል፡፡ ፈረንጆቹ ይህ ውጤት እንዲቀለበስ ከልብ ከፈለጉ አንድም ሰው ሳይሞት ሊደርሱ የሚያስችል ሰርዓት አላቸው ነገር ግን የሰጡት ድጋፍ ህይወት አድን መሆኑ እንዲታወቅ ችግሩ እስኪሰማን ብዙ ሀይወት መጥፋቱ በሚዲያ ታይቶ ቅሰቀሳ እስኪደረግ ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሃል ምትክ የሌለው የሰው ልጅ ህይወት ያልፋል፡፡ ይህ እንዳይሆን መንግሰት አሁን ከጀመረው ተራ ፕሮፓጋንዳ ወጥቶ ወደ ቀጥተኛ ህዝቡን ያሳተፈ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48191

Saturday, November 7, 2015

ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ የምትወዳትን ሀገሯን ጥላ አሜሪካ ገባች


በቅርቡ ከሕወሓት መንግስት እስር ቤት የተለቀቀችው ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ዛሬ አሜሪካ ገባች::
ዛሬ ኖቬምበር 7, 2015 ዋሽንግተን ዲሲ ዱልስ ኤርፖርት የደረሰችው ርዕዮት በዲሲና አካባቢዋ በሚኖሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ደማቅ የሆነ የ እንኳን ደህና መጣሽ አቀባበል አድርገውላታል::

በሕወሓት መንግስት እስር ቤት ውስጥ ስቃይ ሲደርስባት የቆየችው ጠንካራ ሴት በበቀል ተነሳስተው ህክምና ሁሉ ሳይቀር ከልክለዋት ሲበቀሏት እንደነበር በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል:: ዓለም አቀፍ ተቋማት በታሰረችበት ጊዜ ሲሸልሟት የቆየችው ር ዕዮት ለበርካታ ሴቶች ተምሳሌት በመሆን ትጠቀሳለች::


ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ምናልባትም በሰሜን አሜሪካ ቆይታዋ ትምህርቷን ልትቀጥል እንደምትችል ይገመታል::

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48066

Friday, November 6, 2015

የሕወሓት መንግስት በመደለያዎች እና በግዳጅ ጭምር የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በየሥፍራው እየመለመለ መሆኑ ተሰማ

የሕወሓት መንግስት ኢትዮጵያውያን ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ ልኮ ሬሳቸውን በአደባባይ ሲያስጎትት

የህወሓት አገዛዝ ልዩ ልዩ ማማለያዎችንና መደለያዎችን በመጠቀም በግዳጅም ጭምር ወጣቶችን ለእግረኛ ተዋጊ ጦር ሰራዊትነት ለመመልመል በመላ አገሪቱ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ውስጥ ለተንሰራፋው የህዝቡ የከፋ ድህነትና ስራ አጥነት መንስኤ የሆነው የህወሓት አምባገነናዊ አገዛዝ ድህነታቸውን ተጠቅሞ ዕልፍ አዕላፍ ወጣቶችን በአገር መከላከያ ስም በመመልመል በየጠረፉ በሚደረጉ የሽምቅ ውጊያዎች ውስጥ በመጨመር ያለቀባሪ በየበረሃው ወዳድቀው እንዲቀሩ በማድረግ በደምና አጥንታቸው የስልጣን ዘመኑን ለመቀጠል ሲፍጨረጨር መቆየቱ በግልፅ የሚታወቅ እውነታ ነው፡፡


በስልጣንና የንዋይ ፍቅር የነሆለለው ዘረኛው የህወሓት ቡድን ምስኪን ኢትዮጵያዊ እናቶች ኩበትና እንጨት ለቅመው ሽጠው፣ ለባለፀጋ ተገርደው በችጋር አለንጋ እየተገረፉ ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን ወደ ሶማሊያ ምድር በማስገባት በጥይት እያስጨፈጨፈ ሬሳቸው ሳይቀር በሞቃዲሹና በሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ልክ እንደውሻ በድን በገመድ ታስሮ እንዲጎተት እያደረገ በምስኪኖች ሞት እሱ ረብጣ ዶላር እያፈሰ ይገኛል፡፡

       በሶማሊያ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች

የህወሓት አገዛዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ጦር መልምሎ የማሰልጠን ህልሙን ዕውን ለማድረግ ወጣቱን ያማልላሉ ብሎ ያወጣቸው ሦስቱ የማስመሰያ ቅጥር የሙያ መስኮች ለመከላከያ ኢንጅነርኢንግ ኮሌጅ ትምህርት፣ ለአየር ኃይል አብራሪነት እና ለልዩ ኮማንዶና አየር ወለድ የሚሉ ናቸው፡፡

በመሆኑም ለመከላከያ ኢንጅነርኢንግ ኮሌጅ ከፍተኛ ትምህርት በሚል ሰበብ ቴክኒክና ሞያ ት/ቤት ተመርቀው ስራ ማግኘት ያልቻሉትን በእግረኛ ተዋጊ ሰራዊትነት ለመመልመል ከፍተኛ ጉትጎታ ላይ ነው፡፡ 


ለአየር ኃይል አብራሪነት ደግሞ ከከዚህ ቀደሙ የመመልመያ መስፈርት በተለየ ሁኔታ በፊዚክስ፣ ሂሳብ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ “C” በቂ ነው የሚል አዲስ የቅጥር መስፈርት አውጥቷል፡፡ 


በየመንደሩ የተሰገሰጉት መልማይ ዲስኩራም ካድሬዎችም “ዳርፉር ሄዳችሁ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ብር ዝቃችሁ ትመለሳላችሁ…” በማለት ወጣቱን የእርጎ ባህር እያሳዩ ወላጆችን ደግሞ “ልጆቻችሁ በመንግስት ተምረው ኢንጅነርና ፓይለት እንዲሆኑላችሁ እና ከችጋር እንዲያወጧችሁ መምከርና በገሰፅ አለባችሁ…” እያሉ የድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ ደም በከንቱ እንደ ጅረት መፍሰሱን እንዲቀጥልና በአገራችን ላይ የተጫነው የባርነት አገዛዝ ዘመን እንዲራዘም ቀን ከሌሊት እየተጉ ነው፡፡


ህወሓት ከዚህ ቀደምም በ1980ዎቹ ዓ.ም መጨረሻ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 12ኛ ክፍልን አጠናቀው ዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ ወጣቶችን ለኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ስልጠና በሚል አታሎ በገፍ መልምሎ በሙያ ዘርፉ ከተመረቁ በኋላ የሚያገለግሉት “በአገር መከላከያ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ እንደሆነና በመጀመሪያ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ ግዴታቸው እንደሆነ አሳምኖ ወደየ የእግረኛ ተዋጊ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ካስገባና አሰልጥኖ ካወጣቸው በኋላ ቆይቶ በፈነዳው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ማግዶ ሁሉንም አስጨርሷቸዋል፡፡ 


የሀወሓት አገዛዝ ከማማለያው ጎን ለጎን የድሃው ህዝብ ልጅ የሆኑ ወጣቶችን አስገድዶ የመመልመል ሙከራም እያደረገ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ “በደቡብ ክልል” በጎፋ ሳውላና በቁጫ የሚኖር እያንዳንዱ ወላጅ ቢያንስ አንድ አንድ ልጅ እንዲያዋጣ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ 



ሆኖም የህወሓት አገዛዝ የቱንም ያክል ማማለያና መደለያ ቢያቀርብ እንዲሁም በጉልበት ቢያስገድድ እስካሁን ድረስ ተታሎ አንድም የተመዘገበ ወጣት እንደሌለ እንዴውም በተቃራኒው ወጣቱ የሚደርስበት ጭቆና አንገሽግሾት እየተደራጀ ጫካ በመግባት ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48032