Monday, November 30, 2015

በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የሕዝብ ተቃውሞ በአደባባይ ቀጥሏል * ፌደራል ፖሊስ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ 3 ተማሪዎችን ገደለ

የአዲስ አበባ አዲሱን ማስተር ፕላን በመቃወም በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ አድማሱን እያሰፋ መሆኑ ተሰማ:: የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳሉት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተጀመረውና ጎማ ጭምር በአደባባይ በማቃጠል የተስፋፋው የሕዝብ ቁጣ ትናንት እና ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ቀጥሏል::

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሰላማዊ መንገድ ቁጣቸውን ለመግለጽ የተሰበሰቡ ተማሪዎች ከፌደራል ፖሊስ በቆመጥና በጠመንጃ ሰደፍ የተደበደቡ መሆኑን በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ለዘ-ሐበሻ ገልጸው በተፈጠረው ብጥብጥ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የ3 ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል::

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ተማሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ምንም ዓይነት ንብረት ሳያወድሙ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ፖሊስ እርምጃ ሊወስድ ችሏል:: አሁንም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ አለመረጋጋት እንዳለ ዘገባዎች ጠቁመዋል::
የኦሮሞ ተማሪዎች ቁጣ በአምቦ እንዲሁም በነቀምቴ ከተሞችም ቀጥሎ ተማሪዎቹ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ውለዋል:: የአይን ዕማኞች ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት በአምቦ ፌደራል ፖሊስ መንገድ በመዝጋት የተማሪዎቹን ቁጣ ለማብረድ ጥረት ቢያደርግም ከከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ መለስተኛ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎቹ ተቃውሞ ገንፍሎ ወጥቷል::

አዲሱን የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃውም በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚደረገው ቁጣ አሁንም እየተስፋፋ ሲሆን ሕዝቡ ይህ ማስተር ፕላን እንዳይተገበር የሕይወት መስ ዋዕትነት ሳይቀር እንደሚከፍል በመዛት ላይ ይገኛል::


በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ማስፋፋት ስም በሰበታ ከተማ ለመለስ ዜናዊ መንደር ግንባታ በከተማው ለባለሃብት የተሰጠ የመሬት ፈቃድን የሚያሳይ ምስጢራዊ ደብዳቤ ዘ-ሐበሻ ከቀናት በፊት ለሕዝብ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል::

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48607

No comments:

Post a Comment