ዛሬ በሀገራችን ከፍተኛ ርሃብ፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስራ አጥነት፤ ስደት እና ሌሎችም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶች በሰፊው ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ወቅታዊ ጉዳዮች ከህዝብ ጋር ተወያይቶ አቋም ለመውሰድና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመሰንዘር ህዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የእውቅና ደብዳቤ ለማስገባት በተደጋጋሚ ጥረት ያደረግን ቢሆንም የአፈና መዋቅሩ የእውቅና ደብዳቤውን መቀበል ባለ መፈለጉ ለ5 ጊዜ ተጉላልተን በ6ኛው በሪኮመንዴ(በፖስታ) ለመላክ ተገደናል፡፡
የእውቅና ደብዳቤው በሪኮመንዴ የደረሰው አስተዳደሩ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ላይ ሆኖ ‹‹ህዳር 18/2008 ዓ.ም አልፏል›› በሚል ለተጨማሪ ጊዜ ደብዳቤውን ሳያስተናግድ ቀርቷል፡፡ ህዳር 18 ያላለፈ መሆኑን ካስረዳን በኋላ ለሶስት ቀናት በተደጋጋሚ ብንመላለስም ‹‹ከደህንነትና ፖሊስ ጋር ካልተመካከርኩ እውቅና አልሰጥም›› ሲል እምቢታውን ገልጾአል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአባላትና ደጋፊዎቻችን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ልናደርገው የነበረው ውይይት ሊደናቀፍ ችሏል፡፡
ከዓለም የነጻነት የትግል ታሪክ እንደምንገነዘበው በአገዛዝ አፈና የተገታ የህዝብ ጥያቄ ኖሮ አያውቅም፡፡ አፈናው የነጻነትን ጊዜ ቢያዘገይ እንጅ ፈጽሞ ሊያስቀርም አይችልም፡፡ ስለሆነም ጭቆናው ወደ ነፃነት የሚያስኬደውን ጉዞ እልህ አስጨራሽ ከማድረግ በቀር ዘላቂነት ኖሯቸው የነጻነት ጥያቄውን ፈጽሞ ማዳፈን እንደማይችሉ አገዛዙ ሊረዳ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ለማይቀረው የነፃነት ትግል ቆርጦ እንዲነሳና ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48484
No comments:
Post a Comment