Saturday, January 30, 2016

በጋምቤላ የሟቾች ቁጥር 8 ደረሰ ውጥረቱ እንዳየለ ነው በርካቶች በቦምብ ፍንዳታ ቆስለዋል

ዘ-ሐበሻ በሰበር ዜና ባለፈው ሀሙስ በጋምቤላ በኑዌር እና በአኝዋክ ብሄረሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት የሟቾች ቁጥር 6 መድረሱን መዘገቧ ይታወሳል:: ግጭቱ እስከ ዛሬ ድረስ መቀጠሉ ተዝግቦ የሟቾች ቁጥር አሻቅቧል::


አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደዘገበው በጋምቤላ ክልል በኑዌርና በአኝዋክ ብሔሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት የክልሉ የፀጥታ ሃይል አባላትን ጨምሮ የ8 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካቶች በቦንብ ፍንዳታ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በግጭቱ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን ከትላንት በስቲያ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ ባንኮችና የንግድ ተቋማት የተዘጉ ሲሆን ትናንት ረፋድ ላይም በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ግርግር ተከስቶ እንደነበር ታውቋል፡፡

ለቀናት በዘለቀው ግጭት የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ም/ኃላፊን ጨምሮ 8 ሰዎች መሞታቸውንና በከተማዋ ሁለት ቦታ በፈነዳ ቦንብም በርካቶች መቁሰላቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይልን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት ግጭቱን ለማረጋጋት ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰው በትናንትናው ዕለትም ከተማዋ በውጥረትና ግርግር ስትዋከብ መዋሏን ገልፀዋል፡፡


የግጭቱ መነሻ ከ15 ቀናት በፊት በክልሉ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ም/ዲንና በክልሉ ም/ፕሬዚዳንት ሹፌር መካከል በመኖሪያ ቤት መሬት ጉዳይ በተፈጠረ የግል ፀብ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ ጠቡን ተከትሎ ም/ዲኑ የአኙዋክ ተወላጅ ሹፌሩን እጁ ላይ በጥይት መተው ማቁሰላቸውን ገልፀው በዚህም ሳቢያ ጉዳዩ የብሄር ግጭት መልክ እንደያዘና ወደ ተማሪዎች የቡድን ፀብ እንደተዛመተ አስረድተዋል፡፡


ግጭቱ ከእለት እለት እየተባባሰ ቀጥሎም አንዲት የኑዌር ተወላጅ ተማሪ በግጭቱ ጉዳት ደርሶባት ህክምና እየተከታተለች ሳለ ህይወቷ በማለፉ ግጭቱ መካረሩን የጠቆሙት ምንጮች፤ የኑዌርና የአኙዋክ ብሄር ተወላጅ ተማሪዎች የእርስ በእርስ ግጭት መፍጠራቸውን ገልፀዋል፡፡


የክልሉ ልዩ ሃይል ግጭቱን ለማርገብ ሙከራ ሲያደርግ ቢቆይም ሁኔታው ባለመረጋጋቱ የመከላከያ ሰራዊት በትናንትናው እለት በከተማዋ ተሰማርቶ ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡


በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ም/ኃላፊ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም በትናንትናው ዕለት ኃላፊው አዲስ አበባ መምጣታቸውን ገልፀው፤ “መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልፀውልናል ሲል አዲስ አድማስ ዘገባውን አጠናቋል::


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/50460

No comments:

Post a Comment