Saturday, March 17, 2018

ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተባለ

ባለፈው ሣምንት ቅዳሜ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት በነዋሪዎች ላይ የፈጸመው ግድያ በየአቅጣጫው ቁጣን ቀስቅሷል። የኮማንድ ፖስቱ ድርጊቱ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ቢገልፅም የመከላከያ ኃይሉ ጥቃት ሆን ተብሎ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት እንደኾነ የገለጡ አሉ


ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ዜጎች ወደ ኬንያ ሊሰደዱ እንደሚችሉ የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር (WFP) ሥጋቱን ገለጸ። የድርጅቱ የኬንያ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ፒተር ስሜርዶን ተፈናቃዮችን በተመለከተ ሲናገሩ፦ «በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ምናልባት ቁጥራቸው ሊጨምር ይችላል ብለን እንጠብቃለን» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወደ ኬንያ የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን «አሁን ቁጥራቸው ከ9, 600 በላይ ናቸው ተብሎ ይገመታል» ያሉት ስሜርዶን አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል። ከትናንት ጀምሮም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት እና የዓለም የምግብ መርኃ-ግብርን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ወደ ኬንያ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ለመርዳት ሁኔታውን እያጠኑ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የተሰደዱ ዜጎችን ለመመለስ «ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ»መሆኑን ገልጿል። የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ «ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚመለከታቸው ከክልልና ከፌድራል መንግሥት ከአካባቢ አስተዳደር ቡድን ተዋቅሮ ወደ ቦታው ሔዷል። ሕብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ ነው። የተጎዱ ቤተሰቦችን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ ነው። የተፈናቀሉ እና ወደ ኬንያ ድንበር የሔዱ ዜጎቻችንን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።
http://www.dw.com/am/%E1%8B%88%E1%8B%B0-%E1%8A%AC%E1%8A%95%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%88%B0%E1%8B%B0%E1%8B%B1-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8B%8D%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%89%81%E1%8C%A5%E1%88%AD-%E1%88%8A%E1%8C%A8%E1%88%9D%E1%88%AD-%E1%8B%AD%E1%89%BD%E1%88%8B%E1%88%8D-%E1%89%B0%E1%89%A3%E1%88%88/a-43025309

No comments:

Post a Comment