Wednesday, March 21, 2018

የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ “ሕዝብን የገደሉ ይጠየቁ” በማለታቸው ታሰሩ



ልበ ሙሉ፡ ደፋር፡ ጀግና፡ አንደበተ ርትዑ፡ የወገን ጥቃት የሚያመው፡ ትንታግ፡ ልበ ደንዳና ኦቦ ታዬ ደንደአ። የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊ ናቸው። በዚህ የጭንቅና የምጥ ወቅት የተገኙ ኮከብ በመሆናቸው ልናመሰግናቸው፡ ከጎናቸውም ልንቆም የሚገባን እንደሆነ ይሰማኛል። አቶ ታዬ በሁለት ቃለመጠይቆች ላይ ባሳዩት ፍጹም ድፍረትና የወገን ተቆርቋሪነት ነጥረው የወጡ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው። ዛሬ ጭራቆቹ እጅ ላይ ወድቀዋል።
የትግራዩ ገዢ ቡድን የለማን ኦህዴድ ለማዳከምና ለመሰባበር እንቅልፍ አጥቶ እያደረ ነው። የኦሮሚያን የወረዳ፡ የከተማና የዞን ባለስልጣናትን በማሰር የጀመረው እንቅስቃሴ ወደላይ ከፍ ብሎ የካቢኒ አባላት ጋ ደርሷል። አቶ ታዬ የትግራዩን ገዢ ቡድን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለህዝባቸው ያላቸውን ፍጹም ተቆርቋሪነት በማሳየታቸው በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸው ታውቋል። በተለይ ሰሞኑን በሞያሌ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ”በስህተት” በሚል መገለጹን ተከትሎ አደባባይ በመውጣት ”ስህተት አይደለም፡ ግልጽ የጦር ወንጀል ነው። የመከላከያም ሆነ የኮማንድ ፖስቱ አዛዦች በህግ ሊጠየቁ ይገባል” ማለታቸው በትግራዩ ገዢ ቡድን ሰፈር ጸጉር እስኪነቀል ያበሳጨ መሆኑ ተሰምቷል።
ከዚህ ቀደምም የትግራዩ ገዢ ቡድን ቄሮዎች ላይ ምርመራ ጀምሬአለሁ ያለ ሰሞን ሚዲያ ላይ ወጥተው ”ምን አገባህ” በማለት ምላሽ መስጠታቸው ከህዝብ ከፍተኛ ከበሬታን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ከትግራዩ ገዢ ቡድን ደግሞ ጥርስ አስነክሶባቸዋል። እሳቸው ብቻ አይደሉም። የአምቦ ከተማ ፖሊስ አዛዥ፡ የሞያሌ ከተማ ከንቲባ፡ ሌሎችም የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት እያሳዩ ያሉት የህዝብ ወገንተኝነት በደማቁ የሚነሳ ነው። ከትግራዩ ገዢ ቡድን ዱላ ይልቅ የህዝባቸው ቁጣ የሚያስፈራቸው ናቸው። መንገዳቸውን መርጠዋል። ዘላቂ ጉዞ ከህዝብ ጋር እንጂ ከሚያልፍ ስርዓት ጋር እንዳልሆነ አውቀውታል። ካወቁ አይፈረድባቸውም። ለምንስ ይቀጣሉ? እየሰጠመ ካለ መርከብ ዘንድ ምን አላቸው? ቄሮን የመስለ መከታና ጋሻ እያላቸው ? ?
የትግራዩ ገዢ ቡድን ዙሩን ማክረር ፈልጓል። ለህዝብ የሚበጀው፡ ለሀገር የሚጠቅመው እንዲህ ዓይነቱ በትዕቢትና ድንቁርና የሚነዳ አመራር አልነበረም። ድምሩ ዜሮ የሆነ፡ አጥፍቶ መጥፋት መስመር ላይ የቆመ አካሄድ አወዳድቅን አጉልና ዘግናኝ ከማድረግ ውጪ የህዝብን የነጻነት ተጋድሎ አይቀለብሰውም። የአቶ ታዬ ደንደአ እስር ህዝብን ለቁጣ የሚፈነቅል ተጨማሪ ምክንያት እንጂ ወደ ቤቱ የሚያስገባ፡ በፍርሃት ተሸብቦ አንገቱን ደፍቶ እጅ የሚያሰጠው አይሆንም።
ሺ ታዬዎች ተፈጥረዋል። ሚሊየን ለማዎች በቅለዋል። ለትግራዩ ገዢ ቡድን የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ ሆኖበት እንጂ ለነጻነት የቆመን የህዝብ ልብ ወደ ኋላ የሚመልሰው ምንም ዓይነት ምድራዊ ሃይል የለም። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ይባላል። የትግራዩ ገዢ ቡድን ከዚህ በኋላ የራሱን መጨረሻ የማሳመር ሃላፊነቱ የራሱ ብቻ ነው። አወዳደቁ አጉል እንዳይሆን ነገሮችን የማለስለስ ስራ እንጂ እንዲህ ማጦዝ ከማንም በላይ የሚጎዳው ራሱኑ ነው።
ትላንት ዛሬ አይደለም!!!!
https://ecadforum.com/Amharic/archives/18716/

No comments:

Post a Comment