መረጃ የማግኘት ነጻነት ከዋነኞቹ የዴሞክራሲ መገለጫዎች ወይም እሴቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ መረጃ የማግኘት ነጻነቱ የተከበረለት
ህዝብ በሀገሩ የስልጣን መንበሩ ላይ የተቀመጠውን አስተዳደር (መንግስት) የመቆጣጠር ኃይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደርና
ሌሎችን ንቅዘቶች በማጋለጥ የመንግስትን ተጠያቂነት በማስፈን ሂደት ውስጥ ህዝብ ንቁ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ መረጃ የማግኘት ነጻነቱን
ሊጎናጸፍ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መረጃ የሚያደርሱት ሚዲያዎች በስፋት መኖር የግድ ነው፡፡ ለዚህም ነው በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር
ውስጥ የሚዲያ (ፕሬስ) ሚና እንዲጎላ የሚደረገው፡፡
በተቃራኒው በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ገዥዎች የሚዲያ (ፕሬስ) ነጻነትን
በማፈን ህዝብ መረጃ እንዳያገኝ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ አምባገነኖች ስርዓቱን የሚተቹ የፕሬስ ውጤቶችን ይዘጋሉ፣
ጋዜጠኞችን ያስራሉ፣ ያሳድዳሉ፣ አለፍ ሲልም ይገድላሉ፤ ያስገድላሉ፡፡ አምባገነኖች ለይስሙላ የሚዲያ ነጻነት መረጋገጡን የሚያሳዩ
ህጎችን በማውጣት በውጭ ሆኖ ለሚመለከታቸው አካል ዴሞክራት በመምሰል በውስጥ ተግባራቸው ግን ካወጧቸው ህጎች ፍጹም ተቃራኒ በመሆን
የአፈና ስራ ያከናውናሉ፡፡ የግል ፕሬሶችን በቀጥታም ሆነ በእጃዙር ጨምድዶ በመያዝ፣ ፕሬሶች ህጉን ተከትለው በፈቃዳቸው ያሻቸውን
እንዳይሰሩ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ አይነቶቹ የአምባገነኖች ተግባራት በበርካታ ሀገራት ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡
ለአብነትም ለረጂም አመታት ቻይናን እየገዛ ያለው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በሀገሩ የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ውጤቶች ላይ ባሻው ጊዜ ሁሉ
ህገ-ወጥ እርምጃዎችን በመውሰድ ይታወቃል፡፡ ይኸው የቻይና ገዥ በ2012 ብቻ ከ16 በላይ ዌብሳይቶችንና ብሎጎችን ከርችሟል፡፡
ይህ አምባገነን ስርዓት በምድረ ቻይና የመረጃ መረብ እቀባ በማድረጉ ምክንያት፣ ሀገሪቱ በተለያየ ጊዜ ከታዋቂዎቹ ዓለም አቀፍ የመረጃ
ምንጮች ጎግልና ያሁ ድረ-ገጾች ጋር አተካራ ውስጥ ስትገባም ይታያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቻይና በሀገሯ የሚታተሙ ጋዜጦችንና መጽሔቶችንም
በመክሰስና በመዝጋት ስሟ በአሉታ ይነሳል፡፡
ቻይና ዲንግ ዲያን የተሰኘውን ከፍተኛ ተነባቢ ሳምንታዊ ጋዜጣ እ.ኤ.አ
በ2006 መዝጋቷንም እዚህ ጋር እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ የቻይና ገዥዎች ጋዜጣውን የዘጉት በሀገሪቱ ያለውን የማህበራዊ ቀውስ፣
በሙስና የተጨማለቀውን አስተዳደር፣ በከተሞች ያለውን የከፋ የአየር ብክለት፣ ያልተመጣጠነ የዜጎች የደመወዝ ክፍያን፣ ልቅ የመሬት
ይዞታን እና ሌሎች ችግሮቹን በተከታታይ ማጋለጡን ተከትሎ እንደነበር ይወሳል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የቻይና መሪዎች ትችትን ለመቀበል
አለመፍቀድ እንዲህ አይነት እርምጃዎችን እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡ ቻይናውያን ጋዜጠኞች በቻይና መንግስት የሚወሰደው እርምጃ ፍጹም
ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው ሲሉ ቢከራከሩም ሰሚ አግኝተው የሚያውቁ አይመስሉም፡፡
በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ያለው እውነታም ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ በእነዚህ
አምባገነን ስርዓቶች ገዥዎች ፕሬሱ በተቋም ደረጃ ጎልብቶ በሁለት እግሩ እንዲቆም የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የራሳቸውን የግል
ስልጣን ጠብቆ ለመቆየት ነጻ ፕሬሶችን ሰለባ ያደርጓቸዋል፡፡ በእርግጥም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ፣ አምባገነኖች በነገሱባት ሀገር ፕሬሱና
ሙያተኛው በነጻነት ተደራጅቶና ጎልብቶ ተቋም እንዲመሰርት አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህም ይመስላል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
በ2009 አፍሪካን ሲጎበኙ ጋና አክራ ላይ ‹‹አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን (መሪዎችን) ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትን ነው የምትሻው›› ሲሉ
ሀቁን የተናገሩት፡፡
በእርግጥም አፍሪካ ጠንካራ ተቋማት የላትም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የጠንካራ
ተቋማት እጦት ችግር ደግሞ ከብዙ የአፍሪካ ሀገራትም የከፋ ነው፡፡ በተለይ ለሌሎች ተቋማት መጎልበት አይነተኛ ሚና የሚጫወተው የሚዲያ
ተቋም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ምንም በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አምባገነኖቹ ገዥዎች ድክመቶቻቸውን በሚያጋልጥባቸው
ሚዲያ ላይ የሚወስዱት ህገ-ወጥ እርምጃ አሉታዊ ሚና አለው፡፡
ፕሬሱ ላይ የተመዘዘው አዲሱ ሰይፍ
የኢህአዴግ ገዥዎች ፕሬሱን በማዳከም ሂደት ላይ ከቻይና ‹‹ምርጥ ተሞክሮ››
ሳይወስዱ አልቀሩም፡፡ ልክ እንደ ቻይና ሁሉ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ ዌብሳይቶችን…ይዘጋሉ፤ ይከስሳሉ፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ያለው
የፕሬስ ነጻነት ህገ-መንግስታዊ እውቅና አግኝቷል፤ ዋስትና ግን የለውም፡፡ ምክንያቱም ህገ-መንግስታዊ እውቅና ያገኘው የፕሬስ ነጻነት
በተለያዩ አፋኝ አዋጆች ዋስትናውን አጥቷል፡፡ የፕሬስ ተቋማትም ሆነ ሙያተኞች (ጋዜጠኞች) ህገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት
ለመስራት ሲንቀሳቀሱ በተለያዩ ተልካሻ ምክንያቶች በህገ-ወጥ እርምጃ በተደጋጋሚ ተደናቅፈዋል፤ እየተደናቀፉም ይገኛሉ፡፡ በዘመቻ
መልክ የግሉን ፕሬስና ጋዜጠኞችን የማሳደድ ስራ ከተከናወነበት ምርጫ 97 ጀምሮ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ይህን ህገ-መንግስታዊ
እውቅና የተቸረውን ነጻነት ሲገረስስ ታይቷል፡፡
አስገራሚው ጩኸት ደግሞ ኢህአዴግ እነዚህን የአፈና ስራዎች ሲሰራ ‹ህገ-መንግስታዊ
ስርዓቱን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ› በሚልና በልማት ሽፋን መሆኑ ነው፡፡ ህግን እየጣሱ ህግን ለማስከበር ስል ነው የሚለው የኢህአዴግ
መንግስት ከሰሞኑ ደግሞ ሌላ የአፈና መስመርን ዘርግቷል፡፡ ይኸውም ‹‹ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአመፅ ለመናድ በማሴር የተጠረጠሩ
የህትመት ውጤት አሳታሚዎችና ድርጅቶች›› ላይ በ‹ፍትህ ሚኒስቴር› አማካኝነት ክስ መመስረት ነው፡፡
ተጠርጣሪ ተከሳሽ አሳታሚዎችና ድርጅቶች የክስ ቻርጅ ሳይደርሳቸው እንደማነኛውም
ሰው የስርዓቱ አፍ በሆነው በኢቴቪ መስማታቸውን የገለፁት የክስ ይዘት፣ ለብዙዎቻችን ግርምትን የሚያጭር ነው፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር
መግለጫ ስለጉዳዩ ሲያትት እንዲህ ይላል፤ ‹‹በየጊዜው ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የአመፅ ቅስቀሳና
የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት፣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል እንዲፈረስ እና ህዝብ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ
የሚያደርጉ የወንጀል ተግባራትን በመፈፀም ተጠርጥረዋል፡፡››
ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ተነባቢነት እንዳላቸው የሚታወቁት አምስት መጽሔቶችና
አንድ ጋዜጣ ናቸው፡፡ እነዚህም ፋክት፣ ጃኖ፣ ሎሚ፣ አዲስ ጉዳይ እና እንቁ መፅሄቶችና አፍሮ ታይምስ የሚባል ጋዜጣ አሳታሚዎችና
ድርጅቶች ናቸው። ምናልባትም ኢህአዴግ ክሱን ለመመስረት መስፈርቱ ፕሬሶቹ ከፍተኛ ተነባቢነት ማግኘታቸው ሳይሆን አይቀርም፤ አለበለዚያም
በምንም አይነት መልኩ ምንም ባደርግ አትተቹኝ ባይነት መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ ለመሆኑ ‹‹…ህዝብ በመንግስት ላይ ያለአግባብ
አመኔታ እንዲያጣ በማድረግ…›› ማለት ምን ማለት ነው? ሲጀመርስ ስርዓቱ በህዝብ ዘንድ አመኔታ አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ
ይሆናል፡፡
ይህን መሰሉ የመንግስት እርምጃ የግሉ ፕሬስና ጋዜጠኞቹ ላይ የሚያሳድረውን
አሉታዊ ተጽዕኖ ኢህአዴግ ጠንቅቆ የሚያውቀው ይመስላል፡፡ ከአሁን በፊት እንደታየው ከሆነ መንግስት እነዚህን መሰል አሳታሚዎች ክስ
ሲመሰርትባቸው ጋዜጠኞቹና አሳታሚዎቹ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ የበፊት ተሞክሮው ማህደር የሚነግረው እውነታ አለ፡፡ የኸውም ጋዜጠኞቹና
አሳታሚዎቹ ክሱ በሚያሳድርባቸው ጫና ሀገር ጥለው መኮብለል፣ አልያም ስራቸውን እርግፍ አድርገው መተው እንደሆነ አይቶታል፡፡ ይህን
አይነት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል የሚወጣ ‹መረጃ› እነ አዲስ ነገርና አውራምባ ታይምስን የመሳሰሉ ጋዜጦችን ከህትመት ውጭ አድርጓቸው
እንደነበርና ጋዜጠኞችንም ለስደት እንደዳረጋቸው ኢህአዴግ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የዚህኛው ክስ ጉዳይም ከዚህ ጋር የተመሳሰለ
ምላሽን እንዲያስገኝለት በማሰብ የመሰረተው ክስ ሊሆን ይችላል፡፡
የራሷ ሲያርባት…
አንዳንዴ ከራስ ግዙፍ ጉድፍ ይልቅ የሌላን ጥቃቅን ችግር ማየት የተለመደ
ይሆናል፡፡ ለምሳሌ መንግስት በእነዚህ አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ላይ የመሰረተው ክስ ተገቢነት የሚኖረው ከሆነ ኢህአዴግም
በተመሳሳይ የሚከሰስባቸው አግባቦች መኖራቸውን ልብ ያለው አይመስልም፡፡ ይኸውም መንግስት በራሱ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ሚዲያዎች ዘወትር
ህዝብን ባዶ ተስፋ እየመገበ ከማወናበዱ በተጨማሪ፣ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ኃይላት ከህዝብ ለማራቅ የሚያደርሰው የስም ማጥፋትና
ማጥላላት አልታወሰውም፡፡ መቼም በዶክሜንተሪ ፊልም ስም በተለያዩ አካላት ላይ የሚሰራው ስራ ምን ያህል ጤነኛ እንዳልሆነ ከራሱ
ከኢህአዴግ ሰዎች የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡
ስለሆነም መንግስት አሳታሚዎችንና ድርጅቶችን ‹‹…የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት
ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል እንዲፈረስ እና ህዝብ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ የወንጀል ተግባራትን
በመፈፀም…›› ከጠረጠረና ከከሰሰ፤ እሱ ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ‹‹ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር›› እያለ ስማቸውን
ሲያጎድፍ እንዴት አያፍርም ያስብላል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን መንግስት ምርጫ 2007 ዓ.ም ሳይደርስ ህዝብ መረጃ
የሚያገኝባቸውን ፕሬሶች ከወዲሁ ከመስመር እንዲወጡ ማድረጉን ተያይዞታል፡፡ ቀደም ብሎ በተለያዩ ፕሬሶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ጦማሪያን
ላይ ሲወስደው የቆየውን እርምጃ አሁንም ገፍቶበታል፤ ገናም ይቀጥልበታል፡፡ ለዚህ ማሳያ ምልክቶች የሚሆኑት ደግሞ በአሳታሚዎችና
ድርጅቶቹ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ቀጣይ መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ በግልጽ መናገሩ ነው፡፡ ‹‹በህገ-መንግስቱ የተበጁትን
ገደቦች በማን አለበኝነት በመጣስ ስራዬ ብለው ብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ በሚጥል መልክ አመፅና ሁከትን የሚቀሰቅሱ፣ አክራሪነትንና
ሽብርተኝነትን የሚያወድሱ እንዲሁም የሚያበረታቱ፣ በህዝቡ መሃከል የዘርና የሃይማኖት ጥላቻን የሚቀሰቅሱ፣ የህዝብ መሪዎችንና የተቋማትን
መልካም ስምና ዝና በሀሰት የሚያጠፉና የሚወነጅሉ አንዳንድ ህትመቶች እንዳሉም ሊታወቅ ይገባል›› ሲል ማስፈራሪያ አዘል መግለጫውን
አሰምቷል፡፡
‹አያ ጅቦ…›
አሁን በአምስቱ የመጽሔት እና አንድ ጋዜጣ አሳታሚዎች ላይ የተመሰረተው
ክስ ብዙ የተንሸዋረሩ ምክንያቶችና ሰበቦችን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባስጠናው ‹የአዝማሚያ
ጥናት›፣ መሰረት ‹‹አብዛኛዎቹ በህትመት ላይ ያሉ መጽሔቶች የጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልሳኖች ናቸው›› ሲል ድምዳሜ ላይ መድረሱ
ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህም የኢህአዴግ መንግስት በ‹ጥናት› አረጋግጠናል በሚል ‹‹አያ ጅቦ ሳታማሃኝ ብላኝ›› ማለቱ እንደሆነና በቀጣዩ
እርምጃ ሊወሰድባቸው የተመረጡ ፕሬሶች መኖራቸውን ያሳየ ነበር፡፡ በዚህም አሁን ክስ የተመሰረተባቸው የፕሬስ አሳታሚዎች በዚያ
‹ጥናት› ስማቸው በክፉ ተነስቶ ጥርስ የተነከሰባቸው እንደነበሩ ማየቱ በቂ ነው፡፡
ሌላው ማመሃኛ ወይም ማደናገሪያ ደግሞ መንግስት ‹ይኽን ክስ እንድመሰርት
የተገደድኩት በህዝብ ግፊት ነው› ለማለት የሞከረበት ድንግርግሮሽ ነው፡፡ ‹‹የጥቃታቸው ሰለባ የሆነው ህዝብ በእነዚህ የህትመት
ውጤቶች የህግ ከለላ በተሰጣቸው ጥቅሞቹ ላይ ያለማቋረጥ የሚደርሰውን ጥሰት ለማስቆም መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በተለያዩ
መንገዶች ሲጠይቅ ቆይቷል›› ይላል መንግስት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል በሰጠው መግለጫው፡፡
በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት ከረጂም ጊዜ ተሞክሮው እንደታየው አካሄዳቸው
ያላማረውን (የሚተቹትን፣ ድክመቶቹን የሚያጋልጡትን) ማናቸውንም የግል ህትመት ውጤቶች በተለያዩ ዘዴዎች ከመስመር ማስወጣቱን ልብ
ማለት ይቻላል፡፡ መንግስት አዲስ ዘመንን፣ ኢቴቪንና አይጋ ፎረም የመሳሰሉ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሰፊ ማጥላላት ሲከፍትባቸው የነበሩትንና
ያሉትን ፕሬሶችና ጋዜጠኞች ስንመለከት ኢህአዴግ ህግ የማይገዛው፣ በአንጻሩ ግን ህግን በማስከበር ስም ሌሎች ላይ ጥቃት እያደረሰ
የሚገኝ መሆኑን እናያለን፡፡
ተቋም እንዳይኖር ማድረግ
ኢህአዴግ ፕሬሱ በተቋም ደረጃ እንዲጎለብት አይፈቅድም፡፡ ስለሆነም የግል
ፕሬሱ እንደ ፕሬስም ሆነ ጋዜጠኞቹ በነጻነት ተደራጅተው ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ አይደረግም፡፡ በዚህ አመት ላይ ራሳቸውን በማህበር
ለማደራጀት የሞከሩ ጋዜጠኞች እንኳ እጣፈንታቸው ከመበታተን ያለፈ አልሆነም፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ጫና አሉታዊ ሚና አለው፡፡
ለምሳሌ ሁለቱ አመራሮች (የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ እና የህዝብ ግንኙነት የነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ) ስርዓቱ
ባደረሰባቸው ጫና ሀገር ጥለው ተሰድደዋል፡፡
ኢህአዴግ መደራጀት መብት ነው ሲል፣ በራሱ ማዕቀፍ ጥገኛ እስከተሆነ ድረስ
ማለቱ እንደሆነ በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ላይ ነጻና ገለልተኛ ማህበራትን ማየት ብርቅ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም በየማህበራቱ
የኢህአዴግ እጅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አለ፡፡ ስለሆነም የፕሬሱን ጉልበት ማዳከሚያ ዋና መሳሪያው ያገባኛል የሚሉ አካላት በነጻነት
እንዳይደራጁ ማድረግ ነው፡፡
እስካሁን ድረስ የግል ፕሬሱ አንድ የጋራ ጠንካራ ማተሚያ ቤት እንኳ ሊኖረው
አልቻለም፡፡ ፕሬሱ የአንጋፋ የመንግስት ማተሚያ ድርጅት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጥገኛ ነው፡፡ ሌሎች የንግድ ማተሚያ ቤቶችም
ቢሆን አንድም አቅማቸው የሚያወላዳ አይደለም፤ ሁለትም በተዘዋዋሪ መንገድ በስርዓቱ ተጽዕኖ ስር የወደቁ ናቸው፡፡
የተመዘዘውን ሰይፍ ለማጠፍ…
በአጠቃላይ አሁን ያለው የሀገራችን የፕሬስ ነጻነት እጅግ አሳሳቢና አደገኛ
ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡ እስካሁን ከተለመደው የጋዜጠኞቹ እስርና ድብደባ እንዲሁም ስደት በከፋ ሁኔታ አሁን ደግሞ
አሳታሚዎች ላይ ክስ መመስረት መቻሉ መንግስት ምን ያህል የግል ፕሬሱን ማሽመድመድ እንደፈለገ ጉልህ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስለሆነም
ይህን በፕሬሱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማቃለል የተደራጀ ርብርብ በሚመለከታቸው ተቆርቋሪ አካላት ዘንድ መደረግ ይኖርበታል፡፡ መንግስት
ህገ-መንግስቱን አክብሮ ፕሬሱ በነጻነት እንዲቀሳቀስ መፍቀድ ግዴታው መሆኑን በተለያዩ ስልቶች (ለምሳሌ የፕሬሱ አባላት የሚያስተባብሩት
የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ፣ የተዘጉ ፕሬሶችን የቀደሙ ኮፒዎች ይዞ በአደባባዮች በህብረት መታየት፣ አፍን በጥቁር ፕላስተር
አሽጎ ተቃውሞን መግለጽ…) በመሳሰሉት ማስገደድም የተገባ ይሆናል፡፡
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34447
ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ ሚዲያው ‹‹ጥቁር ሳምንት›› (black week)
በሚል ለአምስት ቀናት ዘመቻ (campaign) መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚያ የጥቁር ሳምንት ዘመቻ ወቅት በመጨረሻው ቀን አስተባባሪዎቹ
አዲስ አመትን በማስመልከት ‹አዲስ አመት በዓልን ከነጻነት ታጋዮች ጋር› በሚል የታሰሩ የነጻነት ታጋዮች እንዲጠየቁ ጥሪ መተላለፉ
አይዘነጋም፡፡ በመሆኑም የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ዝግጅት ክፍል ጳጉሜ 5 ቀን 2006 ዓ.ም በቂሊንጦ የሚገኙ
የዞን 9 የጡመራ ቡድን አባላትንና የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በመጠየቅ የዘመቻውን አካል አከናውነዋል፡፡ ቀጥሎም
የጥቂት እስረኞችን መልዕክት በአጭር በአጭሩ አቅርበናል፡፡
ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
‹‹ሀገሬ ላይ እርግጠኛ የሆንሁበት ጉዳይ ቢኖር እኔን እንደ ዜጋ የሚጠብቀኝ መንግስት የሌለኝ መሆኑን ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ አልጠበቀኝም፡፡
ህገ-መንግስቱ ጥሩ ቢሆንም አልተከበረም፡፡ ይህ ሁሌም የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው፡፡
ታስሬ ባለሁባቸው ቀናት ሁሉ የታዘብኩት ነገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ
የሆነ የባለሙያ እጥረት በሁሉም ዘርፍ መኖሩን ነው፡፡ አቅም ያላቸው ዜጎች ከስርዓቱ በመገፋታቸው ክፍተቱ እንዲሰፋ ሆኗል፡፡ በጣም
ነው የሚያሳዝነው፤ የሚሰሩ ሰዎች በተገቢው ቦታ ላይ አለመኖራቸውን አይቻለሁ፡፡ የሚያሰራ ስርዓት ስለሌለ ብዙዎች ህሊናቸውን መርጠው
በመራቃቸው ይመስለኛል አቅም ያላቸው ሰዎች የራቁት፡፡ ይህ ለሀገር አሳሳቢ ነው፡፡
የሚቆጨኝ ነገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ተቋማት በእንግሊዝኛ የተሰሩ
የጥናት ስራዎችን በመምረጥ አሰባስበን በአማርኛ ቋንቋ በጆርናል መልክ ለመስራት አስበን ያን ሳንሰራ በመታሰራችን ነው፡፡
አሁን በተለያዩ ሁኔታዎችና ጉዳዮች ላይ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያው በኩል
የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እኛን አስረው ሌላው ዝም እንዲል ፈልገው ኖሮ ከሆነ እንዳልተሳካላቸው የሚያሳይ
ነው፡፡ ለሀገር የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች በየጊዜው ማበባቸው አይቀሬ ነው፡፡ እየታየ ያለውም ይሄው ነው፡፡ ምንግዜም የሚበረቱ ሰዎች
ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡››
አይመዲን ጀበል፣ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል
ልትጠይቁን ስለመጣችሁ በጣም እናመሰግናለን፡፡ በተለይ ወጣቶቹ እያደረጋችሁ
ያለው እንቅስቃሴ እንሰማለን፡፡ በጣም ደስ ይላል፡፡ እስካሁን በአገር ጉዳይ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የቆዩት የ1960ው ትውልድ አባላት
ናቸው፡፡ አሁን ወጣቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም
ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ያሲን ኑሩ፣ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል
‹‹እስር፣ እንግልትና ሌሎችም በደሎች የአምባገነኖች እርምጃ መለያ ባህሪያት
ናቸው፡፡ አምባገነኖችን አንድ የሚያደርጓቸው እነዚህ ባህሪያት ናቸው፡፡ አምባገነኖች ከታሪክ አይማሩም፡፡ የዛሬ 20 አመትም ሆነ
50 አመት ወደ ስልጣን የሚወጣ አምባገነን ይህን ነው የሚደግመው፡፡
መንግስት በኃይማኖቶች መካከል ልዩነት መፍጠር ይፈልጋል፡፡ እናንተ ክርስቲያኖች
የኃይማኖት ድንበር ጥሳችሁ ከእኛ ከሙስሊም ወንድሞቻችሁ ጋር መቆማችሁን እናደንቃለን፡፡ በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ
መብት በመቆም የሚያደርገውን ጥረት እናደንቃለን፡፡ እኛን ለመጠየቅ እስር ቤት ድረስ ስለመጣችሁ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ትግሉ ከዚህም
በላይ መስዋዕትነት ያስከፍላልና በርቱ፡፡››
ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ
‹‹ማዕከላዊ የገባነውን የመጀመሪያ ሰሞን ለእኛ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በማንኛውም
ጊዜ እስር ሊኖር ይችላል በሚል ማዕከላዊ የሚደረጉትን ነገሮች ለማሳወቅ እንጥራለን፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የጻፍናቸው ጽሁፎች ለዚህ
ያግዛሉ ብየ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም በእኛ ላይ ከደረሱብን ነገሮች ሌሎች ይማሩባቸዋለን ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ሲሆን የሚታሰሩ
ሰዎች የሚደርስበት ችግር አዲስ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ወደ ቂሊንጦ ከመጣን በኋላ የተሻለ ነገር ቢኖርም አሁንም ድረስ መጽሃፍና
ጋዜጣ አይባልንም፡፡
በጥቁሩ ሳምንት ዘመቻ ያደረጋችሁትን ነገር ሰምተናል፡፡ በጣም ደስ የሚል
ስራ ሰርታችኋል፡፡ መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን ደስ ብሎናል፡፡ እስሩ ቀጣይነት እንደሚኖረው ቢታወቅም፣ በየትኛውም ሁኔታ በርታትችሁ
እንድትቀጥሉ እፈልጋለሁ፡፡
በየቀኑ ጋዜጠኞች በሚደርስባቸው ጫና አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን እንሰማለን፡፡
ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡››
ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
‹‹ከመታሰሬ በፊት ማዕከላዊ ውስጥ ስለሚፈጸሙ በደሎች በተለያዩ ሪፖርቶች
ላይ ማንበብ ችዬ ነበር፡፡ ማዕከላዊ ከገባሁ በኋላ ያየሁት ግን ሰፊና ከጠበኩት በላይ ነው፡፡ በተለይ ትጥቅ ትግልን የመረጡ ተቃዋሚዎች
አባላት ናቸው የተባሉ አሊያም በሚዲያው የማይታወቁና ጠያቂ የሌላቸው አካላት ላይ የሚደርሰው በደል ዘግናኝ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ
ተማሪዎችም ተመሳሳይ ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡ ድሮ ማዕከላዊ ውስጥ ይደረጉ እንደነበር ሰምቼ ነገር ግን ይሆናሉ ብዬ የማላምናቸውን
ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጸሙ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡
የማዕከላዊ መርማሪዎች አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ ምርመራ ማድረግ ሳይሆን ጥፋተኛ
መሆናችንን እንድናምንላቸው ነው ሁሌም ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያነሱልን፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች በጣም የሚገርሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል
በምርመራ ወቅት ‹‹እከሌ ጋር ሻይ እየጠጣን›› ብለን የተናገርነውን ነገር እነሱ ‹‹ስብሰባ አድርገን›› ብለው ይጽፉታል፡፡ ሻይ
መጠጣት በእነሱ ስብሰባ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ የሚሰራው ህጋዊ ስራ ህገወጥ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለአብነት ያህል ሰማያዊ
ፓርቲ ግንቦት 25/2004 ዓ.ም ባደረገው ሰልፍ ተገኝቼ ፎቶ አንስቼ ነበር፡፡ ይህ ፎቶ ግራፍ በክስ ቀርቦብኛል፡፡ አስቡት በዚህ
ሰልፍ ኢቲቪና ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎችም ፎቶ አንስተዋል፣ ቪዲዮ ቀርጸዋል፡፡ መርማሪዎቹን ‹‹ይህ ስራዬ ነው፡፡ አያስወነጅለኝም››
ብትል አያምኑልህም፡፡ ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስም ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው ሰልፍ ላይ ተገኝተሃል የሚል ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡
በተመሳሳይ ዩጋንዳ እያለሁ ባቋቋምኩት ጋዜጣ ላይ ሙሃመድ ሰልማን ‹‹ፒያሳ
ሙሃመድ ጋ ጠብቂኝ›› በሚል ከጻፈው መጽሃፍ ላይ ያሉ ጽሁፎችን ጋዜጣው ላይ አውጥቻቸው ነበር፡፡ ሆኖም ይህም በክስ ቀርቦብኛል፡፡
‹‹መጽሃፍ ላይ ነው የወሰድኩት፡፡ መጽሃፉ ህጋዊ ሆኖ አገር ውስጥ ይሸጣል›› ብትል ማንም አይሰማህም፡፡ ፖሊስ ህዝብን ለመጠበቅ
የቆመ አካል ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ነገር ግን ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ገና ሳይፈረድብን ‹‹እናንተስ ለምን ሽብር ትፈጥራላችሁ?››
ያሉን ፖሊሶች አጋጥመውናል፡፡ ቀድመው ፈረዱብን ማለት ነው፡፡
በምርመራ ወቅት በጣም የሚያስገርሙ ነገሮች ተነስተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል
ጆን ኬሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ወቅት መርማሪዎቹ የሚገርም ጥያቄ አንስተውልን ነበር፡፡ ‹‹ጆን ኬሪ ጓደኛችሁ ነው?›› ብለው ጠይቀውናል፡፡
በጣም የሚገርም ነው፡፡ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን የእኛ ጓደኛ እንደሆነ አድርገው አቅርበውታል፡፡ ደግሞም ይህንንም ህገወጥ
አድርገው ነው የሚያቀርቡት፡፡ በሌላ በኩል አንዴ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ከግንቦት ሰባት ሌላ ጊዜ ደግሞ ከኦነግ ጋር ግንኙነት
እንዳለን ይገልጹልናል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በምንም መልኩ የሚገናኙ አይደሉም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ጋዜጠኛ የሚከሰሰው በመጻፉ አይደለም፡፡
በጋዜጠኝነት ብትከሰስ አንድ ነገር ነው፡፡ እነሱ ግን የሚያነሱብህ ክስ ሌላ ነው፡፡
ፌስቡክና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ የነበርን ሰዎች ያለመረጃ ስንቀመጥ
ከባድ ነው፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 75 ቀናት ነገሮች አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከዛ በኋላ ግን ቢያንስ ኢቲቪን መመልከት ችለናል፡፡
ኢቲቪ በሚያቀርባቸው ጉዳዮች ላይ የየራሳችን ትርጉም እየሰጠን አገራችን ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን ምን እየተካሄደ እንዳለ መረዳት እንችላለን፡፡
ወደ ቂሊንጦ ከመጣን በኋላ ነገሮች የተሻሉ ናቸው፡፡ ከጠያቂዎቻችን መረጃዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡››
ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34486
የቀድሞው የጋምቤላ መሪ በክልሉ ለደረሰው ጭፍጨፋ የህወሃት ባለስልጣናትን ተጠያቂ
ማድረጋቸውን ኢሳት ዘገበ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞት ኦባንግ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ 400 ሰዎች የተገደሉበት የጋምቤላው
ጭፍጨፋ እንዴት እንደተከናወነ በዝርዝር ሁሉን ነገር ተናግረዋል።
እንደ ኦሞት ገለጻ የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ አባይ ፀሐዬ
ግድያውን በተመለከተ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ያሉ ሲሆን በክልሉ ስለሚፈጸመው ሙስናና የመሬት ወረራ የቀድሞው ባለስልጣን በዝርዝር ተናግረዋል።
የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞድ ወደ ውጭ ከወጡ በኋላ ለመጀመሪያ
ጊዜ እንደሰጡት በተነገረው በዚህ ቃለምልልሳቸው ላይ 400 ሰዎች በግፍ በአባይ ፀሐዬ ከፍተኛ ሚና መገደላቸውን መዘርዘራቸው ወደፊት
በነዚህ ባለስልጣናት ላይ ለሚከፈተው ክስ ጥሩ ምስክር ሊሆን ይችላል ተብሏል።
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34458
የወያኔው መንግስት አላሰራ ያላቸው እና ጫናውን ያሳረፈባቸው ሶስት ጋዜጠኞች
አገር ለቀው መውጣታቸው ታውቋል።
በዚህም መሰረት
1ኛ/ ሚሊዮን ሹሩቤ – የማራኪ መጽሄት ባለቤት እና አዘጋጅ
2ኛ/ ኤሊያስ ጉዲሳ – የቃልኪዳን መጽሄት ባለቤት እና አዘጋጅ
3ኛ/ መድሃኒት ረዳ – የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ሪፖርተር
በገዛ አገራችው መስራት ስላልቻሉ እናት አገራቸውን ኢትዮጵያን ለቀው ተሰደዋል። የወያኒው መንግስት ከምርጫ 2007 ቀደም ብሎ ነጻ
ፕሬሶችን በማጥፈታ በራሱ አምሳል አዳዲስ ፕሬሶችን በመቅረጽ በ97 የደረሰበትን ሽንፈት አሁን እንዳይደርስበት በስፋት እየሰራ ሲሆን
ሕዝብ የመረጃ ደሃ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት በዚህ አመት ብቻ ወደ 30 የሚጠጉ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ ሌሎችን ደሞ ወደ እስር
ቤት እንዲገቡ አድርጓል።
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34414
በአፋር ክልል በረእሰ መዲናው በሰመራ የሚገኘው ብቸኛው ዩኒቨርሲቲ ለ10 ቀናት
ሲሰጥ የቆየው የተማሪዎች ሰልጠና ባለፈው ሰኞ ተጠናቀቋል። በስልጠናው የክልሉ የፓለቲካ መሪዎች የተገኙ ሲሆን በአጣቃላይ ሰለ መጭው
ምርጫ ቅስቀሳ እንደነበረ ምንጮችን ገልፆል።
እንደ ምንጮቻችን ዘገባ ከሆነ ለመጪውው ምርጫ ኢህአዴግን ምረጡ ካልመረጣቹሁ
ግን ስራ አታገኙም በሚል ብዙ ማሰፈራራት የበዛበት ስልጠና እንደነበረ ታውቋል።
በዚህ አመት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች በሰልጠናው የተገኙ
ሲሆን በተማሪዎች በኩል ለሚነሱ ወቅተዊ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማስፈራራትና ማስጠንቀቅ እንደነበረ ታይቷል።
በመጪው ምርጫ ኢህአዴግ እና የክልሉ ፓርቲ አብዴፓ በዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች
ላይ ያላቸው ድፍረት በግልፅ በታየበት በዚህ ስልጠና በክልሉ በግልፅ ስለሚታዩ ችግሮች ላይ የሚናገሩ ተማሪዎች ስማቸው እየተመዘገበ
እንደነበረ የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በዘንድሮው ምርጫ በመላው ኢትዮጵያ ሊነሳ ስለሚችለው ሁከት ተማሪዎችን ከወዲሁ
የማስጠንቀቅ ስልጣና ይመስላል ሲሉ አሰተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ 9 ክልሎች እስከ አሁን ብዙዎቹም የሚገባቸውን ያህል
ባይሆኑም በትምህርት አመስፋፋት ኋላ በመቅረት አፋር ክልል መሪነቱን ይይዛል።
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34308
የሸዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሽ ተጨማሪ 28 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡
ታሳሪዎቹ ዛሬ ጠዋት 3፡30 ላይ በአራዳ ምድብ ችሎት እንደሚቀርቡ ተነግሮ የነበር ቢሆንም ቀጠሮው ተቀይሮ 8፡30 ላይ በቀረበው
ችሎት ‹‹ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ›› በሚል ተመሳሳይ ምክንያት 28 ቀን ተቀጥሮባቸዋል፡፡ መስከረም 22/2007 ዓ.ም ይቀርባሉ
ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ ገልጸዋል፡፡
ችሎቱ ወደ ከሰዓት የተዛወረበት ምክንያት ‹‹ዳኛ ስላልነበረ ነው›› የተባለ
ሲሆን ችሎቱን ለመከታተል የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ተወካዮችን ጨምሮ በርከት ያለ ህዝብ ቢገኝም ቤተሰብም ጭምር ችሎቱን መከታተል
ሳይችል ቀርቷል፡፡
ለዚህም የተሰጠው ምክንያት ‹‹ችሎቱ በጽ/ቤት የተካሄደ በመሆኑ ተመልካች አይይዝም›› የሚል መሆኑን ጠበቃ ተማም
ገልጸዋል፡፡
ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ ቀጠሮውን አስመልክቶ ‹‹እስካሁን የምታቀርቧቸው
ምክንያቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡
2 ጊዜ 28 ቀን ሲቀጠርባቸው ምንም ሳትሰሩ ነው የመጣችሁት፡፡ አሁንም ተጨማሪ 28 ቀን ተቀጥሮባቸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ደንበኞቼ እየተጉላሉ ነው፡፡›› በሚል ውሳኔውን መቃወማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ጠበቃው ታሳሪዎቹን ከቤተሰብ ውጭ ማንም እንዳይጠይቃቸው እየተደረገ
መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ዳኞቹ እንደተለመደው ‹‹በሌሎች ዘንድም ሊጠየቁ ይገባል›› የሚል ትዕዛዝ እንደሰጡ ታውቋል፡፡
ጠበቃ ተማምም በበኩላቸው ‹‹ፍርድ ቤት ሁል ጊዜም ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ግን ተግባራዊ ሲሆን አይታይም፡፡›› ሲሉ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው
ትዕዛዝ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34222
ብስራት ወ/ሚካኤል
በተለያዩ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች የራሱ “አዲስሚዲያ”
ብሎግን ጨምሮ በተለያዩ ድህረ-ገፆች አዘጋጅ እና ፀሐፊ ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤል መሰደዱ ታወቀ፡፡ ጋዜጠኛው ቀደም ሲል የፍኖተ-ነፃነት
ጋዜጣ አዘጋጅ፣የኢቦኒ መፅሔት ዋና አዘጋጅ፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ኢሳው መፅሔት ባልደረባና አምደኛ፤ በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣና
በቅርቡ ወደህትመት የገባው ቀዳሚ ገፅ ጋዜጣ ላይም የተለያዩ የፖለቲካ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ
በራሱና በብዕር ስም እንደሚፅፍ ይወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተመሰረተውና በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥርና ጫና ላይ የወደቀው የኢትዮጵያ
ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) መስራች አባል፤ በኋላም የማኀበሩ ትምህርትና ስልጠና ኃላፊ በመሆን እያገለገለ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛው ከዚህ በፊትም በመንግስት ደህንነት ኃይሎች በምሽት እገታ እንደገጠመው፣ ከስልክ ጠለፋ እስከ ዛቻና ማስፈራራት ይደርስበት
እንደነበር ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች ቢያመለክቱም፤በተለይ ከጥቅምት 2006 ዓ.ም. ከአዲሱ ጋዜጠኞች ማኀበር መመስረት ሂደት
ጀምሮ እና በሚያዚያ ወር 2006 ዓ.ም. 3 ጋዜጠኞችን እና 6 የዞን 9 ብሎገሮች በመንግስት ከታሰሩ በኋላ የመንግስት ደህንነቶች
ክትትል ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ቀጣዩ እስር እሱ ላይም ሊፈፀም እንደሚችል በመረዳት ለቅርብ ጓደኞቹ አሳውቆ
ነበር፡፡
ብስራት ባለፈው ነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. አርብ ጠዋት አዲስ ባወጣው የስልክ መስመር የማዕከላዊ ስልክ ጥሪ ካስተናገደ በኋላ
ለጊዜው ከአዲስ አበባ ውጭ መሆኑን በማሳወቅ ለሰኞ እንደሚቀርብ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ባለፈው እሁድ ድንገት ሀገር ጥሎ መሰደዱ ታውቋል፡፡
በቅርቡ ከታሰሩት ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የእስር ስም ዝርዝር ውስጥ የማኀበሩ አመራሮች መኖራቸውና በቀጣይም መንግስት በአመራሮቹ ዙሪያ
መረጃ እየሰበሰበ መሆኑ ምንጮች አረጋግጠው እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የማኀበሩ ፕሬዘዳንት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ፣ የህዝብ
ግንኙነት ኃላፊው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ፣ ገንዘብ ያዥ ጋዜጠኛ ሃብታሙ ስዩም እና መስራች አባል ጋዜጠኛ ተሰማ ደሳለኝ መሰደዳቸው
አይዘነጋም፡፡ በአጠቃላይ ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤልን ጨምሮ በ2006 ዓ.ም. ብቻ 25 የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ፤3 የውጭ ዜጎች
ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ደግሞ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34148