Wednesday, September 10, 2014

በፕሬሱ ላይ የተመዘዘው ሰይፍ


መረጃ የማግኘት ነጻነት ከዋነኞቹ የዴሞክራሲ መገለጫዎች ወይም እሴቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ መረጃ የማግኘት ነጻነቱ የተከበረለት ህዝብ በሀገሩ የስልጣን መንበሩ ላይ የተቀመጠውን አስተዳደር (መንግስት) የመቆጣጠር ኃይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደርና ሌሎችን ንቅዘቶች በማጋለጥ የመንግስትን ተጠያቂነት በማስፈን ሂደት ውስጥ ህዝብ ንቁ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ መረጃ የማግኘት ነጻነቱን ሊጎናጸፍ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መረጃ የሚያደርሱት ሚዲያዎች በስፋት መኖር የግድ ነው፡፡ ለዚህም ነው በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚዲያ (ፕሬስ) ሚና እንዲጎላ የሚደረገው፡፡

በተቃራኒው በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ገዥዎች የሚዲያ (ፕሬስ) ነጻነትን በማፈን ህዝብ መረጃ እንዳያገኝ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ አምባገነኖች ስርዓቱን የሚተቹ የፕሬስ ውጤቶችን ይዘጋሉ፣ ጋዜጠኞችን ያስራሉ፣ ያሳድዳሉ፣ አለፍ ሲልም ይገድላሉ፤ ያስገድላሉ፡፡ አምባገነኖች ለይስሙላ የሚዲያ ነጻነት መረጋገጡን የሚያሳዩ ህጎችን በማውጣት በውጭ ሆኖ ለሚመለከታቸው አካል ዴሞክራት በመምሰል በውስጥ ተግባራቸው ግን ካወጧቸው ህጎች ፍጹም ተቃራኒ በመሆን የአፈና ስራ ያከናውናሉ፡፡ የግል ፕሬሶችን በቀጥታም ሆነ በእጃዙር ጨምድዶ በመያዝ፣ ፕሬሶች ህጉን ተከትለው በፈቃዳቸው ያሻቸውን እንዳይሰሩ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ አይነቶቹ የአምባገነኖች ተግባራት በበርካታ ሀገራት ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡

ለአብነትም ለረጂም አመታት ቻይናን እየገዛ ያለው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በሀገሩ የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ውጤቶች ላይ ባሻው ጊዜ ሁሉ ህገ-ወጥ እርምጃዎችን በመውሰድ ይታወቃል፡፡ ይኸው የቻይና ገዥ በ2012 ብቻ ከ16 በላይ ዌብሳይቶችንና ብሎጎችን ከርችሟል፡፡ ይህ አምባገነን ስርዓት በምድረ ቻይና የመረጃ መረብ እቀባ በማድረጉ ምክንያት፣ ሀገሪቱ በተለያየ ጊዜ ከታዋቂዎቹ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች ጎግልና ያሁ ድረ-ገጾች ጋር አተካራ ውስጥ ስትገባም ይታያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቻይና በሀገሯ የሚታተሙ ጋዜጦችንና መጽሔቶችንም በመክሰስና በመዝጋት ስሟ በአሉታ ይነሳል፡፡


ቻይና ዲንግ ዲያን የተሰኘውን ከፍተኛ ተነባቢ ሳምንታዊ ጋዜጣ እ.ኤ.አ በ2006 መዝጋቷንም እዚህ ጋር እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ የቻይና ገዥዎች ጋዜጣውን የዘጉት በሀገሪቱ ያለውን የማህበራዊ ቀውስ፣ በሙስና የተጨማለቀውን አስተዳደር፣ በከተሞች ያለውን የከፋ የአየር ብክለት፣ ያልተመጣጠነ የዜጎች የደመወዝ ክፍያን፣ ልቅ የመሬት ይዞታን እና ሌሎች ችግሮቹን በተከታታይ ማጋለጡን ተከትሎ እንደነበር ይወሳል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የቻይና መሪዎች ትችትን ለመቀበል አለመፍቀድ እንዲህ አይነት እርምጃዎችን እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡ ቻይናውያን ጋዜጠኞች በቻይና መንግስት የሚወሰደው እርምጃ ፍጹም ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው ሲሉ ቢከራከሩም ሰሚ አግኝተው የሚያውቁ አይመስሉም፡፡

በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ያለው እውነታም ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ በእነዚህ አምባገነን ስርዓቶች ገዥዎች ፕሬሱ በተቋም ደረጃ ጎልብቶ በሁለት እግሩ እንዲቆም የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የራሳቸውን የግል ስልጣን ጠብቆ ለመቆየት ነጻ ፕሬሶችን ሰለባ ያደርጓቸዋል፡፡ በእርግጥም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ፣ አምባገነኖች በነገሱባት ሀገር ፕሬሱና ሙያተኛው በነጻነት ተደራጅቶና ጎልብቶ ተቋም እንዲመሰርት አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህም ይመስላል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በ2009 አፍሪካን ሲጎበኙ ጋና አክራ ላይ ‹‹አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን (መሪዎችን) ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትን ነው የምትሻው›› ሲሉ ሀቁን የተናገሩት፡፡
በእርግጥም አፍሪካ ጠንካራ ተቋማት የላትም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የጠንካራ ተቋማት እጦት ችግር ደግሞ ከብዙ የአፍሪካ ሀገራትም የከፋ ነው፡፡ በተለይ ለሌሎች ተቋማት መጎልበት አይነተኛ ሚና የሚጫወተው የሚዲያ ተቋም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ምንም በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አምባገነኖቹ ገዥዎች ድክመቶቻቸውን በሚያጋልጥባቸው ሚዲያ ላይ የሚወስዱት ህገ-ወጥ እርምጃ አሉታዊ ሚና አለው፡፡

ፕሬሱ ላይ የተመዘዘው አዲሱ ሰይፍ

የኢህአዴግ ገዥዎች ፕሬሱን በማዳከም ሂደት ላይ ከቻይና ‹‹ምርጥ ተሞክሮ›› ሳይወስዱ አልቀሩም፡፡ ልክ እንደ ቻይና ሁሉ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ ዌብሳይቶችን…ይዘጋሉ፤ ይከስሳሉ፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነጻነት ህገ-መንግስታዊ እውቅና አግኝቷል፤ ዋስትና ግን የለውም፡፡ ምክንያቱም ህገ-መንግስታዊ እውቅና ያገኘው የፕሬስ ነጻነት በተለያዩ አፋኝ አዋጆች ዋስትናውን አጥቷል፡፡ የፕሬስ ተቋማትም ሆነ ሙያተኞች (ጋዜጠኞች) ህገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት ለመስራት ሲንቀሳቀሱ በተለያዩ ተልካሻ ምክንያቶች በህገ-ወጥ እርምጃ በተደጋጋሚ ተደናቅፈዋል፤ እየተደናቀፉም ይገኛሉ፡፡ በዘመቻ መልክ የግሉን ፕሬስና ጋዜጠኞችን የማሳደድ ስራ ከተከናወነበት ምርጫ 97 ጀምሮ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ይህን ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተቸረውን ነጻነት ሲገረስስ ታይቷል፡፡

አስገራሚው ጩኸት ደግሞ ኢህአዴግ እነዚህን የአፈና ስራዎች ሲሰራ ‹ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ› በሚልና በልማት ሽፋን መሆኑ ነው፡፡ ህግን እየጣሱ ህግን ለማስከበር ስል ነው የሚለው የኢህአዴግ መንግስት ከሰሞኑ ደግሞ ሌላ የአፈና መስመርን ዘርግቷል፡፡ ይኸውም ‹‹ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአመፅ ለመናድ በማሴር የተጠረጠሩ የህትመት ውጤት አሳታሚዎችና ድርጅቶች›› ላይ በ‹ፍትህ ሚኒስቴር› አማካኝነት ክስ መመስረት ነው፡፡

ተጠርጣሪ ተከሳሽ አሳታሚዎችና ድርጅቶች የክስ ቻርጅ ሳይደርሳቸው እንደማነኛውም ሰው የስርዓቱ አፍ በሆነው በኢቴቪ መስማታቸውን የገለፁት የክስ ይዘት፣ ለብዙዎቻችን ግርምትን የሚያጭር ነው፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር መግለጫ ስለጉዳዩ ሲያትት እንዲህ ይላል፤ ‹‹በየጊዜው ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የአመፅ ቅስቀሳና የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት፣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል እንዲፈረስ እና ህዝብ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ የወንጀል ተግባራትን በመፈፀም ተጠርጥረዋል፡፡››

ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ተነባቢነት እንዳላቸው የሚታወቁት አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ናቸው፡፡ እነዚህም ፋክት፣ ጃኖ፣ ሎሚ፣ አዲስ ጉዳይ እና እንቁ መፅሄቶችና አፍሮ ታይምስ የሚባል ጋዜጣ አሳታሚዎችና ድርጅቶች ናቸው። ምናልባትም ኢህአዴግ ክሱን ለመመስረት መስፈርቱ ፕሬሶቹ ከፍተኛ ተነባቢነት ማግኘታቸው ሳይሆን አይቀርም፤ አለበለዚያም በምንም አይነት መልኩ ምንም ባደርግ አትተቹኝ ባይነት መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ ለመሆኑ ‹‹…ህዝብ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ በማድረግ…›› ማለት ምን ማለት ነው? ሲጀመርስ ስርዓቱ በህዝብ ዘንድ አመኔታ አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

ይህን መሰሉ የመንግስት እርምጃ የግሉ ፕሬስና ጋዜጠኞቹ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ኢህአዴግ ጠንቅቆ የሚያውቀው ይመስላል፡፡ ከአሁን በፊት እንደታየው ከሆነ መንግስት እነዚህን መሰል አሳታሚዎች ክስ ሲመሰርትባቸው ጋዜጠኞቹና አሳታሚዎቹ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ የበፊት ተሞክሮው ማህደር የሚነግረው እውነታ አለ፡፡ የኸውም ጋዜጠኞቹና አሳታሚዎቹ ክሱ በሚያሳድርባቸው ጫና ሀገር ጥለው መኮብለል፣ አልያም ስራቸውን እርግፍ አድርገው መተው እንደሆነ አይቶታል፡፡ ይህን አይነት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል የሚወጣ ‹መረጃ› እነ አዲስ ነገርና አውራምባ ታይምስን የመሳሰሉ ጋዜጦችን ከህትመት ውጭ አድርጓቸው እንደነበርና ጋዜጠኞችንም ለስደት እንደዳረጋቸው ኢህአዴግ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የዚህኛው ክስ ጉዳይም ከዚህ ጋር የተመሳሰለ ምላሽን እንዲያስገኝለት በማሰብ የመሰረተው ክስ ሊሆን ይችላል፡፡

የራሷ ሲያርባት…

አንዳንዴ ከራስ ግዙፍ ጉድፍ ይልቅ የሌላን ጥቃቅን ችግር ማየት የተለመደ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ መንግስት በእነዚህ አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ላይ የመሰረተው ክስ ተገቢነት የሚኖረው ከሆነ ኢህአዴግም በተመሳሳይ የሚከሰስባቸው አግባቦች መኖራቸውን ልብ ያለው አይመስልም፡፡ ይኸውም መንግስት በራሱ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ሚዲያዎች ዘወትር ህዝብን ባዶ ተስፋ እየመገበ ከማወናበዱ በተጨማሪ፣ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ኃይላት ከህዝብ ለማራቅ የሚያደርሰው የስም ማጥፋትና ማጥላላት አልታወሰውም፡፡ መቼም በዶክሜንተሪ ፊልም ስም በተለያዩ አካላት ላይ የሚሰራው ስራ ምን ያህል ጤነኛ እንዳልሆነ ከራሱ ከኢህአዴግ ሰዎች የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡

ስለሆነም መንግስት አሳታሚዎችንና ድርጅቶችን ‹‹…የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል እንዲፈረስ እና ህዝብ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ የወንጀል ተግባራትን በመፈፀም…›› ከጠረጠረና ከከሰሰ፤ እሱ ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ‹‹ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር›› እያለ ስማቸውን ሲያጎድፍ እንዴት አያፍርም ያስብላል፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን መንግስት ምርጫ 2007 ዓ.ም ሳይደርስ ህዝብ መረጃ የሚያገኝባቸውን ፕሬሶች ከወዲሁ ከመስመር እንዲወጡ ማድረጉን ተያይዞታል፡፡ ቀደም ብሎ በተለያዩ ፕሬሶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ጦማሪያን ላይ ሲወስደው የቆየውን እርምጃ አሁንም ገፍቶበታል፤ ገናም ይቀጥልበታል፡፡ ለዚህ ማሳያ ምልክቶች የሚሆኑት ደግሞ በአሳታሚዎችና ድርጅቶቹ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ቀጣይ መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ በግልጽ መናገሩ ነው፡፡ ‹‹በህገ-መንግስቱ የተበጁትን ገደቦች በማን አለበኝነት በመጣስ ስራዬ ብለው ብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ በሚጥል መልክ አመፅና ሁከትን የሚቀሰቅሱ፣ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን የሚያወድሱ እንዲሁም የሚያበረታቱ፣ በህዝቡ መሃከል የዘርና የሃይማኖት ጥላቻን የሚቀሰቅሱ፣ የህዝብ መሪዎችንና የተቋማትን መልካም ስምና ዝና በሀሰት የሚያጠፉና የሚወነጅሉ አንዳንድ ህትመቶች እንዳሉም ሊታወቅ ይገባል›› ሲል ማስፈራሪያ አዘል መግለጫውን አሰምቷል፡፡

‹አያ ጅቦ…›

አሁን በአምስቱ የመጽሔት እና አንድ ጋዜጣ አሳታሚዎች ላይ የተመሰረተው ክስ ብዙ የተንሸዋረሩ ምክንያቶችና ሰበቦችን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባስጠናው ‹የአዝማሚያ ጥናት›፣ መሰረት ‹‹አብዛኛዎቹ በህትመት ላይ ያሉ መጽሔቶች የጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልሳኖች ናቸው›› ሲል ድምዳሜ ላይ መድረሱ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህም የኢህአዴግ መንግስት በ‹ጥናት› አረጋግጠናል በሚል ‹‹አያ ጅቦ ሳታማሃኝ ብላኝ›› ማለቱ እንደሆነና በቀጣዩ እርምጃ ሊወሰድባቸው የተመረጡ ፕሬሶች መኖራቸውን ያሳየ ነበር፡፡ በዚህም አሁን ክስ የተመሰረተባቸው የፕሬስ አሳታሚዎች በዚያ ‹ጥናት› ስማቸው በክፉ ተነስቶ ጥርስ የተነከሰባቸው እንደነበሩ ማየቱ በቂ ነው፡፡

ሌላው ማመሃኛ ወይም ማደናገሪያ ደግሞ መንግስት ‹ይኽን ክስ እንድመሰርት የተገደድኩት በህዝብ ግፊት ነው› ለማለት የሞከረበት ድንግርግሮሽ ነው፡፡ ‹‹የጥቃታቸው ሰለባ የሆነው ህዝብ በእነዚህ የህትመት ውጤቶች የህግ ከለላ በተሰጣቸው ጥቅሞቹ ላይ ያለማቋረጥ የሚደርሰውን ጥሰት ለማስቆም መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በተለያዩ መንገዶች ሲጠይቅ ቆይቷል›› ይላል መንግስት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል በሰጠው መግለጫው፡፡

በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት ከረጂም ጊዜ ተሞክሮው እንደታየው አካሄዳቸው ያላማረውን (የሚተቹትን፣ ድክመቶቹን የሚያጋልጡትን) ማናቸውንም የግል ህትመት ውጤቶች በተለያዩ ዘዴዎች ከመስመር ማስወጣቱን ልብ ማለት ይቻላል፡፡ መንግስት አዲስ ዘመንን፣ ኢቴቪንና አይጋ ፎረም የመሳሰሉ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሰፊ ማጥላላት ሲከፍትባቸው የነበሩትንና ያሉትን ፕሬሶችና ጋዜጠኞች ስንመለከት ኢህአዴግ ህግ የማይገዛው፣ በአንጻሩ ግን ህግን በማስከበር ስም ሌሎች ላይ ጥቃት እያደረሰ የሚገኝ መሆኑን እናያለን፡፡

ተቋም እንዳይኖር ማድረግ

ኢህአዴግ ፕሬሱ በተቋም ደረጃ እንዲጎለብት አይፈቅድም፡፡ ስለሆነም የግል ፕሬሱ እንደ ፕሬስም ሆነ ጋዜጠኞቹ በነጻነት ተደራጅተው ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ አይደረግም፡፡ በዚህ አመት ላይ ራሳቸውን በማህበር ለማደራጀት የሞከሩ ጋዜጠኞች እንኳ እጣፈንታቸው ከመበታተን ያለፈ አልሆነም፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ጫና አሉታዊ ሚና አለው፡፡ ለምሳሌ ሁለቱ አመራሮች (የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ እና የህዝብ ግንኙነት የነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ) ስርዓቱ ባደረሰባቸው ጫና ሀገር ጥለው ተሰድደዋል፡፡

ኢህአዴግ መደራጀት መብት ነው ሲል፣ በራሱ ማዕቀፍ ጥገኛ እስከተሆነ ድረስ ማለቱ እንደሆነ በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ላይ ነጻና ገለልተኛ ማህበራትን ማየት ብርቅ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም በየማህበራቱ የኢህአዴግ እጅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አለ፡፡ ስለሆነም የፕሬሱን ጉልበት ማዳከሚያ ዋና መሳሪያው ያገባኛል የሚሉ አካላት በነጻነት እንዳይደራጁ ማድረግ ነው፡፡
እስካሁን ድረስ የግል ፕሬሱ አንድ የጋራ ጠንካራ ማተሚያ ቤት እንኳ ሊኖረው አልቻለም፡፡ ፕሬሱ የአንጋፋ የመንግስት ማተሚያ ድርጅት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጥገኛ ነው፡፡ ሌሎች የንግድ ማተሚያ ቤቶችም ቢሆን አንድም አቅማቸው የሚያወላዳ አይደለም፤ ሁለትም በተዘዋዋሪ መንገድ በስርዓቱ ተጽዕኖ ስር የወደቁ ናቸው፡፡

የተመዘዘውን ሰይፍ ለማጠፍ…


በአጠቃላይ አሁን ያለው የሀገራችን የፕሬስ ነጻነት እጅግ አሳሳቢና አደገኛ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡ እስካሁን ከተለመደው የጋዜጠኞቹ እስርና ድብደባ እንዲሁም ስደት በከፋ ሁኔታ አሁን ደግሞ አሳታሚዎች ላይ ክስ መመስረት መቻሉ መንግስት ምን ያህል የግል ፕሬሱን ማሽመድመድ እንደፈለገ ጉልህ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ይህን በፕሬሱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማቃለል የተደራጀ ርብርብ በሚመለከታቸው ተቆርቋሪ አካላት ዘንድ መደረግ ይኖርበታል፡፡ መንግስት ህገ-መንግስቱን አክብሮ ፕሬሱ በነጻነት እንዲቀሳቀስ መፍቀድ ግዴታው መሆኑን በተለያዩ ስልቶች (ለምሳሌ የፕሬሱ አባላት የሚያስተባብሩት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ፣ የተዘጉ ፕሬሶችን የቀደሙ ኮፒዎች ይዞ በአደባባዮች በህብረት መታየት፣ አፍን በጥቁር ፕላስተር አሽጎ ተቃውሞን መግለጽ…) በመሳሰሉት ማስገደድም የተገባ ይሆናል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/34447

No comments:

Post a Comment