Tuesday, December 9, 2014

ተንበርክኮ ከመኖር በዓላማ ፀንቶ መሞት ይሻላል!! – በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ

                ተንበርክኮ ከመኖር በዓላማ ፀንቶ መሞት ይሻላል!!

በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ዝነኛው ገጣሚና መምህር ኃይሉ ገብረዮሐንስ በስደት
ከሚኖርበት አገር ስዊድን( ስቶኮልም ከተማ) ጥቅምት መጨረሻ 2007 ዓ.ም ማረፉን የሰማው በከፍተኛ ሀዘን ነው።

ሃይሉ ገብረዮሐንስ በመምህርነት ሙያው እንደ አንድ ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመፍጠር
የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል። የዚያ ትውልድ ግንባር ቀደም የለውጥ ሃዋሪያ ሰለሆነም የአገር ባለውለታ ነው።
በተፈጥሮ ባገኘው ተሰጥኦና በትምህርት ባዳበረው ገጣሚነት ቀስቃሽ ፣አነቃቂ፣ ትምህርታዊ፣ ፍልስፍናዊና ሥነ ጥበባዊ
የሆኑ ግጥሞችን በማቅረብ ይታወቃል። ገሞራው ከወጣትነት እድሜው ጀምሮ ለጭቁን ህዝቦች አርነት መውጣት
በፅናት የታገለና በተግባር ያስመሰከረ ነው። እምቅ መልዕክት በያዙት ግጥሞቹ የተነሳም ስቃይ፣ ግርፋትና እስር
ደርሶበታል።

ሃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ከዛሬ አስራ ሁለት አመት በፊት በ “ኢትኦጵ” መፅሄት፣ ቅፅ 2 ፣ ቁጥር 020 እንደ
ኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 1995 ዓ.ም እትም ላይ ስላለፈው ሕይወቱ እንዲህ ብሎ ነበር።

“በተፍፃሜተ ዘመነ ነገስት ወቅት እኔ የተሰለፍኩበት የብዕር ትግል እጅግ ጎልብቶ ነበር፤ የእኔም ብዕር እንዲህ እንደዛሬው
ከመዳከሙ በፊት እጅግ ስል ስለነበረ ብልት እየመረጠ ይጠዘጥዝ ነበር። ከታህሳስ መፈንቅለ መንግስትና ሳኒታ ላይ
‘ሲኦል’ የምትል ግጥም በዩኒቨርስቲው መድረክ ላይ ይዤ ብቅ ብል ገነቲቱን አገር ኢትዮጵያ ሲኦል አላት ብለው ጅራፍ
አለንጋቸውን ይዘው መግረፍ ጀመሩ። ከዩኒቨርስቲው አባረሩኝ፤ ያለትምህርትና ያለስራ ብዙ ወራት አሳለፍኩ፤ እንደገና
ስመለስ ይግረማችሁ ብዬ ‘በረከተ መርገምን’ ይዤ ቀረብኩ። አበዱ የህቡእ ወረቀቶችን ሳሰራጭ በማውቃቸው ሰዎች
ጠቋሚነት ተይዤ ተቀጠቀጥኩ። በሀገሪቱ ሚዲያ “መርዘኛው ብዕረኛ” (poison pen writer)(በአዲስ ዘመን ጋዜጣ
ላይ በ1966 ዓ.ም ነበር የወጣው) የሚል ዓዋጅ ታወጀብኝ ቤተ ወፌ ላላም ሰቅላ በመግረፍ የተግባር ግዳጇን ተወጣች።
ያ ሁሉ የብዕር አመፅ የፈጠረው ዋጋ ነበር። “ በማለት ነበር ስላለፈው የጨለማ ዘመን የተናገረው።

ሃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) የጻፋቸው ግጥሞች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉና ዘመን ተሻጋሪ ናቸው።
ህይወቱን ሙሉ መከራና ስደት ሳይበግረው እየተንከራተተ ለራሱ ያልኖረ፣ ሀቅን ይዞ ለተበደሉ ዜጎች ሲሟገትና አገሬ
ኢትዮጵያን እያለ ለእኩልነት መስፈን ሕይወቱን የሰጠ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር። ኃይሉ ገብረዮሐንስ “በረከተ
መርገም” በሚል ያሳተመውን መፅሃፍ መዘክር ወይም መታሰቢያ ያደረገው ለመብት አልባ ዜጎች ሁሉ ነው።
በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ የዚህን የለውጥ ፋና ወጊ ምሑር ህልፈት የሚገልፀው
በመሪር ሃዘን ነው። ከዚህ በታች የሚገኘውን አጭር ግጥምም ለመታሰቢያነት ያቀርባል፡

ገሞራው ( ኃይሉ ገብረዮሐንስ)

ቅኔ ዘራፊ ሊቅ - ተመራማሪ ፈላስፋ፣
ዕውነትን ተመርኩዞ - እንደጠበቃት የለፋ፣
አገሩንና ዕምነቱን - ጉግማንጉጎች እንዳያረክሱ፣
የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች- ሉዓላዊነቷን እንዳይገሱ፣
ሲከላከል የኖረ - በተባ ብዕሩ በእርሳሱ፣
ምን ላንዲት ኢትዮጵያ - ለአፍሪካና ለመላ ዓለሙ፣
የሰው ልጆች በተዘሩበት - በምድሪቱ ለታደሙ፣
ፍትህ- ርትእ - ብልፅግና በእኩልነት፣
እያለ በመዋተት - ቆጠረ የስንቱን ቤት፣
ቻይና - ኖርዌይ - ስዊድን፣
ምኞቱም አልሰመረ - ከሕመሙም ቀረ ሳይድን።
እሳተ ገሞራው ኃይሉ - ያሰረፀው ቁም ነገር፣
ውሎ ቢያድር እንጂ - መሆኑማ መች ሊቀር?!
ለወደድናቸው የምንሞት - ለጠላቶቻችን መጋኛ ፣
እምነቱ - ጽናቱ - ኃይሉ- ኃይል ይሁነን ለእኛ።
አርአያነቱን እንከተል!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች!!

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/36958

No comments:

Post a Comment