ላለፉት 23 አመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተቀምጠውን ዘራፊውን እና ጨቋኙን የወያኔ ጁንታ በጀመርነውና በተያያዝነው አዲስ አመት ለመቅበር የአንድነት እና የለውጥ ሃይሎች ልዩነቶቻችንን በማቻቻል በጋራ ልንታገል የሚገባና ለህዝባችንና ለሃገራችን ስር ነቀል ለውጥ ልናመጣ የሚያስችለንን ምዕራፍ የምንጀምርበት አመት መሆን አለበት። ባሳለፍናቸው በርካታ የትግል አመታት ውስጥ የተቃዋሚዎች እርስ በእርስ መፈራረጅና መወነጃጀል የወያኔን እድሜ ከማራዘም ውጪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያተረፈው አንዳችም ነገር የለም። የአንድነት የተቃዋሚ ሃይሎች ጥንካሬ እንዲጎለብት በየድርጅቱ ውስጥ ያሉትን እንከኖች በማጥራት በጋራ እና በተቻቻለ የሃሳብ መግባባት ተቻችሎ እና ተግባብቶ ሁለገብ የትግል ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል።
ኢትዮጵያ ሃገራችን ሀሳብን በነፃነት ያለፍርሀት መግለፅ የማይቻልባት፤ የዜጎች የኑሮ ደረጃ ከዕለት ዕለት እየተባባስ የሚሄድባት፤ ዘመናዊ የመረጃ መገናኛዎች ሆን ተብለው የታገዱባት፤ የህዝቦቿን ጥንታዊና ብርቅዬ የሆነውን መከባበርና አንድነት በዘር ጥላቻና በሀይማኖት ለመከፋፈል አገዛዙ የሚጥርበት፤ ዜጎች አለአግባብ የሚታሰሩባት፣ የሚገደሉባት፤ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰደዱባት፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያልተካሄድባት፤ ዜጎች ከመኖሪያቸውና ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉባት፤ ለሕግ ተገዢ ያልሆነ መንግሥት ያለባት፤ ዜጎች የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ በስተቀር በነፃነት ሠርተው መኖር የማይችሉባት፤ ነፃ ሚዲያ የሌለባት፤ ዜጎች ለሀብት ንብረታቸው ዋስትና የማያገኙባት፤ ህዝባዊ መንግሥት የሚናፍቅ ህዝብ ያለባት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ መጠቀሚያ የሆኑባት፤ ቤቶች በቁመታቸው ማደጋቸው እንደዕድገት የሚቆጠርባት ሀገር ሆናለች።
የኢትዮጵያን አንድነት ከጥያቄ ውስጥ ያስገባውና የመበታተን አደጋ ላይ የጣለው፣ የዘር መርዝ በመርጨት ሌት ተቀን በመስራት ላይ የነበረው መለስ ዜናዊና በሱ ስር የሚመራውና ጥሎት የሞተው የኢሕአዴግ ጎሰኛ ስብስብ ነው። ይኸው ጎሰኛ ስብስብ ለመበታተን የሚረዳ አስተሳሰቡን ሕጋዊ ሽፋን በመስጠት በአንቀጽ 39 ደንግጎታል። የዛ ጥንስስ ነው አሁን በየቦታው ለሚካሄደው የጠባብ ጎሰኛ እንቅስቃሴ ማንሰራራት ምክንያት የሆነው። ለሕዝቡ የተሻለ ኑሮ፣ ለዲሞክራሲና ሰላም፣ ለአገር አንድነት እናስባለን የሚሉ ሁሉ ይህን አጥፊ ሂደት ሊቋቋሙት ይገባል። በተለይም የየማህበረሰቡ የተማረው ክፍል ከጎጥ ዋሻ ወጥቶ በሚያውቀው ከባቢና ቋንቋ የሚስተጋቡትን የጥፋት ቅስቀሳዎች መቃወም ይኖርበታል። አሁን ሁሉም የሚፈተንበት ወቅት ነው። ማን ለሰላም፣ ማን ለሰው ልጆች በጎ ነገር፣ ማን ለሰብአዊ መብት፣ ማን ለአንድነትና አገራዊ ነጻነት እንደቆመ የሚታይበት ጊዜ ነው። እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ የቤት ስራዎችን መስራት የግድ ይላል። ለዚህም ነው እኛ የአንድነት ሃይሎች ከትንሽነት ብዙነት፣ ከጠባብነትም ሰፊነት ይሻላል የምንለው።
በእድገት ተራምደዋል በሚባሉት ሃገራት የምንኖር ለዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ግንባታ የጋዜጠኝነት፣ የመፃፍና የሚዲያ ነፃነት ምን ያህል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያረግ እንዲሁም በዲሞክራሲ ላይ በተመሰረቱ የሃገራት ውስጥ የመፃፍ፣ የመናገርና የነፃ ሚዲያዎች መኖር ምን ያህል ታላቅና ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እያየንና እያስተዋልን ነው። ነገር ግን እንደሃገራችን ኢትዮጵያ አይነት የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ስርዓት ይቅርና እጅግ መሰረታዊ የሚባሉት ሰብዓዊ መብቶች በእንጭጩ የተቀበሩባት ሃገር መናገርና መፃፍ እንደወንጀል እየተቆጠረ ነው። ከብዙ በጥቂቱ ሰሞኑን በዞን 9 ጦማርያን ላይ፣ ቀደም ብሎም በጋዜጠኞቹ በእስክንድር ነጋና በርዕዮት ዓለሙ ላይ የደረሰውን ማየቱ ብቻ በቂ ይሆናል። ሀገርንና ህዝብን አስተዳድራለሁ ብሎ ከዜጎች ይሁንታ ውጪ ስልጣኑን የተቆጣጠረው እንደ ወያኔ ያለ አምባገነናዊ ስብስብ 'እንዴት የአስተዳደር ችግሮቼ በጋዜጠኛና በብሎገሮች ፅሁፍ ይተቻል፣ እንደፈለገሁ አስራለሁ/ እገድላለሁ' ብሎ ለሃገርና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል በጎ ሃሳብና መፍትሄ የጠቆሙና ያወያዩ፥ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትና ለሃገር ማደግ በጨዋነት እይታቸውንና እውቀታቸውን ለማካፈል ብዕራቸውን ያነሱ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ሁሉ እየሰበሰቡ የሌለባቸውን የ'ሽብርተኛነት' ስም እየሰጡ በየእስር ቤቱ ማጎር፣ ፍትህን ማጓደልና የፍርድ ሂደቱንም አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ እስኪሆን ድረስ በማራዘም ሌሎችንም በማስፈራራት መወያያና የመማማርያ መድረኮችን ማፈን ብሎም እንዲጠፉ ማድረግ ለጊዜው ከሆነ ነው እንጂ በዘላቂነት የትም አንደማያደርስ ወያኔ ከወዲሁ ሊያውቀው ይገባል።
ተደጋግሞ ከተለያዩ የህግ ባለሙያዎች እንደተገለጸው አለምዓቀፍ ህግን በተጻረረ መልኩ ኦኬሎ አኳይንና አንዳርጋቸው ጽጌን ከመንገድ ያውም ከሰው አገር በጉቦ አስጠልፈውና አፍነው በመውሰድ ያው የተለመደ ግፋቸውን እየፈጸሙ ይገኛሉ፣ ይህ የሚያሳየው ወያኔ እጁ ምን ያህል ረጅም እንደሆነ ነው። እነዚህ ሁለት የፍትህና የእኩልነት ታጋዮች ኦኬሎ አኳይንና አንዳርጋቸው ጽጌ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንደ ሌሎች የተቃዋሚ መሪዎች የበኩላቸውን ለማበርከት ደፋ ቀና ሲሉ በወያኔ መረብ ውስጥ ቢገቡም ለፍትህና ለእኩልነት እንዲሁም ለሃገር ነጻነት የከፈሉት አስተዋጽኦ መቼም የማይረሳ ታላቅ መስዋእትነት ያበረከቱ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው።
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የአንድነት ሃይሎች በመተባበር፣ በመጣመርና በመዋሃድ ሃይልን፣ እውቀትን፣ ህብረትን እንዲሁም ገንዘብን በማቀናጀት የወያኔን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ከርሰ መቃብር ለአንዴና ለመጨረሻ አሸቀንጥሮ ወርውሮ ሃገርንና ህዝብን ለነጻነት ለማብቃት በጋራ መታገል ግዴታችን መሆኑን አውቀን በአንድነት ስርዓቱን ማስወገድ ማንኛውም ሃገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሊነሳለት እና ሊተገብረው የሚገባ መሆኑን በመግለጽ የበኩሌን ሃሳብ ለማቅረብ እወዳለሁ::
አንድነት ኃይል ነው !!
ድል ለሰፊው ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!
Posted By.Dawit Demelash
1 .http://www.ethiomunich.com/component/k2/item/68-%E1%8B%A8%E1%8B%88%E1%8B%AB%E1%8A%94-%E1%8B%A8%E1%88%B5%E1%88%88%E1%88%8B-%E1%8A%A5%E1%8C%81-%E1%88%A8%E1%8C%85%E1%88%9D-%E1%89%A2%E1%88%86%E1%8A%95%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%8D%8D%E1%89%B5%E1%88%85%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%8A%A9%E1%88%8D%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B5%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%89%B3%E1%8C%8B%E1%8B%AE%E1%89%BD-%E1%8A%A8%E1%89%B5%E1%8C%8D%E1%88%89-%E1%89%85%E1%8A%95%E1%8C%A3%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%8A%93%E1%8D%88%E1%8C%88%E1%8D%8D%E1%8C%8D%E1%88%9D
2. http://quatero.net/pdf/dawit-demelash.pdf
3.http://www.ethiox.com/blog/?p=1022
No comments:
Post a Comment