Saturday, November 29, 2014

በዛሬ ቅዳሜ የሚሊዮኖች ድምፅ የህሊና እስረኞች መርሀ ግብር የዞን 9 ዘጠኝ ጦማሪያንን ታስበው ይውላሉ



በዛሬ ቅዳሜ የሚሊዮኖች ድምፅ የህሊና እስረኞች መርሀ ግብር የዞን 9 ዘጠኝ ጦማሪያንን ታስበው ይውላሉ፤ እንደሚታወቀው በቃሊቲ ያሉት እስር ቤቶች በተለያዩ ዞኖች ተከፋፈሉ ሲሆን፤ ከዞን አንድ እስከ ዞን ስምንት ይደርሳሉ፤ እኛ በታሰረችው ሀገር በሰፊው እስር ቤት የምንገኝ ደግሞ የዞን ዘጠኝ ታሳሪዎች ነው የምንባለው፤ ስለዚህ ሁላችንም ያለነው ዞን ዘጠኝ ውስጥ ነው፤ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ይህ እውነት ስለገለጡ ነው የታሰሩት።

የሚሊዮኖች ድምፅ የህሊና እስረኞች መርሀ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ ብዙ አስደናቂ ነገሮች እየተስተዋሉ ነው ያሉት፤ በትናንትናው ዕለት የአንድነት አባላት ብቻ ተለይተው እነእስክንድር ነጋንና እነ አንዷለም አራጌን በቃሊቲ እንዳይጠይቁ ተከልክሏል፤ መከልከል ብቻ አይደለም ታግተው ውሏል፤ አብዛኞቹ ከሰዓት ላይ ሲለቀቁ፤ አራቱ ደግሞ ማታ ላይ ተለቋል፤ ትግስት ካሳዬ ምትባል የአንድነት የወረዳ አመራር አባል ደግሞ ስትፈታ እዚያው አሳድሯታል።


ታላቁ የህሊና እስረኛ እስክንድር ነጋም ‹‹በርቱ! እንቅስቃሴያችሁ ህጋዊና ሰላማዊ ይሁን እንጂ ትግላችሁን ቀጥሉ!›› የሚል መልዕክት አስተላልፏል። በተጨማሪም አሳሪዎቹ የማናገር ነፃነቱን እዚያው እስር ቤትም ውስጥ ሊገድቡት በመኮሩበት ሰዓት፤
‹‹መብቴን አሳልፌ አልሰጥም፤ የትም ብሆን ስለመብቴና ሀገሬ ያገባኛል፡፡ እዚህ ከሚጠይቁኝ ሰዎች ጋር የፈለኩትን ማውራት እችላለሁ፡፡ እናንተ ከፈለጋችሁ በር ላይ መልሷቸው እንጂ እኔ ጋር ከመጡ በኋላ ስለሀገሬ ከእነሱ ጋር መነጋገር መብቴ ነው፡፡


 አዎ የትም ቦታ ብሆን፣ መቼም ቢሆን ስለ ሀገሬ ያገባኛል!›› በማለት አሁንም ለመብቱ ያለው ቁርጥ አቋም አሳይቷል። እስክንድር ቃሊቲ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ካለ፤ እኛ በሰፊው እስር ቤት ያለነው ታሳሪዎች ምን እንጠብቃለን! እምቢ ለመብቴ እምቢ ለነፃነቴ እምቢ ለሀገሬ ማለት አለብኝ! ሁላችንም የዞን ዘጠኝ ታሳሪዎች ነን!

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/36653

Wednesday, November 26, 2014

ታሪክን ማደብዝዝም ማጥፋትም አይቻልም!

በአለማችን በተለይ አፍሪካ ዉስጥ የአገርን ብሄራዊ ኃብት የሚዘርፉ፤የህዝብን መብት የሚረግጡና አገርን እነሱ ባሰኛቸዉ አቅጣጫ ብቻ ይዘዉ የሚነጉዱ አያሌ ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት አሉ። እነዚህ ህዝብን የሚበድሉ መንግስታት ሁሉም በጥቅሉ አምባገነን ይባሉ እንጂ በመካከላቸዉ ጎላ ብሎ የሚታይ ትልቅ ልዩነት አለ። ሀኖም የቱንም ያክል ልዩነት ቢኖርም እንደ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች እንመራዋለን የሚሉትን ህዝብ የሚንቁና የኛ ነዉ የሚሉትን አገር የሚጠሉ አምባገነን መንግስታት የሉም፤ በታሪክም ኖረዉ አያዉቁም። አምባገነን መንግስታት የስልጣን ዘመናቸዉን ለማራዘምና ከስልጣን ጋር ተያይዞ የሚመጣዉን ክብር፤ ዝናና ጥቅማ ጥቅም እንዳይቋረጥ ሲሉ የሚቃወማቸዉንና ለስልጣን ዘመናቸዉ አደጋ ነዉ የሚሉትን ሁሉ ያስራሉ፤ ይደበድባሉ ወይም ይገድላሉ። እነዚህን ነገሮች የወያኔ መሪዎችም ያደርጋሉ፤ ነገር ግን በወያኔና በሌሎቹ አምባገነን አገዛዞች መካክል እጅግ በጣም ትልቅ ልዩነት አለ። ለምሳሌ ወያኔዎች ዘረኛ አምባገነኖች ናቸዉ፤ የወያኔ መሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ጥገት ላም አንጂ እንደ አገራቸዉ አይመለከቱም። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያን፤ ህዝቧንና ታሪኳን ይንቃሉ፤ ያንኳስሳሉ።

ባለፉት አምስትና ስድስት አመታት በግልጽ እንደተመለከትነዉ የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬቱ አፋናቅለዉ ለምለም መሬቱን ለባዕዳንና ለህወሓት የጦር መኮንኖች ሰጥተዋል። መሬቴንና ቤቴን አልለቅም ብሎ የተቀናቀናቸዉን ደግሞ በጅምላ ገድለዋል። በከተሞች ዉስጥም ከተሜዉን ምንም ካሳ ሳይከፍሉት ዕድሜ ልኩን ከኖረበት ቤቱ እያፈናቀሉ ከነቤተሰቡ ሜዳ ላይ ጥለዉት መሬቱን ባለኃብት ለሚሏቸዉ የወያኔ ባለሟሎች ሰጥተዋል። በአጠቃላይ የወያኔ መሪዎች በኢትዮጵያ አንድነት፤ በታሪኳና በህዝቧ ላይ እንዲህ ነዉ ተብሎ ለመናገር የሚዳግት ትልቅ በደል ፈጽመዋል። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በእናት አገራችን ላይ ያደረሱት በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለምና ዛሬ ወደዚያ ዝርዝር ዉስጥ አንገባም፤ ዛሬ ትኩረት የምንሰጠዉ ወያኔ ደግሞ ደጋግሞ ከዘመተባቸዉና ሙሉ ኃይሉን ካሳረፈባቸዉ የአገራችን እሴቶች አንዱ ታሪካችን ነዉና የዛሬዉ ቆይታችን በዚሁ በታሪካችን አካባቢ ይሆናል።

ታሪክ በአንድ አገር ዉስጥ እያንዳንዱ ትዉልድ ከሱ የቀደመዉ ትዉልድ በግል፤ በቡድንና በማህበረሰብ ደረጃ የተጓዘበትን መንገድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ካለፈዉ የምንማርበትና የወደፊቱን ጉዟችንን ለመጀመር በመረጃነት የሚያገለግለንን እዉቀት የምናገኝበት የጥበብ ድርሳን ነዉ። የማንም አገር ታሪክ ዉብ ሆኖ የሚያምርና የማያምር ሁለት ገጽታዎች አሉት፤ የማያምረንን የታሪክ ጠባሳ ወደ ኋላ ሄደን ማከም በፍጹም እንደማንችል ሁሉ የወደፊቱን ታሪካችንንም የብዙ ማህበረሰባዊ መስተጋብሮች ዉጤት ነዉና ያሰኘንን ቅርጽና ይዘት ልንሰጠዉ አንችልም። የታሪክ ዋናዉና ትልቁ ቁም ነገር የታሪኩ ባለቤት የሆነዉ ማህብረሰብ እራሱን ወደ ኋላም ወደ ፊትም የሚመለትበት መስኮት መሆኑ ነዉ። ምንም አይነት ታሪክ የሌለዉ ህብረተሰብ የለም፤ ካለም ከየት አንደመጣና ወዴት አንደሚሄድም አያዉቅም።

አገራችን ኢትዮጵያ ረጂምና ጥንታዊ ታሪክ ካላቸዉ ጥቂት አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት። ይህ ረጂም ታሪካችን ደግሞ አንገት ቀና የሚያስደርግ የድልና የገድል ታሪክ አንደሆነ ሁሉ አንገት የሚያስደፋ የግፍና የበደል ታሪክም አለበት። የዛሬዉ ትዉልድ ኢትዮጵያዊ ካለፈዉ ታሪኩ ከበደሉም ከገድሉም ተምሮ የወደፊት አካሄዱን ከሞላጎደል መቆጣጠር የሚችል እድለኛ ትዉልድ ነዉና አባቶቹ ባቆዩለት ታሪክ ሊኮራ ይገባል። አንድ ህዝብ በታሪኩ እንዲኮራ ደግሞ ታሪኩ በተደጋጋሚ ሊነገረዉ ሊተረክለትና በጽሁም መልክትም በገፍ ሊቀርብለት ይገባል። የአገራችን የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ለዚህ የታደለ አይደለም ምክንያቱም እንመራሀለን የሚሉት መሪዎቹ ታሪኩን የሚያንቋሽሹና የሚንቁ መሪዎች ናቸዉ።

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ካደረሱትና ዛሬም በማድረስ ላይ ካሉት በደሎች አንዱና ዋነኛዉ የኢትዮጳያን ታሪክ ለባዕዳንና የታሪኩ ባለቤት ለሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አሳንሰዉና እንደ ተራ ዕቃ አቃልለዉ ማቅረባቸዉ ነዉ። የወያኔ መሪዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ መጀመሪያ ከተናገሯቸዉ ንግግሮች አንዱ የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ የመቶ አመት ታሪክ ነዉ ያሉት አስቀያሚ ንግግር ነዉ። በዚህ አባባል ላይ የጸና አቋም ካላቸዉ የወያኔ መሪዎች ዉስጥ ዛሬ በህይወት የማይገኘዉ መለስ ዜናዊና ጓደኛዉ ስብሐት ነጋ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ። የሚገርመዉ እነዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ መቶ አመት የወሰኑት ሁለት ግለሰቦች የተወለዱት የኢትዮጵያ ህዝብ የዛሬ 119 አመት በአፄ ሚኒልክ መሪነት ወራሪዉን የጣሊያን ጦር አይቀጡ ቅጣት በቀጡበት አድዋ ዉስጥ ነዉ።

ወያኔ ካለፈዉ መስከረም ወር ጀምሮ ባደበዘዘዉ ቁጥር እያሸበረቀ ያሰቸገረዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማቆሸሽ ጠባሳዉ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ የክፋት ስራ እየሰራ ነዉ። ኢትዮጵያን የመሰለ ባለታሪክ አገር ገድሎ ለሞተዉ ዘረኛ ሰዉ ትልቅ ማዕከል በህዝብ ገንዘብ የሚያሰሩት የወያኔ መሪዎች ማስቀመጫ ቦታ ጠፋ እያሉ አያሌ ብርቅ የሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍትን ከወመዘክር አይወጡ በችርቻሮ እየሸጡ ነዉ። እነዚህ ወያኔ የሚሸጣቸዉ መጽሐፍት የተጻፉት በተለያዪ ዘመናት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ በነበሩት የእንግሊዝ፤ የፈረንሳይ፤ የጣሊያን፤ የስፔንና የጀርመን የታሪክ ጸሐፊዎች ነዉ። ከሰሞኑ ከአዲስ አበባ የሚመጡ ዜናዎች እንደሚያመለክቱት ወያኔ በዉጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎች የተጻፉትን የታሪክ መጽሐፍትና ተጠረዝዉ የተቀመጡ ቆየት ያሉ ጋዜጣዎችን በርካሽ ዋጋ እየቸበቸቡ የግሮሰሪ ዕቃ መጠቅለያ አድርጓቸዋል።

ይህንን አሳፋሪ የሆነ የወያኔ የመጽሐፍ ሽያጭ እንደ ተራ ወንጀል የምናልፍ ኢትዮጵያዉያን ካለን እጅግ በጣም ተሳስተናል። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የሚሰሩትን ስራ አበክረዉ የሚያዉቁ ሰዎች ናቸዉ፤ እያሰሩ ያሉት ስራ ደግሞ ግልጽ ነዉ። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የተጻፈ ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን እያወደሙ ያሉት ባህላችንን፤ ወጋችንንና ቅርሶቻችንን ጨምር ነዉ እንዳልነበረ ያደረጉት። ለምሳሌ በብዙ የአለም አገሮች ዉስጥ ረጂም ዕድሜ ያስቆጠሩ ህንፃዎች፤ የታሪካዊ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችና የተለያዪ የአገር ቅርሳቅርሶች ልዩ እንክብካቤ እየተደረገላቸዉ ከዘመን ወደ ዘመን እንዲተላለፉ የደረጋል። ኢትዮጵያ ወስጥ ግን ዕድሜ ለወያኔ ከፍተና ታሪካዊ እሴት ያላቸዉ ህንፃዎች በልማት ስም እንዲፈርሱ ይደረጋል። የጀግኖችን አጽም ያረፈበት የመቃብር ቦታም በግሬደር እየተደረመሰ የንግድና የችርቻሮ ቦታ ይሆናል።

ሌለዉ ወያኔ በታሪካችን ላይ የሚያደርሰዉ ጥፋት ታሪካችንን እንዳንማርና የታሪክ ተማራማሪዎቻችን በጥንታዊ ታሪካችን ላይ ምርምር እንዳያደርጉ እጅና እግራቸዉን ማሰሩ ነዉ። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኛዉ የታሪክ ዲፓርትመንት የኢትዮጵያን ታሪክ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ታሪካችንን ከተለያየ አቅጣጫ በማጥናትና ምርምር በማድረግ ለታሪካችን መበልጸግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ተቋም ነዉ። ሆኖም ይህ በተለያዪ መንግስታት ዉስጥ ለረጂም አመታት ትልቅ ስራ ሲሰራ የቆየዉ የታሪክ ዲፓርትመንት ዛሬ አለ ተብሎ መናገር በማይቻልበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ወያኔ የቀድሞ ታሪካችንን እያወደመ የሚቀጥለዉን ታሪካችንን ደግሞ በራሱ አቅጣጫ እያጣመመ በመጻፍ ላይ መሆኑን ነዉ።

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ አስመልክቶ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈዉ በተወሰኑ ሰዎች ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ነዉ ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ የረጂሙን ዘመን የአገራችን የኢትዮጵያ ታሪክ ከአንድ ሞቶ አመታ የበለጠ ዕድሜ የለዉም እያሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ዛሬ በገፍ ለጨረታ ያቀረቧቸዉ የታሪክ መጽሐፍት ቁልጭ አድርገዉ የሚናገሩት ደግሞ ታሪካችን 3000 አመታት በላይ መሆኑንና የተጻፈዉም በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በተለያዪ ኢትዮጵያዉያንና የዉጭ አገር ሰዎች ጭምር መሆኑንደ ነዉ። ዛሬ ወያኔ እንደ ርካሽ ዕቃ እያወጣ የሚቸበችባቸዉ መጽሀፍት ለዚህ አሳዛኝ ዕጣ የበቁት ይህንን የወያኔ አይን ያወጣ ዉሸት ስለሚያጋልጡ ነዉ።

አገራችን ኢትዮጵያን እንወዳለን የምንል ኢትዮጵያዉያን በሙሉ ይህ በአፋችን ሁሌም የምንለዉ ቃል በተግባር የምንተረጉምበት አጋጣሚ ፊት ለፊታችን ላይ ተደቅኗል። ኢትዮጵያ አንደ ገና ዳቦ ከላይና ከታች ወያኔ ባነደደዉ ረመጥ እሳት እየተለበለበች ነዉ። ይህንን እሳት ማጥፍትና አገራችንን ከወያኔ መታደግ ካለብን ግዜዉ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነዉ።

አያሌ ኢትዮጵያዉያን የወያኔን የመጽሐፍ ሽያጭ አስመልክቶ የወሰዱትን ቆራጥና ብልህ እርምጃ ግንቦት ሰባት የፍትህ፤ የነጻነትና፤ የዲሞክራሲ ንቅናቄ እጅግ በጣም ያደንቃል። በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚገኙ አያሌ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን የአገርና የወገን ሃላፊነት ተሰምቷቸዉ ወያኔ ለጨረታ ያቀረበዉን መጽሐፍ በመግዛት የአገራቸዉን ታሪክ ለመታደግ ያደረጉት ጥረት በዋጋ ሊተመን የማይችል ትልቅ አገራዊ ስራ ነዉ። አገራችን ዛሬ ባለችበት ሁኔታ ነገ አትገኝም የሚል እምነታችን የጸና ነዉና እነዚህን የገዛችኋቸዉን መጽሀፍት በጥንቃቄ በመያዝ ሀላፊነትና የአገር አደራ ለሚሰማዉ በህዝብ የተመረጠ መንግስት አንድታስረክቡ አደራ እንላችኋለን። ከአሁን በኋላም ቢሆን የወያኔን ፀረ አገርና ፀረ ህዝብ ስራ እየተከታተላችሁ እንድታከሽፉና በሚያልፈዉ ህይወታችሁ የማያልፍ ታሪክ ሰርታችሁ ወያኔን በማሰወገዱ ዘመቻ ዉስጥ ሙሉ ተሳትፎ አንድታደርጉ አገራዊ ጥሪ እናስተላለፋለን።


http://www.ginbot7.org/2014/11/23/%E1%89%B3%E1%88%AA%E1%8A%AD%E1%8A%95-%E1%88%9B%E1%8B%B0%E1%89%A5%E1%8B%9D%E1%8B%9D%E1%88%9D-%E1%88%9B%E1%8C%A5%E1%8D%8B%E1%89%B5%E1%88%9D-%E1%8A%A0%E1%8B%AD%E1%89%BB%E1%88%8D%E1%88%9D/

·