Tuesday, November 18, 2014

የቆሰለ አውሬ ለያዥ ለገራዥ አስቸጋሪ ነው፡፡

November 18th, 2014

የሙግትና የአዕምሮ አክሮባት ከመሥራት ይልቅ፤ የህዝቡስ ሁኔታ እንዴት ነው? ማለት ዋና ጉዳይ ነው፡፡
በሀገራችን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የተባለው ተረት ዕድሜው እጅግ ረጅም ነው፡፡ የሥርዓቶቻችንን ያህል አርጅቷል፡፡ በተግባር ሲተረጐም ግን ገና ዛሬ የተወለደ ነው የሚመስለው፡፡ በየቢሮው፣ በየማህበሩ፣ በየፓርቲው የምናየው ሀቅ ነው፡፡ “አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ”፣ “እከክልኝ ልከክልህም” አብሮ ሲተረት የኖረ ነው፡፡ ማናቸውም ዕቅድና ስትራቴጂ ህዝብ ኑሮ ላይ ያነጣጠረ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ማለት የእርስ በርስ ሙግትና የአዕምሮ አክሮባት ከመሥራት ይልቅ፤ የህዝቡስ ሁኔታ እንዴት ነው? ማለት ዋና ጉዳይ ነው፣ ማለት ነው፡፡
ሕዝቡ የኑሮ ውድነት ከበደኝ! የእቃ ዋጋ ንረት አስመረረኝ! ግፍ በዛብኝ! ሸምቶ መቃመስ አቃኝ የሚል ምሬት ሲያሰማ.. ሹመኞች አፍ ለማስያዝንና ለማሸማቀቅ ይሽቀዳደማሉ፡፡ የህዝብን የኑሮ ደረጃ ዝቅ ብሎ ወርዶ የሚያይ መሪ፣ አለቃ፣ ኃላፊ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ያስቀናል፡፡ የዋጋ መናርና የታክስ ማሻቀብ አንድን ማህበረሰብ የጦርነትን ያህል ያጠፋዋል፡፡ ለዚህ ነው መሪዎች ሁሉ የህዝባቸውን ኑሮ በቅርብ ያስተውሉ የሚባለው፡፡ ህዝብ የሀገር ሙቀት መለኪያ ነው፡፡ ህዝብ የሚከፍለው ግብር ከሚያገኘው አገልግሎት ጋር ካልተመጣጠነ የቀዘቀዘች አገር ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነት እና በገሃድ የሚታየው ህዝብ ደሞዙ ከሚኖረው ኑሮ ጋር ስለማይመጣጠን ኖረ አይባልም፡፡ ህዝብ ከዕለት ዕለት ህይወት እየከበደው በመሄዱ ከሳቁ ምሬቱ፣ ከደስታው ሐዘኑ እየበረታ ሥርዓቱን፣ አገዛዙን፣ ገዢዎቹን፣ አስተዳዳሪዎቹን እጅግ ጠልቷቸዋል፡፡ ሀገሩም የእሱ አትመስለውም፡፡ ህዝብ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማግኘት ነግ-ሠርክ መሰለፉ ፤ አልፎ ተርፎም ከናካቴው ዕጥረት የሚከሰትበት ሁኔታ፣ ብሶቱ ወሰን የለውም በብሶት ተሞልቷል፡፡ ህዝብ በመኖሪያ ቤት ችግር እየተሰቃየ ሲሆን መሰረታዊ የኑሮ አስፈላጊ ነገር ጎሎበታል ፡፡
ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ይህንን የሚገልፅበት መንገድ እንዳያገኝና በፍርሃት ተሸማቆ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ “አዲስ ያይጥ – ወጥመድ በሰራህ ቁጥር” አዲስ አይጥ የምትወለድ ከሆነ፣ ወይ ወጥመዷ ላይ ወይ አጥማጁ ላይ ችግር አለ ማለት ነው” ይባላል፡፡ በሙስና የተሞላ ልማት ዘርዛራ ወንፊት ነው፡፡ ዕብቁንም፤ እንክርዳዱንም፤ እያሳለፈ፤ እያዩ እህል አለን እንደሚሉት አይነት የዋህነት ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ መጨረሻው ድህነት ነው፡፡ ድህነት ሲመጣ ቃላት ይበዛል። ስብሰባ፣ ንግግር፣ የማይተገበር ቃል – መግባት እንደህይወት ይወሰዳል፡፡ እንደኑሮ ይለመዳል፡፡ይህ በወያኔዎች በተግባር እያየነው ያለው ሃቅ ነው::
ሃገራችን እና ወገናችን በጨለማ ውስጥ እየዳከረ ባለበት በዚህ የወያኔ አገዛዝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በመረባረብ የዜግነት ግዴታውን አውቆ ለህዝቦች መብት እና ነጻነት መታገል አለበን። ሃገሪቷ በዚህ አደጋ ውስጥ ባለችበት ሰአት ላይ ህዝብ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ለኑሮ ውድነት ለሞት ለስደት እየተዳረገ ኢትዮጵያዊነት እየተዋረደ ከመሆኑም ባሻገር ሃገሪቷን ወደ ፍርስራሽነት ለመቀየር የሚሮጡ ጥቂት ሆዳሞች ባሉበት ልንቀብራቸው ይገባል።
http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/16277#more-16277

No comments:

Post a Comment