Friday, November 7, 2014

በሀገሪቱ ላሉት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች እስርና ወከባ መፍትሄ አይሆንም!

Nov.7.2014

አምባገነኑ የኢህአዴግ ስርዓት ፖለቲካዊ እስርን እንዳንድ ተቀዋሚዎች የማዳከሚያ ስልት በመውስድ ህግ ወጥ በሆነ ሁኔታ አባሎቻችን በማሳርና በማዋከብ ላይ ይገኛል። አንድነት ከምስርታው ጀምሮ አመራሮቹና አባላቱ የተለያየ ሽፋን በመጠቀም ለእስርና ለእንግልት ተዳርጓል፤ አሁንም እየታሰሩና እየተዋከቡ ይገኛሉ፤ በቅርብ ደግሞ ለየት ባለ ሁኔታ አጠቃላይ ፓርቲው በሚያዳክም መልኩ በሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚገኙ የአንድነት አባላት እያሳደደ በማሰር ላይ እንደሚገኝ ከየአከባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በወላይታ ዞን የአንድነት የአመራር አባላት ከፍተኛ የሆነ ደብደባ የተፈፀመባቸው ሲሆን እነዚህም አቶ ማሞ ጎሙ የዞኑ የአንድነት ሰብሳቢ፣ አቶ ወኖ መናሳ የዞኑ የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እና አቶ አልታዬ አቦታ የዞኑ የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ይገኙበታል፤ ይህን ድብደባ በሚፈፀምበት ወቅት የከተማው ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ሌሊሼ ኦፌ በቦታው ቆሞ እያየ የነበረ መሆኑ ደግሞ ህግ አለ በሚባልበት ሀገር ዜጎች ምንም ዓይነት የህግ ከለላ እንደሌላቸው የሚያሳይ እጅግ አሳዛኝ የሆነ እውነታ ነው።

እንደዚሁም ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም. በምዕራብ አምርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የሚገኙ የአንድነት አባላት አቶ አንጋው ተገኝ የአካባቢው የአንድከት ሰብሳቢ፣ አቶ አባይ ዘውዱና አቶ እንግዳው ዋኘው የአካባቢው የአንድነት አመራር አባላት፣ በሌላ በእኩል አቶ በላይነህ ሲሳይ በመተማ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ፤ አቶ አለባቸው ማሞ በመተማ አባል እና አቶ አለበል ዘለቀ የወረታ የአንድነት የአመራር አባል ምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበ የፌደራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው፣ ከዚያም ወደ አልታወቀ ቦታ ወስደው እንደሰወሯቸው ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ በመቀሌ የአንድነት አባል የሆነው ወጣት ሺሻይ አዘናው ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም. በመንግስት የድህንነት አካላት ከሚሰራበት መስሪያ ቤት የተወሰደ ሲሆን ወደ ቤቱ በመሄድ እዚያ ያገኙትን ወረቀት ሁሉ ወስደው በመኪና ወደ አልታወቀ ቦታ ይዞውት ሄደዋል።

በአጠቃላይ በአንድነት አባላት ላይ እየተካሄደ ያለው ህግወጥ የእስር ዘመቻ ሲታይ ገዥው ፓርቲ አንድነትን ለማዳከምና በተሻለ አቋም ላይ እንዳይገኝ ለማድርግ እያካሄደው ካለው ዘርፈ ብዙ ዘመቻዎች አንዱ አካል ነው ብለን እናምናለን። ነገር ግን ይህ በሀገሪቱ ውስጥ ለተንሰራፋው ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ አይሆንም ብለን እናስባለን። ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የህዝቡን ብሶት ወደ ሌላ አቅጣጫ ሄዶ ሌላ ያልታሰበ ጥፋት እንዳያስከትል ስጋት አለን። ስለዚህ ስርዓቱ ሁሉም ነገር በኃይል እፈተዋለሁ የሚለው ነገር የትም የሚያደርስ አይሆንም፤ ነገም በህግና በታሪክ ሊያስጠይቅ የሚችል እንደሆነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል።

አንድነት በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነ እየታወቀ ገዥው ፓርቲ ይህን ያህል ርቀት ሄዶ ፓርቲውን ለማዳከም መንቀሳቀሱ በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን ለህዝብ ለማስረከብ ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ ነው። እንግዲህ ኢህአዴግ እንደስርዓት ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ወቅት ላይ እንገኛለን። አሁን እየሄደበት ያለው መንገድ ጠፍቶ ለመጥፋት ካልሆነ በስተቀር ብዙም ሩቅ የሚያደርስ ነው ብለን አናምንም።

በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምናስተላልፈው መልዕክት አሁን በመንግስት እየተወሰደ ያለው የእስር ዘመቻና ወከባ ሳይደናገጥና ተስፋ ሳይቆርጥ ትግሉን መደገፍና መቀላቀል አለበት እንላለን። አምባገነኖች በኃይል ስልጣን ላይ ሊቆዩ የሚችሉት ህዝቡ በአንድነት ሆኖ በቃኝ በዚህ መንገድ ከእንግዲህ አልገዛም የሚል ቁርጥ ያለ አቋም እስኪይዝና በአንድነት እስኪነሳ ድረስ መሆኑ መታወቅ አለበት። በመሆኑም፤ በቀጣይነት ለምናደርጋቸው ህዝባዊ ንቅናቄዎች ከጎናችን ሆኖ ለለውጥና ለነፃነት በሚደረገው ሰላማዊ ትግል ላይ እንዲሳተፍና የማይተካ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ
ጥቅምት 28/2007 ዓ.ም


http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/16182

No comments:

Post a Comment