Friday, November 21, 2014

ከ400 በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት መሬት በሙስና ተቸበቸበ



በደቡብ ወሎ ዞን በኮምቦልቻ ወረዳ ቀበሌ 11 በተለምዶ ጋሪሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ 470 ሰዎች ቦታው ለኢንቨስትመንት ይፈለጋል ተብሎ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ እንዲፈናቀሉ ከተደረገ በሁዋላ፣ በካሬ ሜትር 1 ብር ከ46 ሳንቲም መሬታቸው እንዲጨጥ ተደርጓል።

ጉዳዩ የህዝብ መነጋገሪያ ሆኖ ከቆየ በሁዋላ ሰሞኑን ከህዝቡ እየጨመረ የመጣውን ግፊት ተከትሎ በተደረገ ህዝባዊ ስብሰባና የካቢኔ አባላት ስብሰባ፣ የወረዳው አዛዦች ከተፈናቃዩ ደሃ ህዝብ የወሰዱትን መሬት በሙስና መቸብቸባቸውን እርስ በርስ እየተገላለጡ ይፋ አድርገዋል።

የወረዳው ላይዘን ኦፊሰር አቶ ሃብቶም የተባሉ ግለሰብ፣ አስተዳዳሪውን አቶ አበራ አበረን በአዲስ አበባና በባህርዳር መሬት ገዝተው ቤት መስራታቸውንና ቡልዶዘሮችን ገዝተው እያከራዩ መሆኑን ሲያጋልጡ፣ ምክትል ከንቲባው ደግሞ በባንክ ሂሳባቸው 8 ሚሊዮን ብር እንደተገኘባቸው እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ቤቶችን መገንባታቸውን አጋልጠዋል። አጋላጩ አቶ ሀብቶምም በከተማዋ ሁለት ቦታ ገዝተው ቤት መስራታቸውን መቀሌ ላይ ተጨማሪ ቦታ መግዛታቸው በሌሎች ባልደረቦቻቸው ተጋልጧል።

ሶስቱም ባለስልጣኖች ለጊዜው ከስራቸው ቢታገዱም እስካሁን የተወሰደባቸው እርምጃ የለም።

አንዳንድ ተፈናቃይ አርሶደአሮች ለኢሳት እንደገለጹት አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ በማጣታቸው ለስደትና ለረሃብ መዳረጋቸውን ለኢሳት ገልጸዋል ።
ሰዎቹ ከስራ ቢሰናበቱም ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው መስራታቸው አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ከ100 በላይ አርሶደሮች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አርሶ አደሮቹ የመሬት ዋስትና ወረቀት እንዲሰጣችሁ በነፍስ ወከፍ 4 ሺ 500 ብር ክፈሉ ተብለው የተጠየቁ ቢሆንም፣ አርሶአደሮች ግን እስከዛሬ ግብር እየከፈልን ኖረናል፣ አሁን ተጨማሪ አንከፍልም በማለት ተቃውመዋል። ይህ ተከትሎ መሬታቸውን እየተቀሙ መሬቱ ለኢንቨስተር እየተባለ እየተቸበቸበ ነው።


አብዛኞቹ ባለስልጣኖች ከኢንቨስተሮች ጋር አክሲዎን እንዳላቸው መንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። በአካባቢው የሚታየው ተደጋጋሚ ግጭት ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/36443

No comments:

Post a Comment