Wednesday, February 27, 2013

ሞት በምልጃ፤ የበረሃ ጣዕር!

ማስለቀቂያ ካልተከፈለ – ኩላሊት ለገበያ
tigist gebre

“አቧራ ይጨሳል። ከዚያ ያፈኑትን ይዘው ይሰወራሉ” አስደንጋጩ ታሪክ ውስጥ ያለው ስዕላዊ ገለጻ ነው። አንድ ወቅት አዲስ አበባ የህጻናት ሌቦች ተበራክተው ነበር። በወቅቱ በርዳታ ስም ተመዝግበው የፈጣሪ ስም እየጠሩ ህጻናትን በመነገድ የከበሩ ወረበሎች በደንብ የተደራጁና የሚቀናቀናቸውን የማስወገድ አቅም ስለነበራቸው “አቧራው ጨሰ” የሚል ስያሜ የኮድ ስም ተሰጥቷቸው ነበር። አሁንም አሉ። “ህጻን እናሳድጋለን” እያሉ በዘረጉት ሰንሰለት የህጻናትን ደም የሚጠጡ “አንቱ” የተባሉ ሰዎች!! የውጪ አገር ዜጎች ጭምር …
በሱዳን ሰዎችን በማፈን ሲና በረሃ የሚሰውሯቸው ራሻይዳዎች የተደራጁ ናቸው። ከአረብ ምድር የፈለሱ ናቸው የሚባልላቸው እነዚህ ጎሣዎች በሱዳንና በኤርትራ የሚገኙ ሲሆን በተለይ በኤርትራ ያሉቱ ከዘጠኙ ጎሣዎች መካከል የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አኗኗራቸው የዘላን በመሆኑ ከኤርትራ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ እነዚህ ጎሣዎች እጅግ አሰቃቂ የሆነ የአፈናና የጭከና ድርጊት ሲፈጽሙ በወጉ ታጥቀውና ዘመናዊ ተሽከርካሪ በመያዝ ነው። የሚታፈነውን ሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ አዋራ ይነሳል። የሚከንፉበት ተሽከርካሪ አሸዋውን ተርትሮት ሲወረወር የሚነሳው ጭስ ሲበተን እነሱ የሉም። ቀሪው ተግባር “ሚስትህን፣ ወንድምህን፣ እህትሽን፣ ዘመድሽን ለሚያርዱ የሰውነት ክፍል ሌቦች አሳልፈን ሳንሰጥ ዶላር ክፈል ወይም ክፈይ” የሚለው ድርድር ነው። ይህ ድራማ መሰል ንግድ ሲከናወን ተገደው ይሁን የንግዱ ተባባሪ በመሆን በውል በማይታወቅ ሁኔታ የድርድሩ አስተርጓሚ ሆነው የሚሰሩት ኤርትራዊያን እንደሆኑ ተሰምቷል። ኢትዮጵያዊያኖችም አሉበት ይባላል። ማንም ይስራው ማን ድርጊቱ አሰቃቂ መሆኑ ብዙዎችን አስለቅሷል። አስጨንቋል።
በደላሎች እስራኤል ለመግባት ጉዞ ከጀመሩት ወገኖች መካከል ስንቶቹ በሲና በረሃ ሟምተው እንደቀሩ መረጃ የለም። ከሱዳን ምድር ወጥተው ግብጽ በመሻገር ሲና በረሃ እንደ ከብት ተበልተው የሚጣሉት ወገኖች ስቃይ ለሰሚው ግራ ነው። ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ መከራ ከቀን ቀን እየተባባሰ ነው። አሰቃቂ ዜናዎች መስማት ለየእለቱ የሚያስፈልገን መሰረታዊ ጉዳይ እስኪመስል ተለመዷል። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ “እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል” የሚለው የሁሉም ወገን “ዳር ቋሚዎች” ጥያቄ ነው።
“ለጆሮ የሚሰለች ነው፣ እርዳታ መስጠት ታከተን፣ የሚል መልስ የሚሰጡ አጋጥመውኛል። ድርጊቱ ተደጋግሞ ለጆሮ የሚያሰለች ደረጃ እስኪደርስ እነዚህ ወገኖች የት ነበሩ? ቢያንስ ሌሎች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስ ምን ሰሩ? በውጪ አገር ያለን ወገኖች የሚረዳውንና የማይረዳውን መለየት የተሳነን ይመስለኛል” በማለት በሚኔሶታ የሚኖሩት ወ/ሮ ሰብለ አስተያየታቸውንና ተማጽኗቸውን ያሰማሉ።
የካቲት 3፤2005 (2/10/2013) የቪኦኤ አማርኛ ክፍለ ጊዜ ያሰማው እረፍት የሚነሳ ዜና እስካሁን አልተቋጨም። ሱዳን ሸገራብ በሚባለው ሰፊ የስደተኞች ጣቢያ ከባለቤታቸውና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩ ወ/ሮ ትዕግስት ገብሬ ጥር 22 ቀን 2005 ዓ ም ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ከቤታቸው ይወጣሉ። በካምፕ ውስጥ ከሚገኘው ቤታቸው ወጥተው በግምት ሰላሳ ሜትር ሳይርቁ ታፈኑ።
ባለቤታቸው አቶ መልካሙ ባዬ ለቪኦኤ እንደተናገሩት አፋኞቹ ራሻይዳዎች ናቸው። ራሻይዳ የቆዳቸው ቀለም ጠየም ያለ የሱዳን፣ የኤርትራና የግብጽ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ቀደም ሲል ከሶስት እስከ አራት ሺህ ዶላር እየተቀበሉ በደላላ አማካይነት ስደተኞችን በሲና በረሃ ወደ ግብጽ ያሻግሩ ነበር። እስራኤል በሲና በረሃ ወደ ድንበሯን ዘልቀው የሚገቡበትን የስውር መንገድ ስትዘጋው ራሻይዳዎቹ የገቢ ምንጫቸው ተዘጋ። ገንዘብ የለመዱት ወንበዴዎች የንግዱ ስልት ቀየሩና ሰው ማፈን ጀመሩ። አፈናውንም ከሚያካሂዱባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ ድንበር አቋርጠው የሚጓዙትን አድፍጠው በመያዝ፣ ስደተኞችን ከስደተኛ ካምፕ አፍኖ በመውሰድ፣ ከሌሎች አፋኞች ስደተኞችን በአነስተኛ ገንዘብ በመግዛት እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ሜሮን እስጢፋኖስ ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ ሰብለ ደምሴ ይህንን ዜና ሲሰሙ ደነገጡ። ዜናውን ካሰራጨው የቪኦኤ ዝግጅት ክፍል አድራሻ በመጠየቅ አቶ መልካሙን አገኟቸው። አቶ መልካሙ በቃለምላልሳቸው ወቅት እንደተናገሩት ሁሉ ለወ/ሮ ሰብለ የደረሰባቸውን ሁሉ አጫወቱ። ወ/ሮ ሰብለ “የሰማሁት ሁሉ እረፍት ነሳኝ። የማውቃቸውን ሰዎች ማስቸገር ጀመርኩ። ጊዚያዊ የባንክ ሂሳብ በመክፈት ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመርኩ። ህይወት ለማትረፍ እየጣርኩ ነው” ሲሉ ጥሪ ያካተተ አስተያየት ሰነዘሩ።
ወ/ሮ ትዕግስት ገብሬ አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው። አፋኞቹ 35 ሺህ ዶላር ካልቀረበላቸው የሰውነት አካል ክፍል ለሚዘርፉት አራጆች ያስረክቧቸዋል። እዚያ ከደረሱ ድርድር የለም። የሰውነት ክፍላቸው የበለጠ ዋጋ ስለሚያወጣ ሌሎች ወገኖች ላይ እንደተፈጸመው እርሳቸውም ላይ ይከናወናል።
የ12 እና የ 1 ዓመት ከስምንት ወር ልጅ ያላቸው ወ/ሮ ትዕግስት ባለቤታቸውን በስልክ እንዲያነጋግሩ ይደረጋሉ። ባለቤታቸውም ይሰቃያሉ። እግራቸውና እግራቸው መካከል ብረት ተደርጎባቸዋል። ይደበደባሉ። ይህ ሁሉ የሚደረገው ባለቤታቸው የተጠየቁትን ገንዘብ ባስቸኳይ እንዲከፍሉላቸው ለማስጨነቅ ነው። ባለቤታቸው እንደተናገሩት “ምንም አማራጭ የለኝም። የተጠየቀውን ገንዘብ ማግኘት አልችልም። ልጆቼ ወደፊት ሲጠይቁኝ ለምኜ አቃተኝ ለማለት እየለመንኩ ነው። ባለቤቴ ግን ምንም ማድረግ እንደማልችል ታውቃለች፤ … ” ብለዋል።
የ 12 ዓመቷ ልጃቸው ሱፊ “እኛንም እንዳይወስዱን ስለምንፈራ ከቤት አንወጣም” በማለት ልብ የሚነካ መልስ ከቪኦኤ ለቀረበላት ጥያቄ መልስ ሰጥታለች፡፡ “እናቴን አፈኗት” ያለችው ህጻን የበርካታዎችን ልብ እረፍት ነስታለች። ወ/ሮ ሰብለ “እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሲቃ ተሞላበት ጉዳይ እየሰማን በውጪ ያለን ወገኖች እንዴት 30 ሺህ ዶላር ማዋጣት አቃተን” ሲሉ ይጠይቃሉ። ወ/ሮ ትዕግስት ጸሃይ ቢተርፉ ለሌሎች በማስተማር ተመሳሳይ ችግር በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እንዳይደርስ የማድረግ ስራ ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
በሰብአዊ ተግባርም ሆነ በየትኛውም ዓይነት ማህበር ተመሳሳይ ስራ ተሳትፎ እንደሌላቸው ያስታወቁት ወ/ሮ ገነት፣ ይህን ጉዳይ የሳቸውን ልብና አእምሮ ዕረፍት ነስቶት ለዚህ ተግባር ራሳቸውን እንደሰጡ ሁሉ፣ ሌሎችም ይህንን ልብ ሰባሪ አደጋ ሌሎች ወገኖችም ሰምተው ተባባሪ እንዲሆኑ በሚል ለጎልጉል አስተያየት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ለመንግስት ስለማሳወቃቸው ተጠይቀው በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጸሐፊ ስልካቸውን በማፈላለግ ካገኙ በኋላ ማነጋገራቸውን ይገልጻሉ። በምላሹም “ይልቁኑ አፋኞቹ ስልካችሁን እንዳያውቁ ተጠንቀቁ። እየደወሉ ይጨቀጭቋችሁዋል” የሚል የማስፈራሪያ ማስጠንቀቂያ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ቴዲ አፍሮ በፑንት ላንድ ሞት የተፈረደበትን የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ቀድሞ በመድረስ ህይወቱን እንደታደገው አቶ መልካሙ አስታውሰው በተመሳሳይ የባለቤታቸውን ህይወት ሊታደግ የሚችል ወገን ሊኖር እንደሚችል ተቁመው ለማንኛውም “መፍትሔው እግዚአብሔር ዘንድ ነው” የሚል መልዕክት በቪኦኤ በኩል አስተላልፈዋል።
ወ/ሮ ሰብለ በበኩላቸው “ፈቃደኛነቱ ካለ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን” በማለት የጀመሩት የነብስ ማዳን ስራ በቅርብ ወዳጆቻቸው መደገፉን አስታውቀዋል። አያይዘውም ሩጫው ከጊዜ ጋር መሆኑንን አመልክተዋል።
ገንዘቡ ከተገኘ ለአፋኞቹ እንዴት ይደርሳል? ወ/ሮ ትዕግስትስ እንዴት ነጻ ይሆናሉ? በሚል ወ/ሮ ሰብለ የሰሙት ነገር እንዳለ ለተጠየቁት፣ ሰዎቹ እስራኤል አገር ወኪል አንዳላቸውና፣ ገንዘቡ ለወኪሎቻቸው ሲገባ ግብጽ ወስደው እንደሚለቋቸው፣ ይህንን ለማከናወን የሚችሉ ሴት አቶ መልካሙ ማዘጋጀታቸውን እንደነገሯቸው የሴትየዋን ስም በመጥቀስ ተናግረዋል።
“በድብደባና በስቃይ ደክሜያለሁ። አሁን ገንዘቡ ተከፍሎ ቢለቁኝም በረሃውን አቋርጬ ግብጽ የምደርስበት አቅም የለኝም። እሞታለሁ። አትክሰሩ። እኔ አልተርፍም። የምትችሉ ከሆነ ህይወቴን ይወስዳት ዘንድ ለፈጣሪ ጸልዩ” ይህ ሲና በረሃ ታፍኖ የቆየ ኤርትራዊ ወጣት ለወንድሞቹ የተናገረው የመጨረሻ ንግግር ነበር። ወንድሞቹ እስራኤል አገር በስደት ሃዘን ተቀመጡ። ከዚያ በኋላ ስልካቸውን ቀየሩ። ወንድማቸውን በስልክ ድምጽ ነፍሱ ሳይወጣ ሞቱን ተቀበሉ” ሲሉ የሰሙትን ወ/ሮ ሰብለ አጫውተውናል። በሌላም በኩል በተመሳሳይ ታፍና የነበረች አንድ ወጣት የሚከፈለው ተከፍሎ በቅርቡ ከግብጽ አዲስ አበባ እንደገባች አመልክተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሙት የሲና በረሃ አሰቃቂ ስቃይ ሳቢያ የወ/ሮ ትዕግስት ገብሬን ህይወት ለማትረፍ ራሳቸውን ከፊትለፊት ያቆሙት ወ/ሮ ሰብለ ሊያነጋግራቸው ለሚፈልግ ሁሉ የኢሜል አድራሻቸውን አስታውቀዋል። yegetasew@yahoo.com
ዝግጅት ክፍሉ፦ በተመሳሳይ፣ በተለያዩ ስፍራዎች የሚፈጸሙትን የወገኖቻችንን ስቃይ አስመልክቶ ላልሰሙ ትምህርት ይሆን ዘንድ ጽሁፍ ለምትልኩልና ወገኖች ሁሉ ቅድሚያ እንደምንሰጥ ለመግለጽ እንወዳለን። በተለይም በሱዳን የስደተኞች ካምፕ ከ30- 40 ዓመት የኖሩ ስደተኛ ወገኖች ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያዊን ተሳትፎ ምን እንደሚመስል ብትጠቁሙን ጉዳዩን እንደምናጣራው ከወዲሁ እንገልጻለን።
ወ/ሮ ሰብለና ለተመሳሳይ አላማ የተነሱት እህቶች የሚከተለውን ደብዳቤ ለእምነት ባልደረቦቻቸውና ለቤተክርስቲያን ያቀረቡትን የተማጽኖና እንቅስቃሴያቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።


  Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment