Monday, February 11, 2013

አርቲስትና አክትቪስት ታማኝ በየነ በኦስሎ፣ ኖርዌይ (ልዩ አጭር ጥንቅር)

ጉዳያችን (GUDAYACHN)
የዛሬዋ የእሁድ ምሽት ከታማኝ የኦስሎ የኢሳት ገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር ጋር ያሳለፍኩት ምሽት ነበር። ምንም እንኳን መርሃግብሩን በሙሉ ለመፈፀም ባልችልም የአክትቪስት እና አርቲስት ታማኝን በቪድዮ የተደገፈ ገለፃ ግን ለመከታተል እድሉ ገጥሞኛል።
Ethiopian satellite television, norway
ኦስሎ ለኢሳት ገቢ ማሰባሰብያ መርሃግብር ከተገኘው ሕዝብ በከፊል (photo GUDAYACHN BLOG EXCLUSIVE)
ገብስማ ፀጉሩ ከነጭ ሸሚዝ እና ሽሮ መልክ የያዘ ክራቫት ጋር ታማኝን ግርማ ሞገስ አጎናፅፎታል። ታማኝ ወደ መድረኩ ሲመጣ ከታላቅ አክብሮት ጋር ከአምስትመቶ በላይ የሆነው ታዳሚ ከመቀመጫው ተነስቶ ተቀበለው። ታማኝ አፀፋውን እየመለሰ ምስጋናውን ገለፀ። ቀደም ብለው ከጎናቸው ከነበረው ሰው ጋር ይነጋገሩ የነበሩ ሰዎች በፀጥታ ወደመድረኩ ማስተዋል ጀመሩ። ታማኝ ሰላምታውን በአማርኛ ብቻ አልነበረም ያቀረበው ”አሰላም አለኩም” በማለት ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያለውን አክብሮት ሲገልፅ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተቸረው። ላፕቶፑን አስተካክሎ ከጀርባው በኩል ወዳለው ስክሪን ተመለከተ ትክክል ነው። ንግግሩን ቀጠለ እና እንዲህ አለ-
”ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው በስቶኮልም እና በጄኔቭ ከተመለከትቁት ሕዝብ ኦስሎ ዛሬ የበላይነቱን ይዟል።” ጭብጨባ አጀበው ቀጠለና:-
”…እኔ አርቲስት ነኝ በአርቲስትነት መኖር እችል ነበር። መፅሐፉ የሚለው ከፊትህ ውሃና እሳት ቀርቦልሃል እጅህን ወደወደድከው ጨምር ነው። እኔ እጄን ወደ ውሃ ከትቼ በአርቲስትነቴ እየደነስኩ መኖር አያቅተኝም ነበር። ነገር ግን የእውነት ጉዳይስ? የኢትዮጵያ ጉዳይስ? ዝም ብሎ የሚኖር ህሊና አለን?… እድሜዬ እንደምታዩኝ ላይሆን ይችላል። ፖለቲካ ያቃጥላል፣ ያናድዳል። ሆኖም ግን እስከመጨረሻ ለመፅናት ነው ቃል የገባሁት።”
ቀጠለናም የሙስሊም ወንድሞቻችን ጉዳይ ማንም ችላ ሊለው የማይገባ መሆኑን ”በሰላማዊ መንገድ ‘ድምፃችን ይሰማ’ ማለታቸው እንዴት አድርጎ ነው አሸባሪ የሚያደርጋቸው? ባለፈው የቀረበውን ድራማ አይታችሁታል። አንድ ላይ እኛም ድምፃችን ይሰማ! እንበል” ሲል በአዳራሹ የነበረው ተሰብሳቢ ሁሉ በአንድ ላይ ”ድምፃችን ይሰማ! ድምፃችን ይሰማ!” ሲል አዳራሹን አናወፀው።
በመርሃግብሩ ላይ በቪድዮ የተደገፈው የአቶ ሃይለማርያም እና የአቶ መለስ ተመሳሳይ ንግግሮች በጣም አዝናኝም አስገራሚም ነበሩ። አቶ መለስ በሕይወት እያሉ ለፓርላማ ያደረጉት ንግግር አቶ ሃይለማርያም እንዴት ከአቶ መለስ እረፍት በኃላ እንደደገሙት የሁለቱንም ንግግር እያሳየ አስገረመን። ከሁሉ ያሳቀን ግን ”አቶ ሃይለማርያም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኙት ስም ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” አለና መልሱን መለሰልን።” ባጃጅ ነው የሚባሉት ለምን መሰላችሁ? ባጃጅ ሶስት እግር ነው ያለው አቶ ሃይለማርያምም በሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሚመሩ ባጃጅ ተብለዋል በኢትዮጵያ ሕዝብ… ወደ ስልጣን ሲመጡ ተስፋ ነበረኝ በኃላ ስመለከት ግን በጣም ጎበዝ ኮራጅ ሆኑብኝ አንዳንድ ተማሪ አለ አንዴ አይቶ እጥብ አድርጎ የሚኮርጅ አቶ ኃይለማርያምም አነጋገራቸው፣ ውሃ አጠጣጣቸው፣ እጅ አጣጣላቸው ሁሉ አቶ መለስን ነው የሆኑት።” ሳቅ አጀበው።
አክቲቪስት እና አርቲስት ታማኝ በዛሬው መርሃግብር ብዙ ማለት እንደማይፈልግ ቶሎ ወደ እሳት የገንዘብ ማሰባሰብያ መርሃግብር እንደሚገባ ገትልፆ ንግግሩን ባይገታው ኖሮ ታዳሚው ገና እንዳልጠገበ ከፊቱ ይነበብ ነበር።
በመጨረሻ ግን ታማኝ ዛሬ ካሳየን ፎቶዎች ውስጥ በአድዋ ዘመቻ ጊዜ ዘማች ኢትዮጵያውያን (ክርስትያን እና ሙስሊም ኢትዮጵያውያን) በአራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት ክርስትያኖች ወደ ቤተክርስቲያን ሙስሊሞች ወደ መስጊድ አቅጣጫ ፊታቸውን እንዴት አዙረው ለሀገራቸው ለየ አምላኮቻቸው እንደፀለዩ እና ወደ ውግያው እንደሄዱ በወቅቱ ከነበረው ፎቶ ጋር እያመሳከረ ያሳየን ትእይንት እጅግ መሳጭ እና በመርሃግብሩ የተገኙትን ሙስሊም ወንድሞቻችንን ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን ልብ የገዛ ነበር።
ታማኝ ሲናገር ኢትዮጵያዊነት ውስጡ ይንቀለቀላል። አዎን የፖለቲካ ሰው አይደለም ወይንም ፖለቲካ ሙያው አይደለም። ሀገር መውደድ ግን ሌሎች ፖለቲካን እሳት ብለው ውሃ እየተራጩ ከንፈር ሲመጡ፣ ታማኝ እውነትን ብሎ እጁን እሳት ውስጥ ከቶ ስለ እውነት ለመሞት ቆርጦ የተነሳ ውድ ኢትዮጵያዊ ነው። ”ወይ እስክንድርን ሁን። አለበልዝያ ስሜን መልስ” ነው ያለው ታላቁ እስክንድር አንድ በፍርሃት ሲርድ ላገኘው ወታደሩ። የዛሬዋ የታማኝ ምሽትም ”ወይ ታማኝን ሁኑ አለበለዝያ ስሙን መልሱ” የምታሰኝ ነበረች    

 Posted By.Dawit Demelash




No comments:

Post a Comment