Thursday, May 16, 2013


በባለሥልጣናትና በባለሀብቶች ላይ ምርመራው የተጀመረው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መመርያ መሆኑ ተገለጸ


-ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዕርምጃው መዘግየት ተጠይቋል
-ኮሚሽነሩ ያለመከሰስ መብት ያለው የለም አሉ
ባለፈው ዓርብ በፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተጠርጥረው በተያዙት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶችና ትራንዚተሮች ጉዳይ ላይ ማክሰኞ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት በሰጡት የሥራ መመርያ መሠረት ጥናት ተደርጐ የተከናወነ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ኮሚሽነሩ የመሥሪያ ቤታቸውን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግንቦት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከማቅረባቸውም በተጨማሪ፣ በዚሁ ቀን ከሰዓት በኋላ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከፓርላማ አባላት ባለፈው ሳምንት በተያዙት ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶችና ሌሎች ላይ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
ኮሚሽኑን የሚከታተለው ምክር ቤት የሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ከሕዝብ የሰበሰባቸው ጥያቄዎች ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ «ዕርምጃው ቆራጥነትን የተሞላበት ቢሆንም ሕዝቡ አምርሮና አልቅሶ በመንግሥት ላይ ጥርጣሬ ካደረበት በኋላ ነው የተወሰደው፡፡ ለምን ይህን ያህል ጊዜ ዘገየ?» የሚል ይገኝበታል፡፡
«ኮሽ ባለ ቁጥር ተኩስ አይከፈትም» በማለት ምላሻቸውን መስጠት የጀመሩት ኮሚሽነሩ፣ የሕዝብ እሮሮ መኖሩ እውነት ቢሆንም ዕርምጃውን ለመውሰድ ጥናት እንደሚያስፈልግ፣ ይህም ጥናት ረዥም ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል፡፡
‹‹የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ በጥቃቅን ጉዳዮች ነው ጊዜያችሁን የምታጠፉት፣ ትንንሽ አሳዎችን እንጂ ትልልቅ አሳዎችን አታጠምዱም፤» በሚል ኮሚሽኑን ይወቅሱ እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ አሁን የተወሰደው ዕርምጃ ተግባራዊ እንዲሆን ጥናትና ምርመራውን ያዘዙት አቶ መለስ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ 
ጥናቱ የተጀመረው አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ማለትም የዛሬ ዓመት ከአሥር ወር አካባቢ መሆኑን፣ ከአቶ መለስ ሕልፈት በፊት በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ጥናቱ ተጠናቆ ለውሳኔ ቀርቦ እንደነበረ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
‹‹በጥናት ውጤቱ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ሳይሰጥ በአቶ መለስ ላይ የጤና ችግር፣ እንዲሁም ሌሎች ጊዜ የሚፈልጉ አስቸኳይ ጉዳዮች ተፈጠሩ፡፡ በኋላም የመንግሥት እንደገና መደራጀትና ሌሎች ነገሮች እንደነበሩ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ነው ዕርምጃ የተወሰደው፤›› ሲሉ የዘገየበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ 
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ ጥናት የተሠራበት ምክንያት፣ በንግድ ኅብረተሰብ ውስጥ የተደላደለ ውድድር እንዳይኖር በኃላፊዎች የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ችግር በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በሚነደፍበት ወቅት ትኩረት እንዲደረግባቸው ከተለዩ ተቋማት መካከል በቀዳሚነት የተለየው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
‹‹ግማሹ ግብር ከፋይ ነው ግማሹ ግብር አይከፍልም፡፡ ግማሹ ታክስ ከፍሎ ዕቃ ያስገባል፡፡ ግማሹ ታክስ አይከፍልም፡፡ በዚህ ምክንያት በንግዱ ኅብረተሰብ ውስጥ ሚዛናዊና የተደላደለ ውድድር እንዳይኖር ችግር ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለልማት የሚውለው ገንዘብ በመንገድ ላይ እየቀረ ነው፤›› በማለት ያብራሩት ኮሚሽነሩ፣ በቅድሚያ በዚህ ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑ ታምኖበት ጥናቱ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ሌላው ከሕዝብ ተሰብስቦ በቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ጥያቄ ዕርምጃው ለምን አሁን ተወሰደ? እንዲሁም አብረው የወሰኑ ሌሎች ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ሊኖሩ ስለሚችሉና ሁሉም ላይ ዕርምጃው አንዴ ባለመወሰዱ መረጃ ሊደብቁ ራሳቸውንም ሊያሸሹ ዕድል አይሰጥም ወይ? የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ዕርምጃ ለመውሰድ ጥናቱ ጊዜ መውሰዱን ገልጸው፣ ከዚህ ውጪ ግን ሌላ ምክንያት እንደሌለ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ 
‹‹ዕርምጃ የሚወሰደው ሁኔታው ወይም ሙስናው ሲፈጠርና በጥናት ላይ የተመሠረተ ማስረጃ ሲኖረን ነው፡፡ ይጠፋሉና መረጃ ያሸሻሉ የሚለው ጥያቄ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደበቅ ነገር የለም፡፡ ይህንንም ሕዝቡ ሰሞኑን ባሳየው ተነሳሽነት መረዳት እንችላለን፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ በአጠቃላይ የፀረ ሙስና ትግል በዘመቻ የሚፈታ አለመሆኑንና ቋሚ በሆነ ሒደት የሚከናወን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናት ላይ የተወሰደው ዕርምጃ የመጨረሻው አለመሆኑን፣ ሌሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎችን በመለየት ዕርምጃ መውሰዱ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በጥናት ውስጥ የሚገኙ ጉዳዮች መኖራቸውን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ጋር በቅንጅት እንዴት ሊሠራ እንደቻለ ተጠይቀው፣ የፍትሕ አካላትና የሕግ ማስከበር ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በቅንጅት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ከደኅንነት ተቋሙ ጋር በብሔራዊ ባንክ የወርቅ ሙስና፣ እንዲሁም በመሬት ጉዳዮች ላይ በቅንጅት መሠራቱን ይህም ተቋማት ያላቸውን የሰውና የቴክኖሎጂ አቅም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 
በቅርቡ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ግለሰቦች ላይ እስካሁን አንድም ዓይነት የሰብዓዊ አያያዝ ጉድለትና በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅትም ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት አለመፈጸሙን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ሰኞና ማክሰኞ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ከቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ መደረጉን በአቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ያለመከሰስ መብት እያላቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግን ይህ መብታቸው ተጥሶ መሆኑን በጠበቃቸው በኩል አቤት ብለዋል፡፡
ነገር ግን አቶ ዓሊ ይህንን በሚመለከት ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲያስረዱ፣ ‹‹ያለመከሰስ መብት ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያለመከሰስ መብት ያለው ተጠርጣሪ አለ ብለን አናምንም፡፡ ወደ ዝርዝሩ መግባት ሳያስፈልግ በአሁኑ ወቅት ከተጠርጣሪዎች ውስጥ ማንም ሰው ያለመከሰስ መብት የለውም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የኮሚሽኑ ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አቶ መላኩ የአዲስ አበባ ተመራጭ ቢሆኑም አዲስ ምርጫ በመካሄዱ ያለመከሰስ መብት አላቸው ተብሎ አይታመንም፡፡ 
ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ ትዕዛዝ ሰጥቶ አቶ መላኩ ያለመከሰስ መብት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ በቀጣዩ ሳምንት እንዲያረጋግጡ አዟል፡፡ 
ኮሚሽነር ዓሊ፣ ‹‹ኮሚሽኑ ሕግ ለማስከበር የተቋቋመ ነው፤ ይህንን ኃላፊነት ተቃርኖ ሕግ በመጣስ ጀማሪ አይሆንም፤›› ሲሉ ለፓርላማው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ዓሊ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ዝናብን ጠብቆ እንደሚዘራ መኸር ሳይሆን በየጊዜው የሚቀጥል ጥናትና ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በገቢዎች ላይም ይቀጥላል፡፡ በሌሎቹ ተቋማትም ጥናቱና ዕርምጃው ይቀጥላል፤›› ሲሉ አቶ ዓሊ የሥራውን ቀጣይነት አስረድተዋል፡፡ 

             Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment