Friday, May 24, 2013

የደህንነት ሹሙ ስዊድን ይመጣሉ

አዲስ አደረጃጀትና አዲስ ሬዲዮ በስካንዲኔቪያ
eprdf1


በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) የብሔራዊ ደህንነትና የደኅንነት አገልግሎት ሁለተኛ ሰው የሆኑት አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ ስዊድን እንደሚመጡ ተሰማ። በስካንዲኔቪያ አገራትና በድፍን አውሮፓ በሚኖረው ዲያስፖራ ላይ የሚያተኩር “የግል” መሰል የሬዲዮ ስርጭት ለመጀመር መታሰቡም ተሰምቷል።
የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንዳስታወቁት አቶ ኢሳያስ ስዊድን ይመጣሉ የተባለው በመጪው የሰኔ ወር ነው። የኤርትራዊ ዜግነት ያላቸውና አቶ መለስ በእጅጉ ይተማመኑባቸው እንደነበር የሚነገርላቸው አቶ ኢሳያስ ስዊድን ከደረሱ በኋላ ሊያከናውኑ ስላሰቡት ተግባር ዝርዝር ለመረዳት ጊዜው ገና እንደሆነ ምንጮቹ አመልክተዋል።
“ሆኖም ግን” ይላሉ ምንጮቹ፣ ” ሆኖም ግን አቶ ኢሳያስ ድርጅታቸው ኢህአዴግ በስካንዲኔቪያን አገሮች በተደጋጋሚ ያጋጠመውን ውግዘት አስመልክቶ አዲስ አደረጃጀት እንደሚገነቡ ታውቋል፡፡”
የኢህአዴግና የስርዓቱ ደጋፊዎችን ለማብዛት በልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም አባላትን የመመልመሉ ስራ በተጠናከረ መልክ እንደሚሰራበትና የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ ለመጠርነፍ ይዋቀራል የተባለው አዲሱ ድር /ኔትወርክ/ ትኩረት የሚያደርገው “አብዛኛው አድፋጭ” ወይም “silent majority” ላይ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎቹ ተናግረዋል። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲዎችን ማደራጀት አንዱና ዋናው የአደረጃጀቱ አግባብ እንደሆነም ተጠቁሟል።
ቀደም ሲል በስካንዲኔቪያን አገራት የዲያስፖራ ድር /ኔትወርክ/ በበላይነት ይመሩ የነበሩ የደህንነት ሰው ተጠርተው ይሁን በፈቃዳቸው ወደ አገር ቤት መሄዳቸውን ያመለከቱት የመረጃው ምንጮች፣ እኚሁ ሰው በአገር ቤት ቆይታቸው በስካንዲኔቪያ ስላለው የዳያስፖራ ሁኔታ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል በእቅድ ደረጃ የተያዘው “ተቃዋሚ የሚመስል የሬዲዮ ስርጭት” የመክፈት አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቆሙት የጎልጉል የመረጃ ሰዎች “ለስካንዲኔቪያ አገራት የሬዲዮ ስርጭት ለመክፈት የታሰበው ኖርዌይ ቢሆንም አሁን ግን ስዊድን ተመርጣለች” ብለዋል።
በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስለሚገኙና ስቶክሆልም ባለው ኤምባሲ አማካይነት ዜጎች ወደ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ በዚያው ስለሚያመሩ የሬዲዮ ስርጭቱን ስዊድን ለማድረግ እንደታሰበ ከምንጮቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
ከዓመት በፊት ታዋቂ ጋዜጠኞችን በማሰባሰብ አሜሪካ አገር የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭት ለመጀመር ታስቦ እንደነበር በተለያዩ ጊዚያት መዘገቡ አይዘነጋም። ኢሳትን ለመመከት ታስቦ አሜሪካን ይቋቋማል የተባለው የኢህአዴግ የዜና ማሰራጫ ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ መረጃው ይፋ በመሆኑ ይሁን በሌላ ምክንያት እውን ሊሆን አልቻለም።
የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት ቪ.ኦ.ኢ (VOE) በሚል ምህጻረ ቃል በኢትዮጵያ አጎራባች አገር የሬዲዮ ስርጭት ለመክፈት ኢህአዴግ የጸና አቋም እንዳለው፣ የሚከፈተውም የዜና ተቋም በአህጉር ደረጃ ታዋቂ እንዲሆንና የዜና ኤጀንሲ ይዘት የሚኖረው ነው።
      Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment