Thursday, March 14, 2013

በፕሬስ የሚካሄድ ስም ማጥፋትን በተመለከተ የወንጀል ሕጉ ሊሻሸል ነው



መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:-በግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ በፕሬስ የሚካሄዱ የስም ማጥፋትን ለመዳኘት የወንጀል ሕጉን ለማሻሻል መታቀዱ ተጠቆመ፡፡
ከ2005-2007 የሚቆየውና እስካሁን ሳይጸድቅ በውይይት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃግብር ሰነድ ላይ እንደተመለከተው በመገኛኛ ብዙሃን አማካይነት የሚካሄዱና በተለይ በግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ ያነጣጠሩ የሰም ማጥፋት ዘመቻዎችን ለማስቆም የወንጀል ሕጉን ለማሻሻል ጥናት ይካሄዳል፡፡
ይህው ሰነድ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርብ የስም ማጥፋት ክስ በሕገመንግስቱ በተቋቋሙ የህግ አውጪ፣የህግ አስፈጻሚወይም የፍርድ ቤት ባለስልጣኖች ላይ ካልሆነ በስተቀር በግለሰቦችና የግል ድርጅቶች ላይ ሲሆን፣  በአቃቤ ሕግ ሳይሆን በግል ተበዳይ ክስ ቀርቦ የሚታይበት ስርዓት ተዘርግቷል ሲል ስርዓቱን ያሞካሻል፡፡
ፍርድ ቤቱ ክሱ ሲቀርብለት ተከሳሽ ባለበት እንዲሁም ተከሳሽ ባልተገኘ ሰዓት ደግሞ በጋዜጣ በማሳወጅ በሌለበት
ቢበዛ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንዲሰጥ በማድረግ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ላይ ሊቀርብ የሚችል ማንኛውም
ክስ በአጭር የይርጋ ጊዜ እንዲታገድ በማድረግ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ከመስራት እንዳይስተጓጎሉ ጥበቃ
በማድረግ ኀሳባቸውን የመግለጽ ነጻነታቸው እንዲጠበቅላቸው ሆኗል ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
ሰነዱ በግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ያነጣጠሩ ጥላቻ አዘል ንግግሮችና ስም ማጥፋትን በተመለከተ የሚገዛ ህግ በጥናት
ይረቀቃል ሲል በሰነዱ ላይ ቢያሰፍርም፣  አሁን በስራ ላይ ያለው ሕግ ምን እንደጎደለበት በግልጽ ያመለከተው ነገር
የለም፡፡ሆኖም ግን ሰነዱ መንግስት አሁንም ፕሬሱን በስም ማጥፋት ስም ለማሳደድ ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚጠቁም
ሆኗል፡፡
መንግሰት በዚህ ሰነድ ላይ ለህትመት ሚዲያ ከቴክኒካዊ ምዝገባ በስተቀር የፈቃድና የፈቃድ እድሳት አሰራር
እንዳይኖር መደረጉን እንደትልቅ ስኬት ያስቀመጠ ቢሆንም ፣ በተግባር ግን የብሮድካስት ባለስልጣን በምዝገባ ወቅት
“እናጣራለን” በሚል ከስልጣኑ ውጪ የምዝገባ ፈቃድ የሚከለክልበት፣በፈቃድ እድሳት ወቅት ማረጋገጫ በመከልከል
እንደ ፍትህ፣አዲስታይምስ ጋዜጣና መጽሔቶች በአስተዳደራዊ ክልከላ ከህትመት ውጪ እንዲሆኑ ከተደረገው ጋር ሲተያይ
ሪፖርቱን ኢተአማኒ እንደሚያደርገው ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጦች ሙሉ በሙሉ ከገበያ እንዲጠፉ መደረጉ ይታወሳል።
     Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment