Saturday, March 2, 2013

በሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ንግግር የተቆጣው መንግሥት ማብራሪያ ጠየቀ

March 2, 2013 Leave a comment

በመገንባት ላይ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል በማለት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር ባደረጉት ንግግር ምክንያት የተቆጣው የኢትዮጵያ መንግሥት ሳዑዲ ዓረቢያ ማብራርያ እንድትሰጥ ጠየቀ፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሡልጣን ባሳለፍነው ሳምንት በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በተካሄደው የዓረብ አገሮች የውኃ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ኢኮኖሚያዊ ዓላማ ያለው ሳይሆን የፖለቲካ ሴራ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ ንግግር ያስቆጣው መንግሥት ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ 70 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም ያለው በመሆኑና 700 ሜትር ከፍታ ስላለው ቢደረመስ የሱዳን ዋና ከተማን ካርቱምን ከማጥለቅለቁም በላይ የግብፅን ታላቁን አስዋን ግድብም አደጋ ያመጣበታል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ግድብ ምክንያት በዋነኝነት የምትጎዳው አገር ግብፅ እንደሆነች፣ ምክንያቱ ደግሞ ከሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ጋር ስትወዳደር ሌላ አማራጭ የውኃ አቅርቦት እንደሌላት ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለግብፅ ጠንቅ እንደሆነች አስረድተዋል፡፡ የዓባይ ተፋሰስ የራስጌ አገሮችም ስለውኃ አጠቃቀም የሚያነሱት የመብት ጥያቄም በግብፅ ላይ አደጋ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር የተሰጠውን አስተያየት ኃላፊነት የጎደለውና አፍራሽ ነው ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የተፋሰሱ አገሮች በትብብር እየሠሩ ባሉበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ንግግር መሰማቱ በእጅጉ ያሳፍራል ብሏል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ ‹‹ንግግሩ ያልተጠበቀና በአገሮቹ መልካም ትብብር ላይ የተደረገ ጣልቃ ገብነት ነው፤›› በማለት የተናገሩ ሲሆን፣ በተለይ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ካላት መልካም ግንኙነት አንፃር ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ላደረጉት የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ጉዳዩን እንዳላነሱባቸው፣ ነገር ግን በዲፕሎማቲክ መርህ መሠረት የአገሪቱ አምባሳደር ተጠርተው መንግሥታቸው በአስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፣ የምክትል ሚኒስትሩ ንግግር ከሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣን የሚጠበቅ አለመሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ተናገሩት የተባለውን ማጣራት እንዳለባቸው የተናገሩት የግብፅ አምባሳደር፣ አገሪቱ የግብፅም የኢትዮጵያም ወዳጅ መሆንዋን ጠቅሰው፣ እንዲህ ዓይነት ንግግር የማይጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ በተለይ በሱዳን፣ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል በዓባይ ግድብና በዓባይ ተፋሰስ ዙርያ ለተጀመረው ትብብር አዎንታዊ ሚና እንደምትጫወት እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡


             Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment