Tuesday, July 23, 2013

በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኘው ኩታበር ወረዳ አንድነት ፓርቲ ሐምሌ 7 ቀን 2005ዓ.ም. በደሴ ያካሄደውን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በመቃወም ህዝቡ ሰላማዊ እንዲወጣ ኢህአዴግ እያስገደደ መሆኑን ፍኖተ ነፃነት ዘገበ

 ሐምሌ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰልፉ ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠዋት ላይ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡  በወረዳው ቀበሌ 05፣06 እና 07 ሰፊ የማስፈራሪያና የቅስቀሳ ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ጋዜጣው የኢህአዴግ ካድሬዎች ገበሬውን በግድ ከአቅሙ በላይ የዘር ማዳበሪያ ውሰድ እያሉ ከፍተኛ ገንዘብ ከማስከፈላቸው በተጨማሪ ለአማራ ልማት ማኀበር፣ለአባይ፣ ለመሬት ግብር እየተባለ የሚጠየቀው መዋጮ በመብዛቱ ነዋሪዎቹ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ሲናገሩ ወደ እስር ቤት እየተወሰዱ ና ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከአካባቢው እየተሰደዱ መሆኑንም ገልጿል።
አንድነት ፓርቲ በተለያዩ ከተሞች የጠራውን ሰልፍ ተከትሎ የኢህአዴግ ከፍተኛ ሹማምንት በተለያዩ ቦታዎች እየተነቀሳቀሱ ህዝቡ እንዳይገኝ ለበታች አመራሮች መመሪያ እየሰጡ ነው።
ተቃዋሚዎች እየወሰዱት ባለው እርምጃ የተደናገጠ የሚመስለው ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች የሙስሊሙን የድምጻችን ይሰማ ጥያቄ ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሊያውሉት እየተሩዋሩዋጡ ነው በማለት ይተቻል።
አንድነት ባወጣው የህዝባዊ ንቅናቄ እቅድ መሰረት ሀምሌ 21 እና 28 በአዲስ አበባ 2 ቦታዎች እንዲሁም ሀምሌ 28 በወላይታ ሶዶና በመቀሌ ህዝባዊ ስብሰባዎች ሲደረጉ፣ በተመሳሳይ ቀን ሀምሌ 28 በባህርዳር፣ ጅንካና አርባምንጭ የተቃውሞ ሰልፎች ይደረጋሉ።
ነሃሴ 12  አዳማ፣ ባሌ፣ ወሊሶ እና ፍቼ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያስተናግዱ ነሃሴ 26 ደግሞ ጋምቤላና አሶሳ ያስተናግዳሉ። ድሬዳዋ አዋሳ፣ አምቦና ደብረማርቆስ   ነሀሴ 26 ህዝባዊ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ። መስከረም 5፣ 2006 ዓም ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ የታሰሩበትን 2ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የማጠቃለያ የተቃውሞ ሰልፍ ይደረጋል።





No comments:

Post a Comment