Wednesday, July 31, 2013

በሻሸመኔ የመንግስት ባለስልጣናት መስጊድ ዘረፉ ተፈፀመ

በሻሸመኔ ጩሉሌ ሀበራ ቀበሌ በሚገኘው በመስጊዱራህማ መስጊድ ም/ኢማምና የመስጊዱ ኮሚቴዎች በህገወጥ መንገድ ታስረዋል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአንድነት ፓርቲ አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡በሻሸመኔ ጩሉሌ ሀበራ ቀበሌ በሚገኘው በመስጊዱራህማ መስጊድ ም/ኢማም ሼህ አማን ተሺተን ጨምሮ 15 የመስጂዱ ኮሚቴ አባላት የታሰሩት ባለፈው እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2005ዓ.ም የመስጂዱ ንብረት የሆነን ከአንድ ሄክታር ላይ የታጨደ በግምት ከ10 ኩንታል በላይ የሚመዝን ታጭዶ የተከመረ ጤፍ የመንግስት አካላት በግድ በመውሰዳቸው በተነሳ አለመግባባት ነው፡፡ በግጭቱ ከ30 በላይ ሰው ከሁለቱም ወገን የቆሰለ ሲሆን ከመንግስት ወገን ያሉት ተጎጂዎች ወደ ሀኪም ቤት ተወስደው እርዳታ ሲደረግላቸው የመስጂዱን ንብረት አናስወስድም ካሉት ወገኖች መካከል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ግን አንዳችም የህክምና እርዳታ እንዳያገኙ መደረጋቸውን የሚናገሩት የተጎጂዎቹ ወኪሎች “በአካባቢያችን መንግስት እየፈፀመ ያለውን የመብት ረገጣና የኢትዮጵያ ህዝ እንዲያውቅልን እርዱን” በማለት ተማፅነዋል፡፡ ተወካዮቹ ጨምረው እንደገለፁት የቀበሌው ሹማምንት 20 ኩንታል በላይ የሚመዝን በቆሎ ከመስጂዱ አስገድደው መውሰዳቸውንና በዚሁ ጉዳይም ክስ እንደተመሰረተባቸው አስረድተዋል፡፡ ፍኖተ ነፃነት ስለቅሬታው ለማጣራት ያደረገው ሙከራ የአካባቢው ባለስልጣናት ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡

No comments:

Post a Comment