Tuesday, September 24, 2013

ሙስሊም ወንድማማች ዕገዳ ተጣለበት

september 24.2013

ውሳኔው የሙርሲን “ቅርንጫፍ” ድርጅቶችንም ይጨምራል

m b


የካይሮው አስቸኳይ ጉዳዮች ፍርድቤት የሙስሊም ወንድማማችን እና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሙሉ ከማንኛውም እንቅስቃሴ አገደ፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የዜና አገልግሎትን ጠቅሶ አልጃዚራ እንደገለጸው ዕገዳው መሐመድ ሙርሲ ይመሩት የነበረውን እና ከሙስሊም ወንድማማች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውን የእስላማዊው እንቅስቃሴ የፖለቲካ ክንፍ የነጻነትና ፍትሕ ፓርቲንም ሊጨምር ይችላል፡፡
በሕዝብ ድምጽ ሥልጣን የተረከቡትን መሐመድ ሙርሲ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የሙስሊም ወንድማማች ደጋፊዎችና ከፍተኛ አመራሮች አሁንም እየታሰሩና እየተገደሉ ይገኛል፡፡
ከፖሊስና፣ ከደኅንነትና ከመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች ጋር የሚደረገው ውዝግብ ደም አፋሳሽ ከመሆን አልፎ በወንድማማቾቹ እንቅስቃሴ ላይ “የአሸባሪነት” ታርጋ አስለጥፎበታል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፈው ወር በተከሰተው ግጭት የሙስሊም ወንድማማች ደጋፊዎች ከ600 በላይ ክርስቲያኖችን መግደላቸውና ቤ/ክናትን ማቃጠላቸው እንደሚገባው አልተዘገበም በማለት አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ወቀሳ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
የሰኞው ዕለት ዕገዳ በአሁኑ ጊዜ በወንድማማች ኅብረቱ ላይ የሚካሄደውን የተፋፋመ ወከባ በሕጋዊ መልኩ ያጠናክረዋል የሚል ግምት እየተሰጠበት ቢሆንም የግብጽ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ሁኔታው እንደዚያ እንዳልሆነ ለአልጃዚራ ዘጋቢ ተናግሯል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ እየተካሄዱ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎች ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ መቀጠል ይችላሉ፤” ሆኖም የሙርሲን መነሳት በመቃወም አስመስለው የሽብር ተግባር ለመፈጸም የሚፈልጉ ሁሉ የትም ሊያመልጡ እንደማይችሉ አስጠንቅቋል፡፡
85ዓመታትን ያስቆጠረው እስላማዊው እንቅስቃሴ በ1946 በሕግ ታግዶ የነበረ ሲሆን በቅርቡ ሕጋዊነቱን አግኝቶ ወደ ግብጽ ፖለቲካ ውስጥ ከገባ በኋላ የበርካታዎችን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ የዚህም ውጤት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በግብጽ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ የፓርላማውን አብላጫ ወንበርና የፕሬዚዳንትነቱን መንበር መቆጣጠር ችሏል፡፡
በካይሮው አስቸኳይ ጉዳዮች ፍርድቤት የተላለፈው ውሳኔ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበርን፣ በመያድ ስም የተመዘገቡት የሙስሊም ወንድማማች ድርጅቶችን እንዲሁም “ማንኛውም ከሙስሊም ወንድማማች ጋር የተገናኘ ድርጅት ወይም ንብረት ወይም የገንዘብ ዕርዳታ የሚያገኝ ተቋም” ላይ ዕገዳው የተላለፈበት መሆኑን ይናገራል፡፡ ሆኖም በወንድማማቹ ማኅበር ሥር ያሉትን ትምህርትቤቶችና ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሌሎች የማኅበራዊ ተቋማት ዕገዳው እንደሚመለከታቸው ግልጽ አልሆነም፡፡
ውሳኔውን አስመልክቶ የወንድማማች ማኅበሩ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኢብራሂም ሙኒር ዕገዳውን “አምባገነናዊ ውሳኔ” ያሉት ሲሆን በዚህም ውሳኔ እንኳን ቢሆን ማኅበሩ እንደማይጠፋ ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም “በአላህ ዕርዳታ እንጂ በአል-ሲሲ (የጦር ኃይሎች ዋና ኃላፊ የሆኑትን ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል-ሲሲን ማለታቸው ነው) የፍርድቤት ትዕዛዝ የሚፈርስ አይደለም” ብለዋል፡፡
በብያኔው ወቅት ያስቻሉት ዳኛ፤ የማኅበሩ “ገንዘብ፣ ንብረትና ህንጻዎች እንዲወረሱ” ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡ በግብጽ ካቢኔ ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ ፍርድቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አሁን የሚወረሰውን ሃብት እንዲያስተዳድርም ተወስኗል፡፡ ውሳኔውን ይግባኝ ማለት እንደሚቻል አብሮ ተጠቁሟል፡፡
ከአባላቱ በሚገኝ መዋጮ የሚተዳደረው የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር “አላህ ዓላማችን፤ ቁርዓን ሕጋችን፤ ነቢዩ መሪያችን፤ ጂሃድ መንገዳችን ናቸው፡፡” በሚሉ መሠረታዊ መመሪያዎች እንደሚተዳደር ይታወቃል፡፡ (ፎቶ: news.yahoo.com)

No comments:

Post a Comment