የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማስቀጠል መንግሥት ግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ.ም. የዓባይ ወንዝ የፍሰት አቅጣጫ መቀየሩን በይፋ ካስታወቀ በኋላ፣ በተለይ ከግብፅ በኩል የሚሰማው ዛቻና ማስፈራራት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት የግብፅ ፖለቲከኞች በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት የተናገሩት ግድቡን በቦምብ የማጋየትና አማፂያንን በመርዳት ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ፣ በዚህ ሳምንት ገጽታውን ቀይሮ በፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ አማካይነት ሰላምንና ፀብን ያጣቀሰ ንግግር ተሰምቷል፡፡ ባለፈው ሰኞ ባለሥልጣናትን አስከትለው ከግብፅ እስላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተወያዩት ሙርሲ፣ የህዳሴው ግድብ በአገራቸው ብሔራዊ ደኅንነት ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑን በመግለጽ፣ ግብፅ ማናቸውንም አማራጮች ትጠቀማለች ብለዋል፡፡
ተመራጩ መፍትሔ ውይይትና ድርድር ነው ቢሉም፣ ግድቡን እንደ ሥጋት ተመልክተውታል፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞችም ከግብፅ ፍላጎት በተቃራኒ እየተገነባ በመሆኑ ግንባታው መቆም አለበት እያሉ ናቸው፡፡ የፕሬዚዳንት ሙርሲ ተቃዋሚዎች ደግሞ ግድቡን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል አይቻልም በማለት ተቃውመዋቸዋል፡፡ በግብፅ ባለሥልጣናትና አክራሪ ፖለቲከኞች ድርጊት የተበሳጨው የኢትዮጵያ መንግሥት ማክሰኞ ከቀትር በኋላ በሰጠው መግለጫ፣ የግብፅ ፖለቲከኞች የሚያካሂዱትን አፍራሽ ድርጊት እንዲያቆሙ አሳስቧል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ለአገሩ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የግብፃውያን ፖለቲከኞች ፕሮፓጋንዳ የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር መሆኑን በማስገንዘብ፣ በዚህ ማስፈራራት ኢትዮጵያ ለአንዲት ሰከንድም ቢሆን የግድቡን ግንባታ እንደማታቆም መንግሥት አስታውቋል፡፡
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment