አርዐያ ተስፋማርያም፣ ሰሜናዊው ኮከብ
አርዐያን የማውቀው በሃገራችን ይታተሙ ከነበሩት ነጻ ጋዜጦች በሲሳይ አጌና ባለቤትነት ይተዳደር በነበረው ስመ ጥሩው ኢትዮጽ ጋዜጣ ላይ በተመስጦ እከታተለው ከነበረው የጋዜጣው አምዶች ውስጥ ከህወሐት መንደር በሚል አብይ ርዕስ ስር በተከታታይ ይቀርብ የነበረው የወያኔን ገበና ገላጭ ጽሑፍ እየሩሳሌም አርዐያ በሚል የብዕር ስም ይጽፍ የነበረው ብርቱው ጋዜጠኛ አርዐያ ተስፋማርያም ምንም ቅርርብ ኖሮን ባያውቅም የጽሁፉ እድምተኛ በመሆን ብዙ ቁም ነገር የቀሰምኩበት በመሆኑ በቅርብ የማውቀው ያህል የሚሰማኝ ከመሆኑም በላይ የደረሰበት ግፍና በደል ከእርሱ አልፎ ቤተሰቡን ጭምር ችግር ላይ መጣሉን ስከታተለው የነበረ ሲሆን እንዲህ አይነቱን በዚህ በኔ ትውልድ ውስጥ በብርሃን ተፈልጎ የማይገኙ ጥቂቶች ብቻ ጥቅምና ምቾትን ንቀው መስሎ በማደርና ሕሊናን በመሸጥ ከሚገኝ የተደላደለ ህይወት ትቶ ላመነበትና አላማ ጸንቶ ለተሰለፈበት ሙያ ተግቶ በቆራጥነት የሚቆም ዜጋ ተምሳሌትነቱ ለትውልድ ጠቃሚ በመሆኑ አንድ ነገር ለማለት ሳመነታ ሰሞኑን በአጋጣሚ ይህን ጎበዝ ጋዜጠኛ የተመለከተ ስብሰባ መኖሩን ስመለከት ሳስበው የቆየሁትን ለመተንፈስ አጋጣሚው መልካም ከመሆኑም በላይ የዝግጅቱ ማስታወቂያ ላይም ያለኝን ቅሬታ ለወገን ለማካፈል ፈለግሁ።
እንዳለመታደል ከተቆራኘን ክፉ ባህል አንዱ አንገታቸውን ደፍተው ስራቸውን በማስቀደም ለሃገርና ለወገን በሚጠቅም ሙያ ተሰማርተው ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ ወገኖቻችንን አዳማቂና አጫፋሪ ከሌላቸው ከነመልካም ስራቸው ትውልድ ሳያውቃቸው ተረስተው የሚኖሩበት ልማድ ማስወገድ ባለመቻላችን ስንት በተለያየ ዘርፍ በጎ ተግባር የፈጸሙ ታላላቅ ወገኖችን ሳንረዳቸው አልፈውብናል። ነገር ግን አሟሟቂና አጨብጫቢ ያላቸውን ለታይታና ለዝና የሚራወጡትን በየመድረኩ የሚቀላምዱትን ሲሞቅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ የሚሉትን የፖለቲካ ቁጭበሉዎች ስሜታችንን እያደነዙ ሙገሳና ተስፋችንን ይዘው ስንቶች ሸጠውናል፤ ስንቱስ የተፋውን እየላሰ የተናገረውን እያጠፈ ወደ አሳዳጆቻችን ጉያ ገብቷል ስንት ጉድ አይተናል ዝርዝሩን ለታሪክ እንተወው። እንደ አረዐያ ያለ ደፋርና ጽኑ ጋዜጠኛ እስከ ሞት የታመነ ባለሙያ ተሰባስበን ልናከብረው ልናመሰግነውና ተምሳሌትነቱን ለትውልድ ለመመስከር መድረክ ማመቻቸት ሲኖርብን ለዚህ ሰው ፈንድ ሬዚንግ በሚል የተደረገው ጥሪ በእውነቱ ለእኔ በጣም ቅር አሰኝቶኛል፤ ቢሆንም ግን ሃገሬን እወዳለሁ የሚል ቅን ዜጋ በዝግጅቱ ላይ በመታደም ይህን ወንድም በአጋጣሚው ልናከብረው ወገናዊነታችንን ልንገልጽለት ይገባል።
በሃገራችን ባለፉት ሁለት አስዕርተ አመታት በተለይ እውነት መናገር የሚያሰገድል ፤ የሚያሳስርና፤ የሚያሰድድ ሆኖ የመቆየቱን ያህል ሐሰት መመስከር በሹመት ላይ ሹመት በሃብት ላይ ሃብት በሚያስገኝበት ሃገር ያውም የስልጣን ምደባ ከዘር ጋር በሚሰጥበት የአገዛዝ ሁኔታ ውስጥ እንደ አረዐያ ያለ የትግራይ ተወላጅ ከነተባ ብዕሩ ብዙም መልመጥመጥ ሳያስፈልገው ቢያንስ በየኤንባሲው ካሉት ሻንጣ ተሸካሚ ዲፕሎማት ተብዬዎችና ወሬ ቃራሚ የወያኔው ደንቆሮ ሰላዮች በተሻለ ሹመትና ገንዘብ ለማግኝት የሚችልበት እድል እያለው እውነትን የሙጥኝ በማለት ባሳየው ጽናት በግፈኛ ወያኔዎች የተፈጸመበት ግፍ ለጆሮ እስኪከብድ ድርስ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ከነነብሱ ከድልድይ ላይ እስከመወርወር ዋጋ የከፈለ ጋዜጠኛና ያልተዘመረለት ጀግና ወግና መዓረግ ባለው መልኩ ልናከብረውና ልናመሰግነው ይገባል።
በአሁኒቷ ኢትዮጽያ የትግራዩ ነጻ አውጪ ነኝ ባዩ የባንዳ ጥርቅም የተቆራኘው ክፋትና ተንኮል ከጠባብ ጨለምተኛ የዘር ፖለቲካ ጋር ተዳምሮ የህዝባችንን ህላዌ እያዳከመ አብሮነታችን እያመከነና ጠላትነት ለቀጣዩ ትውልድ በውርስ እስኪተላለፍ ድረስ ጮርቃ ህጻናት ሳይቀር ከትምህርት ገበታቸው ተወልደው ካደጉበት ቅያቸው በዘር ቆጠራ ሃብት ንብረታቸው ተገፎ ዜጎች ሲፈናቀሉ ተው ከማለት ይልቅ በዘረኝነት የተሸበበው አብዛኛው የትግራይ ተወላጅ ምሁርና ዲያስፖራ ቢያንስ ከሰብዓዊነት አንጻር ድርጊቱን ማውገዝ ተገቢ ሆኖ ሳለ ዝምታን መምረጡ እየታዘብነው ባለበት በዚህ ወቅት ሃገርና ወገንን አስቀድመው ከተበደለውና ከተከፋው ጋር አብረው የቆሙትና ይህን ሕገ-አራዊት አገዛዝ ይወገድ ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ከሚያደርጉ በጣም ጥቂት የትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻችን አንዱ ይህ ስሙን የምንዘክረው ይመስገን ብለን የምንለው የወገን ኩራትና የኢትዮጽያዊነት ተስፋ የሆነው አርዐያ ተስፋስላሴ የሰሜን ኮከብ ብለን ብናሞግሰው የሚያንስበት እንጂ የሚበዛበት አይሆንም።
አረዐያ በህጻን ልጁ ላይ በደረሰባት የጤንነት መታወክና ከሚያስፈልጋት ከፍተኛ የህክምና እርዳታ አንጻር ብዙ እንግልትና መከራ ማየቱን በታላቅ ሃዘን ተከታትየዋለሁ ፤ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የነበረው ይህ ሰው የደረሰበት ችግር አቋሙን ሳያስለውጠው በጽናት የሄደበት ረጅምና አስቸጋሪ ጉዞ አስቤው ፤ በዚህ በምድረ አሜሪካ ከሃገሩ የመኖር ነጻነት አጥቶ ጥገኝነት ተሰጥቶት የሚኖረው የተገፋውና የተዋረደው ወገን የሆነው ስደተኛ ዲያስፖራ ሃገር ቤት ላለ በላብና በወዙ ለሰራው ዛኒጋባ ከትግሉ ሜዳ ፈርቶ ሲሸሽ የቀረውም ወደ አዲስ አበባ ለመሸታ ከሚያደርው ጉዞ ላለመደናቀፍ የሃገር ጉዳይ የወገን መከራ አይቶ እንዳላየ በምንቸገረኝነት ዝምታን ሲመርጥ በምናይበት ከሺህ ማይል ርቀት ላይ ሆኖ የሚርድ ደካማ በተንሰራፋበት ማህበረሰብ ውስጥ ደሃ ተበደለ ፍትህ ተጓደለ ብሎ የመጮህ መንፈሳዊ ሃላፊነት የነበረባቸው ካህናትና ቀሳውስት እንኳን ስለ ፍትህ ሊያነሱ ቀርቶ ስለ ገዳማትና ባህታውያን እንግልት ድምጻቸውን ለማሰማት
በጥቅም ካቴና በታሰሩበት የሞራል ክስረት በረበበት ሃይመኖታዊ ህይወት ውስጥ ይህ ሰው እንግዲህ በራሱና በቤተሰቡ ህልውና ላይ የከፈለው ዋጋ ከቶስ በምን ሚዛን ይሆን የምንለካው።
ለአምላክ ምስጋና ይግባውና ይህ ትውልድ ተምሳሌት አላጣም ፤ ምቾት ዝና ጥቅምና ሐብት ያላታለላቸው ለአመኑበት አላማ በጽናት የቆሙ በነሱ እንግልት እኛ እንድናርፍ በግዞት የሚማቅቁት አንዷለም እስክንድር ፤ አበበ፤ ዘሪሁን ፤ ርዕዮት፤ውብሸት እና ሌሎችም ምሳሌነታችው ዛሬ ላለነው ነው። አርዐያ ተስፋማርያም የነዚህ የሰላምና የነጻነት አርበኞች አካል በመሆኑ ሊከበር ሊወደስና ሊደገፍ የሚገባው ስለሆነ ለዚህ ታላቅ ወንድም የምናደርግለት እገዛ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሆን አሰተባባሪ ወገኖች ተግተው ሊያተጉን ይገባል። ለማጠቃለል ሃገር ወገን ብለው ያቅማቸውን የሚያበረክቱትን ወንድሞች ለማድነቅና ስማቸውን ላመንሳት የግድ አጫፋሪ መጠበቅ አለያም ችግር እስኪገጥማቸው መቆየት የለብንም ፤ ይህ ያለመከባበር አሮጌ ባህል ማስወገድ አለመቻላችን ትግሉንም በእጅጉ የሚጎደ በመሆኑ እስከ ዛሬ ስንጓዝበት ከነበረ ክፉ ልማድ ተቆጥበን ክዋክብቶቻችንን የመንከባከብ ባህልን በማጎልበት ለተተኪው ትውልድ የሞራል ውርስ ለመተው ከጸረ ወያኔው ትግል ጎን ለጎን አብረን ልናሴደው ይገባል።
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment