Thursday, June 20, 2013

ቀን የጎደለብን ስደተኞች ቀን!



ዛሬ የስደተኞች ቀን መሆኑን ወዳጄ ሰሚር ፌስ ቡክ ላይ ባጋራን ማስታወሻ እና የአልጀዚራ ድረ ገፅ ማስፈንጠሪያ አስታወስኩ፡፡ አንዳንዱ ቀን “እንኳን አደረሳችሁ” ተባብሎ ቢቻል ጠላ ተጠምቆ ድፎ ዳቦ ተደፍቶ እና ዶሮ ወጥ ተወጥውጦ ያከብሩታል፡፡ አንዳንዱ ቀን ደግሞ በሀዘን “ምን ይሻላል ምን ይበጃል” የሚለውን እያንጎራጎሩ ያከብሩታል፡፡ ታድያ “ቀን የጎደለብን ስደተኞች ቀን” በተለይ ለእኛ ኢትዮጵያያን የሀዘን ቀናችን አይደለምን!?
የአልጀዚራ ድረ ገፅ፤ በግብጽ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን የተጋረጠባቸውን ስጋት ያስነብባል፡፡ ግብፃዊያን ሆዬ፤ “ከአባይ ትነኩ እና ደማችሁን ነው የምንጠጣው” አይነት ዛቻ ኢትዮጵያውያን ላይ እየዛቱባቸው እንደሆነ አልጀዚራ ነገረኝ፡፡
ግብፃዊያኑ የሚያደርጉትን ሲያሳጣቸው እንጂ እነዚህ ዜጎች ላይ የፈለጉትን ያህል መጥፎ ነገር ቢያደርሱ የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ግድ አይሰጠውም፡፡ መንግስታችን እንደ ሰካራም አባት ነው፡፡ ውጪ ስንደበደብ እንዴት ተመትተህ ትመጣለህ… ብሎ መልሶ ይደበድበናል እንጂ ልጆቼን ለምን ነካችሁ ብሎ ጥያቄ እንኳ አይጠይቅም፡፡
አሁን በቅርቡ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትራችን ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖም ከግብፅ ውጪ ጉዳይ  ሚኒስትር ጋር መሃመድ ከሪም ጋር አባይን አስመልክቶ ውይይት መጀመራቸውን ሰምተናል፡፡ ዶክተርየው በውይይታቸው፤ የዜጎቻችንን ነገር አደራ ሲሉ አልሰማንም፡፡ ምናልባት ብዙ ጥቃት ብዙ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ወደፊት ዶክመንተሪ ሰርተው ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ሆነው ያለቅሱልን ይሆናል፡፡
የሆነ ሆኖ ዛሬ ቀን የጎደለብን የኛ የስደተኞች ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች በየቀኑ እንሰደዳለን፤ በተለይ መንግግስታችን “ውጡልኝ ከዚህ ቤት” እያለን እና ኑሮ ሮሮ እየሆነብን ቁጭ ብሎ ከመታመም እየሄዱ መሞት ይሻላል ብለን በባህር በየብሱ የምንሰደድ ብዙ ነን!
ድሮ ድሮ አረቦች ወደ እኛ ሀገር ይሰደዱ ነበር፡፡ ተሰደውም ሚጢጢ ሱቅ ከፍተው አላፊ አግዳሚውን ጋሼ እያሉ፤ እነርሱም “ጋሼ ባለሱቁ” ተብለው፤ ኑሯቸውን ይገፉ ነበር፡፡ አሁንም ጭምር በየሰፈሩ “አረቦ ሱቅ” የሚባሉ ቤቶች የዚህ ታሪክ ዱካ ናቸው፡፡ ዛሬ እነዛው አረቦች ወይም ልጆቻቸው በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ተገጣጥሞ ቢሰፋ ከሀገር የሚሰፋ መሬት ለግላቸው ተሰጥቷቸው እያረሱ እየበሉ ነው፡፡
የእኛ እህቶች ደግሞ በአሁኑ ወቅት፤ በአረብ ሀገራት ለስራ ብለው ተሰደው በሚደርስባቸው ሴራ፤ የስነ ልቦና እና የአካል ጉዳት አንዳንዴም እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት እያጋጠማቸው ለሀገራቸው መሬት እንኳ ሳይበቁ በየሜዳው እየቀሩ በሰው ሀገር ጭካኔ እየተበሉ ነው፡፡ የአረብ ሀገር ባለሀብቶችን የሚንከባከበው መንግስታችን በአረብ ሀገራት የሚጉላሉ ዜጎቹን ጉዳይ ዶክመንተሪ ፊልም ከመስራት ያለፈ “አባከና” ሲላቸው አላየንም፡፡
በኬኒያ፣ በታንዛኒያ፣ በየመን፣ በሶማሌ፣ በሱዳን በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን እየተሰደዱ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥም አልደላቸውም በስደቱም አልተመቻቸውም፡፡
“እንደው የእኔን ነገር ዝም ነው ዝም ነው
ውጪም አልተመቸኝ ቤቴም ንዝንዝ ነው”
እንዳለችው ሴትዮ በሀገር ውስጥም በውጪም አበሳችንን እያየን ነው፡፡ ይህንን አበሳችንን ቀለል የሚያደርግልን ማን ይሆን!? አናውቅም! ዝም ብለን ግን ተስፋ እናደርጋለን…
አንድ ቀን ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡
አንድ ቀን ሀገራችን ለሁላችንም የምትበቃ ትሆናለች!
እስከዛው ድረስ ግን፤ ቀኑ እስኪሞላ የስደኞችን ቀን እኛ ስናከብረው “ቀን የጎደለብን…” የሚለውን ከፊት ለፊቱ ጨምረን “ቀን የጎደለብን ስደተኞች ቀን” ብለን ነው ማለት ነው !  
     Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment