ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ቃሊቲ የሚገኘው እስር ቤት ከገባ ከዐሥራ ስምንት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ለዚህን ያህል ጊዜም ከባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እና ከልጁ ናፍቆት በስተቀር አንድም ሰው ገብቶ እንዲጠይቀው አልተፈቀደለትም ወይም በወዳጅ ዘመዶቹ የመጠየቅ መብቱ ተነፍጎ ነበር፡፡ ከቀናት በፊት ግን ይህ መብቱ ተከብሮለት ሰዎች ገብተው እንዲጠይቁት መፈቀዱን ሰማኹና ዛሬ ጠዋት እስክንድርን ለማየት ወደ ቃሊቲ አመራሁ፡፡ እስክንድርንም አገኘኹት ብዙም ተጨዋወትን፡፡ እስክንድር ለዚህን ያህል ወራት እስር ቤት መቆየቱን ተጠራጠርኩ ጥንካሬው አሁንም አብሮት አለ፡፡
ከእርሱ ይልቅ እርሱን ያሳሰበው በውጭ ያሉት ወዳጆቹ ጤንነት እስኪመስለኝ ድረስ በጋራ የምናውቃቸውን ሰዎች እና ጓደኞቻችንን ስም እያነሳ ጠየቀኝ፡፡በቻልኩት መጠን ሰላምታ እንዳቀርብለትም አሳሰበኝ፡፡ በመጨረሻም እንዲህ አለኝ፤‹‹የታሠርኩት ከሕግ ውጭ መኾኑን ተረድታችሁ በሁሉም መንገድ እንድፈታ ለወተወታችሁ፣ላሰሰባችሁ፣አሁንም እየወተወታችኹ ላላችኹና ባላችኹበት ላሰባችኹኝ ኹሉ ዲሞክራሲ በአገራችን ሰፍኖ ከእስር ወጥቼ በአካል ምስጋናዬን እስካቀርብላችሁ ድረስ ባላችሁበት የከበረ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ›› መልዕክቱን… እንደማስተላልለት ቃል ገብቼለት ተሰናብቼው ወጣሁ፡፡ በገባሁት ቃል መሠረትም ምስጋናውን አድርሻለኹ፡፡
እስክንድር ነጋ የሞያ አጋሬ ብቻ አይደለም፤በቀናነታቸው እና በአስተዋይነታቸው የመጀመሪያውን የወዳጅነት ቦታ ከምሰጣቸው ጓደኞቼ ውስጥ የምመድበው ሰው ነው፡፡ እስክንድር በአሳሪዎቹ እጅ ወድቆም ስለ ሌሎች ማሰብ ባለማቋረጡ እየተገረምኩ ቃሊቲን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ወዳጆቼ በዚህ ቤት መታሠር ሚያቆሙት መቼ ይኾን ስልም ራሴን ጠየኹ!
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment